ገለታው ዘለቀ
በድርጅት ከዚያም ከፍ ብሎ በመንግስት ደረጃና በሃገር ደረጃ ግምገማ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ ያምናል። የኣንድ ድርጅት ብቃትም በግምገማው ችሎታና ጥራት ሊለካ ይችላል።የኣንድ ሃገር የፖለቲካ መረጋጋት በፖለቲካ ለሂቆቹ የጠራ የሃገር የምናብ ስእልና ብስለት ሊለካም ይችላል። የፖለቲካ ቤቶች ሲኮለኮሉ፣ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ ከፍ ያለ ግምገማን ይጠይቃል። ሃገሪቱ ያለፈችበትን የህይወት ጎዳና፣ የገጠማትን ችግር መንስዔና ውጤቶች በሰፊው መገምገም ለሚመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረትና ለሚቀረጹ ፖሊሲዎች ጥራት ወሳኝ ነው። እንግዲህ በሃገራችን ኢትዮጵያ ግምገማ በሰፊው የተወራለት ጉዳይ የሆነው በዚህ መንግስት ጊዜ ነው። ህወሃት በጫካ ኑሮው ጊዜ የነበረው ማህበራዊ ህይወትና የትግሉም ባህርይ የየቀን ውሎውን እየገመገመ እንዲሄድ የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ስለከተተው በግለሰቦች ድክመትና ጥንካሬ ዙሪያ ሲገማገም ነው ያደገው። የግምገማው ዓይነት ኣውጫጭኝ ኣይነት ግምገማ ተፈጥሮ ያለው ነው። በመርህ ደረጃ ግምገማ መኖሩ በራሱ ጥሩ ሆኖ ሳለ የግምገማውን ባህርይና ያመጣውን ፍሬ ማየት ግን ኣለብን።
ህወሃት “ኢሃዴግ” ስልጣን ከያዘ በሁዋላ የመጣው ይህ ግምገማ ከድርጅት ኣልፎ ታች በየመስሪያ ቤቱ እንዲሁም ገበሬው ድረስ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል። ባህሪው ለየት ያለ በመሆኑና ያልተለመደ በመሆኑ ኣስተማሪዎችን፣ የህክምና ባለሙያዎችን፣ የግብርና ባለሙያዎችን ወዘተ ግራ ኣጋብቶ ነበር። ግራ ያጋባበት ምክንያት በሃሳብ ደረጃ መጥፎ ስለሚባል ኣይመስለኝም። ችግር ያመጣው ኣውጫጭኝ ኣይነት በመሆኑና ከሲስተምና ከፖሊሲ ይልቅ በግለሰቦች ባህርያትና ክህሎት ብቃት ላይ ያተኮረ በመሆኑ እንዲሁም የግምገማው መስፈርት የጠራ ባለመሆኑ የግለሰቦችን ግላዊ ህይወት ሳይቀር ኣደባባይ በማውጣቱ መዘበራረቅን ኣምጥቶ ነበር።
“ኢሃዴግ” ግምገማ ሲል በጣም የሚብከነከነው በኣክተሮቹ ፣ በሲስተሙ ተዋንያን ላይ በመሆኑ የግለሰቦቹን ድክመትና ጥንካሬ በኣደባባይ ኣውጥቶ መወያየት ኣንድን የስራ ሃላፊ ወይም ባለሙያ ያለውን ጠንካራ ጎንና ደካማ ጎን ኣብጠርጥሮ በገበያ ላይ ማውጣት ነው ትልቁ ግምገማ። የሰውን ልጅ ይለውጠዋል የሚል እምነት ኖሮት እንደሆነ ኣላውቅም። የግምገማው ስነ ልቦና ትንሽ ለየት ይላል።ግለሰቦች ባህርያቸውን በጥልቀት ይገመገማሉ። በተለይ በፖለቲካ ድርጅቶች ኣካባቢ የሚበሉበትን የሚጠጡበትን ቤት ሁሉ እያነሱ ማብጠልጠል ሁሉም በየማስታወሻው በኣንድ ኣባል ላይ የያዘውን እያወጣ ድክመት ነው ያለውን በጉባዔ ፊት ለዚያ ሰው መግለጥ ዋና ተግባር ነው።ህወሃት በግለሰቦች በተለይም በታችኛው ኣካል ኣካባቢ ግምገማውን ያብዛ እንጂ እንደ ድርጅት እንደ ሲስተም ሲበዛ ሚስጥረኛና ግልጽነት የጎደለው ድርጅት ነው።
“የኢህ ኣዴግ” ኣይነቱ ግምገማ በሌሎች ኣገሮች ከሚደረጉ ግምገማዎች ሁሉ የሚለይ ይመስላል። በግምገማ ክህሎትን፣ ባህርይን ለማረቅ የሚሞክር ኣካሄድ ይመስላል። የድርጅት ኣባላት ሲናገሩ በኣንድ ሰው ዙሪያ ሁለት ቀን ድረስ የሚፈጅ ግምገማ የሚደረግበት ጊዜ ኣለ። ውሳኔ ያንስሃል፣ ትፈራለህ፣ ታዳላለህ፣ ከእከሊት ጋር ትወጣለህ፣ ብስለትና እድገት ኣይታይብህም፣ ሙስና ውስጥ ገብተሃል፣ ከእከሌ ጋር ያለህ ቅርበት በዝቱዋል፣ ከእከሌ ጋር ለምን ተኳረፍክ፣ ትኮራለህ፣ ኣድርባይ ነህ፣ ወዘተ ወዘተ…. እየተባለ የሚገመገም ብዙ ሰው ኣለ። ኣባላት ሁሉ እየተነሱ ግለሰቡን ቁጭ ኣርገው ያብጠለጥላሉ። ሂስህን ዋጥ፣ ኣልውጥም… ዋጥ፣ ኣልውጥም… ብዙ ሰዓት ይፈጅና ተገምጋሚው “ውጫለሁ” ካለ ይታለፍና ሌላው በተራው ደግሞ እንዲሁ ይብጠለጠላል። ኣንዳንዴም ኣባላት በሆነ ነገር ያናደዳቸውን ሰው ለማጥቃት ሲያስቡ በዚያ ሰው ዙሪያ ሲሰልሉ፣ ድክመት የተባሉትን ሲያሰባስቡ ይቆዩና በግምገማው ሰዓት ኣንጀታቸውን የሚያርሱበት መድረክ እንደሆነም ይነገራል። በኣጠቃላይ እምነቱ ግን የሰዎችን ድክመት በተለይ በኣደባባይ በማውጣትና በመግለጥ የሰው ልጅ ይማራል፣ ምን ኣልባትም በግል በሱፐርቪዥን ከሚድረገው ግምገማ ይልቅ በኣደባባይ በቡድን ፊት መጋለጡ ለባህርይ ለውጥ የተሻለ ነው የሚል ነገር ይመስላል። ኣጠቃላይ ሂደቱ ባህርይንና ክህሎትን ለመቅረጽ ነው ብለን በቅንነት እንውሰድና በተግባር ግን በተለይ በሃገር መሪዎች ኣካባቢ ሰፋ ባለው በሃገር ደረጃ በርግጥ ይህ ኣካሄድ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ወይ? ህወሃት “ኢህዓዴግ” በዚህ የግምገማ ስልቱ የተሻሉ መሪዎችን ኣፈራልን ወይ? ኣገራችን መሪዎችን ኣገኘች ወይ? ግልጽነትና ተጠያቂነት እያደገ ሙስና ቀነሰ ወይ? ኣድረን ወደ ዴሞክራሲ ተመነደግን ወይ? የሚለውን መገምገም ተገቢ ነው። ግምገማ ቀላል ነገር ኣይደለም። ፍርድ ነው። ለዚህ ደግሞ ከፍ ያለ ተመልካችነትን የሙያ ቅርበትን ይጠይቃል። “ኢህኣዴግ” ግምገማ የሚለው እርስ በርስ ከተሞሸላለቁ በሁዋላ ሂስ በመዋጥና ባለመዋጥ የሚቋጭ ነው ። ከዚህ በላይ ግን የግምገማው ውጤት ከፍትህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት የሌለው ተገንጥሎ የወጣ ነው። ለማናቸውም ግን ግምገማው ጥሩ ነው ጥሩ ኣይደለም ከሚለው በላይ ለዛሬው ጽሁፍፌ መነሻ የሆነኝ ምን ትርፍ ኣገኘን? የሚለው ጉዳይ ነው ::
ከፍ ሲል እንዳልኩት “ኢህኣዴግ” ከተፈጠረ ጀምሮ ከዚያም በፊት በህወሃት ጊዜ ግምገማ በተለይም በግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ግምገማ የሚካሄድ ሲሆን በርግጥ ከዚህ ፍሬ ኣግኝተን መሪዎችን ኣፈራን ወይ? መሪዎቹ ክህሎት ጨመሩ ወይ? ትህትናና ዴሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት በመሪዎቹ ኣካባቢ እያደገ መጣ ወይ? ብለን ኣጥብቀን መጠየቅ ኣለብን። ኣቶ ኣባዱላ ገመዳ ላለፉት ሰላሳ በላይ ኣመታት የሰላ ግምገማ ተካሂዶባቸው ኣሁን ክህሎት ጨምረዋል ወይ? ። “ኣዎ!” ከተባለ ከሰላሳ ዓመት በፊት ምን ዓይነት ሰው ነበሩ ማለት ነው? ብለን እንደመማለን። ለኣርባ ኣመት ገደማ የተገመገሙት እነ ኣባይ ጸሃየ፣ እነ ሳሞራ፣ እነ ስዩም ወዘተ በዓርባ ዓመት ግምገማ ውስጥ ኣልፈው ለምን የተሻለ ስብእና ኣላዳበሩም? እነ ኣዲሱ ለገሰና እነ ስብሃት ነጋ ሌሎች መሪዎች በዚህ ግምገማ ተወቅረው…. ተወቅረው …..ተወቅረው….. ምን ወጣቸው? እንዴውም በተግባር የምናየው ህግን ሲጥሱ፣ ኣድረው ጭካኔ ሲያሳድጉ፣ ዴሞክራሲ እንዳያድግ ሲያደርጉ ነው። ይህን ስናይ የዚህ “የኢሃዴግ” ግምገማ ጉዳይ የሆነ ችግር ያለበት መሆኑን እንረዳለን። በዚህ ዙሪያ ነው ኣንዲት ትንሽ ኣስተያየት ለማቀበል የፈለኩት። ቅን የሆኑ “የኢሃዴግ” ኣባላትም ይሰሙኛል ብየ ኣምኜ ነው።
በሃሳብ ደረጃ እንዲህ ኣይነቱ ግምገማ ጥሩ ቢመስልም የሳተው ትልቁ ነገር ግን ሊፈጥር ያሰበው ስብእና መያዣ ኣቁማዳ ተበጅቶለት ኣናይም። የግምገማው ሂደት “ኢሃዴግን” ራሱን እንደ ድርጅት በሲስተምና በፖሊሲ ደረጃ ኣብጠርጥሮ ከመገምገም ይልቅ በኣክተሮቹ፣ በግለሰቦቹ የግል ባህርይና ክህሎት ላይ በማተኮሩ የሰላሳ ኣመቱ ግምገማ ፍሬ ኣላመጣም። ኣንዳንዶቹን እንዴውም በደንብ ኣድርጎ ያደነዘዛቸው ይመስላል። ግምገማን ከመልመዳቸው የተነሳ “ሂሴን ውጪያለሁ” ምንትሴ…… እያሉ ማለፉን መርጠው ለውጥ ሳይመጣ ቀርቶኣል። ኣንዳንዶቹም የሰው ሃጢያት ሲዘረዘር ደስ እያላቸው የግምገማ ጊዜ ሱስ የሆነባቸው ይህን ጊዜም የሚደሰቱበትም እንዳሉ ይሰማል። “የኢሃዴግ” ግምገማ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረገው በግምገማ መድረኩ ለማጠብ የሞከረውን ኣባላቶቹን ኣጣጥቦ ኣመድ ላይ መጎለቱ ነው።። ለምሳሌ ኣንድ የፖሊስ ተጠሪ ለህገ መንግስቱ ታዛዥ ኣይደለህም ወዘተ….. ተብሎ ቢገመገምና ሂሱን ውጦ ከመድረክ ቢመለስ ነገ የት ነው የሚገባው? መቼ ፖሊስ ራሱ ነጻ ተቋም ሆኖ ተፈጠረ? የብር ዋጋው ሲወርድ (devaluate ሲደረግ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሃላፊ ሳያውቅ በሚወሰንበት ኣገር እንዴት ሆኖ ነው ይህ የባንክ ሃላፊ ውሳኔ ያንስሃል፣ ኣቅም ያንስሃል፣ ወዘተ እየተባለ ሊገመገም የሚችለው? በነጻነት መፍረድ በማይቻልበት ኣገር እንዴት ሆኖ ነው ኣንድ ዳኛ በሙያው የሚገመገመው? ዋናው ችግር ይህ ተቋም ነጻ ኣለመሆኑ ሲሆን ግለሰቡን ገምግመው ኣብጠልጥለው ሂሱን ኣስውጠው ቢልኩት ነገ ሄዶ የሚቀመጠው ኣመድ ላይ ነው። ለዚህ ነው ግምገማው ሲስተሙን ራሱን ጨክኖ የሚፈትሽ ባለመሆኑ የግለሰቦች ኣውጫጭኝ ሆኖ የሰላሳና የኣርባ ዓመት ፍሬው ባዶ የሆነው።
“ኢሃዴግ” ባለፉት ኣመታት ከግለሰቦች ኣውጫጭኝ ይልቅ ሲስተምን የሚያይ “የኢሃዴግን” ተፈጥሮና ፖሊሲዎቹን በሚገባ የሚገመግም ቢሆን ኣገሪቱ ወደ ተሻለ ዴሞክራሲና ልማት ታድግ ነበር። “ኢሃዴግ” ጨክኖ ራሱን እንደ ሲስተም እያየ ምርጫ ቦርድን ነጻ ኣድርገን ፈጥረናል ወይ? ወታደሩ ነጻ ነው ወይ? ፍርድ ቤት ውስጥ ጣልቃ ኣንገባም ወይ? ባንኮችና ኣጠቃላይ የሃገሪቱ ተቋማት በነጻነት ይሰራሉ ወይ? ህወሃት “በኢሃዴግ” ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ምን ኣደረገው? ይህ ትክክል ኣይደለም! የብሄር ፖለቲካ የመጨረሻ ግብ ኣለው ወይ? እኛ ራሳችን ተሰባስበንበታል የምንለው “ኢሃዴግ” በርግጥ በዚህ ዓለም በህይወት ኣለ ወይ? በኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሃሳብና “በኢሃዴግ” ተፈጥሮ መካከል ያለው ዝምድናና መስተጋብር ምን ይመስላል? የቱን ያህል ጥብቅ ነው? ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንድነው? በህገ መንግስቱና በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ መካከል ምን ዝምድና ኣለ? የብሄር ፖለቲካና የዴሞክራሲ መርሆዎች ኣብረው ይሄዳሉ ወይ? ህወሃት ለዖህዴድ ምኑ ነው? ወዘተ… ደግሞም ግምገማ በጣም በበዛበት ዘመን በሃገራችን የነበረ ጉቦ እንዴት ወደ ሙስና ያድጋል? እጅግ ብዙ ጥያቄ ለማኝ የሆኑ ጉዳዮች ስላሉ እነዚህ በሚገባ ቢገመግሙ የተሻለ ቤት መስራት ይቻል ነበር። ማህበራዊ ሃብትን የሚንከባከብ የህብረተሰቡን ኢነርጂ የማይቃረን ስርዓትና ፖሊሲ ከተፈጠረ በዚያ ውስጥ የሚኖረው ግምገማ የተሻለ ፍሬ ባመጣ። በመከላከያ ኣካባቢ በኢኮኖሚው ኣካባቢ የህወሃት የበላይነት መታየት የለበትም፣ ኣንድ ግለሰብ ሰረቀ ተብሎ ለሁለት ቀን የሚገመገም ከሆነ የህወሃት ድርጅታዊ ሙስና ለምን በሰፊው ኣይገመገምም? የመሳሰሉትን ስናይ የዚህ መንግስት ትልቅ ችግር ግምገማው ሲስተሙን ጨክኖ የሚገመግም ኣለመሆኑ፣ የሚፈራ በመሆኑ ነው። ሲስተምን ችላ ብሎ ሙስና በተጠናወተው ሲስተም ውስጥ ጥሩ መሪዎችን ለማውጣት መሞከር ኣይቻልም። ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው።በድርጅት ህይወት ውስጥ መጀመሪያ መታየት ያለበት ቤቱ ንጹህ ተደርጎ መሰራቱን ነው። ቤቱ ካልጸዳ በውስጡ ያሉት ኣይጸዱም:: ዝም ብለን ብንቀጥል ደግሞ እጥበቱ ድብኝት ኣጠባ ነው የሚሆነው።
በሃገራችን ኣጠቃላይ የፖለቲካ ቅርጽ ኣካባቢ ይህ ችግር ይታየኛል። ሃገራችንን ኢትዮጵያን ተፈጥሮዋንና ማንነቱዋን በሚገባ መረዳት፣ ያለፈችበትን ህይወት በሚገባ መገምገም ችግሮቹን ኣንጥሮ ማውጣት የቀረን ይመስለኛል። ለዚህም ነው ዛሬ ኣንዱ የብሄር ጥያቄ ኣንዱ የግለሰብ እያለ በሁለት ውጥረት ውስጥ የወደቀችው። ችግርን በሚገባ ኣለመለየትና ኣለመገምገም ወደፊት ለምንሰራው የፖለቲካ ቤትም ሆነ ፖሊሲ ተጽእኖው ከባድ ነው። በመሆኑም “የኢሃዴግ” ኣባላት ጨክነው “ኢሃዴግን” ተፈጥሮውን የህወሃትን ግዝፈት የተቋማትን ነጻነት ኣብጠርጥረው ቢገመግሙ ነበር የምንለወጠው። ይህ ግን ኣልሆነም። ህወሃት በግምገማ ስም የበታቾቹን እያመሰ የሃገሪቱን ሃብት ሲቦጠቡጥ ነው የሚታየው። “ኢሃዴግ” በግለሰቦች ኣካባቢ ግምገማ ጊዜ ያለውን ጭካኔ በሲስተም ላይ ማሳየት ኣይፈልግም። እንዴውም ግምገማን የማይፈልገውን ሰው ለመቅጫም ጥሩ መሳሪያ ኣድርጎ በሚገባ ሲጠቀምበት ይታያል።
“ኢሃዴግ” ቁጭ ብሎ ግምገማውን ራሱን መገምገም ነበረበት። ኣርባ ኣመት የተገመገሙትን ሰዎች እያየ ለምን ወደ ፍጹምነት የተጠጋ ስብእና ኣላዳበራችሁም ብቻ ሳይሆን እንዴት በዚያ ግምገማ ውስጥ ኣልፋችሁ ክፋትንና ተንኮልን ትጨምራላችሁ? ብሎ መጠየቅ ካልቻለ እሴት ኣልጨመረም። ነጻ ያልሆኑት ኣቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ውሳኔ ላይ ደካማ ነዎት፣ ይህን ጉዳይ በሚገባ ኣልተወጡም ሊባሉ ኣይችሉም። ከዚህ ይልቅ “የኢሃዴግ” ኣባላት ቆራጥ ቢሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሃይል የላቸውም! እንደ ቃል ኣቀባይ ኣይነት ነው ስራቸው በሚል የህወሃትን ጣልቃ ገብነትና እጅ ኣዙር ኣገዛዝ መገምገም ፍሬ ያመጣ ነበር። ለኚህ ሰው የፈጀው ሰፊ የግምገማ ሰዓት ድራማ ከመሆን የሚያልፈው ተገምግመው ሲያበቁ ነጻ በሆነ የሃላፊነት ወንበር ላይ የሚቀመጡ ሲሆን ነበር። የቡድን ኣመራርን መቃወሜ ኣይደለም። ይሁን እንጂ በቡድን ኣመራር ስም የህወሃት ፈቃድ ብቻ በሚፈጸምበት ኣገር የኣቶ ሃይለማርያም ድርሻ ከቃል ኣቀባይነት ያለፈ ስራ ስለማይሆን ይህን ደፍሮ የሚሰብር ጠንካራ ግምገማ ያስፈልጋል።
በግምገማ ጊዜ ስለ ሙስና ተነስቶ ሰዎች ይወቀሳሉ። ኦዲተሮች ግን በነጻነት ኣይሰሩም። ኣንዳንዱ በሙስና የሚገመገመው ኦዲት በማይደረግ መስሪያ ቤት ነው። ኦዲት ተደርጎ የኦዲት ሪፖርቱ በማይታወቅበት መስሪያ ቤት የሚሰሩ ኣንዳንድ ግለሰቦችን በግምገማ ላይ ማንሳቱ ምን ኣልባትም በሙስና ስም ለማጥቃት ካልሆነ ፍሬ የሌለው መሆኑ ይታወቃል። ሳይንሳዊ ይሁን ስንልም በኣሰራርና ስራንና ሰራተኛን በማገናኘት ሊስተካከሉ የሚችሉትን በቡድን ኣውጫጭኝና ሂስህን ዋጥ ኣልውጥም ሊስተካከል ኣይችልም።
ከዚህ በፊት ኣንድ የብዓዴን ኣባል ኣናግሬ ኣውቃለሁ። ይህ ሰው በድርጅቱ ውስጥ ስልጣን ያለው ነው። እንዴውም የድርጅት ጉዳይ ሆኖ ነበር። እንዴት ነው እናንተ ብዓዴኖች ህወሃትን ኣታሙትም ወይ ? ብየ ጠየኩት:: በደንብ ነው ውጭ ውጭውን የምንንሾካሸከው ብሎኛል። ኦህዴድም እንደዚሁ ነው። ይህ የሚያሳየው በጣም በተበላሸ ሲስተም ውስጥ ነው ግለሰቦች እየተብጠለጠሉ ያሉት። ይህ ደግሞ ለድርጅቱም ለሃገርም ለውጥ ኣያመጣም።
ኣንዳንዱ ሰው ደግሞ የሚወቀሰው ከተፈጥሮው ክህሎት ጋር በተያያዘ ነው። ውሳኔ ያንስሃል ሲባል ይህ ሰው ወስን…. ወስን…. ወስን…… ስለተባለ ኣይደለም የሚወስነው።ውሳኔ በኣብዛኛው መረጃን ከመረዳትና ከመገምገም ጋር ነው የሚያያዘው።በተለይ በከፍተኛ ስልጣን ላይ ያለ ሰው ውሳኔ የሚያጥረው ብዙ ጊዜ የሚመጡ መረጃዎችን የመተንተንና በኣእምሮ የመሳል ኣቅም ሲያጥረው ይመስለኛል:: ባለስልጣን ሆኘ ባላየውም። የውሳኔና ኣመራር ችሎታ በትምህርትና ከተፈጥሮም ጋር ከተያያዘ ተሰጥዖ ጋር ሊሄድ ይችላል። በስብሰባ ኣባላት ስለጮሁበት ኣይደለም። በዚህ መልኩ የመሻሻል እድል ጠባብ ነው የሚሆነው። ኣንዳንዱ ሰው ትላልቅ ፒክቸሮችን በኣይምሮው የማየትና የመደመም(a strong impression) ብሎም ውሳኔ የመስጠት ተሰጦ ላይኖረው ይችላል። ፖሊሲ ውሳኔ ነው። ሚሊዮን ህዝቦችን ተጽእኖ ሊያደርግ የሚችልን ፖሊሲ ሲያመጡ ወስነው ነውና ለዚህ ምናብ ኣስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮችን የመፈጸም ኣቅምና ፍላጎት ያላቸው ለዚህ ስራ ስሜታቸው የሚነቃቃ ሰዎች ደግሞ ኣሉ። በመሆኑም ስራና ሰራተኛን ማገናኘት የሚፈታውን ችግር “ኢሃደግ” ከየቦታው ታዛዞቹን ይሰበስብና የማይገባ ቦታ እየሰጠ እንደገና ደግሞ ኣቅም ኣነሰህ እያለ ይገመግማቸዋል። ስራና ሰራተኛን ማገናኘት በራሱ የሚፈታቸውን ጉዳዮች ችላ ማለት ኣገራዊ ኪሳራው ሰፊ ነው።
በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት መረጃዎችን የሚያዩበት መጠነ ርእይ ይለያያል። የታችኛው ኣካል በተወሰነ ኣጥር ውስጥ የሚያይ ሲሆን ወደ ላይ ከፍ ያሉ ባለስልጣናት ደግሞ በሰፊ ስኮፕ ያዩታል። ከፖሊሲና ከማህበራዊ ተጽእኖ (Impact) ጋር ስለሚያዩት የሚደመሙት በዚህ ሰፋ ባለ ተጽእኖና በዚያ ተጽእኖ ውጤት ላይ ነው። ለዚህ የሚመጥኑ ሰዎችን በየደረጃው ማስቀመጥ የተሻለ ሲሆን በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ኣንዱን የቴክኒክ ሰው ሚንስትር ማድረጉ ኣገሪቱን በጣም ጎዳት። ከግምገማ ይልቅ በትምህርት ሊበለጽጉ የሚችሉትን መለየት፣ ግምገማውን ሳይንሳዊ ማድረግ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን በተለይ ሲስተምን የማጽዳት ስራ መስራት ጠቃሚ ነበር። ስኮፕ የሌላቸውን ሰፋ ኣድርገው ማየት የማይችሉትን ኣጉሮ ኣጉሮ ምንም ለውጥ ማምጣት ኣይቻልም። በተበላሸ ፖሊሲ ስር የቱንም ያህል የግለሰብ ግምገማ ብናካሂድ ኣንለወጥም።ኢትዮጵያ ትታየናለች ወይ? የጥንት ኣባቶች ድካም ይታየናል ወይ? ስለ ሃገሪቱ ማንነት ስናስብ የጠራ ስእል ኣለን ወይ? እያልን የሚሾመው ቢሾም ይሻል ነበር። ኣንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻን ሲለምን እኔ ተራው ሰውና ኣንድ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ሰው ብናገኝና ብናናግር የሁለታችን ምናብና መደመም መለያየት ኣለበት። እኔ ካለኝ ኣካፍየ ካልሆነ ኣዝኘ እሄዳለሁ። ያ ባለስልጣን ግን ከፍ ካሉ ሃገራዊ ጉዳዮች ጋር ኣገናኝቶ ኣገራዊ ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችል ስእል ሊያይ ይገባል። በዚያ ጎዳና ተዳዳሪ ህጻን ምላሽ ፖሊሲን እስከማስቀየር በሚደርስ ሃይል ይህ ባለስልጣን ሊመሰጥበት ሊመታበት ይገባዋል። ስኮፕ እንዲህ ነው። ኢትዮጵያንም ኣጠቃላይ ኣካሉዋን በሚገባ የማየትና የመረዳት ብቃትን ይጠይቃል። ከዚህ ውጭ በኣካባቢያችን ያለችውን ችግር ኣይተን በዚያችው ዙሪያ የፖለቲካ ድርጅት መስርተን ለዚያች ችግር መፍትሄ ለማምጣት ብቻ የምንሞት ከሆነ ኢትዮጵያን ለመምራት ኣንመጥንም። መሪዎቻችን ባደጉበት ኣካባቢ ያዩትን ችግር በሰፊ ምናብ ካላዩት በብሄር ፖለቲካና በኢትዮጵያዊነት መካከል ውጥረት ውስጥ ገብተው ራእይ ኣጥተው ሊኖሩ ይችላሉ። ምናብ ለመሪዎቻችን በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ታላቁ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ኣንዱ ትልቁ ችሎታቸው ደቡብ ኣፍሪካን በይቅርታ መሰረት ላይ ቆማ በጠራ ምናብ ማየት መቻላቸው ነው። በጣም ግትር ከሆነ የፍትህ ኣስተሳሰብ ኣውጥቶ በዚህ ከፍታ ላይ ያስቀመጣቸው ምናባቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲህ ዓይነት መሪዎችን እንሻለን።
ትልቅ ችግር ያመጣው “ኢሃዴግ” እንደ ድርጅት ራሱን ኣለማየቱ ብቻ ሳይሆን ይህ ኣካል ስልጣን ላይ በመሆኑ ተጽእኖው ኣገራዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረጉ ኣሁን ላለንበት ውስብስብ ችግሮች ቀንደኛ ምክንያት ሆነ። የተቋማትን ነጻነት ለመገምገም ወይም የፓርቲውን ጣልቃ ገብነት ለመገምገም ባለሞሞከሩ ዛሬ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ገለልተኛ ኣልሆነም። ዛሬ “ኢሃዴግ”በኣምስተኛው ዙር “ምርጫ” በኦሮሚያ፣ በኣዲስ ኣበባ፣ በትግራይ፣ በኣማራ በደቡብ መቶ በመቶ ማሸነፉን ሲሰሙ “ኢሃዴጎች” ዴሞክራሲ ኣደገ ነው የሚሉት? ያ “ግምገማ” በርግጥ ሃቀኛ ከሆነ የዚህ ድርጅት ኣባላት እምቢኝ ማለት ነበረባቸው።ይህቺን ጽሁፍ ስጭር የቅርቡን የምርጫ ውጤት ሲሰሙ ኣንዳንዶቹ “የኢሕዓዴግ” ኣባላት ምን ይሉ ይሆን? ብየ ኣስቢያለሁ። እውነተኛ ለኣገር ኣሳቢ የሆነ ፓርቲ ውስጥ ነው ያለሁት የሚል ለኣገር ኣሳቢ የሆነ “የኢህዓዴግ” ኣባል በግምገማ ወጥሮ መጠየቅ ኣዲስ ምርጫ መካሄድ ኣለበት ኣለያ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ነበረበት፣ ኣልነበረበትም?:: በዴሞክራሲ የሚያምኑ ከሆነ ፣ ከዴሞክራሲ መገለጫዎች መካከል ኣንዱና ዋነኛው ምርጫ ሲሆን ውጥንቅጡ በወጣና ተዓማኒነት በጎደለው ምርጫ መቶ በመቶ ኣሸነፍኩ ሲለኝ በርግጥ ለዚህ መሞት ኣለብኝ።መቶ በመቶ ኣሸነፍኩ ብሎ “ኢሃዴግ” ሲያውጅ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆነ የዚህ ፓርቲ ኣባል ድግሱን ኣይበላም። ኣይበላም ብቻ ሳይሆን ይህ ታሪክ እንዲገለበጥ ኣጥብቆ ይሰራል። ኣለያ ቢሞት ይሻለዋል። ኣሁንም ቢሆን ሃቀኛ የሆኑ የኢህዓዴግ ኣባላት ለለውጥ መታገል ኣለባቸው። በስማቸው የሚነግዱትን ጥቂት የበላይ ኣካላት በመፍራት ዝም ማለት የለባቸውም። ለለውጥ ለተሻለ ስርዓት በቻሉት ኣቅም መታገል ኣለባቸው። ህዝባዊ እምቢተኝነት ሲነሳ ከህዝብ ጎን በመቆም ትግሉን ማፋጠን ይጠበቅባቸዋል። ፖሊሶች፣ ዳኞች፣ የባንክ ሰራተኞች፣ ወታደሮች፣ በኣየር ሃይል ኣካባቢ የሚታየውን ኣይነት ትግል ማፋፋም ኣለባቸው። ይህን በማድረጋቸው ከህሊና ፍርድ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን ከለውጥ ባሻገር ኢትዮጵያ ትኮራባቸዋለች።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
geletawzeleke@gmail.com
No comments:
Post a Comment