በአካባቢው ከተንቀሳቀሱ የመንግስት ወታደሮች ውስጥ ቁጥራቸው የማይታወቅ የቆሰሉ ሲሆን፣ አንድ የፖሊስ አባል ለአሰሳ ከባልደረቦቹ ጋር ሲንቀሳቀስ በአካባቢው ባደፈጡ ተቃዋሚዎች በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል፡፡
ከባህር ዳር 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የጢስ አባይ ከተማ የአገዛዙ አመራሮች በየጊዜው በሚያደርጉት ጫና የተማረሩት የከተማዋ ነዋሪዎችና የአካባቢው አርሶ አደሮች ሰሞኑን በተደጋጋሚ በደረሰባቸው እንግልት በመማረር በትላንትናውና በዛሬው እለት በተካሄዱት የእምቢተኝነት ተቃውሞ ግጭቱ ተባብሶ ወደ ጦር መሳሪያ መማዘዝ በመሻገሩ ጉዳት መድረሱን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ለግጭቱ መነሻ የሆነው ባለፈው ነሃሴና መስከረም ወራት በአካባቢው በነበረው የእምቢተኝነት ተቃውሞ ችግር ፈጥራችኋል የተባሉ ወጣቶችን በአካባቢው ይኖሩ በነበሩ የህውሃት አባላት ጥቆማ በየእለቱ እየታፈኑ ወደ አልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው ነው፡፡
የወጣቶች ቤተሰቦች ስለ ልጆቻቸው እንዳይጠይቁ በመታፈናቸው ሁኔታው እየተባባሰ በመሄድ ተቃውሞው የተቀሰቀሰ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የአገዛዙ ወታደሮች ህብረተሰቡን በመናቅ ልጆቻችንን በየጊዜው በማፈን መውሰዳቸውና መግደላቸው ከምንችለው በላይ በመሆኑ ይህን የግፈኞች አሰራር በመቃወም በቤተሰቦቻችን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ለማስቆም መሳሪያ ለማንሳት ተገደናል ሲሉ ነዋሪዎች ለክልሉ ወኪላችን ገልጸውላታል።
በአካባቢው አሁንም በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በእምቢተኝነት ላይ ያሉትን ቤተሰቦችና ወጣቶችን ለመያዝ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
አገዛዙ በአስቸኳይ አዋጅ አማካኝነት አገሪቱን አረጋግቻለሁ በማለት ተደጋጋሚ መግለጫ ቢሰጥም በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የሃይል ጥቃቶች በአገዛዙ ወታደሮችና ደጋፊዎች ላይ እየተፈጸሙ ነው።
No comments:
Post a Comment