Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, January 24, 2017

የፓትሪያርኩን ስም በማጥፋት ወንጀል ክስ የመሠረተበት የሰንደቅ ጋዜጠኛ ነፃ ተባለ



     የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የፓትሪያርኩን ስም በማጥፋት ወንጀል ክስ የመሠረተበት የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬዉ አበበ በዛሬዉ ዕለት ነፃ ተባለ። ፍርድ ቤቱ የመከላከያ ማስረጃዎች አገናዝቦ ጋዜጠኛዉን በነፃ ቢያሰናብትም፤ 100 ሺህ ብር ካሳ በተጠየቀበት የስም ክስ ገና አልተቋጨም።
         ባለፈዉ ሚያዝያ ወር 2008ዓ,ም ነዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ መንበረ ፓትሪያርክ  በሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬዉ አበበ ላይ ክስ የመሠረተዉ። ጋዜጠኛዉ ክስ የተመሠረተበት መጋቢት 25 ቀን 2008ዓ,ም «ፓትሪያርኩ ለኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት ለምዕመናን የድህነት ስጋት» በሚል ርዕስ የተጻፈን ጽሑፍ የተለያዩ አስተያየቶችን በሚያስተናግደዉ የሰንደቅ ጋዜጣ አምድ ላይ በማተሙ ነዉ። ከሳሽ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠቅላይ መንበር ፓትሪያርክ ጽሕፈት ቤት የክስ ጭብጥ ጽሑፉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አሰራር እና የፓትሪያርኩን ስም የሚያጠፋ ነዉ የሚል ነዉ። ክሱ የተመሠረተበት የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬዉ አበበ በመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ መሠረት በአንድ ወር ማለቅ የነበረበት ጉዳይ ዘጠኝ ወራትን እንደፈጀ በማመልከት የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ እንዲህ ገልጿል።
«ጽ/ቤቱ ክሱን ዋነኛ ጭብጡ አድርጎ የመሰረተዉ የፓትሪያርኩን መልካም ስም የሚያጠፋ ዘገባ አቅርበሃል በሚል ነዉ። በዚህ መሠረት እንግዲህ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ስንከራከር ቆይተናል። በእኛም በኩል ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ ካለ በኋላ፤ የመከላከያ ማስረጃዎቻችንን የሰዉ እና የጽሑፍ አቅርበን ስንከራከር ቆይተናል። እናም በዛሬዉ ዕለት ፍርድ ቤቱ በቂ የሆነ መከላከያ ስላቀረባችሁ ጥፋተኛ አይደላችሁም በሚል ዉሳኔ ሰጥቶናል። የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ክስ ዉድቅ አድርጓል ማለት ነዉ።»
የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በተጠቀሰዉ ጽሑፍ ምክንያት የተከሰሰዉ እሱ ብቻ መሆኑን ነዉ የሚናገረዉ፤
«አስተያየት የምናስተናግድበት አምድ አለ፤ የተለያዩ ሰዎችን አስተያየት ነዉ የምናስተናግደዉ፤ ከዚህ ቀደም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሚጽፋቸዉን የተለያዩ ሃይማኖታዊም ሆኑ ሌሎች ጉዳዮችን፤ በድረገጽ የወጡም አንዳንድ ጊዜ ያልወጡም እናስተናግድ ነበር። ግን ይህን የምናደርገዉ የእሱን ፈቃድ ጠይቀን ነዉ። በዚያ መሠረት ይህንን ጽሑፍ እኛ ከማዉጣታችን በፊት በድረገጽ የታተመ ነበር። ጽሑፉ ባጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን አሰራር የሚተች ነዉ። ፓትሪያርኩም ኃላፊነታቸዉን በአግባቡ አልተወጡም፤ ሙስና እና ብልሹ አሰራር በቤተ ክርስቲያን ዉስጥ በብዛት ተንሰራፍቷል የሚል አጠቃላይ ጭብጥ ያለዉ ነዉ እና ስማችን ጠፋ በሚል የጋዜጣዉን ዋና አዘጋጅ ብቻ ነጥለዉ ክስ አቅርበዋል። ጽሑፉን ያቀረበዉን ሰዉ አልከሰሱም። የእኔንም ተቋም ጨምረዉ መክሰስ ይችሉ ነበር። እሱንም አላደረጉም።»
ጋዜጠኛ ፍሬዉ እንደገለፀልን ፍርድ ቤቱ የፓትሪያርኩን ስም አጥፍቷል በሚል የቀረበዉን የወንጀል ክስ ዉድቅ ቢያደርግም የሞራል ጉዳት ደርሶብናል በሚል የአንድ መቶ ሺህ ብር ካሣ የተጠየቀበት እና በፍትሀ ብሄር የሚታይዉ ክስ ግን ገና አልተቋጨም። የሞራል ካሳ ጠያቂዉ ማን ይሆን? ፍሬዉ ያስረዳል፤
«በነገራችን ላይ አንዱ አወዛጋቢ ነጥብ የነበረዉ፤ እኛም ተቃዉመን የነበረዉ በወንጀሉም በፍትሀ ብሄሩም፤ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ፓትሪያርኩን ወክላ ክስ ልታቀርብ አትችልም፤ መብት የላትም። በስም ማጥፋት ጉዳይ ክስ ማቅረብ ያለበት ባለቤቱ ነዉ የሚል መከራከሪያ አቅርበን ነበር። በወንጀሉ ይህን አልተቀበለዉም ጠቅላይ ቤተ ክህነት ማቅረብ ይችላል ብሎ ስንከራከር ቆይተናል። የፍትሀ ብሄሩ ግን መከራከሪያችን ተቀብሎ፤ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ፓትሪያርኩን ወክላ ክስ ማቅረብ አትችልም በሚል የሚመለከታት ጉዳይ ግን ካለ ለይታ ክሷን አሻሽላ ታቅርብ ብሎ በሰጠዉ ብይን መሠረት አሁን ፓትሪያርኩን የሚመለከቱ ጉዳዮች በሙሉ ወጥተዉ አሁን የቀረበዉ (በፍትሀ ብሄሩ ማለቴ ነዉ) ጠቅላይ ቤተ ክህነትን ስም አጥፍቷል የሚሉ ነጥቦች ብቻ ናቸዉ።»
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ መሆኑን የሚናገረዉ ጋዜጠኛ ፍሬዉ አበበ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት አባቶች በዓለማዊ ፍርድ ቤት መከሰሱ የፈጠረበትን ስሜትም ገልጿል።
«የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነኝ፤ በቤተ ክርስቲያን ትልልቅ አባቶች ጭምር የሚታወቅ ክስ ዉስጥ ገብቼ በዚህ ደረጃ መከሰሴ በጣም በጣም ለሞራሌም ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለብኝ ጉዳይ ነዉ። ምክንያቱም ይሄ በቀላሉ በይቅርታ መቀረፍ የሚችል ጉዳይ ነበር። አባቶች እንደመሆናቸዉ መጠን ሊገስጹኝም ይችሉ ነበር። በዓለማዊ ፍርድ ቤት ሙግት መግጠማቸዉ፤ እነሱ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱ ከሆነ እኔ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምሄድበት ምን መሠረት አለኝ? የሚል የሞራል ጥያቄ ሁሉ አስከትሎብኛል።»

No comments:

Post a Comment

wanted officials