Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, January 22, 2017

ኢትዮጵያ ፈርስት? ወይስ አማራ ፈርስት???

ኢትዮጵያ ፈርስት? ወይስ አማራ ፈርስት???
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
እጅግ ያልበሰለው የጋዜጠኛ ጥያቄ!! አንድ የኢሳት ጋዜጠኛ ነው አሉ “አማራ በአማራነቱ መደራጀት አለበት!” ብሎ የሚያምንን የዝግጅቱ እንግዳ አድርጎ ያቀረበውን የአማራ ስሉጥ (አክቲቪስት) “ኢትዮጵያ ፈርስት (መጀመሪያ) ? ወይስ አማራ ፈርስት (መጀመሪያ) ?” ብሎ ጠይቆ ለማሳፈር እንደሞከረ ሰማሁ፡፡
አማራ በአማራነቱ መደራጀቱ የማይጥማቸው ገለሰቦች አማራ የሚደራጀው ሌሎቹ የወያኔ ቅፍቅፍ የሆኑ ጠባብ የጎሳ ድርጅቶች “ቅድሚያ ለጎሳችን!” እያሉ ከኢትዮጵያና ከሕዝቧ ጥቅም በተጻራሪ፣ ህልውናዋን ለአደጋ በሚዳርግ መልኩ ከኢትዮጵያ ይልቅ ጎሳቸውን እንደሚያስቀድሙት ሁሉ አማራም የሚደራጀው እንደነዚሁ ጠቦ ከሀገር ጥቅም በተጻራሪ የሀገርን ህልውናና ደኅንነት ለአደጋ በመዳረግ ቅድሚያ ለራሱ ለመስጠት እየመሰላቸው ከዓመታት በፊት ጀምሮ እኔ አነሣቸው የነበሩትን ነጥቦች በማንሣት “አማራ እንዴት ይጠባል? መጥበብ ለአማራ አያምርበትም! ፣ አማራ በአማራነቱ ተደራጀ ማለት ሀገርን ከራሱ በማስቀደም ከጥንት ጀምሮ ለዚህች ሀገር ህልውናና ደኅንነት ሁለንተናውን መሥዋዕት በማድረግ የከፈለውን ውድ ዋጋ ገደል መክተት፣ ከንቱ ማድረግ፣ አኩሪ ታሪኩን ማጠልሸት ማለት ነው! ፣ የጎሰኝነት አስተሳሰብ ፀረ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) አስተሳሰብ የሆነና በዚህም ምክንያት በሠለጠነው ዓለም የተጠላ የተናቀና የተወገዘ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው!” በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ ይደመጣሉ፡፡
ከዚህ ቀደም አማራ እንዴትና በምን ምክንያት፣ ለምን ዓላማ በአማራነቱ እንደሚደራጅ “የአማራ ሀገር አቀፍ
የፖለቲካ ድርጅት የመመሥረት አስፈላጊነትና ዓላማ አደረጃጀቱ!” በሚለው ጽሑፌ ላይ በጥልቀትና በስፋት ያተትኩት ጉዳይ ስለሆነ እዚህ ላይ ደግሜ አላነሣውም፡፡ ከዚሁ ይልቅ የዚህ ጽሑፌ ትኩረት
እነኝህ የአማራ ሀገር አቀፍ ድርጅት መመሥረቱ የማይጥማቸው ግለሰቦች በፍጹም ያልገባቸውን ነገር ማስረዳትና ነገሩ እንዲገባቸው ማድረግ ነው፡፡ ማሰብ ማገናዘብ የሚችል ጭንቅላት ከሌላቸው በስተቀር ይረዳሉ ይገነዘባሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
እነኝህ ሰዎች ያልገቧቸው ያልተረዷቸውና ሊገቧቸው ሊረዷቸው የሚገቡ በርካታ ቁምነገሮች አሉ፡፡
ስንጠቅሳቸውም፦ እነኝህ ግለሰቦች አማራ በማንነቱ ወይም በአማራነቱ የሚደራጀው ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ለመስጠት መሆኑን፣ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን ለመታደግ መሆኑን፣ አማራ የጠፋባት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ልትሆን ስለማትችል
ወይም አማራን ያጣች፣ የቀደመ ማንነቷ ብርቅዬ እሴቷ የተደመሰሰባት፣ ከስሯ የተነቀለች ኢትዮጵያ በድን ሀገር
ስለምትሆን ይህች ሀገር እንዲህ ዓይነት በድን ሀገር እንዳትሆን እንደሆነ አማራ በማንነቱ የሚደራጀው አያውቁም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች ጠባብ ተገንጣይ ቡድኖች “እንገነጠላለን!” የሚሉበት ምክንያት የአማራ በዚህች ሀገር መኖር
በራሱ ብቻውን የበታችነት ስሜት (Inferiority) እንዲሰማቸው ስለሚያደርጋቸውና ለአማራ ባላቸው ምክንያታዊ
ያልሆነና እውነት ላይ ያልተመሠረተ ጥላቻና ፍራቻ (phobia) እንደሆነ አያውቁም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች ጠባብ ተገንጣይ ቡድኖች አማራ ከዚህች ሀገር ቢጠፋ ወይም ባይኖር የመገንጠላቸውን ነገር ጨርሶ
አያነሡ እንደነበረ ምንም አያውቁም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች ተገንጣዮቹ ጠባብ ቡድኖች የአማራን ከዚህች ሀገር መጥፋት አጥብቀው የሚሹ መሆናቸውን አያውቁም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች አማራንና ትሩፋቶቹን ያጣች ኢትዮጵያ በፍጹም ልትኖር እንደማይገባ አቋም አልያዙም አያምኑም አያውቁም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች ይህች ሀገር ከማንነቷ፣ ከሥልጣኔዋ፣ ከቅርሷ፣ ከብርቅና ድንቅ እሴቶቿ ጋር ወደፊትም መኖር
ካለባት የአማራ መኖር የግድ አስፈላጊ ስለመሆኑ ምንም የያዙት ግንዛቤ የለም!፡፡
እነኝህ ግለሰቦች ኢትዮጵያ መኖር ካለባት አማራ በማንነቱ ተደራጅቶ መታገሉ የግድ የመሆኑ አስፈላጊነት በፍጹም
አልተገለጸላቸውም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች ጠንካራና ኃያል አማራ አለ ማለት ኢትዮጵያ ከክብሯ፣ ከሉዓላዊነቷ፣ ከታሪኳ፣ ከቅርሷ፣
ከማንነቷ፣ ከሥልጣኔዋ፣ ከባሕሏ ከወዘተረፈዋ ጋር የመኖር ዋስትና አገኘች ማለት እንደሆነ አይገባቸውም፡፡
እነኝህ ገለሰቦች አማራ ቅድሚያ ለራሱ ህልውና ካልሰጠ በስተቀር ኢትዮጵያ ከክብሯ፣ ከሉዓላዊነቷ፣ ከቅርሷ፣
ከታሪኳ፣ ከማንነቷ፣ ከሥልጣኔዋ፣ ከባሕሏ፣ ከእሴቶቿ ጋር ፈጽሞ መኖር እንደማትችል ፈጽሞ አያውቁም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው አማራ በመሆኑ ብቻ እንዲጠፋ አዋጅ ተነግሮበት ተፈጻሚ
እየተደረገበት ስላለ፣ የአማራ መጥፋት የሚገደው አካል የሌለ ሆኖ በመገኘቱና የአማራን የቤት ሥራ ሌላው ሊሠራለት
ስለማይችል፣ ራሱን ለማዳን ራሱ መነሣት ግድ ስላለው እንደሆነ አያውቁም፡፡
እነኝህ ግለሰቦች አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው ከሀገርና ከመላ ሕዝቧ ጥቅም በተጻራሪ ጎሳቸውን ማዕከል አድርገው
ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለጎሳቸው ጥቅም እንደሚማስኑት እንደሌሎቹ ጠባብ የጎሳ ድርጅቶች ከሀገርና ከሕዝቧ ጥቅም
በተጻራሪ በመቆም አማራን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዳልሆነ አያውቁም፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር እነኝህ ግለሰቦች “ጠባብነትን እንጠላለን! አጥብቀንም እንቃወማለን!” እንደማለታቸው
እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ጠባብነትን የሚያስተናግዱትን ጎሳ ተኮር ድርጅቶችን በሙሉ ማውገዝ መቃወም ሲገባቸው ወይም
ለጎሳ ተኮሮቹ ሽፋን እየሰጡ ጠባብነትን እንዲያስፋፉ አለማድረግ ሲገባቸው እነሱን አቅፈው ድጋፍ እየቸሩ ያውም
ተመሳሳይ ላልሆነና ሀገር አቀፍ ለሆነ የተቀደሰ ዓላማ እራሱን ለማደራጀት ጥረት እያደረገ ያለውን አማራን ግን
ያለስሙ ስም በመስጠት በማውገዝና እንቅፋት በመሆን ራሳቸውን መጥመዳቸው ነው፡፡
“ቅድሚያ ለጎሳየ!” የሚለው ወያኔአዊ ጠባብ የጥፋት አስተሳሰብ እንዲጠፋ ከተፈለገ የሚጠፋው ይሄንን አስተሳሰብ
በሚያራምዱ ጠባቦችን የሰው ልጅ ምንጩ አንድ እንደመሆኑ ትኩረታቸውን ጎሳ ላይ ማድረግን ትተው ሰብአዊነት ላይና
የዜጎች ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብት ላይ እንዲያደርጉ በማድረግ ሥራ ሲሠራ ነው እንጅ እነሱን አቅፎና
ደግፎ በመጓዝ፣ ድጋፍ አድናቆትን በመቸር አለመሆኑን እነኝህ ግለሰቦች ጨርሶ አያውቁም፡፡ ይህ ጎሳ ተኮር
አስተሳሰብ ከአማራ ውጭ ባሉ ጎሳና ብሔረሰቦች እስካለ ጊዜ ድረስ አማራ በማንነቱ አለመደራጀቱ ለዚህች ሀገር
ህልውናና ደኅንነት መተማመኛ ሊሆን እንደማይችል እነኝህ ግለሰቦች ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡
“ሌሎች ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ጭቆና ስለደረሰባቸው መብታቸውን ለማስከበር በጎሳቸው ወይም በብሔረሰባቸው መደራጀት
አለባቸው!” ብለው የሚያምኑ ግለሰቦች ከጭቆናም በላይ በሰው ልጆች ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ከባዱና የመጨረሻው
የሆነው የዘር ማጥፋት ኢሰብአዊ ጥቃት በግልጽ እና በስውር በወያኔና አጋሮቹ እየተፈጸመበት ያለውን የአማራን
መደራጀት “አግባብ አይደለም!” ሊሉ የሚችሉበት አንድም አመክንዮአዊ አግባብ አለመኖሩን ሊያውቁ ይገባል!!
እውነታው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አማራ መቸም ዘመን ቢሆን ደልቶት አያውቅም! በዚህች ሀገር ግፍና በደል
የተፈጸመበት ጎሳ ወይም ብሔረሰብ አለ ከተባለ የአማራን ኢምንት ያህል እንኳ እንዳልሆነ ጠንቅቀን ልናውቅ
ይገባል፡፡
በየመኖሪያ ጎጆው እየታጎረ በሽዎች የሚቆጠር ሕዝብ ከነነፍሱ እንዲቃጠል ከመደረግ የከፋ ግፍና በደል ምንም
የለምና፡፡ አማራ ለዚህች ሀገርና መላ ሕዝቧ ህልውናና ደኅንነት ዘብ ቆሞ እራሱን እንደሻማ ሲያቀልጥ፣ ልጆቹን
ንብረቱን ሁለንተናውን ሲሠዋ ነው የኖረው፡፡ ለዚህም ነው የአማራ ገበሬ ከሌሎቹ ጎሳዎችና ብሔረሰቦች በተለየ
መልኩ ድህነት የተንሰራፋበትና ጎስቋላ፣ ጎጆውም ደሳሳ ሊሆን የቻለው፡፡ “ለእግሩ እንኳን ጫማ የሌለው ድሪቷም!”
ተብሎ እስኪሰደብ እስኪዘለፍ ድረስ ለተዳረገበት ድህነት የተዳረገው፡፡
አማራ በገዢዎች እየተገፋ፣ እየተንገላታ፣ እየተበዘበዘ፣ ሁለንተናውን እያጣ፣ ለገዢዎች መጠቀሚያ ሆኖ ተጎሳቁሎ
መኖሩን እያወቀም እንዳልከፋው ሆኖ የኖረው ለሀገሩ ህልውና የግድ ሊከፍለው የሚገባ ዋጋ መሆኑን ስላመነና
ስላወቀም ነው፡፡ ያኔ በዚያ ዘመን ኑሮው እንዲህ የሰቆቃ ሆኖ ባይደላውምና የሽዎች ዓመታት ገዢዎቹ የአንድ
ቤተሰብ የትውልድ አባላት ቢሆኑም ቅሉ እነኝህ ከአብራኩ የወጡት ለሽዎች ዓመታት ሀገሪቱን ሲገዙ የኖሩት
የአንድ ቤተሰብ የዘር ኃረግ ያላቸው ገዥዎች ቢያንስ ሊያጠፉት የሚፈልጉ አልነበሩምና ከነጉስቁልናው ኑሮውን
ለመግፋት አልከበደውም ነበር፡፡
አሁን ግን የተለየ ሁኔታ ገጥሞታል፡፡ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር!” ሆነና ነገሩ እንዲጠፋ ተፈርዶበታል፡፡
ተፈርዶበታል ብቻም ሳይሆን እንዲጠፋ በሰፊው እየተሠራበትና እየጠፋም ይገኛል፡፡ ይሄ በመሆኑም የዚህች ሀገር
የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ለራሱ ቅድሚያ ሰጥቶ ራሱን መከላከልና እራሱን በመከላከልም ሀገርን ከጥፋት መታደግ ግድ ይለዋል፡፡ ማለት የፈለኩት በአጭር አማርኛ የሀገርና የአማራ ጥቅም ተወራራሽ እንጅ ተለዋዋጭ ወይም ተተካኪ አይደሉምና “ኢትዮጵያ ፈርስት? ወይስ አማራ ፈርስት?” ብሎ የአንድነት ኃይል የሆነውን አማራን መጠየቅ ሲበዛ አላዋቂነትና ነውርም ነው!!!
ምክንያቱም አማራ እራሱን ቢያስቀድም ራሱ ኖሮ ኢትዮጵያን በኢትዮጵያነቷ ዘለዓለማዊ ለማድረግ፣ እሱ ከሌለ
ኢትዮጵያ በኢትዮጵያነቷ መቀጠል ስለማትችል እንጅ እንደሌሎቹ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ወይም ለማፍረስ አይደለምና፡፡
በመሆኑም አማራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ህልውናና ደኅንነት “አማራ ፈርስት! ወይም ቅድሚያ አማራ!” ሊል ይገባል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

No comments:

Post a Comment

wanted officials