Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, June 29, 2015

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን እየታገልኩ መሆኔ በክስ ማቅለያነት እንዲወሰድልኝ›› ወጣት ቴዎድሮስ አስፋው



እነ ቴዎድሮስ አስፋው ጥፋተኛ ተባሉ

• ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን እየታገልኩ መሆኔ በክስ ማቅለያነት እንዲወሰድልኝ›› ወጣት ቴዎድሮስ አስፋው

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ሰበብ ታስረው ‹‹ኢህአዴግ ሌባ ነው፣ ህገ መንግስቱ ወረቀት ነው፣ ታፍነናል፣ ታስረናል፣ መለስ የሞተው ደንግጦ ነው፣ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በቁሙ የሞተ ነው፣ ቴዎድሮስ ለህዝብ ነው የሞተው›› በሚል ብጥብጥና ሁከት ፈጥራችኋል፣ የሀሰት ወሬ አውርታችኋል ተብለው የተከሰሱት እነ ቴዎድሮስ አስፋው ዛሬ ሰኔ 22/2007 ዓ.ም አዲስ ከተማ ምድብ ችሎት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

ጥፋተኛ ከተባሉት መካከል አንደኛ ተከሳሽ ቴዎድሮስ አስፋው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሲሆን ያሬድ ደመቀ እና አንዋር ከድር የፓርቲው አባል አይደሉም፡፡ እነ ቴዎድሮስ ጥፋተኛ የተባሉት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ ህግ አንቀጽ 486/ለ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ነው ተብሏል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ወጣት ቴዎድሮስ ‹‹የተመሰረተብኝ ክስ የሀሰት ነው፡፡ የተሰማው ምስክርም የሀሰት ነው›› ሲል ውሳኔው ፖለቲካዊ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ዳኛው አንዴ ጠፋተኛ መባሉን በመግለፅ ውሳኔው ፖለቲካዊ መሆኑን ቅሬታ ማቅረብ እንደማይችል ገልጸው ማቅለያ እንዲያቀርብ በጠየቁበት ወቅትም ወጣት ቴዎድሮስ ‹‹የተባለውን ወንጀል ፈጽመዋል ብንባል እንኳ የነበረው ሁኔታ መታየት አለበት፡፡ 30 ኢትዮጵያውያን በጭካኔ የታረዱበት ወቅት ነው፡፡ በታሪካችን እንዲህ አይነት ውርደት አጋጥሞን አያውቅም፡፡ መንግስት የታረዱትን ወገኖቻችን ኢትዮጵያውይነት በሚክድ መልኩ ያወጣው መግለጫ ደግሞ የሚያበሳጭ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን አለመሆናቸውን ላጣራ ከማለቱ በተጨማሪ ለሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን መቀጣጫ እንደሚሆን መግለፁ ደግሞ በጣም አሳፋሪ ነበር፡፡ ተፈፀመ የተባለውን ነገር እውነት ነው ቢባል እንኳ በዚህ ስሜታዊ በሚያደርግ ሁኔታ የተፈፀመ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል›› ብሏል፡፡

ወጣት ቴዎድሮስ አክሎም ‹‹እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ህግ ተርጓሚው ገለልተኛ ሆኖ እንዲሰራ በመታገል ህግ እንዲሰፍን የራሴን አስተዋጽኦ እያደረኩ እገኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን እየታገሉ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል አንዱ መሆኔ በክስ ማቅለያነት እንዲወሰድልኝ›› ሲል የክስ ማቅለያ አቅርቧል፡፡ ከቴዎድሮስ በተጨማሪ ያሬድ ደመቀና አንዋር ከድርም የክስ ማቅለያዎችን አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ቴዎድሮስ ለክስ ማቅለያነት ያቀረባቸው የመንግስት መግለጫ፣ ህግ እንዲሰፍን እየሰራ መሆኑና ቀሪዎቹ ተከሳሾች በማቅለያነት ያቀረቧቸው ጉዳዮችን በማስረጃ እንዲያቀርቡና በማቅለያነት የቀረቡት ጉዳዮችም ማቅለያ መሆን እንደሚችሉና እንደማይችሉ ለመወሰን ለሐምሌ 3/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials