Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, February 26, 2015

ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማቀራረብ እንዲሠሩ ጥሪ ቀረበላቸው


d05a8d7ee8d0e351bf5811d80acac7c7_Lየኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ካርዲናል ሆነው ባለፈው ሳምንት በቫቲካን የተሾሙት ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችን በማቀራረብ በሁለቱ አገሮች መካከል ዘላቂ ሰላምና ወንድማማችነት ዳግም ለመመለስ እንዲሠሩ ጥሪ ቀረበላቸው፡፡
ከሮም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት (ፖፕ) ፍራንሲስ የካርዲናልነት ሹመት ተቀብለው ለተመለሱት ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ፣ ባለፈው እሑድ በአዲስ አበባ ካቶሊክ ልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተደረገው ሥርዓት ቅዳሴና የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ጥሪውን ያቀረቡት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡
‹‹ጥሩ ጎረቤት መሆን ያቃተን ለምንድን ነው? አባትና ልጅ ወንድምና ወንድም ተለያይተው የሚኖሩት ለምንድን ነው? የብፁዕነታቸው መሾም በካርዲናልነት ለመፍትሔው አንድ ትልቅ ዕርምጃ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፤›› ያሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ ‹‹የካርዲናል ብርሃነየሱስ ከፍተኛ ቦታ ላይ መሾም ለአገራችን፣ ለጎረቤቶቻችን ሰላም ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ትልቅ መልክዕት ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ከዓመታት በፊት በኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ተጀምሮ የነበረው የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች በአብያተ ክርስቲያናቱ አማካይነት የማቀራረብ ሒደት፣ ካርዲናልነታቸው ከግብ እንደሚያደርሱት እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የካርዲናልነት ሹመቱ በአገሮቻችን የሚታዩትን ሃይማኖት ተኮር ግጭቶችን ለመፍታትና መቻቻልን ለማስፈን፣ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አመልክተዋል፡፡
‹‹ሹመት አላችሁት እንጂ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነው፣ በትህትና መንፈስ ማገልገል ነው፤›› ያሉት ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ፣ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በአኅጉሪቱም ሆነ በዓለም ደረጃ ሰላም አንድነትን ለማስፈን እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡
በሥርዓተ ቅዳሴ በተከበረው በዓለ ሲመታቸው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባዔ (አመሲያ) ምክትል ሊቀመንበር የኮር፣ ዲፕሎማቲክ አባላት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ አኅጉረ ስብከትና ጳጳሳትና ምዕመናን ተገኝተዋል፡፡
የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በሮም ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ካርዲናልነት በዓለ ሲመታቸው የተፈጸመው ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ሲደርሱ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ወደ መንበራቸው ልደታ ለማርያም ካቴድራል ያመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ቤተ መንግሥታዊ አውቶሞቢል ነው፡፡
ከቸርችል ጎዳና ወደ ካቴድራል በሚያመራው መንገድ እስከ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተጓዙት በእግራቸው ሲሆን ምዕመናን ግራና ቀኝ ሆነው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የ67 ዓመቱ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ፣ ከመንፈቅ በፊት በማላዊ ሊሎንግዌ ከተማ በተካሄደው የ17ቱ የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ኅብረት (አመሲያ) ፕሬዚዳንት ሆነው በመመረጥ በማገልገል ላይ ሲገኙ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለርም ናቸው፡፡ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ራስዋን እሰከቻለችበት እስካለፈው ወር ድረስ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጳጳሳት ምክር ቤትንም በሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ ሆነውም እያገለገሉ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲመተ ካርዲናል አስመልክቶ በላኩት የደስታ መግለጫ መልዕክት፣ ካርዲናል አቡነ ብርሃየሱስ በቤተ ክርስቲያኒቱና በቅድስት መንበር ላከናወኑት ሐዋርያዊ አገልግሎትና ኢትዮጵያም ለእምነቱና ለእምነቱ ተከታዮች ልማት ላደረገችው ዘላቂ አስተዋጽኦ ለተጫወቱት ሚና የተሰጠ ዕውቅና ነው ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በኢትዮጵያ የካቶሊክ እምነት በተንሰራፋበት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ 71 ጳጳሳት ያለፉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከ20 በታች የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ካቶሊክ ጳጳስ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተሾሙት አቡነ ዮሐንስ መጥምቅ ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ካቶሊካዊ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ያገለገሉት አቡነ ጦቢያ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው፡፡
በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመርያ አጋማሽ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ መንበር በሊቀ ጳጳስነት ከ1953 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. የተቀመጡት አቡነ አሥራተ ማርያም የምሩ ሲሆኑ፣ ተከታያቸው ደግሞ ካርዲናል ጳውሎስ ፃድዋ ከ1969 ዓ.ም. እስከ 1991 ዓ.ም. ተቀምጠው ነበር፡፡
አቡነ ጳውሎስ ፃድዋ በቫቲካን ካርዲናል በሆኑ (ግንቦት 17 ቀን 1977 ዓ.ም.) በ30ኛው ዓመት ካርዲናል የሆኑት አቡነ ብርሃነየሱስ፣ የአዲስ አበባ ሜትሮፖሊታንን በሊቀ ጳጳስነት መምራት ከጀመሩ 16 ዓመታት ሞልቷቸዋል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment

wanted officials