ቅጥሩን የፈጸምኩት ግልጽነት በተሞላበትና በሕጋዊ መንገድ ነው›› የኢትዮጵያ አየር መንገድ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዘመናት ይጠቀምበት የነበረውን የአዳዲስ ሠራተኞች ቅጥር በመተው፣ ያለምንም ማስታወቂያ ከ500 በላይ ሠራተኞችን መቅጠሩ ቅሬታ አስነሳ፡፡
አየር መንገዱ ቅጥር መፈጸሙን አረጋግጦ በሕገወጥ መንገድ ሳይሆን፣ ግልጽነት በተሞላበትና በሕጋዊ መንገድ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
አየር መንገዱ ከወራት በፊት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ በማውጣት በርካታ አመልካቾችን ከተቀበለ በኋላ ለተለያዩ የሥራ ዘርፎች ከ37 በላይ አመልካቾችን መቅጠሩን ያስታወሱት የሪፖርተር ምንጮች፣ ሥራ እንዲጀምሩ መሠልጠን እንዳለባቸው ተነግሯቸው ጊዜያዊ መታወቂያ ተሰጥቷቸው እስካሁን ሳይጠሩ እንደ አዲስ ቅጥር መፈጸሙ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡
ቀድሞ ከሚሠሩበት መሥሪያ ቤት በመልቀቅ አየር መንገዱ ከዛሬ ነገ ይጠራናል ብለው በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ ከ500 በላይ አዲስ ሠራተኞችን ያለማስታወቂያ በመቅጠር ወደ ሥልጠና እንዲገቡ ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን እየተናገሩ መሆኑንም ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድም ሆነ ኃላፊዎቹ በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲሰጡበት መጠየቃቸውን የጠቆሙት ምንጮች፣ ከሁሉም ያጡ ሆነው ከነገ ዛሬ ይጠሩናል በሚል ተስፋ ውስጥ ያሉትን ከ37 በላይ ቅጥር የፈጸሙ ሰዎችን በአዲሱ ቅጥር ውስጥ እንዲያካትታቸው ጠይቀዋል፡፡
ያለማስታወቂያ ከ500 በላይ አዲስ ሠራተኞችን ቅጥር ፈጽሟል የተባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በሪፖርተር ለቀረበበት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ቅጥሩን መፈጸሙን አምኗል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የሠራተኞች ቅጥር የፈጸመው በሕገወጥ መንገድ ሳይሆን፣ በትክክለኛና በሕጋዊ መንገድ መሆኑን የአየር መንገዱ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አዚዛ መሐመድ በወኪላቸው በኩል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አዲስ ተቀጠሩ ስለተባሉት ሠራተኞች ምክትል ፕሬዚዳንቷ በወኪላቸው በኩል እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም. ለ31 ዩኒቨርሲቲዎች ደብዳቤ ጽፏል፡፡ አየር መንገዱ በደብዳቤው የገለጸው ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ከ2.5 በላይ ውጤት ያላቸውን ከነአድራሻቸው እንዲልኩ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹም በተላከላቸው ደብዳቤ መሠረት ለአየር መንገዱ የላኳቸው ተማሪዎች ቁጥር 6,000 እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አየር መንገዱ የተላኩትን ተማሪዎች በአድራሻቸው በመጥራት በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. ስድስት ኪሎ በሚገኘው የስብሰባ ማዕከል ፈተና መስጠቱን የገለጹት ወ/ሮ አዚዛ፣ በፈተናው ላይ የተገኙት 4,000 እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያውን ፈተና ያለፉት ተማሪዎች 1,080 መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
በአየር መንገዱ አሠራር ሠራተኛ ሲቀጠር ማንኛውም ቅጥር የሚፈጸመው በሰው ሀብት መምርያ አማካይነት እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ አዚዛ፣ የተማሪዎቹ ቅጥር ትኩረት ስለተሰጠው የተፈጸመው በከፍተኛ የማኔጅመንት ኃላፊዎች መሆኑን፣ በቃለ መጠይቅ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር በመብዛቱ ውጤታቸው ከሦስት ነጥብ በላይ የሆኑት ተደምሮ እንዲያልፉ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በተቀመጠው የመጨረሻ ማለፊያ መሥፈርት 557 ተማሪዎች ማለፋቸውንም ወ/ሮ አዚዛ ተናግረዋል፡፡ የተቀጠሩት ተማሪዎች በአየር መንገዱ በሚሰጣቸው ሥልጠና እየታዩ ለአብራሪነት፣ ለቴክኒሻንነትና ለሌሎች የአየር መንገዱ የሥራ ክፍሎች የሚሆኑት ተለይተውና በደንብ ሠልጥነው ወደ ሥራ እንደሚሰማሩ ምክትል ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል፡፡  557ቱ ተማሪዎች ከሁሉም ዩኒቨርሲቲ የተመረጡ በመሆናቸው፣ ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ያማከለ ቅጥር መሆኑንና የዚህ ዓይነት ቅጥርም ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቀደም ብሎ አየር መንገዱ ባወጣው የሥራ ማስታወቂያ መሠረት ቅጥር ፈጽመውና የሥልጠና ጊዜያዊ መታወቂያ ከወሰዱ በኋላ ያልተጠሩትን በሚመለከት ወ/ሮ ኢዚዛ በሰጡት ምላሽ፣ የአየር መንገዱ አንድ መምርያ ሠራተኛ ሲፈልግ እንዲቀጠርለት ይጠይቃል፡፡ የሰው ሀብት መምርያ በጥያቄው መሠረት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ ከቀጠረ በኋላ፣ እንዲቀጠሩለት የፈለገው መምርያ በበጀት እጥረት ምክንያት ቅጥሩ እንዲቆይለት ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሠረት ቅጥሩ ባለበት ይቆምና በጀት ሲለቀቅ እንደሚፈጸም ተናግረው፣ በዚህ ጊዜ አሠራሩ እንደ ስህተት ገልጸዋል፡፡ረፖርተር