Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, January 22, 2017

በጃዊ ጫካ ውስጥ በርካታ ወታደሮች በረሃብና በውሃ ጥም አለቁ

በጃዊ ጫካ ውስጥ በርካታ ወታደሮች በረሃብና በውሃ ጥም አለቁ


 ኢሳት ዜና :- ከሁለት ሳምንታት በፊት በ12ኛው ክፍለጦር ስር ባለው በፓዊና አሶሳ ሰፍሮ ከሚገኘው የ6ኛ እና 7ኛ ሬጅመንቶች የተውጣጣ አንድ አሳሽ ግብረሃይል በጃዊ በረሃና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው አዲስ ናሽናል ፓርክ ውስጥ የነጻነት ሃይሎች ይገኛሉ በሚል ለአሰሳ ከወጣ በሁዋላ ፣ በአቅጣጫ መጥፋት ምክንያት በውሃና በምግብ እጦት ምክንያት በርካታ ወታደሮች ሲሞቱ ፣ በህይወት የተረፉ ካሉ በሚል በሄሊኮፕተር የታገዘ አሰሳ በመደረግ ላይ ነው። በህይወት ተርፈው የተገኙ አንዳንድ ወታደሮች ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፣ የተወሰኑት የሱዳንን ድንበር አቋርጠው በመሄድ ሱዳን ውስጥ ተገኝተዋል።
የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት በጃዊ ጫካ ውስጥ ያለቁት ወታደሮች ቁጥር በቅርቡ በሰሜን ጎንደር ዞን በቋራና አልጣሽ ፓርክ በምግብ እና በውሃ እጥረት ካለቁት የ24ኛው ክፍለ ጦር ወታደሮች ቁጥር በብዙ እጅ ይልቃል።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው ህዝባዊ ተቃውሞ አገዛዙን ፈተና ውስጥ እየጣለው ነው። ትናንት ሃሙስ በእስቴ ወረዳ መካነእየሱስ ከተማ ከምሽቱ 2 ሰአት ጀምሮ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱንና ሰሞኑን የነበረውን ውጥረት ከፍ ማድረጉን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል። የተኩሱ ምክንያት ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ የኮማንድ ፖስት አባላት ነን የሚሉ ሰዎች በአካባቢው ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ይዘው ከማሰራቸው ጋር ሳይያያዝ እንደማይቀር የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።
አንዳንድ ወጣቶች አሁንም አፈሳ በመፍራት ራሳቸውን የሰወሩ ቢሆንም፣ ካለፈው አንድ ሳምንት ጀምሮ የተለያዩ ጥቃቶችን በህቡዕ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ምሽት በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 4 በመከላከያ እና በፌደራል ፖሊስ አባላት መካካል በተፈጠረ ግጭት አንድ የመከላከያ አባል ሲገደል፣ አንድ ሚሊሺያም በጽኑ ቆስሏል። ይህንን ተከትሎ በከተማው ከፍተኛ ፍተሻ ሲካሄድ ውሎአል።
በወገራ ወረዳ ደግሞ የአስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ የሆነው ሙሉሸት ይዘዘው በደረሰበት ጥቃት ክፉኛ ቆስሎ ጎንደር ሆስፒታል መግባቱ ታውቋል። ግለሰቡ በአካባቢው የነበሩ ወጣቶችን በማስገደል፣ በማሳሰርና በማሳፈን ከፍተኛ ሚና እንደነበረው የሚገልጹት ምንጮች፣ የግለሰቡ ክላሽ ጠመንጃና ሽጉጥ ጥቃቱን ባደረሱ ሰዎች መወሰዱ ታውቋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials