Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 23, 2015

የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ በፓትርያርኩ መታገዱን ተቃወሙ

የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ በፓትርያርኩ መታገዱን ተቃወሙ

አማሳኞች ባለመገሠጻቸው ‹‹እነ እገሌ ምን ተደረጉ? እኛስ ምን እንኾናለን?›› በሚል በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ላይ እየዘበቱና ሀገረ ስብከቱን ለማወክ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
በሃይማኖት ሕጸጽ ስለሚጠረጠሩ ሰባክያንና ሥርዐት አልባ ዘማርያን የሚቀርቡ ማስረጃዎች ውሳኔ ሳያገኙ ምደባና ስምሪት መሰጠቱ ሰንበት ት/ቤቶችን እያዳከመ ነው፡፡
በአማሳኝ አለቆችና በሙዳይ ምጽዋት ገልባጮች ግርግር የውኃ ሽታ የኾነው የሀ/ስብከቱ ተቋማዊ ለውጥ ጥናት ለሰንበት ት/ቤቶች በሚያመች አኳኋን የሚተገበርበት ኹኔታ እንዲጤን ተጠይቋል፡፡
የአ/አ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ድረ ገጽ በቅርቡ ይፋ ይኾናል፤ ሊቀ መንበሩ ‹‹መንግሥት ከኛ ጋራ ነው›› በሚሉ ግለሰቦች ዛቻና ማስፈራራት እየተደረገባቸው ነው፡፡
* * *
‹‹አባ እስጢፋኖስን ከአዲስ አበባ ያስነሣነው እኛ እንጂ ሲኖዶሱ አይደለም የሚሉ አማሳኞች በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ባለመገሠጻቸው አኹንም ተከታዮቻቸውን ይዘው ብፁዕነትዎን ለማስነሣት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እኛ እናስቀይራችኋለን፤ ዕድገት እናሰጣችኋለን፤ እናሾማችኋለን እያሉም ለሠራተኞች ይናገራሉ፤ የማይደግፏቸውን በገንዘብ ኃይል ከቦታቸው እንዲፈናቀሉና ያለፈቃዳቸው እንዲዛወሩ ያደርጓቸዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ በእጃችን ናቸው፤ የምንፈልገውን እናስፈጽማለን ስለሚሉ የሲኖዶሱ ልዕልና ጠፍቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ በግለሰቦች የምትመራ አስመስለዋታል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሰርቀው ባካበቱት ሀብት መልሰው እያወኳት ይገኛሉ፡፡ ይህም የወጣቱን የአገልግሎት ተነሣሽነት እየተጎዳ ነው፡፡›› /የካ፣ አራዳና ጉለሌ ክ/ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት/
‹‹አማሳኝ አለቆችና አንዳንድ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ከመዋቅር ውጭ የአካባቢ ወጣቶችን እያደራጁ ከሰንበት ት/ቤቶች ጋራ በማጋጨትና በፖሊቲካ እየወነጀሉ ሕገ ወጥ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅና የኑፋቄ ዓላማቸውን ለማራመድ ይሠራሉ፤ በዐውደ ምሕረት ፀረ – ሰንበት ት/ቤት ቅስቀሳ ያካሒዳሉ፤ ሰንበት ት/ቤቶችን የሚደግፉ ካህናትን ያሸማቅቃሉ፤ ያዘዋውራሉ፤ ክህነት ያላቸው የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮች ከመቅደስ ያባርራሉ፤ መምህራን የሚጋበዙት በዓላማና በጥቅም ትስስር ነው፤ ሕገ ወጥ አሠራራቸውን የሚቃወሙ በሰበካ ጉባኤያት የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮችን ያግዳሉ፤ ለሰንበት ት/ቤቶች የሥራ ማስኬጃ በጀት አይመድቡም፤ ገቢ እንዳያገኙም ይከላከላሉ፤ ባዶ ይዞታዎችን ለመማርያ አዳራሽ ከመፍቀድ ይልቅ ለጋራዥ ማከራየትን ይመርጣሉ፡፡›› /ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት/
‹‹እንደ ግርማ በቀለና አሸናፊ መኰንን ካሉ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተወገዙ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዓላውያን ጋራ የተሳሰሩና በሃይማኖት ሕጸጽ የሚጠረጠሩ ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን ግለሰቦችን ከአባልነት አግደን ርምጃውን ለብፁዕነትዎ ለማሳወቅ ተገደናል፡፡ በአንዳንድ ሓላፊዎች ግን ‹ተዉአቸው፤ ልጆቻችን ናቸው፤ አትንኳቸው› እየተባለ በሌሎች አጥቢያዎች ኑፋቄአቸውን እያስፋፉ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ዐውደ ምሕረትዋን አታዝበትም፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች አንዱ ዓላማ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን መከላከል እስከኾነ ድረስ ለምንድን ነው ድብቅ ዓላማቸውን እንዲያራምዱና ቤተ ክርስቲያናችንን እንዲበጠብጡ የሚፈቀድላቸው? የምናቀርበው ማስረጃስ ስለምን ወቅታዊና ተገቢ ውሳኔ አያገኝም?›› /ቂርቆስ ልደታና አዲስ ከተማ ክፍላተ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት/
‹‹ቤተ ክርስቲያን የሀብታምና የድኻ ተብላ የምትከፈልበት ዘመን መጥቷል፤ ከአለቆች ጋራ የተሳሰሩ ግለሰቦች በቦሌ መድኃኔዓለም፣ በገርጂ ጊዮርጊስና በሰሚት መድኃኔዓለም የባለጸጋ ልጆችን ከሌሎች አባላት ለይተው ብር እያስከፈሉ፣ የተለየ መጽሐፍና ያማረ ቦታ አዘጋጅተው ሰንበት ት/ቤቱ የማይቆጣጠረው ትምህርት ያስተምሯቸዋል፡፡ አካሔዱ እንዲመረመር ባመለከትነው መሠረት አጥኚ ቡድን በሀገረ ስብከቱ ተልኮ እግድ ተላልፎበታል፡፡ ይኹንና አስተዳዳሪው ማን እንደሚያስፈጽመው እናያለን በሚል የሀገረ ስብከቱን መመሪያ ለማስፈጸም ፈቃደኛ አልኾኑም፤ ይልቁንም በፌዴራል አስለቅምሃለኹ እያሉ የሰንበት ት/ቤት አመራሮች እስርና እንግልት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ነገ ደግሞ በቅዳሴው ልንለይ ነው ወይ?›› /የቦሌ ክ/ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት/
* * *
‹‹የበዓል መዝሙር ከማቅረብ ውጭ እኛም እናንተም አልሠራንም፤ ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው እያለቀሱ የሚናገሩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በማየቴ ተስፋዬ ለምልሟል፤ አኹንም በየመድረኩ በሚቆሙ ተጠርጣሪ ሰባክያንና ዘማርያን ላይ ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ እንዲህ አሉ ብላችኹ አትንገሩን፤ ያሉትን በማስረጃ አጠናክራችኹ አቅርቡልን፡፡››
/መ/ር ይቅርባይ እንዳለ፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ምክትል ሓላፊ/
‹‹የአማሳኞቹን እንቅስቃሴ ዐውቃለኹ፤ ጥቅማቸው እንዳይዘጋባቸው በሰው ሕይወት ከመምጣት ወደኋላ አይሉም፤ በእነርሱ ላይ የምናየው አባቶቻችን ያልነገሩንን ያላስተማሩንን ነገር ነው፤ ከአባቶቻችን የተማርነው በንጽሕና በቅድስና ኾኖ በማገልገል የሚገኘውን በረከት ነው፤ ከየአጥቢያው ስለተነሡት ችግሮችም መረጃዎች አሉን፤ ቤተ ክርስቲያን ሙስናን በመዋጋት ሓላፊነቷን ከመወጣት ወደኋላ አትልም፤ እኔም የመጣኹት ይህን ለማስፈጸም ነው፡፡ መሾምና መሻር የእናንተ ድርሻ ባይኾንም ስለ ቤተ ክርስቲያን ግን አያገባችኹም አይባልም፤ እንዲያውም የሰንበት ተማሪዎች ሐሳብ መጋቢዎች መኾን አለባችኹ፡፡ የሰንበት ት/ቤት ማደራጃ መምሪያ እንደሚገባው አልሠራምና የድርሻውን ይወጣ፤ ሀገረ ስብከቱም ራሱን ይፈትሽ፡፡››
/ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ/
* * *
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፬ ቁጥር ፯፻፹፰፤ ቅዳሜ የካቲት ፲፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
Sunday School student applausing his holiness anti-corruption effortየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅ/ሲኖዶስ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያንን አዋርደዋል፤ አባቶችን ዘልፈዋል›› ያላቸው አማሳኝ አለቆች ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሰብአዊ መብትን የሚፃረር ነው›› በሚል በፓትርያርኩ ትእዛዝ መታገዱ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡
የአ/አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ባለፈው ሳምንት እሑድ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አዳራሽ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባካሔደው የግማሽ ቀን ውይይት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባው አማሳኝ አለቆች ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ ባለመፈጸሙ ቤተ ክርስቲያኒቱ በከፋ ኹኔታ እየታወከችና እየተመዘበረች እንደምትገኝ በተሳታፊዎች ተገልጧል፡፡
ፓትርያርኩ ‹‹አፈጻጸሙ እንዲቆይ›› ያሳለፉትን እገዳ ተከትሎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውሳኔውን ለማስፈጸም ባለመቻሉ፣ አማሳኝ አለቆች እንቅስቃሴያቸውን ለሚቃወሙ አገልጋዮች ስም እያወጡ በገንዘብ ኃይል ከሥራቸው እንዲፈናቀሉና ያለፈቃዳቸው እንዲዘዋወሩ፤ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የድርሻቸውን እንዳይወጡ ከመዋቅር ውጭ ባደራጇቸው አካላት እየከፋፈሉና ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት ሰባት›› በሚል በፖለቲከኛነት እየወነጀሉ ከአገልግሎት በማገድ ለእስርና እንግልት እየዳረጓቸው እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡
‹‹ፓትርያርኩ በእጃችን ናቸው፤ የምንፈልገውን እናስፈጽማለን›› በማለት ዕድገትና ሹመት ለማሰጠት እንደማይሳነው በመግለጽ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንዳለም ተጠቅሷል፡፡ የቡድኑ እንቅስቃሴ በዋናነት ‹‹ሊያሠሩን አልቻሉም›› ያላቸውን የወቅቱን የሀገረ ስብከቱን ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሚወነጅል ሲኾን ከመጪው የግንቦት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በፊት ከሓላፊነታቸው የሚነሡበትን ተቃውሞ የማጠናከር ዓላማ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአማሳኝ አለቆች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አለመፈጸሙ ‹‹እነ እገሌ ምን ኾኑ? እኛስ ምን እንኾናለን?›› በሚል እየተዘበተበትና ‹‹በእግሩ የመጣ በመኪና ይሔዳል›› በሚልም ለከፋ ሙስና በር መክፈቱ ተገልጧል፡፡
ለሀገረ ስብከቱ የታቀደው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ በ‹‹አማሳኝ አለቆችና ቲፎዞዎቻቸው የውኃ ሽታ›› መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፣ ያለተጠያቂነት የሚፈጽሙት ቤተ ክርስቲያኒቱን የመለያየትና የመመዝበር ድርጊት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን የአገልግሎት ተነሣሽነት እየጎዳ ከመኾኑም በላይ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶሱ ልዕልና ጠፍቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ በግለሰቦቹ እጅ ላይ ያለች አስመስሏታል›› ብለዋል፤ ‹‹ወዳልተፈለገ ነገርስ አያመራም ወይ?›› ሲሉም ውይይቱን ለሚመሩት በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሊቀ መንበር ቀሲስ ኄኖክ ዐሥራት ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡
‹‹በሃይማኖት ሕጸጽ የሚጠረጠሩ ሰባክያን ተመድበውብናል›› ያሉ የመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስና የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች በበኩላቸው፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት በዝማሬና በስብከተ ወንጌል የመሳተፍ መብታቸው አስተምህሮዋን በሚፃረሩ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎችና ሕገ ወጥ ሰባክያን ስምሪት መታወኩን በምሬት ገልጸዋል፤ በሰሚት መድኃኔዓለም በግለሰቦች ፍላጎት የባለጸጋ ልጆች ከሌሎች አባላት ተለይተውና ለብቻ ተሰብስበው ሰንበት ት/ቤቱ ሊቆጣጠረው በማይችል መልኩ የሚማሩበትና ቤተ ክርስቲያኒቱን ‹‹የሀብታምና የድኃ›› ብሎ የመክፈል አሠራር መስተዋሉን አስረድተዋል፤ የሰንበት ት/ቤቱ አመራር ይህ ዐይነቱ አካሔድ እንዲታገድ በጠየቀው መሠረት በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተላለፈው መመሪያ በደብሩ አስተዳደር ተቀባይነት ባለማግኘቱ የአመራር አባላቱ እስከ መታሰር መድረሳቸው በእንባ ተገልጧል፡፡
በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ትምህርትና ቃለ ምዕዳን የሰጡት በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ጉበኞች ፈጽሞ እንደማይተኙና እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴ መረጃው እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ እንቅስቃሴአቸው የተደራጀና በከፍተኛ ገንዘብ የተደገፈ እንደኾነ ሊቀ ጳጳሱ ገልጸው፣ ‹‹ጥቅማቸው እንዳይዘጋ በሰው ሕይወትም ከመምጣት ወደኋላ አይሉም›› ብለዋል፡፡ ይኹንና ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያርኩ አንሥቶ ሙስናን ለመዋጋት ወደኋላ እንደማትል ለተሳታፊዎች አረጋግጠዋል፡፡
his grace abune Kelemntos‹‹መሾምና መሻር የእናንተ ድርሻ ባይኾንም ስለ ቤተ ክርስቲያን ግን አይመለከታችኹም አይባልም፤ እንዲያውም የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የአስተዳደሩ ሐሳብ መጋቢዎች ናቸው፤›› ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ ወጣቱ በትጋትና በብልሃት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አጥር ኾኖ ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ከአየጥቢያው በተነሡት ችግሮች ዙሪያም የሚገባውን ያኽል አልሠራም ካሉት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ ኹሉም ራሱን እንዲፈትሽና የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ ውይይቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው አቡነ ቀሌምንጦስ አስታውቀው፣ አማሳኞች የወጣቱን ጥያቄ ከመንገድ በማውጣት ከግንቦቱ ምርጫ ጋራ በተያያዘ ትንኮሳ ከመፍጠር ስለማይመለሱ በዜግነቱም በመንፈሳዊነቱም ጥያቄውን መዋቅር ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
ጠቅላላ ቁጥራቸው ከ760 በላይ የኾኑ የ160 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አመራሮች፣ የሀገረ ስብከቱና የሰባቱም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሓላፊዎች፣ የሀገረ ስብከቱና የሰባቱም ክፍላተ ከተማ የሰንበት ት/ቤት አንድነት አመራሮች እንዲኹም ጥሪ የተደረገላቸው የአህጉረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ተወካዮች በተገኙበት በዚኹ የውይይት መርሐ ግብር÷ ‹‹የወጣትነትን ሕይወት ለቤተ ክርስቲያን መቀደስ›› በሚል ርእስ በሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ክፍል ሓላፊ መ/ር ደምስ አየለ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ በጸደቀው የአምስት ዓመቱ የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ስትራተጂ ማህቀፍ የመንፈቅ ዓመቱ ዕቅድ ክንውን ከየክፍላተ ከተሞቹ ተጠቃለው በመጡ ሪፖርቶች መነሻነት ተገምግሟል፡፡
ሰንበት ት/ቤቶች ወጥ መተዳደርያ ደንብና ተመሳሳይ ሥርዐተ ትምህርት ይኖራቸው ዘንድ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራት፣ 11‚200 አባላትን በጥራት ለማፍራት የተጣለው ግብ አፈጻጸም፣ ከመንፈሳውያን ማኅበራት ጋራ ግንኙነቶችን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች በግምገማው ተዳስሰዋል፡፡ በአጥቢያ አስተዳደርና በሰንበት ት/ቤቶች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት፣ በሥልጠናና የተለያዩ እገዛዎችን በመስጠት ለመፍታት የአንድነቱ አመራር የበኩሉን ሚና መጫወቱ ተጠቅሷል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ድረ ገጽ ግንባታ ተጠናቅቆ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲኾን ሰንበት ተማሪውም በሃይማኖት ሕጸጽ በሚጠረጠሩ ሰባክያንና ሥርዐት አልባ ዘማርያን ዙሪያ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በቅዱስ ሲኖዶስ ለተቋቋመው አጣሪ አካል እንዲያቀርብ ጥሪ ተላልፏል፡፡
በተያያዘ ዜና÷ የውይይት መርሐ ግብሩን እንደ ስጋት ከሚመለከቱ አካላት እንደኾነ የተጠረጠረ ዛቻና ማስፈራሪያ በሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤት አንድነት አመራሮች ላይ እየተፈጸመ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡ በዕለቱ ውይይቱን ሲመሩ የነበሩት የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሊቀ መንበር ቀሲስ ኄኖክ ዐሥራት ዛቻና ማስፈራሪያው ከደረሰባቸው አመራሮች አንዱ እንደኾኑ የጠቆሙት ምንጮቹ፣ ‹‹መንግሥት ከኛ ጋራ ነው፤ ቀባሪ ታጣለኽ፤ አንተን ለማጥፋት ጥቂት ገንዘብ ይበቃናል›› የሚሉ ግለሰቦች ለተከታታይ ቀናት በስልክ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዳደረሱባቸው ገልጸዋል

No comments:

Post a Comment

wanted officials