Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, February 3, 2015

መንግስት ከምርጫው በፊት አፈናውን ያቆማል የሚለው ተስፋ መሟጠጡን ሂውማን ራይተስ ወች አስታወቀ


ጥር ፳፩(ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ድርጅቱ ባወጣው የ2014 አለማቀፍ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ እንደጠቀሰው መንግስት ጋዜጠኞችን፣ ጸሃፊዎችን እና  የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችን እንደፈለገ  ያስራል፣ በሰላም ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ በወጡ ዜጎች ላይ ፖሊስ የሃይል እርምጃ ይወስዳል፤ እንዲሁም ለማፈኛነት እየዋሉ ያሉትን በአለማቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የተወገዙትን አዋጆችን ለመለወጥ ምንም ምልክት አላሳየም ብሎአል።
ባለፈው አመት የኢትዮጵያ መንግስት ማንኛውንም ተቃውሞ ለማፈን መሞከሩን የገለጹት የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሌ ሌፍኮው፣ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎች ከሁሉም በባሰ እንደተሰቃዩና ከመጪው ምርጫ በፊት ሁኔታዎች ይሻሻላሉ የሚለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ እንደተዳፈነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየፈጸመች ያለችው አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የለጋሽ አጋራትን አለመተቸታቸውን  ሂውማን ራይትስ ወች በሪፖርቱ አመልክቷል።ሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፎችን እንዳያደረግ መከልከሉ፣ በኦሮምያ ክልል በሚያዚያና ግንቦት ወሮች የጸጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸው፣ የግንቦት7 ዋና ጻሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ህገወጥ በሆነ መንገድ የመን ውስጥ ተይዘው መሰጠታቸውና የታሰሩበት ቦታ አለመታወቁንም ገልጿል።
ዞን 9 እየተባሉ የሚጠሩ ጸሃፊዎች በጸረ ሽብር ህግ መከሰሳቸውን፣ የ6 ጋዜጣ አሳተሚዎች በተመሳሳይ ወነጀል መከሰሳቸውን የጠቀሰው ሂማውን ራይትስ ወች፣ መንግስት ዌብሳይቶችን መዝጋቱን እንዲሁም ስልኮችን በመጥለፍ መረጃዎችን እንደሚያሰባሰብ አትቷል።
በኦሞ ሸለቆ አካባቢ በርካታ ዜጎች ያለፍላጎታቸውና ተገቢው ካሳ ሳይከፈላቸው እንደሚፈናቀሉም ድርጅቱ አስታውቋል። መንግስት ተደጋጋሚ ወቀሳና ትችት ቢደርስበትም የጸረ ሽብር ህጉንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶችን ለመቆጣጠር የወጣውን ህግ ለመቀየር ፈቃደና አለመሆኑን የጠቀሰው ሂውማን ራይትስ ወች፣ የመንግስትን የልማት እቅድ የተቹ ሰዎች እስራትና ወከባ እንደሚያጋጥማቸው አትቷል።
መንግስት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማፈኑ በመጪው ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽኖ እንደሚኖረው ሌስሌ ሌፍኮው ተናግረዋል። ሂማን ራይትስ ወች በ656 ገጽ ሪፖርቱ በአለም ዙሪያ ያሉ የ90 አገራት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ቃኝቷል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials