የገዥው ፓርቲ መሳሪያ የሆነው ምርጫ ቦርድ አንድነትንና መኢድን ከከፋፈለና ከአፈረሰ በኋላ እጁን ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ቀስሯል፡፡ የህወሓት ተላላኪ የሆነው ወንድሙ ጎላ ዛሬ ጠዋት በኢቢሲ ቀርቦ ‹‹ሰማያዊ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም አልሰማም፡፡ ይቅርታም አልጠየቀም፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ተሰብስቦ የራሱን ውሳኔ ይወስናል፡፡›› ሲል ተደምጧል፡፡
ምርጫ ቦርድ በየወረዳው ለሚገኙ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች «ከቦርድ የሚጠበቅ ውሳኔ ስላለ፣ ሰኞ ተሰብስበን እስክንወስን ድረስ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎቹን ወደ ቅጽ 4 እንዳታዘዋውሩ» የሚል መልዕክት ማስተላለፉን እና «ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረባቸውን ዕጩዎች ከመቀነስ ጀምሮ ፓርቲውን ከምርጫው ለማገድ ፍላጎት እንዳለው ከምርጫ አስፈጻሚዎች መረጃዎች ደርሰውናል» ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
«ፓርቲው ከትግራይ፣ እስከ ሞያሌ ጫፍ ዕጩ ማቅረቡ ለገዥው ፓርቲ ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ሆኖበታል» ያሉት ኢ/ር ይልቃል በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ላይ የሚደረጉት ጫናዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
«ሰማያዊ ሳይጠብቁት በመላ አገሪቱ ዕጩ በማቅረቡ ደንግጠዋል። በአዲስ አበባ 23 ዕጩዎችን አቅርበናል። አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ዕጩ ያቀረቡ ፓርቲዎች ሳይቀር በሚዲያ ሲነገርላቸው ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረባቸውን ዕጩዎች ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም። ዛሬ ጠዋት ደግሞ የምርጫ ቦርድ ባለስልጣናት በቴሌቪዥን ቀርበው «ሰማያዊ በተደጋጋሚ ብንነግረው አልሰማም፣ በመሆኑም ሰኞ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔ ያስተላልፋል ብለዋል። ይህም የሚያሳየው ሰማያዊ በምርጫው እንዳይሳተፍ ችግር መፍጠር እንደሚፈልጉ ነው።» ሲሉ ፓርቲው ላይ እየተፈጠረበት ያለውን ጫና ገልጸዋል።
የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ በዛሬው ዕለት በኢቢሲ(ETV) ቀርበው ሰማያዊ ይቅርታ ባለመጠየቁና ማስጠንቀቂያዎችን ባለመቀበሉ ነገ ሰኞ ጥር 9/2007 ዓ.ም ውሳኔ ያስተላልፋል ብለዋል። ከሌሎች ፓርቲዎች ሰማያዊን በመቀላቀል በፓርቲው ምልክት ለመወዳደር የወሰኑ ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንዲሰረዙ መደረጉና በሌሎች ዕጩዎች ላይም ከፍተኛ ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ነገረ ኢትዮጵያ መዘገቧ ይታወሳል።