Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, January 14, 2017

ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ – (ክፍል ሁለት)





ውድ ፕሮፌስር ጌታቸው ኃይሌ፡

“ለውድ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ የውውይቱ መንስኤ” በእሚል ርእስ ባለፈው ሳምንት ያቀረቡአቸውን የትዕቢት ናዳዎችን፣ የብስጭት ውርጅብኞችንና የመከላከያ እሩምታዎችን ንቄ ትቼ፣ በእርስዎ ደረጃ ዝቅ ላለማለት ስል ከነሱ ውስጥ መልስ መስጠት ያለብኝን ብቻ በመጀመሪያ እሰጥና ወደ ቀድሞ ጥያቄዎቾ እመለሳለሁ፡፡ መልሶቼ ሁሉ ተደምረው የሌሎቹንም ግለሰቦች ሁሉ ጥያቄዎች ይመልሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በጥንቃቄና በቀና ልብ ያነበቡት ሰዎች ሁሉ መጽሀፉ ራሱ ጥያቄዎቻቸውን መልሶላቸዋል፡፡ መሪራስ አማን በላይ የግዕዝና ሱባ መዝገበ ቃላትን ቅጂ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቁዋም መስጠታቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት አሰፍርና በሸር ተልእኮአችሁ አንድነት ምክንያት የሱ ሸር ደስ ስለአሰኞት አንድ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ሰለተባለ ወደ እኔ ስለተላክ ጋዜጠኛ-ነኝ-ባይም ጥቂት እላለሁ፡፡ በተጨማሪም ከኔ የረጅም ዘመን ታሪክ ይልቅ የኢትዮጵያን ታሪክ የመቶ ዐመት ነው የሚሉትን ተገንጣይዎችና አስገንጣይዎች ታሪክ ስለ መምረጥዎ እና ‹‹የጠነዛ ገለጻ‹‹ ስለሚለው ሀረግ ትንሽ መግለጫ እሰጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አፈታሪክ ስለተከሰተበት አንድ ወቅት ትልቁ ባለታሪክ ክቡር ተክለጻድቅ መኩሪያ የጻፉትን እጠቅሳለሁ፡፡

ውድ አንባቢ ሆይ! መሪራስ አማን በላይ ባለ 441 ገጾች የሱባ እና የግዕዝ መዝገበቃላት ለህትመት አዘጋጅተው፣ አንድ ቅጂ ለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቁዋም፣ ሰኔ 17 ቀን 2001 ዐመተ ምሕረት ማበርከታቸውን የሚያሳይ የምስክር ወረቀት እታች ሰፍሮአል፡፡ ሰርቲፊኬቱ ፎቶግራፍ ስለተነሳ በጉልህ አይታይም፡፡ ይህን አስደናቂ፣ ባለም ላይ ብቸኛ የሆነውን መዝገበ ቃላት መሪራስ አማን በላይ ያገኙት ከኑብያ፣ ሱዳን ነበር፡፡ ወሪጅናሌው በድሮ ዘመን የተጻፈው ብራና ላይ ነው፡፡ የጠፋውን ቁዋንቁዋችንን ያተረፈልንን ይህን መዝገበቃላት ለህትመት እንዲመች መሪራስ አማን በላይ አዘጋጅተው ነበር ለዩኒቨርሲቲው የዳረጉት፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ግን መጽሃፉን በዐይናቸው ሳያዩና በጃቸው ሳይዳስሱ፣ እንዲሁም ሳይመረምሩ የሱባውን ፊደላትና ቁዋንቁዋውን አማን በላይ ራሱ የፈለስፈው ነው፣ ብለው ሰውዬውን ዋሾ ለማድረግና ከኑብያ የተገኘ ምንም መጽሃፍ የለውም ለማለት አውቀው ድርቅ ይላሉ፡፡ እሰቲ እግዚአብሄር ያሳያችሁ የአምላክ አእምሮ ካልሆነ በቀር የሰው ልጅ አእምሮ አንድ ጥንታዊ ከ 3000 ዐመት በፊት የነበረንና የጠፋን ቁዋንቁዋ መዝገበቃላቱን ከነፊደሉ በ 441 ገጾች ይፈጥራል? የሱባው እንኩዋን ቀርቶ የግዕዙንስ ብቻ ቢሆን ለመሆኑ ሙሉ መዝገበቃለት ከሱባ ጋር እንዲስማማ አድርገው ከአእምሮአቸው አንቅተው መጻፍ የሚችሉት ምን አይነት ላእለሰብአ(superman) ቢሆኑ ነው? አንባብያን ራሳችሁ ፍረዱ፡፡ ሃቁ ግን ይሀን ጥንታዊ የሱባ እና የግዕዝ መዝገበቃላት መሪራስ አማን ከሌሎች ብርቅዬ የብራና ጥቅሎች ጋር ያገኙት፣ በጀበል ኑባ፣ ኑብያ (ሱዳን) ነበር፡፡ ጥንታዊ ጽሁፎችን ከኑብያ ስለማግኘታቸው ይህ መዝገበቃላት ተጨማሪ መረጃ ነው፡፡ ለክፉም ለደጉም የምስክር ወረቀቱ እነሆ፡፡–

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ ወደ ሁለተኛው ነጥቤ ልግባና፣ ያ ቴዎድሮስ ጸጋዬ የተባለ ሰው መልካም ጋዜጠኛ መስሎ ለሰላማዊ ውይይት ብሎ ወደ ቴሌቪዥን ስቱዲዎው ጋበዘኝ፡፡ እኔም ምንም የጎንዮሽ ተልእኮ የሌለው ሀቀኛ ጋዝጠኛ መስሎኝ ግብዣውን ተቀበልኩ፡፡ ለካስ እሱ ተልእኮው ሌላ ኖሮእል፡፡ ጥያቄ በጥያቄ ላይ እንደማዕበል እየደራረበብኝ ለመመለስ ስሞክር መልሴን ፈርቶ እያፈነኝ በውይይት ፈንታ አተሃራ ገጥሞኝ ከጋዜጠኛ ስነምግባር ውጪ ሞገተኝ፡፡ እኔን እዛ ጋብዞ ራሱ ብቻ እየተናገረ ሊያስቆጣኝ ሲሞክር እኔም ኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ቁጣዬን እንዳላሳይ ተጠንቅቄ በተዕግስት አሳልፌ መተንፈሻ ባገኘሁ ቁጥር የምችለውን ያህል አስረድቼ ፕሮግራሙ አለቀ፡፡ በመጨረሻ ከስቱዲዮው ስሰናበት የኔን የተሻሉ ግጥሞችና ሌሎችም ሥራዎች ማወቅ አለማወቁን ጠየቅኩት፡፡ አዎን አውቃለሁ፤ አለኝ፡፡ ታዲያ ለምን እነሱንም ጠቅሰህ በቀና ኣላስተናገድከኝም አልኩት፡፡ አንተ ብዙ ተከታይዎች ስለአለህ እና ከዚህም በላይ ለመጻፍ እንደሚገባህ ለመጠቆም እና ተከታይዎችህ ያንተን መንገድ እንዳይከተሉ ነው፤ ሲል መለሰልኝ፡፡ ያለው አልተዋጠልኝም ነበር፡፡

የእሱን የእኩይ ተልእኮ የታዘቡት ኢትዮጵያውያን ህልቆመሳፍርት ተመልካቾች የጋዜጠኛ ግብረገብነት የሌለው ጋጠወጥ፣ እንግዳ ጋበዞ እንደማወያየት የሚነታረክ ስድ፣ ሰው ለቃለ-መጠይቅ ጠርቶ ከራሱ ጋር የሚያወራ እብሪተኛ፣ እያሉ በራሱ ፌስቡክ ወረዱበት፡፡ ኢትዮጵያም ስደውል በርካታ ሰዎች እንደተናደዱበት ተረዳሁ፡፡ ሁሉም የሚሉት ተልእኮ ይዞ ቀርቦ፣ አንተን ለማጋለጥ አቅዶ ራሱን አጋልጦ እና እሱ ራሱን አሳንሶ አንተን አገዘፈህ፣ ነው፡፡ ስለዚህ ፍቅሬን አሳነሰው፣ ብለው እርስዎ ደስ ሰለአሎት ነገሩ የተገላቢጦሽ መሆኑን ይረዱት፡፡ እኔ ከእርስዎ በሃሳብ ስላልተስማማሁ ብቻ እሱን መደገፎ በእኩይ አላማችሁ አንድ ዐይነት ሰዎች እንደሆናችሁ አርስዎ በተግባሮ አረጋግጠዋል፡፡ ሸርአችሁ እና መሰሪአዊ የአእምሮ አካሄዳችሁ አንድ ዐይነት ስለሆነብኝ ምናልባት እርስዎ የላኩትም ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ህሊና ያለዎት ትልቅ ሰው ቢሆኑ ኖሮ የኢትዮጵያን ሀዝብ አንድነትና ፍቅር በሚያንጸባርቅ ሀቀኛ መጽሀፍ ላይ ከሚያላግጥ የሸር መልእክተኛ ጋር አይሰለፉም ነበር፡፡ አሁን ግን ኢምንትነትዎን አስመስክረዋል፡፡ አሞሌ ጨው በዝናብ ሲማሙዋ ጂል ይስቃል፤ ብልህ ያለቅሳል፤ እንደተባለው ነው፡፡

ካንተ የ4000 ዐመት ታሪክ የእነዛ የኢትዮጵያ ታሪክ 100 ዐመት ብቻ ነው፣ የሚሉቱ ይሻለኛል፣ አልነበር የአሉት? ይህ አባባልዎ እጅግ አስደማሚ ነው፡፡ ለእኩይ የፖለቲካ ግባቸው ብለው ታላቁንና ረጅሙን እንዲሁም ገናናውን እና አኩሪውን የኢትዮጵያን ታሪክ ከአሳነሱት እና ከአዋረዱት ተገንጣይና አስገንጣይ ኃይሎች ጋር ለመሰለፍ መምረጥዎ የርስዎን ኢትዮጵያዊነት ከዚህ ቀደም ላልጠረጠሩት ለሃቀኞቹ ኢትዮጵያወያን ዱብ እዳ ቢሆንም፣ ተደብቆ ይኖር የነበረውን እውነተኛ ማንነትዎን ዛሬ ይፋ ስለአወጡት፣ እውነትና ንጋት አያደር ይጠራል የተባለውን ሀቅ አስመስክረዋል፡፡

ሌላ እርስዎ ደጋግመው ያነሱትና ያብከነክኖት፣ አንዳንድ ኢትዮጲስት ነን የሚሉ ፈረንጆች ስለኢትዮጵያ ታሪክ የሰነዘሩትን የተሳሳተ አስተያየት ‹‹የጠነዛ‹‹ ማለቴ ነው፡፡ ይህንንም ስል በአእምሮዬ ውስጥ የነበረው ኦሮሞዎች ለኢትዮጵያ ቁስ-አካል ስልጣኔ ያበረከቱት ምንም ፋይዳ የለም ብሎ ኦሮሞዎችን የተሳደበውን እንግሊዛዊው ኢ ኡልንዶርፍንና ስለኢትዮጵያ ያልጠለቀ ግንዛቤ የነበራቸውን፣ በስለላ የሚጠረጠሩትን አንዳንዶቹን ነበር፡፡ ርስዎ፣ ኡሉንዶርፍ ይሀን አቁዋሙን በሁዋላ ስላሻሻለ እንዲወቀስ አይገባም ባይ ነዎት፡፡ ሆኖም ሁዋላ በሰዎች ጫና ሃሳቡን ቢለውጥም መጀመሪያ የተፋውን ስድብ አያስረሳለትም፡፡ ከዛ በተረፈ ነቀፌታው ለስለላ ተግባር ኢትዮጵያን ከሚያጠኑቱ ውጪ፣ ሀገራችንን በቅንነት ሲመረምሩ እድሜያቸውን ያሳለፉትን እነ ፕሮፌሰር ሰምነርን፣ የረጅም ዘመን ወዳጄን ሪቻርድ ፓንክረስትን፣ የሳቸውን ልጅ አሉላን፣ ሃሮልድ ማርከስን፣ ቱቢያናን፣ ላንፍራንኮ ሪቺን፣ ዋሊስ በጅን እና የመሳሰሉትን እይነካም፡፡ ይሀ በዚህ አጋጣሚ ግልጽ ይሁን፡፡ ደግሞም በዛ አባባሌ እኔ ለማለት የፈለኩት እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ታሪካችንን ሁሌ ፈረንጆች እንዲያስተምሩን ከማድረግ ይልቅ የራሳችንን ምሁራን ኮትኩተን አሳድገን እነሱን መስማት ይገባናል ነው፡፡

ስለ አፈታሪክና ጽሁፈ-ታሪክ ትንሽ ለመናገር ፍቃዴ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት የታሪክ ዐይነቶች የሚያዛምዳቸው አንድና አንደ ነገር አለ፡፡ ታሪክ ይባላል፡፡ ሁለቱም ታሪክ ናቸው፡፡ በጅምላዊ አባባል ልነታቸው አንዱ የቃል፣ ሁለተኛው የጽሁፍ መሆኑ ነው፡፡ ጥንት በጽሁፍ ሰፍሮ የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በተለምዶ ዮዲት ጉዲት የምትባለዋ ፈላሻዋ አስቴር እኤአ በ878 ዐመተ ምሕረት አካባቢ የአክሱምን መንግሥት ከአፈረሰችበት ጊዜ ጀምሮ እሰከ አጼ አምደጽዮን ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ (እኢአ 1299) ማለትም ለ 421 ዐመታት ያህል ዳብዛው ጠፍቶ በቃል ወይም በአፈታሪክ ብቻ ይነገር ነበር፡፡ ታላቁን ንጉሠነገሥት አምደጽዮንን ይሀ ነገር አስግቶት፣ እንደ ክቡር ተክለጻድቅ መኩሪያ ትረካ፣ በድፍን ኢትዮጵያ የነበሩትን የኢትዮጵያን ታሪክ በ ቃል የሚያውቁትን ሊቃውንት አሰባስቦ አፈታሪኩን በመጽሃፍ አጽፎ፣ ጠፍቶ የነበረው ታሪካችን እነሆ፣ ብሎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታሪኩን እና ክብሩን መልሶለታል፡፡ ተክለጻዲቅ መኩሪያ እንደሚሉት የጥንቱ መጻህፍት የጠፉት በ ዮዲት ተቃጥለው ነበር፡፡ ስለዚህ አጼ አምደጽዮን እንደገና አጻፉአቸው፡፡ —

“ስለዚህ ከዮዲት ወዲህ እስከ አጼ አምደጽዮን ድረስ ታሪክ የሚጠቀሰውና የሚተረከው “ከአዋቂዎች ቃል በቃል በወረደው ብቻ ነበር፡፡ ይህ ብልህ ንጉሥ እዙፋን ከወጣ ወዲህ ይህ “ቃል በቃል የሚነገረው ታሪክ በቶሎ ከብራና ላይ ሰፍሮ ለልጅ ልጅ እንዲተላለፍ ካልሆነ “ወደ ፊት ሊጠፋ እነደሚችል ተገነዘበ ማለት ነው፡፡ …… ስለዚህ ያለፈ ታሪክ የሚያውቁትን “ሊቃውንቱን ሰብስቦ ታሪክ እንዲጻፍ አዘዘ ይባላል፡፡” (ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐጼ ይኩኖ አምላክ ስስከ ዐጼ ልብነ ድንግል፣ ገጽ 40)

የተክለጻድቅ መኩሪያ ትረካ እንደሚለን ስለዛ ዘመን የሚያወጋው አሁን በመጽሀፍ ማህደር ውስጥ የተቆለፈው ለ 421 ዐመታት በቃል ሲነገር የነበረው ታሪካችን መሆኑ ነው፡፡ ይህ የሚያረጋግጠው፣ ታሪክ በቃልም ቢሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ አፈታሪክን አቅልላችሁ የተሳለቃችሁት እርሶ ፕሮፌሰር ጌታቸውና መሰሎቾ እጅግ ተሳሰታችሁአል ማለት ነው፡፡ አፈታሪክ የታሪክ አንዱ ገጥታው ነውና፡፡



ከዚህ ቀጥሎ፣ ባለፈው ጊዜ ክፍል ሁለት ብዬ አቀርባለሁ ያልኩትን አቅርቤ ርስዎ ያነሱአቸውን በክፍል አንድ ላይ ያላካተትኩአቸውን ነጥቦች አሰፍራለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ልገልጽልዎ የምፈቅደው እኔ የሂስን አዋጅ የተከተለ ገንቢ አቃቂርንና ትችትን በደስታ እንደምቀበል ነው፡፡ አንድ መጽሃፍ ሂስ እንዴት እንደሚደረግ በሩስያ፣ በጀርመን እና በ ዩ ኤስ ኤ ለበርካታ ዐመታት ተምሬአለሁ፤ አስተምሬአለሁም፡፡ የርስዎን ያልተቀበልኩት ግን ሂስም ትችትም ያልሆነ ቁንጽልና አፍራሽ ስላቅ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ ሀቀኛ ሃያሲ የአንድን መጽሀፍ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ያቀርባል እንጂ ደካማ ብቻ የመሰለውን (ደሞ ለሱ ደካማ የሚመስለው ደካማም ላይሆን ይችላል፣) ነቅሶና ቆንጽሎ እያወጣ አይደረድርም፡፡ ስለቅድጅቱ ምንም ሳይል ጉድለት የመሰለውን ብቻ ከደረደረ አላማው ሂስ ማካሄድ ሳይሆን እንከን ቁፈራ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ የኔ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛወ የዘር ምንጭ የተሰኘው መጽሀፌ በሂደት ላይ የአለ ነው እንጂ አንድ ቦታ የቆመ አይደለም፡፡ ገንቢ አስተያየቶች ከአንባቢ ሳገኝ እያሻሻልኩት የሚጉዋዝ ነው፡፡ ለምሳሌ ርስዎ ያነበቡት ቅጂ ውስጥ ያልነበረ በቅርቡ በታተመው ቅጂ ላይ የህዝብ አስተያየት አስጭሮት እንደገና አጠናቅሬ ያወጣሁት መረጃ አለ፡፡ ስለዚህ በአንባቢ ገንቢ አስተያየት መጽሃፉ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡

ይህን ለርስዎ ምላሽ ያዘጋጀሁትን ጽሁፍ ባለፈው ሳምንት ላቀርበው ስል የርስዎ ክፍል ሁለት ቀድሞ ወጣ፡፡ የርስዎ ቀድሞ እንዲነበብና አንባቢውም ንባብ እንዳይደራረብበት አስቤ የኔን እንዲያዝ አደረግኩት፡፡ የርስዎን ጥያቄዎች በከፍል ሁለት እንደማስተናግድ በክፍል አንድ መጨረሻ በግልጽ ባስቀምጥም ይህን ልብ ያላሉና የቸኮሉ አንዳንድ አንባብያን ጥያቄዎቹን አላስተናገደም አሉኝ፡፡ እነሆ ከዚህ በታች ተስተናግደዋል፡፡ ቅደም ተከተላቸውን እንደተመቸኝ ነው ያደረግኩት፡፡ በቢጫ የቀለሙት እርስዎ የተቹዋቸው ናቸው፡፡ ጥቁሮቹ የኔ መልሶች ናቸው፡፡

ግን ከአማን በላይ መጻሕፍት አንዳቸውም እንደታሪክ ምንጭነት ለግምገማ ከሚያበቃ ደረጃ ላይ ያልደረሱ፥ አልፎ አልፎ በእውነት ታሪክ የተቀመሙ ልብ ወለድ ታሪኮች ናቸው።”



ፕሮፌሰር ጌታቸው ሆይ!

እርስዎ፣ እንዳው በጅምላው ልብወለድ፣ ልብወለድ ይላሉ እንጂ፣ ልብወለድ ምን እንደሆነ እና ከታሪክ በምን እንደሚለይ እንኩዋን ከቶም አላብራሩም፡፡ በምሁራዊ ትነተና ህግ መሰረት አንደ ሰው ስለ አንድ ዐእምሮአዊ ሥራ ከመተንተኑ በፊት የሚተነትንበትን መንገድ (ስልት) እና ቃላት ምንነት በግልጽ ማስቀመጥ አለበት፡፡ የኔን እና የመሪራስን ሥራዎች እንዳው በደምሳሳው መሀይሞች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ እርስዎ ልብወለድ ብለው ፈረጁ እንጂ፡ ልብወለድ ማለት ምን እንደሆነ የተለያዩ የሥነጥበብ ጠበብት የተናገሩትን ገልጸው የኛ ሥራዎች እንዴት ልብወለዶች እንደሆኑ አላረጋገጡም፡፡ ስለዚህ ትችቶ ከመሀይማዊነት ተላቆ ምሁራዊ ይሆን ዘንድ እርስዎ ልብወለድ የሚሉትን ቃል ገልጽው ተንትነው፣ ልብወለድ ናቸው ያሉአቸውን የኔን እና የመሪራስ አማን በላይን መጻህፍት ጠቅሰው ገጽ በገጽ እያመሳከሩ ልብወ;ለድ መሆናቸውን ማስረጃ በማቅረብ ለአንባቢው ያረጋግጡ፡፡ ታዲያ ይህን ሲያደርጉ፣ መሪራሰ የጻፉአቸው እርስዎ ልብወለድ የሚሉአቸው፣ መሪራስ፣ እኔ እና አስተዋይ አንባቢዎች ግን ጠፍተው የተገኙ እውነተኛ ታሪካችን የምንላቸው መጻህፍት ቁጥር ወደ ስምንት እንደሚደርሱ እንዳይዘነጉ፡፡



በኔ ግምት መሪራስ አማን በላይና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ብሔራዊ ሚቶሎጂ ደርሰዋል፡፡

ሚቶሎጂ፣ ያውም ብሄራዊ ሚቶሎጂ መድረስ ቀላል መስሎዎታል፡፡ ታሪክን ከመጻፍ ይልቅ ሚቶሎጀን ለመድረስ እጅግ ከባድ እንደሆነ አያውቁምን? እኔንና መሪራስ አማን በላይን ርስዎ ለዚህ ትልቅ ክብር ካበቁን እልል! ነው፡፡ እሰየው! ነው፡፡ እውነት እኛ ብሔራዊ ሚቶሎጂ ከደረስን የኢትዮጰያ ህዘብ ታላላቅ ሀውልቶች ያቆምንልን ይሆናላ! ዐለም የጋራ ማንነቱን፣ የወል ምንጩን እና አንድነቱን ደርሶ ካበቃ ከ 3000 እና 4000 መታት በሁዋላ እኛ የአእምሮ ፈንጠዝያችን እንዲህ ረቅቆ እና መጥቆ በ21ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጰያውያንን አንድ የሚያደርግ የጋራ ታሪክ እና ማንነት፣ በተጨማሪም ፍቅረ-ዝናብንና ሰላምን የሚያወርድ ሚቶሎጂ ወይም አፈታሪክ መጻፍ ከቻልን እጹብ፣ ድንቅ ነዋ! የእኛም የታላቅነት ደረጃ ከጥንቶቹ ሚቶሎጂ ፈጣሪዎች ከእነ ሆመር፣ ከእነ ፖልመሬኒያን እና ሌሎቹም ግዙፍ ሰዎች ጋር በ 21ኛወ ክፍለዘመን ሊመደብ ነዋ! እሰየው!!! እንደ አፍዎ ያድርግልና!!! ለማንኛውም ብሔራዊ ሚቶሎጂ ምን ማለት እንደሆነ በዝርዝር ገልጸው፣ የሚቶሎጂን ምንነት ያገኙበትን ምንጭ ጠቅሰው፣ የእኛ ጽሁፍ፣ ማለትም የመሪራስ ስምንት የታሪክ መጻህፍትና የኔ አንድ የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ እንዴት ሚቶሎጂ እንደሆኑ የመጻህፍቱን ስም እየጠቀሱ ገጽ በገጽ በቂ ማስረጃዎችን በመደርደር ለአንባብያን ያረጋግጡ፡፡ ከዚህም አያይዘው የግሪኩ፣ የህንዱ፣ የጣልያኑ፣ የእሰፔኑ፣ የፈረንሳዩ እና የጀርመኑ ሚቶሎጂ ከኛው እንዴት እንደሚለይና እንደሚመሳሰል ግልጥልጥ አድርገው አወዳድረውና አነጻጽረው አንባቢን ያሳምኑ፡፡ይህንንም ሲያደርጉ፣ ከመጽሃፉ ውስጥ ከእርስዎ አእምሮ በላይ የረቀቁትን አንዳንዶቹን አስደናቂ ክስቶቶች፣ ለምሳሌ ኦሮሞዎች፣ የጎጃም ዘረ-ደሸቶችና እነማይዎች አባታችን (ደሸት) እና ህይወት ከውሀ ውስጥ መነጩ ወይም ተገኙ የሚሉትን አንድ አረፍተ ነገር እና እኔም ከእዚሁ አነጋገራቸው ተነስቼ አባታቸው ውሀ ውስጥ ተጸንሶ ይሆናል፣ ያልኩትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነገሮችን ይዘርዝሩ፡፡ ደግሞም ስለ ውሀ ውስጥ መጸነስ ታምራታዊነት እርስዎ ስለአነሱ፣ የሴትና የወንድ ዘሮች ውሀ ውስጥ ከተገናኙ ሰው የማይጸነስበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ይገንዘቡት፡፡ ልጅ ለመጸነስ ወሳኙ ቦታው ሳይሆን የወንድና ሴት ዘሮች መገናኘት ብቻ ነውና፡፡ ስለ ታምራታዊ ታሪካችን ካወሱ፣ ከእኛ መጽሀፎች ውስጥ ጥቂቶቹን ብቻ ቆንጽለው አውጥተው ሳይሆን የኔና የመሪራስ መጻህፍት ተደምረው ወደ 3000 ገጾች ስለሚደርሱ፣ የርስዎ ማስረጃና ማሳመኛ ቢያጥር ቢያጥር 100 ገጾች ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህን እላይ የተጠቀሰውን ሁሉ ማድረግ ካልቻሉ ግን የእርስዎ ስር የሌለው ትችት አየር ላይ የተንሳፈፈ የመንደር አሉባልታ ነው ማለት ነው፡፡ 100 ውን ገጽ እዚህ ማውጣት ስለሚረዝም የተወሰነውን እዚህ አስቀምጠው የተረፈውን በተቀጽላ (አፔንዲክስ) ሊያያይዙት ይችላሉ፡፡

እዚህ ላይ እጅግ የሚደንቀው ነገር፣ እርስዎ የኔን መጽሀፍ፣ ከመጽሃፉ ምንነት ባልተያያዘ በራስዎ የግል ምክንያት ሚቶሎጂ ነው፣ ብለው ሲፈርጁ የሰሙ አንዳንድ ፊደል የቆጠሩ ሰዎች (አብዛኞቹ መጽሃፉን ያላነበቡ)፣ ራሳቸው የመጽሃፉን ታሪካዊነት ሳይመረምሩ፣ የርስዎን ቃል እንደቃለ እግዚአበሄር ተቀብለው እንደገደል ማሚቶ ማስተጋባታቸው ነው፡፡ ከእዚህም ሁኔታ፣ አንዱ ያለማስረጃ ብድግ ብሎ የሚለውን ራሳችን ሳናጣራ እንደገደል ማሚቶ የምናስተጋባ፣ እንዳው በደመ-ነፍስ የምንነዳ እንደ አለን ተረዳሁ፡፡ ለካስ እርስዎም ይህን ክስተት ከድሮ ጀምሮ ስለተረዱ ኖርዋል ስለ ፍቅሬ መጽሃፍ የፈልኩትን ብናገር ማስረጃ የሚጠይቀኝ አይኖርም፣ ብለው የተነሱት፡፡ ርስዎም ይህን መንጋዊ ሳይኮሎጂ ጠንቅቀው በማወቆ እንዲህ ዐይነቶቹን የህብረተሰባችንን ቀሊል ተጠቂዎች በቀላሉ እያሽከረከሩ ስለድርጊቶ በማንም ሳይጠየቁ ለዘመናት እንደኖሩ እና ዛሬ ሲጠየቁ ጥያቄውን ከድፍረት ቆጥረው እንደተንገበገቡ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ ሕበረተሰባችን ምን ያህል ወደሁዋላ እንደቀረ ይመሰክራል፡፡ ወደሚቀጥለው ሀሰታዊ አባባልዎ ልሻገር፡፡–

ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ ዐዋቂዎች ጥቂት ስለሆኑ አብዛኛው ሕዝብ ድርሰቶቻቸውን እንደ እውነተኛ ታሪክ ወስዶላቸዋል። ሕዝቡ ታሪክ ለመማር ዕድል እስኪያገኝ ወይም የሀገሩን ታሪክ የሚያውቅ አዲስ ትውልድ ተነሥቶ የአንድነታችንን እውነተኛ ምክንያት እስኪረዳ ድረስ በነዚህ መጻሕፍት መጠቀም ሊኖርበት ነው።



ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ አዋቂዎች ጥቂት ናቸው ማለት እውነት እይደለም፡፡ በግላቸው የንባብ ጥረትም ሆነ ቀደም ሲል በትምህርት ቤት የታሪክ ትምህርት እውቀታቸውን ያዳበሩ በርካታ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ ለጊዜው ድምጻቸውን አጥፍተው እንጂ ርስዎ የማያውቁአቸው የአዲሱ ትውልድ አባላት ባለታሪኮች ከኢትዮጵያም ውጪ አሉ፡፡



አብዛኛው ህዝብ ‹‹ድርሰቶቻችንን‹‹ እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርጎ መውሰዱን እና በነሱም አንድነቱን ለማጠናከሪያ መጠቀሙን መገንዘቦ ሲያስመሰግኖት ሀዝቡን ታሪክ አያውቅም ማለትዎ ግን ያስነቅፍዎታል፡፡ ታሪኩን የማያውቀው የግብጽን፣ የአረብን፣ የግሪክን፣ የአውሮፓን፣ የሩስያን እና የቻይናን ታሪክ ብቻ ሲማር የኖረው የእኔ እና የርስዎ ቢጤው እንጂ ሀዝቡ በትውፊትና በ አፈታሪክ ታሪኩን ያውቃል፡፡ በየገዳማቱና ደብሩ ያሉት እንደመሪራስ አማን በላይ ያሉት ሊቃውንት ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ አበጥረውና አንጠርጥረው ማወቅ ብቻ አይደለም ታሪኩንም በጽሁፍ አቆይተውልናል፡፡ ስለዚህም እናመሰግናቸዋለን፡፡

አማን በላይ የጻፋቸው ሁሉ በታሪክ ዓይን ሲታዩ ከሚቶሎጂነት አያልፉም። ሰውየው ሚቶሎጂውን የደረሰው ከእውነተኛው የነገሥታት ታሪክ ላይም የሚያስፈልገውን ያህል እየወሰደ ነው። ለምሳሌ የነገሥታቱ ስም ዝርዝር እውነት የሚመስለው ከእውነተኛ ታሪክ ምንጭ ስለተወሰዱ እንጂ ከጀበል ኑባ ተገኘ ከተባለው ሰነድ ውስጥ ተገኝቶ አይደለም።

ከጀበል ኑባ ተገኘ የተባለውን ሰነድ እርስዎ ስለዐላዩት እዛ ውሰጥ የነገሥታቱ ስሞች አለመዘርዘራቸውን እንዴት አወቁ? ይህን የጠየቅኮት ከርሶው ቃል ተነስቼ ነው፡፡ ስለዐላዩት ነገር መመስከርዎ ቅጥፈት አይሆንብዎትም?

እነዚህ በሱባ ቋንቋ የኢትዮጵያ የብራና ጥቅሎች የተባሉ ምንጮች ግን አማን በላይ ለሚቶሎጂው የፈጠራቸው ስለሆኑ በአካል የሉም። በዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ሽፋን ላይና ውስጥም ያሉት “የሱባ ቋንቋ” ሥዕሎች የአማን በላይ አንጎል የፈጠራቸውና ብዕሩ የሣላቸው ናቸው።

የብራና ጥቅሎቹ አለመኖራቸውን እንዴት አወቁ? እርስዎ ባለፉት 40 ዐመታት ከመሪራስ አማን በላይ ጋር ውለው አድረዋል ወይስ ሰነዶች የሚያስቀምጡባቸውን ስፍራዎች ለርስዎ አሳይተዎት ባዶ ሆነው ዐይተዋቸዋል? ወይንስ የፈለኩትን ያህል ብዋሽ የኢትዮጵያ ህዝብ ያምነኛል ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ ገር ስለሆነ ንቀውት ነው? እርስዎን የመሰለ በእድሜው ትልቅ ሰው እንዴት ነጭ ውሸት ይዋሻል? ለመሆኑ እሳቸው ብራናዎቹን የት ነው ያስቀመጡአቸው? በሱባ ቁዋንቁዋ የተጻፉትን ጽሁፎች እሳቸው ከአንጎላቸው አፍልቀው ሲከትቡ እርስዎ በዐይንዎ በብረቱ ዐይተዋል እንዲህ በእርግጠኝነት የሚናገሩት? ከዐላዩ (እውነቱ ግን ዐላዩም) እሱ የፈጠራቸው ናቸው ሲሉ፣ ደግመው ዋሹ ማለት ነው፡፡

የንግሥተ፣ ሳባ ስም ኤትያኤል የእናቷ ስም አዝሚና ነው። ይህ የአማን በላይ ልብወለድ ታሪክ ከእውነተኛው ታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። እነዚህ ስሞች ከአማን በላይ ሚቶሎጂ ውጪ የትም እሌላ ቦታ አይገኙም። ብሉይ ኪዳን ስሟን ሳይጠራ “የሳባ ንግሥት” (በዕብራይስጥ “ማልከት ሽባ”) ብሎ ነው ያለፈው። ዐረቦች “ቢልቂስ” ይሏታል። ክብረ ነገሥቱ “ማክዳ” የሚለው እሷን ሊሆን ይችላል፤ ግን አጥጋቢ ማስረጃ የለንም።

አረቦች ቢልቂስ የሚሉት ‹‹ቢልቅስን‹‹ እንጂ ‹‹ማልክት ሽባን‹‹ አይደለም፣ ነው የምሎት፡፡ በደንብ ያዳምጡ! ንግሥተ-ሳባ ማለት “የሳባ ከተማ ወይም ሀገር‹ ንግሥት”‹ ማለት እንጂ እናትና አባትዋ ያወጡላት ስም አይደለም፡፡ ክብረ ነገሥቱ “ማክዳ” የሚለው እሱዋኑ ነው፡፡ “ማክዳ” ግን የስድብ ስም ነው፡፡ ልጅዋ ምኒልክ እስራኤል ሄዶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ 40 ሺህ እሰራኤሎችን ይዞ ስለተመለስ፣ የውጪ ሰዎችን ይዞ መምጠቱን እና የወገኖቻቸውን የነ ኢትዮጵን ስርወመንግሥት ጥሎ አዲስ የሰለሞንን ስርወመንግሥት ሊመሰርት ማቀዱን ያልወደዱ የአዘቦና ራያ ሰዎች ስለተዋጉት ርስዋ በሰተጀርባ መጥታ፣ ወገኖችዋን ኢትዮጵያውያኖችን ክዳ፣ ለልጀዋና እሱ ከእስራኤል ይዞአቸው ሰመጣው አጋዝያን አግዛ ስለተዋጋቻቸው “ማክዳ” “ከሃዲዋ” አሉአት፡፡ ይህን ከዚህ በፊት ሰምተው ካላወቁ አሁን ይወቁት፡፡ ዝም ብለው የመሪራስ አማን ፈጠራ ነው ሲሉ አይክረሙ፡፡ ሳባ ወይም ማክዳ መጠሪያ ስምዋ ካልሆነ፣ ታዲያ ስምዋ ማነው? እናትና አባትዋ ስም ሳያወጡላት “እገሊት!” ወይም “አንቺ ልጅ!” እያሉ ነበር እንዴ፣ የሚጠሩዋት? ወደዱም ጠሉም፣ ይህን ተቀበሉ አልተቀበሉም፣ ስለዚህ ከዚህ ቀደም አነበቡም አላነበቡም፣ መሪራሰ በአገኙት ታሪከነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ላይ የተመዘገበው ስምዋ “ኢትያኤል” ነው፡፡ በሱባ ቁዋንቁዋ “ኢትያኤል” ማለት “የእግዜር ስጦታ” ነው፡፡ ቢልቂስ ግን ንግሥተነገሥታት ኢትያኤል በየመን ላይ ሾማ ያነገሠቻት ዘረ,-ኢትዮጵያዊት ሴት ናት፡፡ ይህኛውን ሀቅ፣ ማለትም ቢልቅስና ኢትያኤል ሁለት የተለያዩ ሴቶች ስለመሆናቸው ከመሪራስ መጻህፍት ውጪ ስመ-ጥሩዎቹን ባለታሪኮች እነ ስርገው ሃበለሠላሴን ጠቅሼ አስረግጬ ከትቤዋለሁ፡፡ መጽሀፌ ውሰጥ ገብተው ይመልከቱ፡፡ አረቦች (የመኖች) እና እርስዎ ቢልቂስን አረብ ነች የምትሉት ፍጽም ሀሰት ነው፡፡ ቢልቂስ፣ እናትዋ ኢትዮጵዊት የሆነች አባትዋ የየመን ንጉሥ የነበር፣ አባትዋ ሲሞት አለቃዋ ኢትያኤል (ንግሥተ-ሳባ) በየመን ግዛትዋ ላይ ያነገሠቻት ሴት ነች፡፡ አረቦች እንኩዋን በውናቸው በህልማቸውም የሴት ንገሥት ሾመው አያውቁም፡፡ እንኩዋን ድሮ እስቲ ዛሬ በወንዶች ላይ የነገሠች አንዲት የአረብ ንግሥት ያሳዩኝ፡፡ ሴትን ያነገሥን ስልጡኖቹ እና ረቂቅዎቹ፣ በሴት ልጅ ነጻነት አማኞቹ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን፡፡ ዐራት ነጥብ፡፡



ቀደም ብሎም ቀዳማዊ ምኒልክ የእናቱ ወገን ከሆኑት ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲዋጋ ያገዙት ወታደሮች አግአዚ የተባሉ ከጋዛ የመጡ እሥራኤሎች ነበሩ። አግአዚ የተባሉት ከጋዛ ስለመጡ ነው ይላል። ይህ የልብ ወለድ አባባል ከታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። አግዓዚና ጋዛም ከድምፅ ፣መሳሳይነት ያለፈግንኙነት የላቸውም። ደግሞስ በምን ምክንያት ነው ቀዳማዊ ምኒልክ የእናቱ ወገኖች ከሆኑት ጋር የሚዋጋው

የጦርነቱ መንስኤ እላይ ተጠቅሶአል፡፡ አግአዚ በአማርኛ ሲተረጎም ‹‹ነጻ አውጪ‹‹ ማለት ነው፡፡ ነጻ የሚያወጣ ደግሞ ጦረኛ ነው፡፡ ማሃትማ ጋንዲን ካልሆነ በቀር፡፡ ከጦርነት ጋር ግንኙነት ከሌለው አጋዚ ለምን ‹‹ነጻ አውጪ‹‹ ተባለ? ቀዳማዊ ምንይልክ የውጪ ሰዎችን ይዞ ሲመጣ የእናቱ ወገኖች ባለመደሰታቸው ስለተዋጉትና አጋዚዎች ስለ አሸነፉለት ‹‹ነጻ-አውጪ‹‹ አላቸው፡፡ ከጋዛ የመጡት ሰዎች አጋዚ የተባሉት ምናልባት ከጋዛ የመጡ ስለሆኑ ይሆናል፤ ያልኩት ሌላው ምከንያት ስምና ግብራቸው ተመሳሳይ በመሆኑ ነው፡፡ የቃሉ ስር ተመሳሳይ በመሆኑ፡፡ ዳሩ ግን፣ ይህ የኔ ግምት ነው፡፡ በእዚህ ብዙ አልከራከርዎትም፡፡ ለወትሮው በግእዝ አግአዚ ‹‹ማለት ነጻ አውጪ‹‹ ማለት ነው ተብሎ የለ? ይህን ርስዎ መቼ አጡትና? ይህን ርስዎ ዝም ያሉት ‹‹ማንን፣ ከምን ነው ነጻ የሚያወጣው ብዬ እንዳልጠይቅዎት ነው፡፡ ሆኖም አሁንም መጠየቅዎ አልቀረሎትም፡፡

በኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ላይ ብዙ በኦሮሞ ስሞች የተጠሩ ቦታዎች አሉ። እነዚህ የቦታ ስሞች ኦሮሞዎች በ16ኛው ምእት ዓመት ኢትዮጵያን ሲይዙ የተሰየሙ እንጂ፥ ለዶክተር ፍቅሬ እንደመሰለው፥ ጥንታዊነት የላቸውም። ከ16ኛው ምእት ዓመት በፊት እንደሌሉ ማስረጃው ከዚያ በፊት በተሣሉ ካርታዎች ላይ አለመገኘታቸው ነው።

ዛሬ በኦሮሞ አባቶች ስም የሚጠሩ በርካቶች የቦታ ስሞች ክ 16ኛወ ምእት ዓመት ጀምሮ እንደሚጠሩ ዶ/ር ፍቅሬ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ለዚህም ማስረጃው ዛሬ ወሎ ተብሎ በአንድ የኦሮሞ ባላባት የሚጠራው ክፍለሃገርና የጁ የተሰኘውም ከዛ በፊት ‹‹ገነቴ እና ላኮመልዛ‹‹ ይባሉ እንደነበር፣ የዛሬው ‹‹ሸዋ‹‹ ጥንት (ከ 3000 ዐመታት በፊት) አማሮች ሲኖሩበት ግራርጌ፣ በሁዋላ አህመድ ግራኝን የአገዙት የሰሌ ጎሳዎች ሲሰፍሩበት ደግሞ ‹‹ሰላሌ‹‹ እንደተሰኝ ዶ/ ፍቅሬ በመጽሃፉ ገጾች 259 እና 260 ላይ ፍንትው አድርጎ አስቀምጦታል;; እነዚህን ገጾች ይመልከቱ፡፡

ንግሥተ ሳባን “እየሱስ ክርስቶስ “የአዘቦ ንግሥት” ሲል ጠርቷታል ይልና ማብራሪያውን እንዲህ ሲል ይቀጥላል፤ “አዜብ” የሚለው ቃል ከየት የመጣ ነው? ከንግሥተ ሳባ ህልውና 900 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ይገዛ የነበረ ንጉሥ ስም ነው” ይላል። ይኼ አነጋገር ለሚቶሎጂም እንኳን ይበዛል። ወንጌላውያን ቃሉን በግሪክኛ እንደመዘገቡት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላት “ባሲሊሳ ኖቱ” ነው። ይኽ ወደ ግዕዝ ሲተረጐም “ ንግሥተ አዜብ”፥ ወደ አማርኛ ሲተረጐም “የደቡብ ንግሥት”፥ ወደ እንግሊዝኛ ሲተረጐም “Queen of the south” ይሆናል። ኖቱ፥ አዜብ፥ ደቡብ፥ south አራቱም ትርጕማቸው አንድ ነው። ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ወንጌሎቹ የተጻፉት በግዕዝ መስሎታል።

ስለንግሥተ-ሳባ ማንነት አንደኛ እላይ አብራርቻለሁ፡፡ ሁለተኛ፣ በ 53 ገጸች ከበቂ በላይ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ማስረጃዎች አቅርቤ በማስረጃዎች አስሬዋለሁ፡፡ ሁለተኛ፣ ለርስዎ በጻፍኩልዎት መልስ ከፍል አንድ ውስጥ አስፍሬሎዎታለሁ፡፡ ያጢኑት፡፡ ከዛ ውስጥ ጥቂቱን ለመድገም፣ ርስዎ እንደሚሉት ቢልቂስ ሳባ እና የአረብ ንገሥት ከሆነችስ አረቦች ለምን እንደኛ ሰሎሞናዊ ስርወ-መንግሥት አልመሰረቱም? ለምን እንደ እኛ ታቦት የላቸውም? ለምን እንደኛ በመጽሀፍ ቅዱስ ውሰጥ አልተወደሱም ወይም አልተጠቀሱም? ለምን እንደኛ ትንቢትስ አልተተነበየላቸውም? ለምን እንደ እኛ የሰለሞን ዝርያ ነን የሚሉ ለ 3000 ዐመታት የነገሡ 225 ነገሥታት የላቸውም? ነው ወይንስ የርስዎ ቢልቂስ ከሰለሞን ልጅ አልወለደችም? መልሱን እኔው እነግርዎታለሁ፡፡ አዎን አልወለደችም፡፡ እናትዋ ‹‹ኢትያኤል‹‹ ስትል በልጅነትዋ ስም ያወጣችላት የኛዋ ንግሥተ-ሳባ ግን ከንጉሥ ሰለሞን ምንይልክን ሰለወለደች እሱ ይዞት የመጣው ታቦት እኛ አለን፡፡ ወሪጅናሉ ታቦት የለም ቢባልም እንኩዋን ግልባጮቹ በየቤተክርስትያናቱ ሞልተዋል፡፡ ቀዳማዊ ምንይልክ የሰለሞንን ስርወመንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ መስርቶ እሱን ራሱን ጨምሮ ለ 3000 ዐመታት የነገሡ 225 ነገሥታት እና ንግሥተነገሥታት ነበሩን፡፡ አጼ ኃይለሥላሴ የመጨረሻው ሰለሞናዊው ንጉሠነገሥት ነበሩ፣ እንላለን፡፡ አግአዝያን፣ ፈላሾችና ኦሪታዊው የአይሁዳውያን ሃይማኖትም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገቡና ሊኖሩ የቻሉት ንግሥተ-ሳባ (ኢትያኤል) የኢትዮጵያና የባህርማዶ ንግሥተ-ነገሥታት ሆና ሳለ ከኢትዮጵያ ተነስታ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ፣ ከንጉሥ ሰለሞን ምኒልክን በመውለድዋ ነው እንላለን፡፡ አርስዎ ግን ይህን ታሪካችንን ያጣጥላሉ፤ ይክዳሉ፤ አፈታሪክ ነው ይላሉ፤ እሱንም እስከነአካቴው ለአረቦች ይዳርጋሉ፡፡

“ዶክትር ፍቅሬ ወንጌሎቹ በግዕዝ የተጻፉ መስሎታል፤” ስለአሉት ግን “ዶክተር ፍቅሬ ወንጌሎቹ በኦሮምኛ የተጻፉ መስሎታል፤” ስለ አላሉ አመሰግኖታለሁ፡፡ የዋህ አንባቢ እስከ አገኙ እንደዛ ለማለትም የሚገድዎት ነገር ስለሌለ፡፡

“ጎሳ “ጐሥዐ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ነው” ይላል። ልክ አይደለም፤ በሁለት ቋንቋዎች ውስጥ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸውቃላት ሁሉ ተመሳሳይ ሥርና ትርጕም እንዳላቸው የሚያውቅ

በግእዝ ቁዋንቁዋ የተራቀቁትና የታፈሩት፣ በ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እንደ እርሶው የፊሎሎጊ (የቁዋንቁዋ) ተመራማሪ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን፣ ህያው ልሳን መዝገበ-ቃላት ግዕዝና አማርኛ በተሰኘው መጽሃፋቸው ገጽ 214 ላይ ‹‹ጎሥዐ‹‹ የሚለውን የግዕዝ ቃል ወደ አማርኛ ሲተረጉሙ ‹‹አገሳ፣ ጮኽ፣ ተናገረ፣ አፋሸክ፣‹‹ ብለውታል፡፡ እንግዲህ በግዕዝ ‹‹ጎሥዐ‹‹ የሚለውን ቃል በአማርኛ ‹‹አገሳ‹‹ አሉት እንጂ ‹‹አገሳአ‹‹ አላሉትም፡፡ ይህ የግዕዝ ቃል በአጭሩ የሚገልጸው ድምጽን ከውስጥ ማፍለቅን ወይም መናገርን ነው፡፡ በግዕዝ ‹‹ጎሥዐ‹‹ የሚለውን አማርኛ ተናጋሪው በአማርኛ ‹‹ዐ‹ ን ገድፎ ‹‹ጎሳ‹‹ ይላል፡፡ በግዕዝ ‹‹በለአ‹‹ ‹ሰመአ‹‹ ‹‹ሰባአ‹‹ ‹‹ረግአ‹‹ ‹‹ቀንአ‹‹ የሚለውን በአማርኛ ‹‹በላ‹‹ ‹‹ሰማ‹‹ ‹‹ሰባ‹‹ ‹‹ረጋ‹‹ ‹‹ቀና‹‹ እንደሚል ሁሉ፡፡ ‹‹

በግዕዝ ‹ጎሳአ‹‹ የሚለው ቃል ንግግርን የሚገልጽ ወይም የቁዋንቁዋ ከፍል ስለሆነ የደም ዘርን አይመለከትም፡፡ ስለዚህ የአማራ ጎሳ፣ የኦሮሞ ጎሳ፣ ስንል ቁዋንቁዋን እንጂ ዘርን አይጠቅስም፡፡ በመጽሃፌ ውስጥ በዚህ ዐይነት የጎሳን፣ የዘርን እና የነገድን ልዩነት ግልጥልጥ አድርጌ አስቀምጨዋለሁ፡፡ ይህንን ሁሉ በማስረጃ አስደግፌአለሁ፡፡ ‹‹ጎሳ‹‹ የሚለው ቃል ከግዕዙ ‹‹ጎሥዐ‹‹ እንደወጣ በአመክንዮ አሳይቻለሁ፡፡ እንግዲህ ርስዎ አይደለም ከአሉ፣ ‹‹ጎሳ‹‹ የሚለው ‹‹የአማራ ጎሳ፣ የኦሮሞ ጎሳ‹‹ በተሰኘው ስም ውስጥ የሚገባው ቃል ከየት እንደመጣ እስቲ ይንገሩን፡፡ ጎሳ የሚለው የጋራ ቁዋንቁዋ ያለቸውን ሰዎች በልሳነ-ቃል የሚያዛምዳቸው ስም ከየት ተገኘ?

ገጽ 101 ላይ በአማርኛ ፊደል የተጻፈ ኦሮምኛ ክርታስ (ጥቅል) አትሞ፥ “የጥቅሉን እድሜ በትክክል ልነግርዎ አልችልም፤ እንደሚያዩት ግን እድሜ-ጠገብ ይመስላል። ቢያንስ አንድ ሺ ዓመት እገምተዋለሁ። በአንድ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ነው የተገኘው” ይለናል። አንደኛ፥ ከብራና ጽሑፍ ጋር በቂ ልምምድ የሌለው ሰው ጽሑፉን አይቶ እድሜውን መገመት አይችልም። ሁለተኛ፥ የተጻፈው በአማርኛ ፊደል እንጂ፥ በግዕዝ ፊደል አይደለም። እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚታዩት እነ “ጨ” እነ “ቸ” ከአንድ ሺ ዓመት በፊት አልተፈጠሩም ነበር። ሦስተኛ፤ የጠቅላላ ፊደሎቹ አጣጣል እንደሚያመለክተው፥ የዚህ ጽሑፍ እድሜ ከአንድ መቶ ዓመት አይበልጥም።

እላይ ያልኩት “የጥቅሉን እድሜ በትክክል ልነግርዎ አልችልም፤ እንደሚያዩት ግን እድሜ-ጠገብ ይመስላል። ቢያንስ አንድ ሺ ዓመት እገምተዋለሁ። በአንድ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ነው የተገኘው” ነው፡፡ አዎን ይህን ብያለሁ፡፡ አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ ዕድሜውን በትክክል ለመናገር አልችልም፡፡ ሆኖም አሮጌ መሆኑን ልገምት አሚያግደኝ ነገር የለም፡፡ ማንም ሰው ቢሆን አዲስንና አሮጌን ብራናዎች በማየት በብራናው መልክና ይዞታ አዲስ ይሁን አሮጌ ሊገምት ይችላልና፡፡ ግምት ግን መቶ በሞቶ ርግጠኛ አያደርግም፡፡ ብራናው በካርቦን 14 ወይም ከሱ በተሻለ መሳሪያ እስካልተመረመረ የርስዎም ግምት ከእኔው ግምት አይሻልም፡፡ እዚህ ላይ ግን ብራናው መጽሀፌ ውስጥ የቀረበበት ምክንያትና ቁምነገሩ የብራናውን ዕድሜ ለመመርመር ሳይሆን የኦሮምኛ ቁዋንቁዋ በኢትዮጵያዊ ፊደላት ከዚህ ቀደም ተጽፎ እንደነበር፣ በላቲን እንጂ በኢትዮጵያ ፊደላት ኦሮምኛን መጻፍ አይቻልም፣ ለሚሉት ሰዎች ለማሳየት ነው፡፡ ርስዎ ግን ጸጉር መሰንጠቅ ስለሚወዱ ቁምነገሩን ትተው ከንቱውን የመነጋገሪያ ርዕስ አድርገው ጉንጭ ያስለፋሉ፡፡

ገጽ 84-89 ላይ (መጽሐፉ ሽፋን ላይም) የሱባ መጽሐፍና ፊደላት ይገኛሉ። ሊተረጕማቸውና ምስጢራቸውን ሊፈታ የሚችለው ፈጣሪያቸው አማን በላይ ብቻ ነው። ግን መዝገበ ቃላትም አብሮ ተገኝቷል ሲል ሚቶሎጂውን ተአማኒ አስመስሎታል።

አማን በላይ አዲስ፣ ያውም ጥንታዊ ቁዋንቁዋ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለዛ ቁዋንቁዋ መዝገበ-ቃላት መድረስ ከቻሉ ከርስዎ የቁዋንቁዋ ሊቅ ነኝ፣ ከሚሉት ሺ ጊዜ የሚአይሉ ላዕለ-ሰብ (ሱፐርማን) ናቸው ማለት ነው፡፡ የእዚህ ዐይነት ሰው ግን ገና በዐለም ላይ አልተፈጠረም፡፡ መሪራሰ አማን ግን በጀበል ኑባ፣ ኑብያ ውስጥ ሱባ የተሰኘ የጥንታዊ ቁዋንቁዋ የሰፈረባቸው ፊደላትና መዝገበ-ቃላት (የግዕዝና የሱባ) ስለአገኙ እነዚያን አሳትመዋል፡፡ እኔም አንድ ቅጂ አለኝ፡፡ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሰቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቁዋም ከሳቸው እጅ አንደ ቅጅ መቀበሉንም እላይ ባስቀመጥኩት ሰርቲፌኬት አረጋግጦአል፡፡ ስለዚህም የተቀደሰ ግኝታቸውና ተግባራቸው መሪራሰ አማንን የኢትዮጵያ ሀዝብ ያመሰግናቸዋል፡፡

ከ3 ሺ ዓመት በፊት ቀዳማዊ ምኒልክ “ኦቺ” የተባለና ከመደባይ/ኦሮሞ የተውጣጣ ጠንካራ ሰራዊት ነበረው [ቀ]ዳማይ ምኒሊክ ይህንን ጦሩን “ጨዋ” (ሸዋ) ብሎ ሰየመው እና የዛሬውን ማእከላዊ ኢትዮጵያን ወረረ። ከዚያም ጦሩን በወረረው በዚህ ቦታ ላይ አሰፈረና አገሩን በጦሩ መጠሪያ “ጨዋ” (ሸዋ) ብሎ ጠራው” ይላል።

ታሪካችን እርግጥ ወታደሮችን ጨዋ ይላቸዋል። ግን “ጨዋ” እና ሸዋ በግድ ካላዛመዷቸው የተፈጥሮ ዝምድና የላቸውም። (“ጨዋ” ከ “ፄዋ” የመጣ ሊሆን ይችላል።)

አሁን ‹‹ጨዋ‹ እና ‹‹ሸዋ‹‹ የተባሉትን ቃላት እዚህ የሚያቀርቡት ጸጉር መሰንጠቅ ካልሆነ በቀር ይህን ያህል የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነው? ለምሳሌ አርጎባዎች፣ በሸዋም ሆነ በሌላ ቦታ የነበሩት፣ ‹‹ጨ‹‹ ማለት ስለሚከብዳቸው ‹‹ሸ‹‹ ነው የሚሉት፡፡ ‹‹ጨዋ‹‹ ለማለት ‹‹ሸዋ‹‹ ይላሉ፡፡ ‹ሸዋ‹ የተባለው በዚህ አይነት ምክንያት ቢሆንስ? እንዳውም ነው፡፡ ለምሳሌ በጎጃም አካባቢ የአሉ ባለገሮች ‹‹ቄስ‹‹ እንላለን ብለው፣ ‹‹ጬስ‹‹ ይላሉ፡፡ሰዎቹ ‹‹ቄ‹‹ ማለት አይችሉም፡፡ ስለዚህ በ ‹ቄ‹‹ ፈንታ ‹‹ጬ‹‹ ይላሉ፡፡ ርስዎ ኢትዮጵያን በደንብ እንደማያውቁዋት ይህ ሁሉ ያጋልጣል፡፡ መጽሀፌ ስንትና ስንት ቁምነገር አዝሎ እርስዎ እንደዚህ ዐይነቶችን ጥቃቅን ነገሮች ቆንጽለው እያወጡ አንባቢን መናቅ ይገባልን? እኔንስ ማድከም ይገባልን? ይልቅየው ስለመጽሀፉ አዳዲስ ይዘቶች ቢተነትኑ እና አንባብያንን ቢያስተምሩ ምን አለበት? ለእርስዎ እንቶፈንቶ ሁሉ መልስ እንድሰጥ አስቆጥተውኝ አደከሙኝ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ግን እንቶፈንቶ መስሎ ለታየኝ መልስ አልሰጥዎትም፡፡

“አክሱማይት እና ሁሉም የአክሱማይት ተወላጅ ነገሥታት ከሜሶፖታሚያ ድረስ ግብር የሚያመጡላቸው ንጉሦች በስራቸው ነበሯቸው” ይላል። ይኸንን ልብ ወለድ አባባል ሚቶሎጂ ይቀበለዋል፤ ታሪክ ግን አይቀበለውም። በዚያ ዘመን ከሜሶፖታሚያ ተነሥተው ለአክሱም ነገሥታት ግብር ገብረው ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድባቸዋል? ደግሞስ በዚያን ዘመን በምን ኀይልና መንገድ ነው የአክሱም ነገሥታት ሜሶፖታሚያ (ዒራቅ) ድረስ የሚያስገብሩት?

ይህ ሚቶሎጂ ሳይሆን የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ጊዜ ፈጅቶ ከሜሶፖታሚያም ሆነ ከመካከለኛው ምስራቅ ድረስ መጥተወ ለኢትዮጵያ ነገሥታት ይገብሩ ነበር፡፡ ለዚህ ሲገርመዎት የአማራ ሰራዊት ሜሶፖታሚያ ድረስ ሄደው ሰፍረው ለስማቸው መጠሪያ ‹‹አማራ‹‹ የሚል ከተማ ከትመው እስከዛሬ ድረስ ‹‹አማራ‹‹ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከ 9 ዐመታት በፊት ግን ሺአይቶች ይዘውታል፡፡ ይህም የፍቅሬ ቶሎሳና የአማን በላይ ሚቶሎጂ ሳይሆን የኒውዮርክ ታየምስ ጋዜጣ የዘገበው ነው፡፡ (New York Times, Saturday, October 21, 2008) ፈልገው ይመልከቱት፡፡ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ብዙውን የጥንቱን ዐለም እንደሚያካትት ተደጋግሞ የተነገረ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዛሬ 3000 ዐመት በፊት የእኛው ኢትያኤል (ንግሥተ-ሳባ) ዙፋኑን የወረሰችው አጼ እስያኤል፣ ጦር-ሰራዊቱን ይዞ ዛሬ እስያ ወደተባለው አህጉር ሄዶ ቦታውን ቅኝ ገዝቶ፣ በስሙ “እስያ” ሲል ሰይሞት እስከዛሬ እስያ ተብሎ ይጠራል፡፡ የአፍሪካ አህጉርም ቢሆን፣ በኛው በአፋሮች ነው አፍሪካ ተብሎ የሚጠራው፡፡ የአበውን ገናና ታሪክ ለማያውቀውና ለሚንቀው ለእንደርሶ አይነቱ ሰው፣ ይህ ሁሉ ሚቶሎጂ ነው፡፡ ለእኛ ግን በታሪከነገሥት ዘ ኢትዮጵያ በጥንታውያን አባቶቻችን የተመዘገበ የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ የጥንቶቹ ታላላቆቹ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ደግሞ ያልሠሩትን ታሪክ ሠራን ብለው ዋሽተው በታሪክ አላስተላለፉልንም፡፡ ውሸትን የሚጸየፉ እግዚአብሄርን የሚፈሩ ቅዱሳን ነበሩ፡፡ ስለዚህ፣ ዘመን ጥሎን እንደዛሬው ሳናንስ ይገብሩልን የነበሩት ሀገራት ከኢራቅም ዳርድንበር የዘለሉ ነበሩ፡፡

““አጼ” ወይም “እሴ” ስመ-ክህነቱ “እስያኤል” የተባለው ልእለ-ሰብእ ንጉሠነገሥት 480 ዓመት በህይወት ኖረ ሲባል ያሥገርም ይሆናል” ይላል። በሚቶሎጂ አያስገርምም፤ በታሪክ ግን እርግጥ ያስገርማል። “አጼ” እና “እሴ”ም ከድምፅ ያለፈ ዝምድና የላቸውም።

እነ አዳም፣ እነማቱሳላና ሌሎቹም በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት እሰከ 900 ዐመታት የኖሩት ሰዎች ዕድሜ ሚቶሎጂ ነው፣ ማለት ነው፡፡ የድሮ ዘመን ሰዎች ለምን ረጅም ዕድሜ እንደኖሩና በሁዋላ ዕድሜአቸው ለምን እንደ አጠረ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ተብራርቶል፡፡ በሳይንስም ተጠንቶእል፡፡ እንደ እምነትዎ ይሁንልዎት፣ በእዚህ አልከራከርዎትም፡፡ አጼ ለምን ለረጅም ጊዜ እንደኖረ ግን በመጽሃፌ ውስጥ በማስረጃ ተደግፎ ስለተቀመጠ አንባቢው ሊያየው ይችላል፡፡ “እሴ” እናትና አባቱ ያወጡለት ስም ነው፡፡ “አጼ” የሚለው ከዘመን ብዛት ሰዎች ‹‹እሴ‹‹ እንላለን ብለው ወደ ‹‹አጼ‹‹ የቀየሩት ነው፣ ብዬ አስባለሁ፡፡

. “Magician” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ማጂ ከሚለው ከኦሮምኛ ስም የተወሰደ ነው ይላል። ሁለቱ እንዴት ተገናኝተው ይህ ሊሆን እንደተቻለ የሚያሳይ ተጨማሪ ተረት ያስፈልጋል ።

ከኦሮምኛ የተወሰደ ነው አላልኩም፡፡ ይህንን ልል አልችልም፡፡ የማጂ ሰዎች በጣም ብልህ ስለነበሩ ‹‹ማጂክ‹‹ የሚለው ቃል ምናልባት ከነሱ ስም የተወሰደ ይመስለኛል፣ ነው ያልኩት፡፡የቁዋንቁዋው ሊቀሊቅ ፕሮፌስር ጌታቸው ሆይ! በ ‹‹ነው‹‹ እና ‹‹ይመስለኛል‹‹ መሀል ትልቅ ልዪነት ያለ አይመስለዎትም? ርስዎ ግን እጅግ የሚደንቁ ሰው ነዎት፡፡ አሁን እውነተኛ ማንነትዎን ላውቅ ችያለሁ፡፡ ለማንኛውም ይህ የኔ መላ ምት ነው፡፡ በአማርኛ ››ዐይን፣‹‹ በ እንግሊዝኛ ‹‹ዐይ‹‹፣ በኦሮምኛ ››ፈርዳ‹ (ፈረስ)‹ በጀርመንኛና አረብኛ ‹‹ፈርድ‹‹፣ በአማርኛ ‹‹ፍርሃት‹‹ በእንገሊዝኛ ‹‹ፊር‹‹፣ በአማርኛ ‹‹ሜዳ‹‹ በእንግሊዝኛ ‹‹ሜዶ‹‹ ወዘተ፣ ለምን ሆነ? የሰው ልጆች ቁዋንቁዋ በመጀመሪያ ምንጩ አንድ ስለሆነ ወይም ሰዎች አንደ አይነት ታሪካዊ ግንኙነት ስለኣላቸው ነው፡፡ ርስዎ ሊንጉስት እንደመሆንዎ ስለዚሀ ቃል ከዚህ የተሻለ ማብራሪያ ከአለዎት ያካፍሉን፡፡

ገጽ 59 ላይ የመናዝል ምስል በረጅም የሚቶሎጂ ታሪክ ታጅቧል። ሥዕሉ ለዓሥራ ሁለቱ ወሮች የተሰጡትን የዓሥራ ሁለቱን ከዋክብት ስሞች ይዟል። ሥዕሉ ለአዲሱ ሚቶሎጂ የጠቀመው እኛ ኢትዮጵያውያን ፕላኔቶቹን ሁሉ ከጥንት ጀምሮ የተመራመርን ለመሆናችን ማስረጃ በመሆን ነው። ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ ሥዕሉ እንዲህ ሲል ጽፏል፤ “ከላይ የቀረበውን ምስል በፊርማቸው አረገግጠ‹ወ›ው በኢንተርነት ያደረሱን ዶ/ር አየለ በከሪ ናቸው። ደሸት (?) የዞዲያኩን ምስል የመስራት ሀሳብ የመጣለት ከኖኅ ወደ መልከጼዴቅ ከዚያም ወደ ኢትዮጵ በቅብብሎሽ ከመጣና ለኔም ከደረሰኝ የዩኒቨርስን አፈጣጠር ከሚተርክ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው” ይላል። አተራረኩ ጥሩ ሚቶሎጂ ሊሆን ይችላል። በታሪክ አንጻር ሲታይ ግን፥ ሥዕሉ አዲስ አይደለም፤ ስሙም “መናዝል” ይባላል። በባሕረ ሐሳብ የብራና መጻሕፍት ሁሉ በየገዳማቱ ይገኛል። ሥዕሉ የወራትን ስም ስለሚያመለክት ኮከብ ቈጣሪዎች በነዚያ ወሮች የተወለደን ሰው ጠባይ መናገሪያ ያደርጓቸዋል። እውነቱ ግን፥ እኛ ኢትዮጵያውያን ዘዴውን ከነሥዕሉ የወሰድነውም ዐረቢኛ ከምትናገር የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ነው። የወሰድነው የከዋክብቱን ስማቸውን እንኳ ወደእኛ ቋንቋ ሳንተረጕም እንዳለ በዐረብኛው ነው። አሰድ (አንበሳ)፥ ሰውር (በሬ)፥ ዓቅራብ (ጊንጥ)፥ ሑት (ዓሳንበሪ)፥ ወዘተ.

ትንሽ ልጅ ሳለሁ እቤታችን በመንፈስ ቅዱስ አብርሃ የተደረሰ ፍካሬ ከዋክብት ወ አውደ ነገሥት የሚባል መጽሃፍ ነበረ፡፡ መጽሀፉ በጣና ሃይቅ ከደሸት ወይም ዘረደሸት እንደተገኘ ይመሰክር ነበር እንጂ ከግብጾች ተገኘ አይልም፡፡ ለጊዜው ግን፣ የመናዝልን ትርጉም እርስዎ ካወቁት ደህና ነው፡፡ ካላወቁት ግን፣ መናዝል የኛ ለመሆኑ ማስረጃ “‹መናዝል”‹ የሚለው ስሙ ራሱ ነው፡፡ “‹መናዝል” ኢትዮጵያዊ ቃል ነው፡፡ መና-እዝል፡፡ መና (እግዜር ለእስራኤሎች ከሰማይ ያዘነበው ምግብ)፡፡ በእዚህ ይዘት ውስጥ፣ ‹‹እዝል‹‹ ትርጉሙ ደግሞ ጌጥ፣ ዘርፍ፣ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር “‹መናዝል”‹ ማለት ከዋክብትን የሚመግብ ያማረ መና እንደማለት ነው፡፡ ቃሉ እንደሚመሰክረው፣ “መናዝል” የኛው የራሳችን እንጂ የግብጾች አይደለም፡፡ ርግጥ የግብጽ ጳጳሳት ለ 1500 ዐመታት ኢትዮጵያን እየበዘበዙና እየመዘበሩ ምን ወደ ግብጽ ያላጋዙአቸው መጻህፍት አሉ? የኛኑ መጻህፈት ወስደው ትንሽ ለዋውጠው የእኛ ነው ይላሉ፡፡ የሚያሳዝነው የኛ ጠቢባን አባቶች (ኢትዮጵያውያንን ማለቴ እንጂ እርስዎ “አባቶቼ” የሚሉአቸውን ግብጾቹን አይደለም፤) እግዚአብሄር የፈጠራቸውን ዐለማት ለመጠቆሚያ የመዘገቡአቸውን ፍካሬ-ከዋክብት ግብጾቹና የሁዋላው ዘመናት ኢትዮጵያውያን የጥንቆላ ማድረጋቸው ነው፡፡ እኔም ትንሽ ልጅ ሳለሁ ኮከቤን የማወቅ ጉጉት አድሮብኝ፣ ፍካሬ ከዋክብት ወ አውደ ነገሥት በተባለው መጽሀፍ መመሪያ መሰረት የእኔን እና የእናቴን ስሞችና ቁጥራቸውን እያሰላሁ፣ እያባዛሁ፣ እየገደፍኩና እያካፈልኩ፣ የኮከቤ ቁጥር ጀዲመሬት መሆኑን ደረስኩበት፡፡ የሚገርመው ነገር በሁዋላ የተወለድኩበትን ወርና ቀን በማስላት እንደ ደረስኩበት በእንግሊዝኛውም ሆሮስኮፕም ጀዲ መሬት(ቨርጎ) ሆነ፡፡ ይህን ያወጋሁዎት ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ስለመናዝል እንደማውቅ ላወሳ ነው፡፡ አሁንም በተጨማሪ ዓውደነገሥት ወፍካሬ ከዋክብት እና የአለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ ባሕረ ሐሳብ አለኝ፡፡ ወደቁምነገሩ ልመለስና፣ እኔ የምለው በእነዚህ መጻህፍት ውስጥ የአሉት መናዝሎቹ 12 ከዋክብት የሚሉአቸው ከዋክብት ሳይሆኑ ሕይወት የአለባቸው ዐለማት ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የተገለጡትም በቅዱስ ሄኖክ ሲሆን ሲወርድ ሲዋረድ ወደ እነ ደሸት የደረሱ ናቸው፣ ነው፡፡ ፈላስፋው ደሸት ግን ስለዐለማቱ እየዘረዘር ጻፈ፡፡ በእርግጥም የኦሮሞና የአማራው አባትና አያት ደሸት በመንፈሳዊ ጉዞና ምርምር ሕዋውን ዳስሶ፣ በዬኒቨርስ ውስጥ በርካታ ዐለማት እንደ አሉ አስተማረን፡፡

የዐለማትን መኖር የሚያበስረውን የእሱን መናዝል በሁዋላ የመጡ ሰዎችና ነገሥታት፣ የሰውን ባህሪ መግለጫ ወይም መጠንቆያ አደረጉት፡፡ የዚህም ማስረጃዬ በእጄ የሚገኘው ምናልባት አርስዎም እጅ ተገኝቶ የአማን በላይ ሚቶሎጂ ነው ብለው የሚፈርጁት መጽሀፍ ነው፡፡ ሰረገላ-ታቦር ኢዮር– ስለ ስነ-ፍጥረት ምስጢር፣ የተሰኘው ነው፡፡ በዚህ መጽሀፍ መሰረት፣ እግዚአብሄር 7(ሰባት) ሰማያትን ፈጥሮ ውስጣቸው 99 ዐለማትን አኑሮአል፡፡ የኛ ሰማይ ኢዮር ይባላል፡፡ እውስጡ 12 ዐለማት አሉ፡፡ አንደኛዋ የኛ ዐለም ምድር ነች፣ ሀመልማል ትባላለች፡፡ በሌሎቹ በ 11 ዐለማት ውስጥ የተለያዩ ሕይወት (ነፍሳት)አሉባቸው፡፡ ወሪጅናሉ መናዝል ይህን ሀቅ ነው የሚጠቁመው፡፡ እኔም በመጽሀፌ የዘረዘርኩት ይህን ነው፡፡ እኛ ዘንድ እንጂ፣ የሁሉ ነገሮች ምንጭ እርስዎ የሚያረጉአቸው አረቦች ዘንድ ዣንሸዋ እና መጽሀፈ ሄኖከ ከቶም አልተገኙም፡፡ ስለዚህ ግብጾች መናዝልን ከኛው አግኝተው ጥንት እኛው በሱባ ቁዋንቁዋ የሰየምናቸውን ስሞች ነው መልሰው የሚያስተጋቡት፡፡ የሱባ ቁዋንቁዋ ከሁሉም ቁዋንቁዋዎች ቀዳሚ በመሆኑ አንዳንዶቹ በአረቦች የድግምት ቃላት ውስጥ እንኩዋን የሚገኙት ከሱባ ቃላት ውስጥ የሚደመጡት ቃላት ናቸው፡፡ እነዚህ ቃላት በ ‹‹ልሳነሰብ‹‹ በአንገት ላይ የሚታሰሩ ክታቦች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የጥንት ክታቦች ከአሉዎት ገልጠው ይመርምሩአቸው፡፡ ደግሞም የሰባቱን ሰማያትና የ መቶዎቹን ዐለማት ዝርዝር ለመረዳት ሰረገላ-ታቦርን ገልጠው ይመልከቱ፡፡ ለጊዘው ግን እኔ በአጭሩ ለርስዎም ሆን ለአንባብያን ላቅርብ፡፡ ውስጣቸው የተለያዩ ዐለማት የአሉባቸው የሰባቱ ሰማያት ስሞች የሚከተሉት ናቸው፤–

1ኛ) ኢዮር (12 ዐለማት የአሉት የኛ ሰማይ፡፡ 12ቱ ከዋክብት ብለው ለጥንቆላ የአዋሉአቸው፡፡)

2ኛ) ራማ (እውስጡ 33 ዐለማት የአሉበት)

3ኛ) ኢየሩያ (ገነት ወይም ሰማያዊትዋ ኢየሩሳሌም፣ አዳም ገብቶ የተባረረባት፣ ቅዱስ ጳውሎስ ተነጠቅኩባት፣ ተወስጄ ዐየሁት የኣለው ሶስተኛው ሰማይ)

4ኛ) ውዱድ ወይም ዱድያኤል (እውስጡ 21 ዐለማት የአሉበት)

5ኛ) አርያም (ራሱን የቻለ አንድ ዐለም፣ መንበረ-ጸባኦት ወይም ጽርሀአርያም ያለበት፣ የእየሱስ ክርስቶሰ ክብር በአማኞቹ ፊት ለወደፊት የሚገለጥበት)

6ኛ) ኤረር ወይም ኤሮርያ (33 ዐለማት የአሉበት፣ ከነዚህ ዐለማት ውስጥ ሜምሮስ ከተባለው ነው ሮሃንያ የተባሉት እጅግ ብልሆች በመንኮራኩር ወደ ምድር ወርደው ከቃኤል ሴት ልጆች ግዙፋን ነፊለምን የወለዱት፡፡ ስለነዚህ ነፊለሞች፣ ሙሴ ከኢትዮጵያዊው አማቱ ጋር ለ 40 ዐመታት ሲኖር ከኛው መጽሀፍ ከዣንሸዋ አንብቦ፣ ኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ በቁንጽል ዘግቦአል፡፡)

7ኛ) ሻዳያ (የኤልሻዳይ እግዚአብሔር መኖሪያ እጅግ ቅዱስ ዐለም)

አሁን ደግሞ በ እኛ ሰማይ በኢዮር ስለአሉት 12 ዐለማት ጥቂት ልበል፡፡–

1ኛ) ሐመልማል፣ ሐመል እሳት (አዳምና እኛ የተፈጠርንባት ዐለም)

2ኛ) ረሀም (የፍየልና የበግ መልክ የመሰለ ገጽ የአላቸው አእምሮአቸው ከስው ልጆች እጅግ የላቀ አስተዋይና የነገሮችን ምስጢሮች መመርመር የሚችሉ ፍጡራን ያሉበት ዐለም)

3ኛ) ገውዛ (ፊታቸው የሰው ሆኖ ቀንድና ጅራት ያላቸው፣ አንዳንዶቹም የዝንጀሮና ጉሬዛ መልክ ኖሮአቸው ገላቸው በጸጉር የተሸፈነ ፍጡራን የአሉበት፣ የሰላምና ፍቅር ዐለም)

4ኛ) ሸርታ (እንደ ዳሞትራና ሸረሪት 8 እግሮች ያላቸው መልካቸው እንደ አንበጣ ገጽ የሆኑ ፍጥረቶች ያሉበት ዐለም)

5) ሰውድ (እሳታዊ ፍጡራን የሚኖሩበት ዐለም)

6) ሰንበላ (ህልቆመሳፍርት የተለያዩ እንደኛው ዐለም ርስበርስ የሚባሉ አእዋፍ፣ ንስሮች፣ እንስሶች እና አራዊት የአሉበት ዐለም)

7) ሚሳን (የእንስሳና የአውሬ ገጽ ቢኖራቸውም የተፈጥሮ ባህሪያቸው ቅዱሳን የሚኖሩብት ዐለም ነው፡፡ በተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች እግዚአብሄርን ያመሰግናሉ፡፡ አንዳንዴ በመንኮራኩር (በ ዩፎ UFO Unknown Flying Objec) ተነጥቀው ወደእዚህ ዐለም ይመጣሉ፡፡ የወደዱትንም ሰው ነጥቀው ወደ ዐለማቸው ይወስዳሉ፡፡ የእነሱ ዐለም ከእኛው ስለሚመሳሰል ለተወሰነ ጊዜ እዚህ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሰውም በነሱ አየር ወስጥ ሊኖር ይችላል፡፡ ብናምንም ባናምንም በአሁኑ ዘመን አንዳንድ ሰዎች በ UFO ተጠልፈን ተወስደን ነበር የሚሉትን ነገር የኛ ቀዳሚ አባቶች ያውቁ ነበር፡፡ በዚህ እውቀታቸውም ልንኮራ ይገባል፡፡ )

8) አቅራብ (በባህር ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳት የአሉበት፣ ቅርጻቸው የጊንጥና የዝሆን የሆነ ዐለም)

9) ቀውስ (ከእሳትና ከነፋስ ብቻ የተፈጠሩ በእሳት ባህርና ፈሳሽ ወስጥ የሚኖሩበት የእሳታውያን ዐለም)

10) ዠዲ፣ ጀዲ (ለምድራችን የቀረበ፣ በምድራችን የአሉትን አይነት አእዋፍ፣ እንሳሳትና አራዊት የሚኖሩበት ዐለም፤ እዛ ያሉት አእዋፍ ወደእኛ የሚመነጠቁበት፣ የኛዎቹም ወደዛ የሚነጠቁበት ዐለም)

11) ደለዋ (ስፍር ቁጥር የሌላቸው፣ በምላሳቸው የሚያሸቱና የሚያዩ ፍጡራን የሚርመሰመሱበት የጭለማ ዐለም)

12) ሁት (እንደ ንብ መንጋ ሆነው እንደ ተራራ የሚከመሩ ጥቃቅን ነፍሳት የሚኖሩበት ዐለም)

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሆይ! በሁዋላ “መናዝል” ብለው ኢትዮጵያውያንና ግብጾች የሰየሙትና ለጥንቆላ የአዋሉት ወሪጅናሌው ይህውሎት፡፡ በእነዚህ ውስጣቸው በዙ ፍጡራን በእሉባቸው ዐለማት ተንተርስው ነው የጥንቆላውን ፍካሬ ከዋክብት የፈለሰፉት፡፡ አብዛኞዎቹ የተሰየሙት ዐለሞቹ ውሰጥ በአሉት ፍጡራን መልክና ስሞች ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በእኛ እጅ ዣንሸዋ በተሰኘው ጥንታው መጽሀፍ ውስጥ ከተገኘው መረጃ ተነስተው አረቦች፣ ግሪኮችና ቻይኖች የነፍሳቱን፣ የእንስሳቱን እና የአውሬዎቹን ስሞች አንዳንዱን ወይም ሁሉንም በየቁዋንቁዋቸው ጽፈው Horoscope ብለው ወይም ሌላ ስሞች ሰጥተው፣ ለጥንቆላ ቢያውሉት እነሱ ከኛ ወስደው ለወጡት እንጂ እኛ ከነሱ አልወሰድነውም፡፡ ይህ ዣንሸዋ የተባለው፣ አሁን ደግሞ ሰረገላ ታቦር ተብሎ በሊቁ መሪራሰ አማን በላይ ከግዕዝ ወደአማርኛ ተተርጉሞና ተብራርቶ የታተመው በዐለም ላይ የትም ቦታ የሌለው መጽሀፍ የተገኘው ከእኛ ዘንድ ነውና፡፡ ይህንንም እርስዎ መሪራስ አማን በላይ የደረሰው የሀራሰማይ (የዩኒቨርስ) ወይም የከዋክብት ሚቶሎጂ ነው ብለው ዐይኔን በጨው አጥባለሁ ብለው ደርቅ እንደማይሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህን ከካዱ ደግሞ እኚህ የፈረደባቸው መሪራሰ አማን ከምድሩ ሚቶሎጂ ወደ ሕዋው መጥቀው በአስትሮኖሚ እውቀታቸው በዐለም ላይ እሰከዛሬ ከተከሰቱት የፈለኪያና የከዋከብት ጥናት ሳይንቲስቶች ሁሉ እጅግ የላቁቱ ናቸው ማለት ነው፡፡

እንዳው ለነገሩ እስቲ ልጠይቆትና፣ የምድሩን ሚቶሎጂ መሪራስ አማን የሚፈጥሩት ለምን ይሆን? ደሞስ ከምድሩ ሚቶሎጂ አልፈው ተርፈው፣ አሻቅበው ወደ ሰማየ ሰማይት መጥቀው የሰማየ ሰማያት ሚቶሎጂ የሚፈጥሩት ለምን ይሆን? የዚህ አይነት ዕጡብ፣ ድንቅ ሚቶሎጂ የሚያፈልቅ ምን አይነት አንጎል ቢኖራቸው ይሆን? እኔን ግን የሚገርመኝ ጠቢባኑን የጥንት አባቶቻችንን ርስዎ እየናቁ ደሞ ስለ ዐለማትና ከዋክብት ያውቁ ነበር፣ ልትሉን ነወይ፣ ማለትዎ ነው፡፡ ርስዎ ወደዱም ጠሉም፣ አዎን ጥንታውያን አባቶቻችን ዐለማቱን በፈጠራቸው በእግዚአብሄር መንፈስ ተመርተው፣ ከአረቦችና ፈረንጆች ቀድመው ስለ ሌሎች ዐለማት መኖር አሳምረው ያውቁ ነበር፡፡ እርስዎ የማይገባዎትን ነገር ሁሉ ሚቶሎጂ ብለው ስለሚበትኑ ከርስዎ ጋር ምንም መነጋገር አለመቻሉ ያስተክዛል፡፡

ደሸት (ደሴት) ማነው? እንደ ሚቶሎጂው አቀራረብ፥ የአማሮችና የኦሮሞዎች አባት ነው።–አማሮችና ኦሮሞዎች ከአንድ አካባቢ ከጐጃም፤ ከአንድ አገር ከኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው ለማለት ነው። የታሪክ መጻሕፍት የሚናገሩት ስለ ጣና “ደሴት” ስለሆነ “ደሴት” የኦሮሞና የአማሮች አባት ስም ሆነ። “ደሴት” island ነው። “ደሸት” ከሚለው ስም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ሆኖም፥ ስለ ደሸት (ደሴት) የተጻፈው ልብ ወለድ ታሪክ “ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን” ለሚሉት ማስረጃ ስለሆነ፥ ሊነበብ የሚገባው ነው። እንዲህ ይላል፤ “ስለ ደሸት ስንናገር ምንም እንኳን ተረት ቢመስልም ሀቅ ስለሆነውና ለየት ስለሚለው ውልደቱ [= ልደቱ] መናገር ጠቃሚ ነው። የቤላም(በልዓም) የልጅ ልጅ የሆነችው እናቱ ነቢይትዋ ሼምሼል መነኵሲት ነበረች። ከወንድ እርቃ በግዮን አካባቢ በገዳምም ውስጥ መንፈሳዊ ህይወት ትመራ ነበር። አንድ ቀን በግዮን ወንዝ ሳይሆን አይቀርም ገላዋን ስትታጠብ የወንድ ዘር በማሕፀንዋ ዘልቆ ገባና ደሼት (ደሴት) ተፀነሰ። . . . ይህ የሆነው ከሦስት ሺ አምስት መቶ ዓመት በፊት ስለሆነ ማስረጃው ሁሉ ቢጠፋ አያስገርምም” ይላል። ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን የሚሉት፥ የኦሮሞና የአማራ አባት ደሼት (ደሴት) እውሀ ውስጥ ስለተፀነሰ ነው ማለት ነው። ግሩም የሚቶሎጂ ትረካ ነው። ግን ከታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። ነቢዩ በልዓም ይኖር የነበረው ሜሶፖታሚያ (ዒራቅ) ነበር። ሚቶሎጂውን ለማሟላት ሼምሼልን ከዚያ አንሥቶ ጎጃም ላይ የጣላትን የነፋስ ሰረገላ ፈጥሮ ታሪኩ ቢጨመርለት ጥሩ ነበር። “ደሸት” እና “ደሴት” የአንድ ሰው ስሞች ናቸው፡፡ ልዩ መስለው የሚታዩት በአማርኛ ‹‹ደሴት‹‹ በእብራይስጥ ‹‹ደሸት‹‹ ስለሚባል ነው፡፡ ለምሳሌ በአማርኛ ‹‹ሰላም‹‹ ስንል በእብራይስጥ ‹‹ሸሎም‹‹ ይላሉ፡፡ ህጻን ሆነን ጂዎግራፊ ስንማር ‹‹ደሴት‹‹ የሚለው ቃል በውሀ የተከበበ መሬት ነው፣ ተብለን ነበር፡፡ ይህ ቃል ከየት እንደመጣ ያወቅኩት ስለደሸት ወይም ደሴት ከሰማሁ በሁዋላ ነበር፡፡ ጠቢቡ ደሸት/ደሴት በጣና መሬቶች ላይ ስለተፈጠረና ስለኖረ ከሱ ስም የተነሳ በውህ የተከበበ መሬት ሁሉ ደሴት ተባለ ብዬ፣ አስባለሁ፡፡ ርስዎ ይህ አይደለም ከአሉ ሊነጉዊስት እንደመሆንዎ መጠን እሰቲ የቃሉን ምንጭ ጀባ ይበሉና፡፡አባታችን (ደሸት) እና ህይወት ከውሃ ውስጥ ወጡ የሚሉት የኦሮሞ እና የአማራ (እነማይና ዘረደሸቶች) ናቸው፣ (በቂ ምክንያት ስለአላቸው) እንጂ ፍቅሬ ቶሎሳ አይደለም፡፡ ይህን ርስዎ ሚቶሎጂ የሚሉትን የደሸትን ከ ”ውሀ ውስጥ ስለመውጣት” ታሪክ የመሪራስን ግኝት እንኩዋን ወደጎን ብንተወው ኦሮሞዎችና አማሮች ምንጫቸው አንድ ደሸት መሆኑን እኔ በመጽሃፌ ውስጥ በአመክንዮ አረጋግጫለሁ፡፡ ለምሳሌ ኦሮሞዎች ህይወትና አባታችን ከውሀ ወጣ፣ ይላሉ፡፡ የጎጃሞቹ ዘረ-ደሸት እና እነማይ (የውሀዎቹ) የሚባሉት አማሮች፣ ስማቸው እንደሚያረጋግጠው፣ የደሸት ዘሮች የሆንን ከውሀ የተገኘን ነን፤ ይላሉ፡፡ በጎሳቸው ኦሮሞዎች እና አማሮች የሆኑት ሁለቱም ሀዝቦች ዘረ ምንጫቸው “ከውሃ ውስጥ የወጣው” (የተጸነሰው) አንድ ደሸት ስለመሆኑ ከዚህ የበለጠ ምን የመጽሃፍ ማረጋገጫ ያሻዋል? ሁሉን ነገር ሚቶሎጂ ነው እያሉ ቢያንስ ይሄን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ስለአልጣሉት አመሰግኖታለሁ፡፡ ምክንያቱም የሚከተለውን ስለአሉ– “ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን” ለሚሉት ማስረጃ ስለሆነ፥ ሊነበብ የሚገባው ነው፡፡‹ ነቢዩ በልዓም ይኖር የነበረው ሜሶፖታሚያ (ዒራቅ) ነበር። ሚቶሎጂውን ለማሟላት ሼምሼልን ከዚያ አንሥቶ ጎጃም ላይ የጣላትን የነፋስ ሰረገላ ፈጥሮ ታሪኩ ቢጨመርለት ጥሩ ነበር።ነቢዩ በልአም የኖረው በኢራክ መሆኑ በባለታሪኮች ተስተባብሎአል፡፡ የአማርኛው መጽሀፍ ቅዱስ የሚለው ፋቱራ በተባለች ከተማ ሲሆን፣ የእንግሊዝኛው እውቅና ያለው የንጉሥ ጀምስ ትርጉም ከተማዋን Pethor ይለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መጽሃፍ ቅዱሰ ማህበር ባሳተመው (ቀኑ ባልጠተጠቀሰ)አማርኛ መጽሃፍ ቅዱሰ ውስጥ በምዕራፍ 22፣ 1-7፣ እንዲህ ይላል– የእስራኤልም ልጆች ተጉዋዙ፣ በኢያሪኮ ፊትለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞአብ ሜዳ ሰፈሩ፡፡…….. በዚያም ጊዜ፣ የሰፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ፡፡ በወንዙ አጠገብ ባለችው በህዝቡ ልጆች በፋቱራ ወደተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለአም ….. ይጠሩት ዘንድ መልእክቶኞችን ላከ፡፡ ስለ በልአም መኖሪያ ቦታ እርስዎ ያነበቡት ፋቱራን (ፔትሆርን)፣ በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መሃል ሊሆን ይችላል የሚለውን ዘመን ያለፈበት መላምት ነው፡፡ ይህም የድሮ እሳቤ ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን የቲዎሎጂ ሊቃውንትና አርኪዎሎጂስቶች፣ ከብዙ ምርምር በሁዋላ፣ ኢራቅ በጣም እሩቅ ስለሆነ ይህ ቦታ እቅርቡ፣ በሙት ባህር አጠገብ (እስራኤል ጎን) እንደሆነ በአመክንዮና በቁስ-አካል ማስረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡ መረጃው እንዲህ ይላል፡፡–Because it seems a bit unlikely that the Mobite king Balak sent all the way to Assyria (now Iraq) for a prophet, and that Balaam hence came all the way to Canaan on a donkey, scholars have been looking for ways to place him closer. In 1967 an extra-Biblical text was found in Deir Alla in the Jordan valley. It mentions the “cursing prophet Baalam, son of Beor, which makes it likely that he lived there, and not in Mesopotamia. In 1989 a tablet was found at the same location, which seemed to bear the name Pethor. Many concluded the Two Rivers mentioned in Deuteronomy 23:4 may very well refer to the Jabbok and the Jordan.” (www.Abarim-Publications.com.) Abarim Publications ከገቡ በሁዋላ Pethor የተባለውን ይመልከቱ፡፡ እስራኤላውያን ጠላቶች እስራኤሎችን እርገምልን የአሉት ሰዎች የኖሩት በዛሬው እስራኤል አቅራቢያ በሞአብ ግድም ነው እንጂ በኢራክ አልነበረም፡፡ እሱ የኖረው የትየለሌ ኢራክ ውስጥ ከሆነ የት አግኝተውት ነው እስራኤልን እርገምልን፣ የሚሉት? ነቢዩ በአህያ ነው ይጉዋዝ የነበረው፡፡ ያውም ብዙ ዐመት ባገለገለችው ባረጀች አህያ፡፡ ታዲያ ከኢራክ እስራኤል ድረስ ባንድ አሮጌ አህያ መጉዋዝ ይቻላል? ብዙ የአህያ ውርንጭሎች እንኩዋን እየተቀያየሩ በየበርሀው ነቢዩን ቢሸከሙት ጉዞው አያሌ ወራት ሳይፈጅ ይቀራል? ነው ወይንስ ባላቅ የኢራቅ ንጉሥ ነበር? እንደዛ ከሆነ፣ እሩቅ የአሉትን የኢራቅ ሰዎች በፍልስጥኤም አካባቢ በሞአብ የሰፈሩት እብራውያን ምን ያሰጉዋቸው ነበርና ነው ኢራቅ የአሉት በልአምን እርገምልን የሚሉት? እዚህም ላይ ተሳስተዋል፡፡ This doesn’t stand to reason ይላሉ አሜሪካኖች፡፡ በልአም ኢራክ አልነበረም የሚኖረው፡፡ ለሽርሽር ወደ ሞአብ/እስራኤል መጥቶ ነው ካላሉን በቀር፡፡ የመካከለኛውን ምስራቅ ካርታንና መጽሀፍ ቅዱስን ገልጠው ይመልከቱ፡፡ አውነቱ ግን ዘመዳችን በልአም ከኢራቅ ይልቅ የትውልድ ሀገሩ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ጥንትና አሁንም እንደሚያደርጉት ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ እስራኤል ተጉዞ ነው እንጂ፡፡ የኢትዮጵያ ሰው ለመሆኑ ማረጋገጫው ስሙ በእነ ኢትዮጵ የዘር ሀረግ ውስጥ መገኘቱና የሸምሸልን አባት ልጁን ቀራሚድን እና የልጁን ልጅ ሸምሸልን ጣና ላይ ትቶ በመንፈሳዊ ሥራ እግዚአብሄርን ለማገልግል ወደ ሞአብ ወይም እስራኤል አካባቢ ሄዶ መኖሩ ነው፡፡ዣንሽዋ በተባለው መጻሀፋችን (ነቢዩ ሙሴ ኢትዮጵያዊው አማቱ ዮቶርአብ ዘንድ አግኝት ስለአነበበው መኖሩን ባረጋገጠውና የእግዚአብሄር ጦርነት መጽሀፍ ሲል በሰየመው፣( ዐሪት ዘሕልቆ 21 ቁጥር 14) ቢዖር ከኢትዮጵ እንደወረደና የኦሮሞ እና የአማራ ግንድ የሆነው የደሸት ቅድመ-አያት እና የሸምሸል አያት እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ የበልዖም የዘር ሀረግ እነሆ፡፡– ኢትዮጵ ቀዳማው ቢዖርን ወለደ፣ ቀዳማዊ ቢዖር አራምን፣ አራም ናጌን፣ ናጌ ሀጌን፣ ሀጌ ዳግማዊ ቢዖርን፣ ዳግማዊ ቢዖር በልአምን፣ በልአም ቀራሚድን፣ ቀራሚድ ሴቷን ነቢይ ሸምሸልን ወለደ፡፡ ሸምሸል የኦሮሞን እና የአማራን አባትና አያት ነቢዩ ደሸትን ወለደች፡፡ መጽሃፍ ቅዱሱ የበልአም አባት ቢዖር እንደሆነ ደርሶበታል፡፡ ከዚያ በላይ ያለውን ግን አልጠቀሰውም፡፡ የፈረንጅ ቲዎላጂስቶችም አያውቁትም፡፡ የእኛ ሰው እንደመሆኑ እኛ ግን በመጽሀፋችን ከገናናው ኣባታችን ከኢትዮጵ ጀምረን መዝግበነዋል፡፡ እንደ ፈረንጆቹ ለእርስዎ ቢዳፈንቦትም የእሱን ማንነት እኛ አሳምረን እናውቃለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ታላቅና የታላላቅ ሰዎች ዘር ነን፡፡ ይህን ቢያውቁት ኖሮ እርስዎም ነዎት፡፡ ነገር ግን እርስዎ ያልገባዎትን ወይም የገባዎትን ታሪካዊ ሀቅ Mythology ነው ብለው በማቃለል እህ! ብሎ የሚያዳምጦትን ያሳስታሉ፡፡ ምክንያቱም፣ የመሪራስን ብርቅዬ ብራናዎች በእጆ ማግባት ስላልቻሉ በንዴት ለመበቀል፡፡ የርሶ ችግር ይሄና ይሄ ብቻ ነው፡፡ ይህን ላልተገነዘበ የዋህ ሰው ግን ትችቶ ንጹህ የምሁራዊ ድርጊት ይመስለዋል፡፡ እርስዎ ቀና ሰው ስላልሆኑ፣ አርቀው የሚያዩ እየመሰለዎት አርቀው ለማየትና ነገሮችን ማገናዘብ አልቻሉም፡፡ ስለዚህም በአላዋቂ ድፍረትና የአልተማረ ሰው ጭካኔ በኔ ላይ ይሳለቃሉ፤ እንዲህ እያሉ–‹‹ ነቢዩ በልዓም ይኖር የነበረው ሜሶፖታሚያ (ዒራቅ) ነበር። ሚቶሎጂውን ለማሟላት ሼምሼልን ከዚያ አንሥቶ ጎጃም ላይ የጣላትን የነፋስ ሰረገላ ፈጥሮ ታሪኩ ቢጨመርለት ጥሩ ነበር።‹‹ ስለዚሀ ሸርአዊና ትእቢታዊ አነጋገርዎ አንባቢው ይፍረደኝ፡፡ በራስዎ ትክክለኛነት መቶ በመቶ ተማምነው ለአፎ ለከት ሳይኖረው ሰውን በድፍረት መዝለፎ ምሁርነትዎ እንኩዋን ቢቀር፣ እኚህ ሰው እውን ኢትዮጵያዊ ኣዛውንት ናቸውን፣ ብዬ ራሴን እንድጠይቅ አርጎኛል፡፡

እኔና እርስዎ በኢትዮጵያዊነት እና በኢትዮጵያ ታሪክ አቁዋም ላይ በጣም የተለያየን ሰዎች ነን፡፡ ርስዎ እኛ አበሾች ነን፣ ይላሉ፡፡ እኔ ‹‹አበሻ‹‹ ማለት ውርደት፣ኢትዮጵያዊነት ግን ኩራት ስለሆነ ኢትዮጵያውያን መባል አለብን፣ እላለሁ፡፡ እርስዎ ንግሥተ-ሳባ ቢልቂስ የተባለች የአረብ ንግሥት ነች፣ ወይም ኢትዮጵያዊ ያልሆነችው ቢልቂስ ነች ንግሥተ-ሳባ የተባለችው፣ ይላሉ፡፡ እኔ በእርግጥ ንግሥተ-ሳባና ቢልቂስ ሁለት የተለያዩ ሴቶች ናቸው፤ ንግሥተ-ሳባ እናትና አባትዋ ያወጡላት ስም ‹‹ኢትያኤል‹‹ ነው፡፡ ቢልቂስ ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነች አለቃዋ ንግሥተነገሥታት (ንግሥተ-ሳባ/ኢትያኤል) በየመኖች ላይ የሾመቻት በማእረግዋ ከንግሥተ-ሳባ ያነሰች ሴት ናት ብዬ ባለ 53 ገጾች ማስረጃ በመጽሀፌ ውስጥ አስቀምጫለሁ፡፡ ንግሥት-ሳባ ኢትዮጵያዊ መሆንዋንም በሚገባ አረጋግጫለሁ፡፡ ፈላስፋውና ነቢዩ ደሸት የኦሮሞ አባት፣ የአማራ አያት መሆኑን በበቂ የመከራከርያ ነጥቦች አረጋግጫለሁ፡፡ ርስዎ ሚቶሎጂ ምን እንደሆን ሳያስረዱ፣ የኛን መጻህፍት ሚቶሎጂነት ተንትነው ዝርዝረው ሳያቀርቡ ከእዚህ እና ከእዛ ትንሽ ቀንጨብ፣ ቀንጨብ አድርገው የማይመራመረውን አንባቢ ያሳስታሉ፡፡ ስለእዚህ፣ አቁወማችንን ይዘን በያለንበት እንቆይ፡፡ በመጨረሻ እንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቆት፡፡—እርስዎ ካላጡ ሥራ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያኮስስ ተግባር ላይ ለመሰማራት ለምን ታጥቀው ተነሱ? የኢትዮጵያን ጠላቶች ከማስደሰት በቀር የኢትዮጵያ ታሪክ መኮሰስና ማነስ ለእርስዎ ምን ይጠቀምዎታል? ወይንስ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያንጸባርቀውን፣ ዐለም ያደነቀውን ታሪከዋን እየተከታተለ የሚቃወም መንፈስ ወይም አባዜ ይዞዎታል ወይስ ምንድነው? እውነት የሆነውን የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጻፍ ካልቻሉ ለምን በሰለጠኑበት የቁዋንቁዋ ሙያ ተሰማርተው ቁዋንቁችን እንዲዳብር የሚረዱ መጻህፍት አይከትቡም? የኢትዮጵያን ቁዋንቁዋዎችን የሚያሳድጉ እስከአሁን ምን ያህል መጻህፍት ጽፈዋል? የእኔ እውነተኛው የታሪክ መጽሀፌ ሚቶሎጂ ነው፣ ከአሉ ከእሱ ገለል ይበሉ፡፡ እራስዎ አነበቡት እንጂ እኔ አንብቡት አላልኮትም፡፡ የእኔ መጽሀፍ ሚቶሎጂም ሆነ እውነተኛ ታሪክ የኢትየጵያ ሀዝብ ከማንነት ቀውሱ እንዲፈወስ እና ደም እንዳይፋስሰ እየአገዘ ነው፡፡ በግል ኢምንት ጉዳይዎ እና ኢጎዎ ነሳስተው መጽሀፌን ለማጣጣል የሚሞክሩት ሙከራ እትዝብት ላይ ይጥልዎታል እንጂ አይሳካልዎትም፡፡ እኔ የማደርገው የፍቅርና ሰላም ነገር እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኝ ስለሆነ ሰው ሊነቀንቀኝ አይችልም፡፡ መጽሀፌ ከእኔ ቁጥጥር ወጥቶ በእግዚአብሄር ቸርነት በመላው ዐለም የኢትዮጵያን ሀዝብ ልብ ማርኮ እንደ ሰደድ እሳት እያነደደው ነው፡፡ ይህ ይሆናል ብዬ እኔ በፍጹም አላሰብኩም ነበር፡፡ የተቀደሰ ሥራዬን እገዚአብሄር የባረከው ስለሆነ ይልቅየው ከእግዚአብሄር እንዳይጋጩ ይጠንቀቁ፡፡ እግዚአብሄር በትእግስት እድሜዎን ያረዘመልዎት ለንስሀ እንዲበቁበት ነው እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡ ከእንዲህ መጽሀፌን ለማጥላላት ለሚያደርጉት ሁሉ ሸራዊ ጥረት ምላሽ አልሰጥዎትም፡፡ ከእርስዎ ጋራ መመላለስ ጊዜና ጉልበት ይጨርሳል፡፡ ብዙ ያልታተሙ መጻህፍት ስለአሉኝ እነሱ ላይ ለማተኮር ዝምታን እመርጣለሁ፡፡ የእኔ ዝምታ ለርስዎ የማሸነፍ ስሜት ከአደለዎት ይሁንሎት፡፡ በአውቆ ሽንፈት ውስጥ ድል አድራጊነት እንደ አለ እኔ አውቃለሁና፡፡ ዝም ስለምል ግን እርስዎ የሚያመጡትን ነገር ሁሉ የሚያፈርሰ መልስ መስጠት አቅቶኝ እንዳይመስልዎት፡፡ ሰው ነገር እያኘከ እልህ ከያዘው ለተቃዋሚው መልስ አይገደውም፡፡ እኔ ግን አእምሮዬንና ልቤን ከእልህ አጽድቼ በሰናይና በኬር ልሞላቸው ስለምፈልግ ከእንግዲህ ከርስዎ ጋር የቃላት ተኩሶች አልለዋወጥም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ካንተ የተሻለ አውቃለሁ ከአሉ፣ እኔን ለቀቅ ያድርጉኝና ከእኔው የተሻለውን የራስዎን ጽፈው ያቅርቡ፡፡ እኔ እላይ የተናገርኩት ሁሉ እውነት ቢሆንም እሱን ለማፍረስና ለማሰተባበል እርስዎ ተመልሰው ብዙ ብዙ እንደሚሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሚቶሎጂ ደጋግመው የሚያወሩ ስለሆነ የኔን እውነት አሌ ለማለት ሚቶሎጂዎን ፈጥረው ብቅ ይላሉ፡፡ ለዛ ሁሉ ሚቶሎጂዎ እኔ አልመልስልዎትም፤ መመለሴ ፋይዳ ስለሌሰው፡፡ ጡረታ ወጥተው አሁን ብዙ ጊዜ እንደአለዎትም ሰምቻለሁና ጊዜዎን ለገንቢ ጉዳይ ይጠቀሙበት፡፡ አሻፈረኝ ከአሉ ብቻዎን መነጋገር ይችላሉ፡፡ እኔ ግን መደበሪያዎ እንድሆንሎት አልፈቅድሎትም፡፡ የመጨረሻው መደበሪያ” የሚለው ቃል ሀረራዊ ነው፡፡ ጊዜ ማሳለፊያ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በበኩሌ እዚህ ላይ ለሁልጊዜ ተሰናብቼዎታለሁ፡፡ You take care! አሜሪካኖቹ እንደሚሉት፡፡

ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ

No comments:

Post a Comment

wanted officials