የከምባታ ህዝብ ሆን ተብሎ መሰረተ ልማት እንዳይገነባለት በመደረጉና በተራድኦ ድርጅቶች የተሰሩት መሰረተ ልማቶች ስራ ላይ እንዳይወሉ በደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች እየተፈፀመበት የሚገኘውን በደል በመቃወም ዛሬ የካቲት 3/2007 ዓ.ም በዱራሜ ከተማ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉን የከምባታ ህዝቦች ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በሰልፉ ወቅትም ነዋሪዎቹ መንግስት ለአካበቢው ምንም አይነት ትኩረት ባለመስጠቱ 10 ከተሞች ላይ መብራት በራሳቸው ገንዘብ ማስገባታቸውን፣ ትምህርት ቤቶችን ራሳቸው እንደሰሩ፣ ቴሌኮሚኒኬሽን የተዘረጋው በህዝቡ ወጭ መሆኑን፣ መንግስት ሰራሁት ያለው ውሃ ከሶስት ሳምንት በኋላ መበላሸቱ ሙስና እንደተበላበትና እንዳልተሰራ እንደሚያምኑ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰልፈኞቹ ‹‹ልማት ስለሌለ ልጆቻችን ስደተኞች ሆነዋል፣ ስራ አጥተው የሚሰደዱትን ልጆቻችን መንግስት ህገ ወጥ ስደተኛ ሊላቸው አይገባም፣ ህገ መንግስታዊ መብታችን ይከበር፣ መንግስት ከምባታን የሚያውቀው በስም ብቻ ነው፣ ተንቀናል፣ መብታችን ለማስከበር እንታገላለን፣ ….›› እና የመሳሰሉትን መፈክሮች እንዳሰሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ የተገኙ ሲሆን ሰላማዊ ሰልፉ ላይ እንዳይገኙ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የመንግስት ሰራተኞችም ሰልፉን መቀላቀላቸውንና በአጠቃላይ ከ20 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በሰልፉ መሳተፋቸውንም አቶ ኤርጫፎ ገልጸዋል፡፡
ሰልፉ የተደረገው በከምባታ ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመምጣቱና የደኢህዴን ባለስልጣናት ችግሩን ለመቅረፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የሚፈጸመውን በደል ለማሰማት ሲሆን የተቃውሞ ሰልፉ ህዝቡ ራሱን በማስተባበር የጠራው መሆኑም ተገልጾአል፡፡