አባዱላ ገመዳ ኦኤምኤን እና የሞራል ኪሳራ – [እንደ ፖለቲካ ሜሞ ነገር] – ከታምራት ነገራ (የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ)
ሰሞኑን የኦህዴድ መስራች የሆነት አባዱላ ገመዳ በሚኒሶታ ከኦኤምኤን ጋዜጠኞች ጋር መቋደስ (ፈረንጆቹ Wine & Dine እንደሚሉት) ለብዙዎች እጅግ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በበርካታ የዳያስፖራ ሰዎች ዘንድ ( ኦሮሞዎችም ሆኑ ኦሮሞ ያልሆኑት ) ኦኤምኤን እንደ አንዱ የተቃዋሚ ድምጽ (ኢሳት፤ ኢትዮሚዲያ ምናምን)ስለሚታይ ክሳቸውም ሆነ ቁጭታቸው በአብዛኛው ኦኤምኤን ከተቃዋሚነት ተንሸራተተ ወደ መንግስት አፈገፈገ የሞራል ኪሳራ ደረሰበት ወደሚል ሲያዘነብል ይታያል፡፡
የኦኤምኤን ተመልካቾች ስለኦኤም ኤን ይሄን የመሰለ ግንዛቤ መያዝ አልነበረባቸውምን በፍፁም፡፡ ኦኤም ኤን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሚያሰራጫቸው ፕሮግራሞች፤ በሚጋብዛቸው እንግዶች፤ በሚዘግባቸው ዜናዎች በአጠቃላይ በቅስቀሳው የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚነት ማዕረጉን በሚገባ አግኝቷል፡፡ ተመልካቾቹም ኦኤምሜንን እንደተቃዋሚ መገንዘባቸው ከውጪ ሲታይ ስህተት አይደለም፡፡
ያው የኢትዮጵያ ነገር ከላይ ከላይ ብቻ ሳይሆን ውስጥ ውስጡንም መበርበር ስለሚያፈልግ ኦኤምኤን የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ ነው የሚለውን ሀሳብ እራሱ በጥቂቱም ቢሆን እንፈትሸው፡፡
1 ኦኤምኤን የኦሮሞ ብሄርተኛ ድርጅት ነው
ስለ ኦኤምኤን ስንነጋገር መጀመረያ መገንዘብ ያለብን ዋነኛ ነገር ኦኤምኤን እነደ ኢሳት የተወሰነ የአንድ ፓርቲ ንብረት፤ ለአንድ ቡድን ኤዲቶሪያል አቋ ተጠያቂ ድርጅት አለመሆኑን ነው፡፡ ኦኤምኤን ተጠያቂነቱ በአብዛኛው ለኦሮሞ ብሔርተኝነት እንጂ ለፓርቲ፤ ቡድን ፤ድርጅት አይደለም፡፡ ይህ ተቋሙን በጣም ልቅቅ ያለ (Amorphous) የሆነ የኤዲቶሪያል ክፍተት ይሰጠዋል፡፡ ለምሳሌ የኦኤምኤን የኦነግ ንብረት ቢሆን ኖሮ እነዲህ ያለ ምግብ እና መጠጥ ከኦህዴድ ባለስልጣን ጋር እጅግ ይከብድ ነበር፡፡ ነገር ግን ኦኤምኤን የኦነግም የኢሳትም የማንም ይሄ ነው የሚባል ድርጅት ተጠያቂነት የለበትም፡፡ ኦኤምኤን ሲቋቋምም ኦሮሞ ፈርስት በሚለው ንቅናቄ ውስጥ የተወለደ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ይህ ንቅናቄ ደግሞ ይሄ ነው የሚባል የፖለቲካ ድርጅት ወይንም ተቋም አላቋቋመም፡፡
ምናልባትም የኦሮሞ ፈርስት ትልቁ ድርጅታዊ መገለጫ ኦኤምኤን ነው ልንል እንችል ይሆናል አንጂ ኦሮሞ ፈርስት ወደምንምም ድርጅት ሲያድግ አላየንም፡፡
2 ይህ የኦኤምኤን እና የኦህዴድ የመጀመሪያው ግኑኝነት አይደለም
እነደው ዛሬ አባዱላ ከኦኤሜን ጋዜጠኞች ጋር በይፋ ተቀምጠው መብላት እና መጠጣታቸው ለብዙዎች አንግዳ ይሁን እንጂ በኦህዴድ/ ኦሮሞ ፈርስት/ ኦኤሜን መካከል የነበረው ግኑኝነት ወይንም ሲግናል ልውውጥ ዛሬ የጀመረ አይደለም፡፡
2.1 የኦሮሞ ፈርስት ቀስቃሾች በቴዲ አፍሮ “ቅዱስ ጦርነት” ኢንተርቪው ምክንያት ከበደሌ ቢራ እና ሄነከን ጋር የነበረውን ግኑኝነት ላይ የግዢ ማዕቀብ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ሲቀሰቅሱ ቅስቀሳቸውን ተቀብሎ አገርቤት ላይ ኦህዴድ ባያስተጋባው እናም እንዲተገበር ጫና ባፈጥር ኖሮ በቴዲ ላይ የተነሳው ቅስቀሳ ከሚኒሶታ ጫጫታ አያልፍም ነበር፡፡ የተነሳውን ቅስቀሳ ኦህዴድ በኦሮሚያ ውስጥ እግር እና እጅ ስለሰጠው በፍጥነት ውጤት ሊያስመሰግብ ችሏል፡፡
2.2 የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን የኦህዴድ ካድሬዎች ሲቃወሙት የኦሮሞ ፈርሰት ቀስቃሾች /ኦኤሜን በሚገባ ጩኸታቸውን በማስተጋባት እና በማስተናበር ከኦህዴዴ የተወረወረውን አጀንዳ ሰፊ ሽፋን እና ቅስቀሳ እንዲያገኝ አድርገው ነበር፡፡
በእነዚህ ነጥቦች ምክንያት እኔ ስለ ኦኤምኤን እና የአባዱላ ቸበርቻቻ ስናወራ ትኩረታችን መሆን ያለበት በ ኦኤሜን ላ ሳይሆን ስለ ኦህዴድ እና ኦኤምኤንን ስለሚገዛው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነው እላለሁ፡፡
3 ኦህዴድ የኦሮሞ ብሔርተኝነት እውነተኛ ልጅ ፤ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዲቃላ፤ የኦሮሞ ብሔርተኝነት አተላ፤ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ልዑል፤ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ትል…
አባዱላ በሚኒሶታ ከኦኤምኤን ጋር ያደረገው ቸበርቻቻ ቀላል ከመሰላችሁ እጅግ ተሳስታችኋል፡፡ እስቲ የትኛው የኢሃዴግ ባለስልጣን ነው ከኢሳት ወይንም ከየትኛውም በዳያስፖራ የሚገኝ ተቃዋሚ ከሚባል ሚዲያም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ጋር እንዲህ በውጭ አገር ቸበርቻቻ አድርጎ በሰላም ወደ አገርቤት የሚመለስ፡፡ እንዲህ ያለው አንዴ ከተቃዋሚ ተብዬዎች ጋር የመንሸረሸር ሰፊ ስፍራ ያላቸው ኦህዴዶች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ መመቻመች ደግሞ የሚመነጨው ከኦህዴድ ልዩ የፖለቲካል ኢኮኖ እና ኦህዴድ እራሱን ከተከለበት የኦሮሞ ብሔርተኝነት አፈር ነው፡፡ እስቲ ሁለቱን ለያይተን እንመርምር፡፡
3.1 የኦህዴድ እና የቀንድ አውጣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚዉ
ስለ ኦህዴድ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስንወያይ አንደኛ የኦህዴድ ደጋፊዎች፤ የኦህዴድ አባልት ፤ የኦህዴድ አመራሮች የራሳቸውን የተለያዩ ፍላጎቶች፤ ጥቅማ ጥቅሞች ማወቅ ፤መምረጥ እና ማስፈፀም አንደሚችሉ ብቁ ነጻ ግለሰቦች (free agents )ስለሚወስዷቸው እናም ስለቀረበላቸው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምርጫዎች መወያየት ማለት ነው፡፡
በኡኑ የኢትዮጵያ ስርአት የኢትዮጵያ ቆራጭ ፈላጩ ወያኔ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ያም ሆኖ ወያኔ ያለ ኦህዴድ ሙሉ ተሳትፎ ኦሮሚያን ለማስተዳደር የሚያስችለውን፤ የሞራል ድጋፍ ፤ የቢሮክራሲ፤ ወታደራዊ እና የደኅንነት ኃይል ማግኘት ፈጽሞውንም አይችልም፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ የብሔር ፌደራሊዝም ቅርፅ ደግሞ ይሔን አጋጣሚ ለኦህዴድ የበለጠ የተመቻቸ አድርጎለታል፡፡
በቀድሞው ስርአት ወለጋን ሆነ ሀረርን ሆነ ኢሉአባቦራን የሚያስተዳድረው ሰው የግድ የአካባቢው ተወላጅ የአካባቢው ቋንቋ ተናጋሪ መሆን አልነበረበትም፡፡ ስርአቱ ባገኘው አጋጣሚ የሚያስተዳድራቸውን አካባቢ ሰዎች ይጠቀማል፡፡ በአካባቢው የሚያገለግለው ሰው ካላገኘ ደንታው አይደለም፡፡ ከሌላ ክፍለሀገር የፈለገውን ይመጥነኛል ያለውን አማርኛ ተናጋሪ አምጥቶ ይሾማል፡፡
ይህ ከሚኒሊክ እስከ ደርግ የነበረው የኢትዮጵያ አስተዳደር ስርአት አሁን ሙሉ ለሙሉ አክትሞለታል፡፡ በአሁኑ የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ቅርፅ ወያኔ ኦሮሚያን ለማስተዳደር እና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚስፈልገውን የሰው ሃይል ለመሾም ከትግራይ ወይንም ከሌላ ክልል ሰው አስመጥቶ ሊሞላው አይቻለውም፡፡ ወያኔ ኦሮሚያን ለማስተዳደር ወደደም ጠላም ኦሮሚያ ካፈራቻቸው ልጆች ጋር ዋጋ መደራደር ይኖርበታል፡፡
በዚህ ድርድር ኦህዴድ ለወያኔ አገዛዝ የሰው ሃይል እና የሞራል ድጋፍ ያቀርባል፡፡ ስርአቱን በአይዮሎጂም ሆነ በእንቅስቃሴ እንቢ የሚሉትን የኦሮሞ ልጆች በማስፈራራት፤ በእስር፤ በአፈና፤ በቶርቸረር እና በግድያ ይመነጥራል፡፡ አሊያም ደግሞ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን በማቅረብ በማባበል ስርአቱን እንዳይቃወሙ ያማልላል፡፡ ወያኔ በበኩሉ ለኦህዴድ ከሚዘርፈው ትልቁ እንጀራ ላይ ለኦህዴድ ፍርፋሪውን ይጥልለታል፡፡
የኦህዴድ አባላትም አንደግለሰብም ሆነ ኦህዴድ እንደድርጅት ኢትዮጵያን ከወያኔ ቀምተው ማስተዳደር፤መግዛት አይፈልጉም፡፡ በኦህዴድ ውስጥ በአብዛኛው የተጠቀጠቁት ግለሰቦች ወያኔ የሚጥልልን ትርፍራፊ ይበቃናል በሚሉ የፍርፋሪ እስፔሻሊቶች የተሞላውም ለዚህ ነው፡፡ ይሄንን አይነቱን የፍርፋሪ ሱሰኝነት ነው የቀንድአውጣ ፖለቲካዊ ኢከኖሚ ያልኩት፡፡
ቀንድ አውጣን በባሕር ውስጥ የምታገኙት ደለሉ ላይ እየተንፏቀ አፈር ሲምግ እንጂ እንደሻርኮች አሳነባሪ እያደነ ሲበላ አይደለም፡፡ ባዮሎጂስቶቹ እነቀንድ አውጣ በምግብ እርከን ውስጥ ያላቸውን ደረጃ ለማሳየት Bottom Feeders ይሏቿል፡፡ እነ አባዱላም የሰው ቀንድ አውጣዎች ናቸው፡፡ እንደእነ መለስ መንግስቱ ኃይለስላሴ ሻርክ ሆነው ኢትዮጵያን ጠቅልሎ ለመግዛት ምኞትም ፍላጎትም ብቃትም የሌላቸው እውነተኛ Bottom Feeders
3.2 የኦሮሞ ብሔርተኝት የሞራል ቀውስ
ኦህዴድን ተችተን ኦህዴድን የመሰለ የቀንድ አውጣ መንጋ የፈለፈለውን የኦሮሞ ብሔርተኝነተን ሳንተች ብናልፍ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ይሆንብናል፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኝነት የኦህዴድ ቀንድአውጣ መፈልፈያ ከመሆኑ በፊት ጥንስሱን የጣሉት እን ጀነራል ታደሰ ብሩ ፤ኮለኔል አለሙ ቂጤሳ፤ ዳንኤል አበበ (የራስ አበበ አረጋይ ልጅ) አይናቸው ያነጣጠረው ኦሮሚያ በሚባል የኢትዮጵያ ቁራሽ ላይ ሳይሆን ኢትዮጵየን ጠቅልሎ ለኦሮሞ በመግዛት ላይ ነበር፡፡ እኒህ እኒህም እውነተኛ የፖለቲካው ባህር ሻርኮች ነበሩ፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ስርአት ሞተር ቁልፍ አንቀሳቃሽ የሆኑ ግለሰቦች የሚኒሊክ ዙፋን ጉልበት በሚገባ የታያቸው፤ የወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነትን እንዲሁም የቤተመንግስት መግቢያ እና መውጫ የተገነዘቡ፤ በእጅጉ የሰለጠኑ ፕሮፌሽናሎች ፤ ኢትዮያን እና አፍሪካ ቀንድን ፖለቲካ ጠንቅቀው የሚያውቁ በሳል ሰዎች ነበሩ፡፡
በ1960ዎቹ የነበረው የስርአት ለውጥ የፈጠረው ግርግር ፤የዘመኑ የአይዲዮሎጂ ነፋስ እና የተማሪዎች ንቅናቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኦሮሞን ትግል መሪነት ከእነዚህ ቴክኖክራቶች እጅ አውጥቶ ከዘኣውንቶቹ የበለጠ አይዲዮሎጂካል እናም ራዲካል ወደሆኑት ወጣቶች እጅ አዘዋወረው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነነት ጥያቄም ኦሮሞ ኢትዮጵያን በበላይነት ይግዛ ከሚል ተጨባጭ እናም ተዓማኒ የፖለቲካ ጥያቄ ይልቅ ኦሮሞ አበሻ አይደለም፤ ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ትገንጠል ፤ ኢትዮጵያ የምትባል ነገር የለችም፤ አልነበረችም ወደሚል የኤዲዮሎጂ እና አንትሮፖሎጂ እቃ እቃ ጨዋታ ዘቀጠ፡፡
ኦነግ ከወያኔ እና ሻቢያ ጋር አዲስ አበባ ሲገባ ለኦህዴድ ትልቅ ትኩረት የሰጠው ሰው አልነበረም፡፡ ወያኔ አዲስ አበበባ ሲመጣ የኦሮሞ ልሂቃን በእውቀትም ይሁን በስሜት በመነዳት በአብዛኛው የተቀላቀሉት ኦነግን ነበር፡፡ ኦህዴድ ጉዞውን ሀ ብሎ የጀመረው እንደኦነግ በአብዛኛው የኦሮሞ ምርጥ ልጆችችን በመያዝ ሳይሆን በትምህርትም ሆነ በልምድ ሆነ በግል ታሪካቸው እዚህ ግባ የማባሉትን ከወዳደቁበት እያነሳ፤ ከየተማረኩበት እየለቃቀመ ነበር፡፡ ኦነግ የሽግግር መንግስቱን ጥሎ ሲወጣ በኦሮሞ ታሪክ ከፍተኛ ሊባል የሚችለው የኤሊት ቀውስ ተነሳ ማለት ስህተት አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መዋቅር ውስጥ ከዘውዱ ስርዓት ጀምሮ የተከማቸው፤ በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠነው እና የስራ ልምድ ያዳበረው የኦሮሞ ቢሮክራሲያዊ ኃይል የኦነግ ልጣፍ ተሰጥቶ ተባረረ ተሰደደ፤ታሰረ ተገደለ፡፡ በወቅቱ ዋጋ እነደሌለው አሸዋ መሬት ላይ የተበተነው የደርግ ጦር ፤ፖሊስ እና ደህንነት ኃይል በአብዛኛው የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ እነደነበር አይዘንጋ፡፡
በዚህ ኦሮሞን ከአትዮጵያ ቢሮክራሲ የማጥራት ስራ ተጠያቂው ወያኔ ና ኦህዴድ ብቻም አይደሉም፡፡ የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞች በትንሹ እንኳን ለኢትዮጵያዊነት ስሜት የነበረውን መምህር ሆነ የመምሪያ ሃላፊ ጎበና በሚለው አዲስ ልጣፍ እየሰጡ ቁም ስቅሉን አሳዩት፡፡ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መዋቅ ውስጥ ለመገንባት ከ50 ዓመት በላይ የፈጀበትን የቢሮክራሲያዊ ኃል 5 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በራሱ ፈቃደኝነት እና ሙሉ ተሳትፎ ሙሉ ለሙሉ ተነጠቀ፡፡ ኦሮሞም በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ዋናው ወሳኝ ተሳታፊ ሳይሆን በኦህዴድ በኩል ህወሃት በትግርኛ ስለ አጠቃላይ ኢትዮጵያ አጀንዳ ፤ሲያቀርብ፤ ሲሲበሰብ እናም ሲያጸድቅ የተወሰነውን በአስተርጓሚ የሚሰማ እና አስፈፃሚ ብቻ ሆነ፡፡
የኦሮሞ ብሔርተኝነት የኢትዮጵያን ጨቋኝ ስርአት ሳይሆን ኢትዮጵያን እራሷን እንደኦሮሞ ችግር እንዲያይ ሆኖ ስለተቀረፀ 1ኛ ኦሮሞ ብሔርተኝነት በአብዛኛው እራሱን በመንፈስ ከኢትዮጵያ አግልሎ ይሄ ነው የሚባል ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ማምጣት የማይችል ልፍስፍስ ሀሳብ ሆነ 2ተኛ የኦሮሞ ብሔርተኝነነት ኢትዮጵያን እራሷን በኦሮሞ ላይ እነደተጫነች ችግር አድርጎ ስለሚገነዘባት ኦህዴድን አመራሩን አባላቱነ የስርአቱ ዋናኛ የጭቆና አካላት መሳሪያዎች እናም ተሳታፊ አድርጎ ከመገንዘብ ይልቅ ኦህዴድም በኦሮሞነቱ ምክንያት ተጨቋኝ ነው ወደሚል ተረት ተረት ውስጥ ወደቀ፡፡
በዚህ አይነት የሞራል ኪሳራ ውስጥ ያለው የኦሮሞ ብሄርተኛ ምኒሊክን እና ኢትዮጵያን እስከሰደባችሁለት ድረስ ዛሬ እናቱን ወስዳችሁ ፊትለፊቱ ብትገሏት እናንተን በአደባባይ ያሞግሳል፡፡ ለዚህ ነው እድሜ ልካቸውን ሙሉ ኦህዴድ የነበሩ የኦሮሞን ልጅ ሲያስገድሉ ሲያስመነጥሩ የነበሩ ቀንደኛ ካድሬዎች ለወያኔ ያሽቃበጡበት ምላስ ሳደርቅ ዳያስፖራ መጥተው ዋነኛ የኦሮሞ ትግል አቀንቃኝ መስለው የሚቀርቡት፡፡ እዛ ኦህዴድ ሳለህ በኦሮሞ ላይ ምን ስትሰራ ነበር ማንን ምን አስደረክ ብሎ የሚጠይቃቸው ግለሰብም ስርአትም የለም፡፡ ኢትዮጵያን መርገም በወንድሞቻቸው ላይ የፈፀሙትን ሃጢያት ሁሉ ይቅር ያስብልላቸዋል፡፡
የኦሮሞ አምላክ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከኣባዱላ አይነት ቀንድ አውጦጭ ነጥቆ ወደ ኦሮሞ ሻርኮች ይመልስልን፡፡
ይህ ጽሑፍ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በፌስቡክ ገጹ ያስቀመጠው ነው::
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=38711#sthash.M8qg36Oc.dpuf
No comments:
Post a Comment