የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት የስዊድን ዜግነት ባለው ዶክተር ፍቅሩ ማሩና በሌሎች 120ሰዎች ላይ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የነፍስ ማጥፋትና የንብረት ውድመት ምክንያት ናቸው በማለት ክስ መስርቶባቸዋል።
ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ ከተነሳው የእሳት አደጋ እራሳቸውን ለማዳን ይጥሩ በነበሩ እስረኞች ላይ የመንግስት ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸው እንዲሁም ከ20የሚበልጡ እስረኞች ከአደጋው ጋር በተያያዘ ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወቃል።
አቃቢ ህግ ለፍርድ ቤቱ አንድም እስረኛ በጥይት ስለመታቱ ወይም የጥይት እሩምታ በእስረኞች ላይ ተከፍቶ እንደነበረ ሳያስረዳና ሳያቀርብ ቀርቷል። አቃቢ ህጉ ዶ/ር ፍቅሩ፣ ኢብራሒም ካሚልና ሸምሱ ሰዒድ የተባሉት እስረኞች ሌሎችን እስረኞችን በማስተባበርና መመሪያ በመስጠት እስር ቤቱን እንዲቃጠል አድርገዋል በማለት ክሱን አሰምቷል።
አቃቤ ህጉ በማከልም ለሟቾቹ ተጠያቂ በእነ ዶክተር ፍቅሩ የሚመራው ቡድን እንደሆነ መከራከሪያውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። በተጨማሪም ለማረሚያ ቤቱ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩት እስረኞች በዚሁ ቡድን ተደብድበውና ተቃጥለው ተገድለዋል በማለት አቃቤ ህጉ ከሷል።
ተከሳሾቹ (121) እስር ቤቱን እንዲያውኩ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ እንደነበረና ከ500,000 ብር በላይ እንደተሰጣቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል ገንዘብ እንዴት ከፍተኛ ቁጥጥር በሚደረግበት የቂሊንጦ እስር ቤት ሊገባ እንደቻለ አቃቤ ህጉ ማብራራት እና መልስ መስጠት አቅቶታል። ይልቁንስ አቃቤ ህጉ በክርክሩ ገንዘቡ የተሰጣቸው ለማረሚያ ቤቱ የጸጥታ ሃይሎች (ፖሊስ) መረጃዎችን የሚያቀብሉ እስረኞችን እንዲገድሉ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቶ ለፍርድ ቤቱ ገልጻል ፡፡
የስዊድን መንግስት በዜጋዋ በዶክተር ፍቅሩ ማሩ እስራትና ጤና ጉዳይ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ሲወያዩ እንደነበረ ይታወቃል። የስውዲን ዜግነት ያላቸው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በሙስና ክስ ተከሰው የአራት አመት ከስምንት ወር እስራት ብይን ከመቀበላቸው በፊት በልብ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ይገኙ ነበሩ። ዶክተር ፍቅሩ የአዲስ ካርዲዮቫስኩላር ማዕከል መሥራችና ባለድርሻም ነበሩ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እነዚህ 121ተከሳሾች ለ23 ሰዎች ህይወት ማለፍና ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት መውደም ተጠያቂ መሆን አለባቸው በማለት ክሱን አሰምቷል።
No comments:
Post a Comment