Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, June 29, 2015

በሰሜን አሜሪካ በየዓመቱ የሚደረገው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል/ESFNA ዛሬ በድምቀት ተከፈተ

በሰሜን አሜሪካ በየዓመቱ የሚደረገው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል ዛሬ በሜሪላንድ በርድ ስታዲየም በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በድምቀት ተከበረ:: ከአሜሪካ እና ከካናዳ የመጡ ከ30 በላይ ቡድኖች በስታዲየሙ በመገኘት በዚሁ በመክፈቻ ዝግጅት ላይ ራሳቸውን አስተዋውቀዋል:: በዚህ ዝግጅት ላይ ለእንግሊዙ አርሰናል ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው ጌድዮን ዘላለም የተገኘ ሲሆን ከሕዝቡም ደመቅ ያለ አድናቆት ተችሮታል:: በዚሁ የመክፈቻ ዝግጅት የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ ባሰሙት ንግግር የዘንድሮው ዝግጅት በርካታ ሕዝብ በመገኘት በመከፈቱ መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ቀናት ደማቅ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል:: እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ረቡዕ ምሽት የብሄራዊ ትያትር 60ኛ ዓመት በዓል በታሪካዊ ሁኔታ ይከበራል; የፊታችን ሐሙስ አርብና ቅዳሜም ከ እግር ኳሱ በተጨማሪ ታላላቅ አርቲስቶች የሚገኙባቸው ትልልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች እንደተዘጋጁና ሕዝቡም በነዚህ ስፍራዎች እየተገኘ እንዲዝናና ጥሪያቸውን አቅርበዋል:: የዘንድሮው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን 32ኛ ዓመት በዓል መታሰቢያነቱ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ላለቁት ኢትዮጵያን መታሰቢያ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተወካይ ባሰሙት ንግግር የሊቢያውን ሰቆቃ አስታውሰው “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አይረሳትም” ብለዋል:: የመድሃኔዓለም ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ተወካይ ቄስ በሪሁን መኮንን በሊቢያው ሰቆቃ ሊያስተምረን ስለሚገባ ነገር ተናግረዋል:: የሁሉም የሃይማኖት መሪዎች ልዩነት ሳይበግራቸው በአንድነት በመቆም ሊሰሩ እንደሚገባ ይህ ሃዘን አስተምሮናል ብለዋል:: በሰሜን አሜሪካ የሙስሊም ኮሙዩኒቲ ተወካይ ሼክ ሱለይማን ነስረዲን በበኩላቸው በሊቢያ የተገደሉት ወገኖች የተገደሉት ክርስቲያን በመሆናቸው ሳይሆን ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሃይማኖቶች መከባበር ለመጠቆም ሞክረዋል:: በዛሬው የመክፈቻ ጨዋታ የላስቬጋሱ አበበ ቢቂላ የሲያትሉን ዳሸን 2ለ0 – ዴንቨር የሚኒሶታውን ኒያላ 4ለ0 – ቺካጎ ፒላደልፊያን 2ለ1 – ኦሃዮ ቦስተንን 4ለ1 ሲያሸንፉ የሎሳንጀለሱ ዳሎል የዲሲው ዩናይትድ 1ለ1 እንዲሁም የሎሳንጀለሱ ስታርስ ከሜሪላንዱ ከቅዱስ ሚካኤል ጋር 1ለ1 ተለያይተዋል:: በሌላ በኩል የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ያሬድ ነጋሽ ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት በዛሬው የመክፈቻ ዝግጅት መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ቀናት በርካታ ሰው እንደሚገኝ ያላቸውን ግምት ገልጸዋል:: በሃይማኖት አባቶቹ መል ዕክት መደሰታቸውንም ገልጸዋል:: በድምቀት የተከፈተው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫልን በስፍራው የሚገኙት የዘ-ሐበሻ አዘጋጆች በየቀኑ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ይዘግቡላችኋል:: -
Like · Comment · 

No comments:

Post a Comment

wanted officials