የተሟላ ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበ 368 ያልተወራረደ ሒሳብ መገኘቱን፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ገቢ መኖሩንና ሌሎችንም ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለምክር ቤቱ አሳውቀዋል፡፡
ዋና ኦዲተር በ2006 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በጀት ተጠቃሚ የሆኑ 135 መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲትን ያልተከተሉ 78 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሕጉ መሠረት ያላወራረዱት ሁለት ቢሊዮን ሃያ አምስት ሚሊዮን ብር መኖሩን ጠቁሟል፡፡ በዚህ ያልተወራረደ ሒሳብ ተጠያቂ ከሆኑት መሥሪያ ቤቶች መካከል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት 666.4 ሚሊዮን ብር፣ የትምህርት ሚኒስቴር 433.4 ሚሊዮን ብር፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር 144.2 ሚሊዮን ብር ሕጉን ባልተከተለ መልኩ ወጪ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በወጣው ሕግና ደንብ መሠረት የመንግሥት ገቢ በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና በሌሎች 12 ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች ላይ በድምሩ አንድ ቢሊዮን ብር ሰላሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ገቢ መኖሩንም ዋና ኦዲተር ይፋ አድርጓል፡፡
በወጪ ለተመዘገቡ ሒሳቦች የተሟላ መረጃ መኖሩን ለማረጋገጥ ባደረገው ኦዲት በ29 መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ 368 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱን ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ገልጸዋል፡፡
ተሟልተው ካልቀረቡ ማስረጃዎች መካከልም ከዕቃ አቅራቢው የተሰጠ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ ላቀረበው የክፍያ ጥያቄ ብቻ በወጪነት የተያዘ፣ ተራና አግባብነት የሌላቸው ደረሰኞች ማለትም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የሌላቸው ደረሰኞችንና የመሳሰሉትን ሕጋዊ ያልሆኑ ማስረጃዎች በመያዝ የተከፈሉ ወጪዎች እንደሚካተቱም ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ (በ2006) መሥሪያ ቤቶች የፈጸሙት ክፍያ ትክክለኛነትን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ በ19 መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ 473.469 ሚሊዮን ብር መኖሩን የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ያሳያል፡፡ ከእነዚህም መሥሪያ ቤቶች መካከል ትልቁን ድርሻ ማለትም የ273.845 ሚሊዮን ብር ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ወጪ የተመዘገበበት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ነው፡፡
ይህ መሥሪያ ቤት ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ግዥዎችን በተመለከተ ኦዲት ያለማስደረግ ሥልጣን ከዓመት በፊት በአዋጅ የተሰጠው ሲሆን፣ የዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝትም ይህንን መብቱን ያልጣሰ እንዲያውም ራሱ መሥሪያ ቤቱ ኦዲት መደረግ ይችላል ብሎ ያቀረበው ሰነድ ላይ የተደረገ ኦዲት ውጤት መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ለፓርላማው ግልጽ አድርገዋል፡፡
የዕቃ አገልግሎትና ግዥ በመንግሥት ደንብና መመርያ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በ63 መሥሪያ ቤቶች ሕግን ያልተከተለ የ957.5 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በአሁኑ ወቅት 98 በመቶ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት የማድረግ አቅም ቢፈጥርም፣ ከዚህ ቀደም በኦዲት ያገኛቸው ችግሮች ዛሬም አለመፈታታቸው አሳሳቢ እንደሆነ አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
‹‹በተለይ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ ተሰብሳቢ ሒሳቦች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ ግንባታዎችና ግዥዎች በልዩ ሁኔታ ሊታዩ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ማስገንዘብ እወዳለሁ፤›› ሲሉ ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል፡፡
የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከፋይናንስ ሕጋዊነት በተጨማሪ የክዋኔ ኦዲት ማለትም የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራ አፈጻጸምን ከተሰጣቸው ኃላፊነትና ከአገሪቱ ሕጐች ጋር ያለውን መጣጣም በመገምገም ሪፖርት ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት በ2006 ዓ.ም. የክዋኔ ኦዲት ከተከናወነባቸው መሥሪያ ቤቶች መካከል የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመሠረተ ልማት ግንባታ አፈጻጸም ይገኝበታል፡፡
በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መመርያ መሠረት መጀመርያ የፕሮጀክት ምርመራ እንደሚደረግ፣ ፕሮፋይል በተዘጋጀላቸው ፕሮጀክት ሐሳቦች ላይ ዝርዝር ጥናት ከመደረጉ አስቀድሞ የፕሮጀክት ረቂቅ ሰነድ ይዘጋጅና ቅድሚያ የሚሰጣቸው የፕሮጀክት ሐሳቦች ወደ ዝግጅት ሒደት እንዲገቡ ይደረጋል ቢልም፣ በኮርፖሬሽኑ እየተተገበሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በ1999 ዓ.ም. በትራንስፖርት ሚኒስቴር መሪነት አጥኚ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ አማራጭ የየብስ ትራንስፖርትን አስመልክቶ ያደረገው ጥናት እንጂ፣ እያንዳንዱን ፕሮጀክት አስመልክቶ የተጠና የፕሮጀክት ጥናት ሰነድ አለመኖሩን ዋና ኦዲተሩ ይፋ አድርገዋል፡፡
የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ክትትል፣ ቁጥጥርና ድኅረ ትግበራው በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የፕሮጀክት አዘገጃጀት ማኑዋል መሠረት ሊካሄድ የሚገባው ቢሆንም፣ በዚያ መልኩ እየተካሄደ አለመሆኑን የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ የሚያገለግል በኮንትራት ውሉ ውስጥ የተጠቀሱ ለግንባታ ሥራ፣ ለቁጥጥርና ክትትል አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችና ማኑዋሎች ለምሳሌ የጥራት ማረጋገጫ ማኑዋል የመሳሰሉትን ኦዲቱ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ኮርፖሬሽኑ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የፕሮጀክት ውሉ በሚለው የጥራት መሥፈርት መሠረት ፕሮጀክቱ እየተከናወነ መሆኑን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በፕሮጀክቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ውስጥ የሚጠቀሱ ምክረ ሐሳቦች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባ ቢሆንም፣ ኮርፖሬሽኑ በሚዘረጋው የአዲስ አበባ ሚኤሶ መስመር ይህ እየሆነ አለመሆኑን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ለአብነትም የባቡር መስመሩ በሚያልፍበት በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በርካታ የቱሪስት መተላለፊያ መንገዶችን ሳያስፈቅዱ መዘጋት፣ ያለፈቃድ መንገዶችን በፓርኩ ውስጥ እየቀደዱ ማውጣት፣ በፕሮጀክቶቹ የሚሠሩ የውጭ አገር ባለሙያዎች የዱር እንስሳትን ያለ ፈቃድ እያደኑ ለምግብነት የሚጠቀሙ መሆኑን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
በሚኤሶ-ደወሌ የባቡር መስመር ዝርጋታ ያለውን የእሳተ ገሞራ መከሰት ሁኔታ ሊገመግም የሚችል ጥናት እንዲደረግ ኮንትራቱን የወሰደው ድርጅት ቢጠይቅም፣ በአካባቢው የላይኛው የመሬት ክፍል ላይ የመሬት መሰንጠቆች እየታዩ እሳተ ገሞራ የመከሰቱን ሁኔታ ሳያጠኑ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲደረግ መፍቀዱ ተገቢ አለመሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
የባቡር ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ ከኮንትራት ውሉ ውጪ ለሚጨመሩና ለሚቀነሱ ጉዳዮች ኮርፖሬሽኑ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አቅርቦ እንዲፈቀድ ማድረግ ሲገባው፣ ኮርፖሬሽኑ ግን የሰበታ ሚኤሶ ፕሮጀክት ከ1.639 ቢሊዮን ዶላር ወደ 1.841 ቢሊዮን ዶላር የኮንትራት ዋጋው ከፍ ሲል ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ቀርቦ ያልተፈቀደ መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment