Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, February 3, 2015

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡ አመራሮቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ችሎት ቀርበዋል፡፡
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች መቃወሚያቸው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረቡባቸው የተለያዩ የክስ ይዘቶች ላይ መቃወሚያቸውን አቅርበውየነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት የጠየቀውን በመቀበል ‹‹በመቃወሚያው ላይ የተነሱት ነጥቦች በአብዛኛው ማስረጃ በማሰማት ሂደት ወቅት ሊረጋገጡ የሚችሉ ስለሆኑ›› በሚል መቃወሚያቸው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ አግባብ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ በሚገኙበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ ‹‹የመብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው›› በሚል አቤቱታ አቅርበው የነበር ሲሆን በአቤቱታው ላይ እስካሁን ከማረሚያ ቤቱ መልስ አለመሰጠቱ ታውቋል፡፡ አቤቱታው በጽሑፍ ተገልብጦ ለማረሚያ ቤቱ መላኩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ለአቤቱታው መልስ ከማረሚያ ቤቱ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
በመሆኑም ይህንኑ የማረሚያ ቤቱን መልስ ለመስማትና የክሱን ሂደት ለመቀጠል ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Like ·  · 

No comments:

Post a Comment

wanted officials