Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, January 23, 2017

ስለሂፕሆፕ የልጅ ሚካኤል እና ቴዲ ዮን ‘እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ ቀዳሚ’ ፉክክር- ከበፍቃዱ ዘ-ኃይሉ

ስለሂፕሆፕ እንጽፋለን!


ከበፍቃዱ ዘ-ኃይሉ | በፌስቡክ ገጹ ካሰፈረው የተወሰደ
አንዳንድ ወዳጆቻችን የልጅ ሚካኤል እና ቴዲ ዮን ‘እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ ቀዳሚ’ ፉክክር በማጣጣል፣ “ደሞ ለሂፕፖፕ!” ዓይነት ሽሙጥ አሽሟ:ጠዋል! አንድም ‘ሂፕሆፕ ደግሞ ምን ጥበብ ይጠይቃል?’ እንደማለት፤ አንድም ደግሞ ‘ከዚህ የበለጠ ስንት የሚያሳስበን ነገር አለ’ እንደማለት። የበለጠ የሚያሳስበንን ለማውራት እስኪፈቀድልን፣ ስለሂፕሆፕ ምርጥነት፣ ባሕላችን ስለመሆኑ ወዘተ… እንጽፋለን።
በነገራችን ላይ የሁለቱ መዘላለፍ የጀመረው ቴዲ ዮ የመጀመሪያውም፣ የመጨረሻውም ወዝ ያላት ሥራውን ‘ጉራጌ ቶን’ን በለቀቀ ማግስት ነው። (ቴዲ ከዚያ በኋላ የዘፈናቸውን ማንም የመንደር ልጅ አምስት ደቂቃ ቢሰጠው ግጥምና ዜማቸውን ጽፎ ይዘፍናቸዋል።) እና፣ ያኔ ቴዲ “እንዘፍናለን እኛ ሂፕሆፕ በአማርኛ” የሚል ስንኝ ማስገባቱ ልጅ ሚካኤልን ከነከነው። ለምን?! “ሂፕሆፕ በአማርኛ” የምትለዋ ቃል ራሷ ከያኔው ፓፍ (ልጅ ሚካኤል) የተቀዳች ነበረች (ልጁ እንደሚያምነው)። ፓፍ ወዲያው በለቀቀው ሲንግል “አራዳ ላራዳ መች ይሸዋወድና” በሚል ተቆጣ። ከዓመታት በኋላ ተወዳጅ አልበሙን አምና ሲለቅ፣ ይኸው ዘፈን ተካቶ ነበር። ለዛ ነው ቴዲ ዮ የመልስ ምት ዘንድሮ የሰጠው። ፉክክሩም የጦፈው ልጅ ሚካኤል እጅግ ስኬታማ በመሆኑ ነው።
ባታስተውሉት ነው እንጂ ልጅ ሚካኤል፣ ሂፕሆፕ እዚህ አገር ከጥቂት የቀን ድግስ (day parry እንዲሉት እነሱ) ታዳሚዎች ውጪ እንዲደመጥ ደክሟል። በምናውቃቸው አባባሎች፣ ተረቶች እና ዜማዎች አስውቦ ያመጣቸው እነ “ዘመናይ ማርዬ”፣ “ሳተናው”…፣ “ሂፕሆፕ ባሕላችን አይደለም” የሚሉ ‘ወግ አጥባቂዎች’ን ሳይቀር ወዝወዝ አድርጓቸዋል። የልጅ ሚካኤል ድምፅም ለዚሁ የተሞረደ ነው፤ የጎደለው ነገር ግን ቢኖር ቆፍጣናነት ነው። ሂፕሆፕ የቁጣ ስልተ-ምት ነው። በሂፕሆፕ ተፈቃሪ ራሷ የምትወደሰው በቁጣ ነው።
ሂፕሆፕ ባሕላችን አይደለም ለሚሉት ግዴታ ማዳመጥ ያለብን የባሕል ሙዚቃ አለመሆኑን እያስታወስኩ (እውነቱን ለመናገር የባሕል የሚባሉት ሙዚቃዎች እኔን ያሰለቹኛል)፣ ሂፕሆፕ ከሽለላ እና ከፉከራ ጋር ዘመዳማች መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ። ‘ፍሪ ስታይል ሂፕሆፕ’ የሚባለውን ዳንሳዊ መወራጨት ካያችሁት፣ የጋራ ሽለላ ላይ ሦስት አራት ሆነው ወዲያ ወዲህ እያሉ የሚፎክሩትን ዓይነት ቁጭ ነው።
ችግሩ፣ ይኼ ለኛ ሳይገባን በፊት የገባው ሶማሌ ካናዳዊው ራፐር ኬናን ነው። ኬናን ‘I come prepared’ በሚለው ዘፈኑ የቀረርቶ ሙዚቃ እያስደመጠ እንዲህ ይላል፣
“…I made the list this year
I’m honour roll, you ain’t know East African rock ‘n roll
You don’t know what time it is like your clock is old
You know ya’ll packin’ like the block is sold…”
መሐል ላይ ኬናን፣ ‘ረአታታታታታታታ…’ ሲል ስትሰሙት ነው ‘ተበላን’ የምትሉት። እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ገና እንሸልልበታለን።
የሆነ ሆኖ ከብዙ ብሶቶች በተጨማሪ በየቴሌቪዥኑ እጅ እጅ የሚሉ ጥንታዊ ባሕላዊ ዘፈኖችን ብቻ እንዲያዳምጥ ጫና የተደረገበት ከተሜ መሸሸጊያው ሂፕሆፕ ነው – በአማርኛም ሆነ በምንኛ። እና አሁን ሲያምረኝ የተባለውም ራፐር ኤም ሲያምረኝ ተብሎ የልጅ ሚካኤል ተፅዕኖ ያረፈበት አልበም አውጥቷል። ኮምኩሙት!
ከሂፕሆፕ ጋር ወደፊት!

No comments:

Post a Comment

wanted officials