ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዘገቡ ከከባድ የተሽከርካሪ አደጋ ተረፉ
‹‹እየከፋ የመጣው የተሽከርካሪ አደጋ መንስዔ የችሎታ ማነስና የሥነ ምግባር ጉድለት ነው›› ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ፣ ከገጠማቸው ከባድ የተሽከርካሪ አደጋ ተረፉ፡፡
የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቦሌ ወደ ሳሪስ በሚወስደው የቀለበት መንገድ ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ 2-68856 ቢኤምደብሊዩ አዲስ አበባ የሆነውን የቤት አውቶሞቢል እያሽከረከሩ ሳሪስ አቦ አደባባይ ላይ ሲደርሱ፣ ከደረሰባቸው ከባድ የተሽከርካሪ አደጋ ከሞት የተረፉት ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ፣ በተለይ ሲኖትራክ ደረቅ የጭነት ተሽከርካሪዎችን የሚያሽከረክሩ ሾፌሮች የተሽከርካሪውን ባህሪ ስለማያውቁትና የልምድ ማነስም ስላለባቸው በተደጋጋሚ አደጋ እያደረሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋና ብዛቱ እየጨመረ የመጣው የተሽከርካሪ አደጋ ዋና መንስዔው፣ የአሽከርካሪዎች የችሎታ ማነስና የሥነ ምግባር ጉድለት መሆኑን ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ሳሪስ አቦ አደባባይ ላይ ሲደርሱ አደባባዩን ለሚዞሩ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ ለመስጠት በቆሙበት፣ የሰሌዳ ቁጥሩ 3-54297 የሆነ አሸዋ የጫነ ሲኖትራክ ከኋላ በፍጥነት እንደመጣ እንደወጣባቸው የተናገሩት ረዳት ኢንስፔክተሩ፣ ከፊታቸው ቆሞ ከነበረ ሌላ ፒካፕ ተሽከርካሪ ጋር ተጣብቀውና የያዙት ቢኤምደብሊው የቤት አውቶሞቢል ከጥቅም ውጪ ቢሆንም፣ እሳቸው ግን በእግዚአብሔር ተዓምር መትረፋቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አደጋውን ያደረሰባቸውን ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ያሽከረክር የነበረው ሾፌር፣ አዲሱን መንጃ ፈቃድ የያዘ መሆኑንና ልምድም የሚያንሰው መሆኑን የገለጹት ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ፣ አደጋውን ሊያደርስ የቻለው ስድስተኛ ማርሽ ላይ የነበረው ፍጥነት አልቀንስ ብሎት መሆኑን ቢናገርም እሳቸው ግን አይስማሙም፡፡ አሽከርካሪው የያዘውን ተሽከርካሪ ፍጥነት መቀነስ የፈለገው፣ ቀላል እንደሆኑትና በነበሩበት ፍጥነት ላይ ማርሻቸውን ቀናንሶ በአጭር ርቀት ማቆም እንደሚቻለው አውቶሞቢሎች የነበረ ስለሆነ፣ በነበረው ፍጥነት መቀነስ ባለመቻሉ አደጋውን ሊያደርስባቸው መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ሲኖትራክና ሌሎች ከባድ ተሽከርካሪዎች ከፊታቸው ያለውን ተሽከርካሪ ርቀት በመገመት ማርሽ እያቀናነሱ ሄደው በጣም ሳይጠጉ በፍሬን በመያዝ ማቆም የሚገባቸው ቢሆንም የችሎታ ማነስ፣ ግዴለሽነት፣ ሌላ አሽከርካሪንና ሕዝብን ያለማክበር የሥነ ምግባር ችግር ስላለባቸው፣ አደጋው እየጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡ የተሽከርካሪ ችግር አንዳንድ ጊዜ ሊከሰት ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ችግሩ እየደረሰ ያለው አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን በሚያሽከረክሩ አዲስ ወይም በቅርብ ጊዜ መንጃ ፈቃድ በያዙ አሽከርካሪዎች ከመሆኑ አንፃር፣ ሙሉ በሙሉ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ላይ ችግር አለ ባይባልም፣ የአሽከርካሪዎቹ ልምድ ማነስ መሆኑ ግን አሌ የማይባል ሀቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማንኛውም መንጃ ፈቃድ የሚወስድ አሽከርካሪ የመንዳት ችሎታውን እያሻሻለ፣ ራሱን እያበቃና እየተሻሻለ ሲሄድ የመንጃ ፈቃዱንም ማሳደጉ ለራሱም ጥሩ መሆኑን የገለጹት ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ፣ አሁን ያለው የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚሄድ እንደማይመስላቸው ተናግረዋል፡፡
ባለሀብቶች ተሽከርካሪ ገዝተው መንጃ ፈቃድ ላለው ሰው መስጠታቸው ለአደጋው መባባስ አንዱ ምክንያት መሆናቸውን የሚናገሩት ባለሙያው፣ የተሽከርካሪውን ባህሪና ቴክኒካዊ ሁኔታዎችን ለሚያውቁና ልምድ ላላቸው አሽከርካሪዎች ቢሰጡ የተሻለ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡ የተሽከርካሪ አደጋ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን ረዳት ኢንስፔክተሩ በንብረት፣ በአካልና በሕይወት ላይ የሚደርሰው አደጋ አስፈሪ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ለአደጋው መጨመር መንስዔ አሽከርካሪዎች ናቸው ብሎ ማለፍ ብቻ ሳይሆን በአሽከርካሪዎች ላይ መሥራት ግዴታ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፣ በሰው ሕይወት ላይ ከሚደርሰው አደጋ በተጨማሪ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት በፈሰሰበትና ተሠርቶ እንኳን ሳይጠናቀቅ ጉዳት እየደረሰበት ያለውን የቀላል ባቡር መስመር መመልከቱ በቂ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የደረሰው ችግር በቴክኒክ ብቃት አለመኖርና በተሽከርካሪ ባህሪ ሳይሆን፣ በአሽከርካሪዎች ችግር መሆኑን አክለዋል፡፡
በአደጉ አገሮችም የተሽከርካሪ አደጋ ሊቆምና ሊቀንስ የቻለው በአሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ በቂ ሥልጠና፣ ክትትልና በባህሪያቸው ሊስተካከሉ ባልቻሉት ላይ መንጃ ፈቃዳቸውን በመንጠቅ ጭምር በመሆኑ፣ በኢትዮጵያም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰድ መግታት እንደሚቻል ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ አስረድተዋል፡፡
የተሽከርካሪ አደጋን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በተለይ በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞችና በፍጥነት ማሽከርከሪያ መንገዶች ላይ የሚታዩ ቸልተኝነት፣ ያለችሎታ ማሽከርከር፣ የአሽከርካሪዎች የሥነ ምግባር ጉድለቶች፣ በተለይ ደግሞ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቶች ላይና ካለመንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ በሚገኙ ላይ በዘመናዊ መሣሪያዎች የታገዙ ጥብቅ ቁጥጥሮችን ማድረግ እንደሚገባም ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው፡፡
Reporter newspaper
No comments:
Post a Comment