Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 9, 2015

ጓዶች ሆይ፦ ምርጫውን እርሱት! (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ -ዝዋይ እስር ቤት )

(መልዕክት-አብዬታዊያን)

ተመስገን ደሳለኝ
ከዝዋይ እስር ቤት

“ባለወር ተተካ
ተቀበለኝ ትግሌን እንካ”
(ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን)

…ሲያሻው እየጋመ፤ ሲያሻው እንደበረዶ እየቀዘቀዘ በመካሄድ ላይ ያለው የፀረ-ጭቆና ትግል እንደዋዛ ግማሽ ክፍለ ዘመን አስቆጠረ፡፡ የሂደቱ ክፉ ጎን ደግሞ የአያሌ ብርቱ ወንድም-እህቶቻችንን የህይወት ግብር እየጠየቀ ዛሬ ድረስ ተጉዟል፡፡ በተለይም ሁለቱ ቀደምት አብዮቶች (የ1966ቱ እና የ1983ቱ) ብረት-ነከስ ናቸውና የትውልድ ክፍተት እስከመፍጠር የደረሰ ዕልቂት ስለመሸከማቸው በደም የተፃፉት ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ከመዓቱ የተረፉት የዓይን እማኞችም ለወቅቱ መከራ ምስክሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አብዮቶች፣ አነሰም በዛም፣ የየራሳቸውን በጎ አበርክቶ ትተውልን ማለፋቸው ባይካድም፤ የተከፈለው መራራ ዋጋ ግን ለውጤታቸው በዝቶባቸዋል፡፡ ህይወት የተማገደላቸው እኒህ የለውጥ ንቅናቄዎች፣ የተነሱለትን ምክኒያት የዘነጉ ዋጋ-ቢስ አገዛዞችን በማዋለድ ተጠናቀዋል፡፡ እኔና የትውልድ ተጋሪዎቼም ቀሪውን የለውጥ ጥያቄ በድል ለማጀብ የቀለም አብዮትን ወደ መምረጡ ጠርዝ የመጣንበት መግፍኤ ይኅው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የ1983ቱ የኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም ውድቀትን ተከትሎ የስልጣን ባለቤት የሆኑት የማሌሊት ጓዶች ናቸው፡፡ ተረኞቹ ባነበሩት ሥርዓት የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ልዕልናን በህገ-መንግስት ሳይቀር መደንገጋቸው የሚስተባበል ባይሆንም፤ ይህንኑ መብት ለመጠቀም በሞከሩ የተቃውሞ ስብስቦች ላይ የወሰዱት ተከታታይ የኃይል ጭፍለቃዎች ግን የ“አዋጁን በጆሮ”ነት ይመሰክራሉ፡፡ በዚህ መሰሉ ግብ-ግብም ህልቆ-መሳፍርት የአገሬ ልጆች የህይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውን፤ እስር ቤቶችን ማጨናነቃቸውንና በስደት መላውን ዓለም ማዳረሳቸውን አንዘነጋውም፡፡ በርግጥም ይህን መዘንጋት ለደመ-ቀዛቃዛ ገዢዎቻችን ተጨማሪ ድል ነውና መቼም ቢሆን አናደርገውም፡፡
ሥርዓቱ በየዕለቱ የሚፈጥረውን መሰል ሰቆቃዎች አስተውለው በዝምታ ሊያልፉ ያልቻሉት፤ የወደቁትን እየተራመዱ፤ የደከሙትን እየተኩ፤ “ፋኖ-ተሰማራ”ን እያንጎራጎሩ ስለመሆናቸው ጠርቶ ከሚሰማው ድምፃቸው መረዳት አይገድም፡፡ የግብፃዊያንን፤ የቱኒዚያዊያንን፤ የዩክሬናዊያንን….አብዮታዊ ድል እያወደሱ ወደፊት የሚያገሰግሱ፤ አደባባዩን በንቃት የሚያማትሩ…. የለውጥ ጥያቄ ያነገቡ አዳዲስ ከዋክብት መፈንጠቃቸውን ጆሮዬ እየሰማ፤ ዓይኔም እያየ በመሆኑ ልቤ በደስታ ሙቀት መሞላቱን ስመሰክር በኩራት ነው፡፡
ጓዶች ሆይ፦ ገዥው-ግንባር ዛሬም እንደትላንቱ በ“ምርጫ” ስም የጭቆና ዘመናችንን ለማራዘም የማይፈነቅለው ቋጥኝ፣ የማይንደው ጋራ፣ የማይገባባት ጉድጓድ እንደሌለ በትዝብት እየተመለከትን ነው፡፡ በድርጅታዊ መዋቅሩ ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረው ምርጫ ቦርድ ፊት-አውራሪነት፤ በካድሬዎቹ ታዛቢነት፤ በጭፍራ “ተቃዋሚ“ ድርጅት አጃቢነት ለአምስተኛው ክሹፍ ምርጫ ነጋሪት እየጎሰመ መሆኑንም እያስተዋልን ነው፡፡ አልቃሻ የፖለቲካ አቋም የተጠናውታቸውን ጨምሮ ራስ-ወዳዶችና ለዘብተኞችን ከጎኑ ማሰለፉ ፍንትው ብሎ የሚታይ ኩነት ሆኗል፡፡ ይህ ሽር-ጉድ በፍፁም ልባችን የምንታመንለትን የ“ህዳሴ (ሦስተኛው) አብዬት”ን ለመቀልበስ ቀን ከሌት እያሴሩ ስለመሆኑ ይነግረናል፡፡
ርግጥ ነው፣ ሥርዓቱ ከሁለት አስርታት በላይ ያለመንገራገጭ መሰንበት የቻለው እንዳሻው በማሰሩና በዘፈቀደ በመግደሉ ብቻ አይደለም፤ መስዋዕትነትን ከሚጠይቅ ትግል ይልቅ አፋዊነትን በሚመርጡ የተቃውሞ ስብስብ ስሁት ስልትም ጭምር እንጂ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ይህ የትላንት ታሪክ ዛሬም ሊደገም ከደጅ ያለ መስሏል፡፡ በሃሳውያን የአመራር አባላት ቁጥጥር ስር የዋሉት ፓርቲዎችም የአገዛዙን የፖለቲካ ንቅዘት መተቸት ስለቻሉ ብቻ በ“ብርቱ” እየሰሩ መስሏቸዋል፡፡ ዘመኑን የሚመጥን አማራጭ የትግል መንገድ ከመከተል፤ ከቤተ-መንግስት የሚወረወርላቸውን ጥቂት የ“ምክር ቤት” ወንበርን በተስፋ መጠበቅ አብዝተው መርጠዋል፡፡ ለወይኑ ዛፍም የእጅ ስንዝር ያህል ርቀት የቀራቸው በማስመሰል ደጋግመው አታለውናል፤ ያለአንዳች ድርጅታዊ ስራ በምርጫ ለመሳተፍ ተዋክበው አዋክበውናል፤ ስተው አስተውናል፡፡ በ“ውድድሩ”ም ቀደሞውኑ የተገመተውን ሽንፈት ሲከናነቡ፤ በ“ተጭበርብረናል” የጓዳ መግለጫ ከመቃወም የዘለለ ሳይራመዱና ከታሪካዊው ስህተታቸው ሳይማሩ በቀጣዩም ለመሳተፍ ቅንጣት ሲያንገራግሩ አይስተዋሉም፡፡ ስለምን ቢሉ? “ምርጫ“ የምትለውን ቃል ነክሰው ከተከተሩ ሀያ አራት አመታትን አስቆጥረዋልና ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ የአውሮፓ ህብረት የዘንድሮውን ምርጫ እንደማይታዘብ ይፋ ባደረገበት አቋሙ ያስተላለፈውን መልዕክት ወርቁን-ከሰሙ ለይተው መረዳት ተስኗቸዋል፡፡ መቼም ኃይለማርያም ደሳለኝ “በበጀት እጥረት ነው” ሲል ማሾፉን ከቁም-ነገር ከወሰዱት የክ/ዘመኑ ታላቅ ስላቅ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም አንድን ምርጫ ዲሞክራሲያዊ የሚያሰኘው በነፃ ውድድር ላይ ሲመሰረት፣ ዜጎች ሁሉ ያለ ተፅዕኖ በፖለቲካው ላይ መሳተፍም ሆነ የሚምኑትን ያለፍርሀት መናገር ሲችሉ፤ እንዲሁም ከምርጫው በኋላ የህዝብን አለቃነት የሚቀበል መንግስት መመስረቱ ሲሳካ መሆኑን ለመረዳት ከፖለቲካ ሀሁ የዘለለ እውቀት አለመጠየቁ ከማንም የሚሰወር አይደለም፡፡ ይህን ለመረዳት ያልተዘጋጀ ግን በመጪው “ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ” ምርጫ ላይ ይሳተፋል፡፡
የሆነው ሆኖ ወደር በማይገኝለት ጥልቅ ብሶት የሰመጠ እና የሥርዓታዊ ምሬትን የመጨረሻ ፅዋ አንጠፍጥፎ የጨለጠ ህዝብ ከእሳተ-ጎመራ የሚልቅ፤ አንደዕቶን የሚንቀለቀል የቁጣ ስሜት ስለማርገዙ ለመመስከር ኮኮብ ቆጣሪ ማፈላለግን አይጠይቅም፡፡ በየግንባራችን ላይ የተቸከቸከው ብሶት-ወለድ ጉርምርምታ የአመፁ ቀናት በቅርብ ስለመሆናቸው ያስረግጥልናል፡፡ ዘመን ተጋሪዎቼም ርቱዕ ፍትህንም ሆነ የዜግነት ክብርን ከህዝባዊ እምቢ-ተኝነት እንጂ ከኮሮጆ ሊያገኙት እንደማይችሉ ካለፉበት የታሪክ ምዕራፍ ከተረዱ ሰነባብተዋል፡፡ ቅዱስ መፅሀፉም “ህግ ከሌለ ህግን የመተላለፍ በደል አይኖርም” እንዲል፤ ሥርዓቱ ከጭቆና ማራዘሚያነት በዘለለ ዋጋ በማያወጡት ቅምጥ ፍርድ ቤቶቹ በኩል እንደፈለገው የሚመነዝራቸውንና ንፁሃንን ለግፍ እስር ወህኒ የሚወረውርባቸውን የህግ አንቀፆች በእንዲህ አይነቱ ንቅናቄ ወቅት በግላጭ መጣሱ የትግሉ ቅዱስ ግዴታ መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ በርግጥ ከለውጡ ቀድሞ በሚኖረው ነውጥ ጥቂቶችን ማሰር ይቻል ይሆናል፡፡ ይህ ግን ትግሉንም ሆነ ድሉን አያቆመውም፡፡ በ1960ዎቹ አጋማሽ ታዋቂው የጥቁሮች መብት ተሟጋች አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ በመኖሪያ ቤቱ ላይ የተቃጣበትን የግድያ ሙከራ ተከትሎ በደጁ ለተሰበሰቡት እንዲህ ሲል መናገሩን ታሪክ መዝግቦልናል፦ “እኔን ብታስሩኝ እንኳን ትግላችንን ማቆም አትችሉም፡፡ ምክኒያቱም የምንሰራው ትክክል የሆነ ሥራ ነውና አምላክም ቢሆን ከእኛ ጋር ነው”
ጓዶች ሆይ፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ! ጥቂት ወራት የቀረውን የይስሙላ ምርጫ ረስተን፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን በባንዲራችን ሕብረ-ቀለማት አሸብርቀን ይህን የተጠላና በክፋቱ ወደር የማይገኝለትን ጨቋኝ-ሥርዓት በሰላማዊ አመፅ ለማስወገድ፤ እሳት በሚተፉ አንደበቶቻችን አደባባዩን ከማንቀጥቀጥ የተሻለ አማራጭ የለንም፡፡ በጩኸት የፈረሰችው ኢያሪኮ ብቻ ሳትሆን የዛሬውም አገዛዝ ስለመሆኑ ለዓለም የምናውጅባቸው ቀናት እጅግ ቅርብ ናቸው፡፡ ከነማርቲን ጋር የነበረው አምላክም ከተበደለው ህዝብ ጎን ይሰለፋል፡፡ ያኔም የሞትንላቸውና የታሰርንላቸው ጥያቄዎቻችን ጥያቄ መሆናቸው ያበቃለታል፡፡ በድላችን ማግስት ምላሽ አግኝተው ታሪክ ይሆናሉ፡
እስከዚያው ግን የነካኩትን ሁሉ በልቶ የጨረሰ ሥርዓት ቀጣይ ባለተራ የሚያደርገው ለዘብተኞችን እና “ምን አገባኝ” ባዮችን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ይህን ሁኔታም ከእኔ ደካማ ቃላት ይልቅ የባለቅኔው ሥንኞች የበለጠ አብራርተውታልና ጥቂት ቀንጭቤ ላብቃ፦

“ዝም ኣልኳቸው ዝም ይበሉኝ
ትቻቸዋለሁ ይተውኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ

ብለህ ተገልለህ ርቀህ
እውነት ይተውኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?!….

….የህሊናህ ሚዛን ረግቶ…
ጉዳዩ ሁሉ ኩልል ሲል
የደፈረሰው ሲያጠልል
እግዜር ያሳያችሁ ብለህ ፍረዱኝ እንዳትል
ከናካቴው ሳይጨርስህ
ምንም ቢሆን ሰላም አይሰጥህ”


ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com

No comments:

Post a Comment

wanted officials