ጸሃፊ አቤል ዋቤላ በእስር ቤት ስቃይ እንደደረሰበት ተናገረ
ጥር ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሽብር ወንጀል ተከሰው ለወራት በእስር ቤት የሚሰቃዩት ዞን ዘጠኝ እየተባሉ የሚጠሩት ጋዜጠኞችና ጸሃፊዎች ዳኛ ይቀየርልን የሚል ማመልከቻ ማቅረባቸውን ተከትሎ ፣ ጉዳዩን ለማየት በተሰየመው ችሎት፣ ወጣቱ ጸሃፊ አቤል ዋቤላ በእስር ቤት ውስጥ የደረሰበትን ግፍ ተናግሯል። አቤል ከፍርድ ቤት ወደ እስር ቤት በሚመለስበት ወቅት እጅህ በሰንሰለት ለምን አልታሰረም በሚል ሰበብ ሌሊቱን ሙሉ እጆቹን በውሻ ሰንሰለት አስረው እንዳሳደሩት ተናግሯል። ማእከላዊ ታስሮ በነበረበት ጊዜ በደረሰበት ድብደባ ጆሮው ላይ ጉዳት በመድረሱ የተነሳ ፣ጆሮው ላይ የሚያደርገውን የድምጽ ማዳመጫ መሳሪያ በእስር ቤት አዛዦች እንደተነጠቀ የሃዘን ስሜት በተቀላቀለበት መልክ ተናገሯል። ማረሚያ ቤቱ በወሰደው እርምጃ ላይ መልስ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ አስተላልፏል። ተለዋጭ ቀጠሮም ለየካቲት 11 ሰጥቷል።
ታሳሪዎቹ የማሃል ዳኛው ይቀየሩልን በማለት ያቀረቡትን ማመልከቻ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ቢያደርገውም፣ ከውሳኔው በሁዋላ የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ በፈቃዳቸው ራሳቸውን ከችሎቱ አንስተዋል። በኢትዮጵያ ወጣት ጻሀፊዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ የአለማቀፍ ማህበረሰቡ መኮነኑ ይታወቃል። ይሁን እንጅ የኢህአዴግ መንግስት በአለም ማህበረሰብ ዘንድ ለሚደርስበት ውግዘት ጆሮ ዳባ እንዳለ ነው።
No comments:
Post a Comment