Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, January 28, 2017

በህገወጥ መንገድ ወደ ዚምባብዌ ገብተዋል የተባሉ 34 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲጓዙ መደረጉ ተገለጸ



የዚምባብዌ ፍርድ ቤት በቅርቡ በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገሪቱ ገብታችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ 34 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲጓዙ መወሰኑን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘገቡ።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባለፈው ወር በህገውጥ አዘዋዋሪዎች ሲዘዋወሩ ተገኝተዋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በፊት ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ አስተርጓሚ ባለመገኘቱ ስደተኞቹ በእስር እንዲቆዩ መደረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያውያኑ ጉዳይ የተመለከተው የዜምባብዌ ፍርድ ቤት የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን መምሪያ 34ቱ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲሚመለሱ እንዲያደርግ ትዕዛዝ መስጠቱን ዚምባብዌ ኒውስ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።
ከ34 ኢትዮጵያውያን መካከል የ11 እና የ12 አመት ታዳጊ ህጻናት የሚገኙበት ሲሆን፣ ስደተኞቹ ዚምባብዌን በመሸጋገሪያነት በመጠቀም ወደ ደቡብ አፍሪካ የማቅናት ዕቅድ እንደነበራቸው ታውቋል።
የዚምባብዌ ፖሊስ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ እንደሌላቸው ገልጿል።
ይሁንና 34ቱ ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ፖሊስ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት በርካታ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል።
የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) በማላዊ ዛምቢያና ጎረቤት ሃገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
እነዚሁኑ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ አለም አቀፍ ድጋፍን በማፈላለግ ላይ እንደሆነ ያስታወቀው የስደተኛ ድርጅቱ ከወራት በፊት ከማላዊ ከ50 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አውስቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመንና የተለያዩ  ሃገራት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አለም አቀፍ የስደተኛ ድርጅቶች ሲገልፅ ቆይተዋል።
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ ወደ 90ሺ አካባቢ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመን የተሰደዱ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በአግባቡ ያልታወቀ ሰዎችም ወደ ተለያዩ ሃገራት መሰደዳቸውን የስደተኞ ድርጅቶች መረጃ የመለክታል።
በተያያዘ ዜናም፣ ባለፉት አምስት አመታት ወደ ዛምቢያ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው በእስር ላይ የነበሩ 147 ኢትዮጵያውያን ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሃገራቸው እንዲጓጓዙ መደረጉን የዛምቢያ መንግስት አርብ አስታወቁ።
የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ያመቻቸ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ለመውሰድ 150ሺ ዶላር (ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ) ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።
በዛምቢያ የአለም አቀፍ ስደተኛ ድርጅት የኮሚኒኬሽን ተወካይ የሆኑት በርታ’ህ ንጉቩሉ (Bertha Nguvulu) ከስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ መካከል ሁለት ሴቶች መሆናቸውን ለሉሳካ ታይምስ ጋዜጣ አስረድተዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials