በሰሞኑ ዜና የሕዉሐት ገዥ ስርዓት 130 ሰዎችን በሙስና በመጠርጠር በቁጥጥር ስር ማዋሉን በአገሪቷ የዜና አዉታሮች መግለፁ ይታወሳል። የ130 ሰዎችን እስር አስመልክቶ የፌደራል ኮሚሽን በሰጠዉ መግለጫ እነዚሁ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የሕዝብን ሃብትና ንብረት የግል ሃብት በማድረጋቸዉ፤ የመንግስት ቤቶችንና የመሬት ይዞታቸዉን ወደ ግል ንብረት በማዞራቸዉ፤ የባንኮችንና የካምፓኒ ባለቤትነተን ለግል ሃብታቸዉ አዉለዋል የሚል ሲሆን ይኽ ክስ ከዚህ በተጨማሪም የታክስ ማጭበርበርንም እንደሚጨምር ምክትል ኮሚሽነሩ ኮማንደር ድስታ አስመላሽ ለአገር ዉስጥ ሚዲያ በሰጠዉ መግለጫ አስታዉቋል።
የፌዴራል ኮሚሽኑ 260 ተጠርጣሪዎች ከሕዝብ በጥቆማ የቀረቡለት መሆኑን ገልጾ ሊያዙ ከሚገባቸዉ 206 ዉስጥ 130ዎቹ ብቻ በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን ሲገልጽ የተቀሩት ለምን በቁጥጥር ስር እንዳልዋሉ ፍንጭ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። እንደ ኮሚሽኑ ገልጻ ከሆነ ኮሚሽኑ አሁን በቁጥጥር ስር ከዋሉት የሙስና ተጠርጣሪዎች ዉስጥ የ 13ቱ ሃብትና ንብረታቸዉ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ መጣሉን ሲገልጽ 8 ትልልቅ የጋራ የሆኑ ካምፓኒዎች 4 ሕንፃዎች፤ 49 መኪናዎች፤ 22 ቪላዎችና 2 ፋብሪካዎችም እንዲሁ እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸዉን አያይዞ ገልጿል።
የተቀሩት ተጠርጣሪዎች በምርመራ ላይ እንደሆኑና ከነዚሁ ተጠርጣሪዎች ዉስጥ የመንግስት ባለስልጣኖች እና ባለ ሙያዎችም እንዳሉበት ሲገለጽ አንዳንድ ለዝግችት ክፍላችን አስተያየታቸዉን እንደሰጡት ከሆነ የሕዉሐት አስተዳደር በቅርብ ሆኖ ድርጅቱን በዋናነት ከሚዘዉረዉ ስብሐት ጀምሮ ከድርጅቱ በአንድም ይሁን በሌላ የለቀቁትን የድርጅቱ አባላቶችን ጨምሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃብትና ንብረት ዘርፈዉ የበለጸጉ መሆናቸዉ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ እያለ ዛሬ በሙስና ስም እያሰራቸዉ ያሉት ባለ ስልጣናት ምን አልባትም ከድርጅቱ በተለያየ ምክንያት ሊያስወግዳቸዉ የፈለጋቸዉን በሙስና ሰበብ ለማግለል የሄደበት መንገድ ሊሆን ይችላል ሲሉም ተጠምደዋል። በተያያዘ ዜናም አሁን የስልጣኑን ቁንጮ ይዘዉ ይኽንን ግፋዊ ሥርዓት ከሚመሩት የሕዉሐት ዋነኞቹ ባለስልጣኖች የአገር ሃብትና ንብረት በመዝረፍ ዋነኛ ተጠያቂ መሆን ሲገባቸዉ አሁን የሚደረገዉ ማንኛዉም ድርጊት የሕዝብን ሃሳብ ለማስቀየር ሥርዓቱ እየተጠቀመበት ያለዉ የሞኝ ዘፈን መልሶ መላልሶ እንደሚባለዉ አይነት ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።
No comments:
Post a Comment