አይ ሲ ሲ እና የአፍሪቃ ህብረት ትችት
ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች በአዲስ አበባ ባለፈው ሰኞ ጉባኤአቸውን ባጠናቀቀበት ጊዜ የሰነዘሩበትን ወቀሳ ውድቅ አደረገ።
ፍርድ ቤቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ የአፍሪቃ ህብረት ፍርድ ቤቱ የተነሳበትን ዓላማ በመሳት እና በዘረኝነት በመገፋፋት፣ ሆን ብሎ አፍሪቃውያንን ብቻ ዒላማ አድርጓል ሲል ያሰማውን ወቀሳ በማጣጣል የፍርድ ቤቱን ገለለተኛነት አስታውቋል። ህብረቱ ይህንን ወቀሳ የሰነዘረው ከኬንያ የ 2007 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ በሀገሪቱ በሰብዓዊነት ላይ ተፈፀሙ ባላቸው ወንጀሎች ምክንያት በአራት የኬንያ ባለሥልጣናት ላይ በ ዘ ሄግ የተመሠረተው ክስ በኬንያ ፍርድ ቤቶች እንዲታይ ለጉባዔው የቀረበውን ረቂቅ ሀሳብ ባፀደቀበት ጊዜ የወቅቱ የአፍሪቃ ህብረት ፕሬዚደንት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ባሰሙት ንግግር ወቅት ነበር።
« ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ የጀመረው ሂደት ስህተት አለበት። የፍርድ ቤቱ ዓላማ ወንጀል እና መጥፎ አገዛዝ ካለቅጣት እንደማይታለፉ ማሳየት ነበር። ነገር ግን ሂደቱ አሁን በዘረኝነት ወደ ማደኑ አሰራር አዘንብሎዋል። »
« ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ የጀመረው ሂደት ስህተት አለበት። የፍርድ ቤቱ ዓላማ ወንጀል እና መጥፎ አገዛዝ ካለቅጣት እንደማይታለፉ ማሳየት ነበር። ነገር ግን ሂደቱ አሁን በዘረኝነት ወደ ማደኑ አሰራር አዘንብሎዋል። »
በናይሮቢ የሚገኙት የሕግ ባለሙያ እና የፖለቲካ ተንታኝ ኦጂና ኦሽዋንግ ይህንኑ የህብረቱን ክስ የሚደገፍ ማስረጃ እንደሌለ እና ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አፍሪቃዉያንን ሲከስ አፍሪቃዉያኑ ራሳቸዉ ተባባሪዎች ነበሩ ሲሉ ነው ለዶይቸ ቬለ የገለጹት።
« ፍርድ ቤቱ በአሁኑ ጊዜ እየተመለከታቸው ካሉት ስምንት አፍሪቃ ጉዳዮች መካከል አምሥቱ በራሳቸው አፍሪቃውያኑ መንግሥታት ወደ ፍርድ ቤቱ የተመሩ ናቸው። የሊቢያ፣ ኮት ዲ ቯር እና የሱዳን ጉዳዮች ብቻ ናቸው በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጥያቄ ወደ ፍርድ ቤቱ የተመሩት። በዚያን ጊዜ አንድም አፍሪቃዊ መሪ በዚሁ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጥያቄ አንፃር ድምፁን አላሰማም። ሁለተኛ፣ በፍርድ ቤቱ እየታዩ ያሉት ወንጀሎች ጭፍጨፋን፣ ክብረ ንፅሕና መድፈርን እና አፍሪቃውያንን ስብዕና የነፈገበትን ወንጀል ይመለከታል። አንድ አፍሪቃዊ የሀገር መሪ ይህንኑ ሥልጣን እንደ ዕድሜ ልክ ሥልጣን ማየትም ሆነ፣ የሕዝብን ስብዕና ለመግፈፊያ ወይም ክብረ ንፅሕና ለመድፈሪያ ወይም ጭፍጨፋ ለማካሄጃ ሊጠቀምበት እንደማይችል ሊያውቅ ይገባል። ይህን በማድረጉ ቢከሰስ ግን ሂደቱ ዘረኝነት ነው ይላል። ይህ ፍፁም ስህተት ነው።»
አይ ሲ ሲ የኬንያን ጉዳይ መከታተል የጀመረው ኬንያ ለ 2007 ቱ ድህረ ምርጫ ሁከት ተጠያቂ ተብለው የተጠረጠሩትን ጉዳይ የሚመለከት ልዩ ፍርድ ቤት ለማቋቋም ፈቃደኛ ባለመሆንዋ ነበር። በኬንያ ምርጫ ወጤት ሰበብ የተወ,ዛገቡትን ተቀናቃኝ ወገኖች የሸመገሉት የቀድሞው የተመድ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን በወንጀል ተጠረጥረዋል የተባሉ ኬንያውያን ፖለቲከኞችን ስም ዝርዝር ለአይ ሲ ሲ ማስረከባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ዝርዝሩን ያገኙት ከኬንያ መንግሥት አካላት እንደነበር የሕግ ባለሙያው እና የፖለቲካ ተንታኙ ኦጂና ኦሽዋንግ አመልክተዋል።
« ኮፊ አናን ለአይ ሲ ሲ ያስረከቡትን ዝርዝር ያዘጋጀው በዚያን ጊዜ የከፍተኛው የኬንያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኛ የመሩት ብሔራዊ ኮሚሽን ነበር። ኮሚሽኑ ከኬንያ ስለላ ድርጅት እና ፖሊስ መኮንኖች፣ እንዲሁም፣ ሌሎች ግለሰቦች ነው ማስረጃውን ያገኘው። ምርመራውን ያካሄዱት እና ዝርዝሩን ያሰረከቡት አውሮጳውያን ወይም አይ ሲ ሲ አልነበሩም። ምክር ቤቱ ልዩ ፍርድ ቤት አላቋቁምም ከማለቱ ጎንም፣ ምንም እንኳን እነዚህ ወንጀሎች በኬንያም እንደ ወንጀል ቢታዩም፣ በሀገሪቱ ያሉት ፍርድ ቤቶች እና የዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ጭምር አንዳችም ርምጃ አልወሰዱም። የዘር ማጥፋት፣ ክብረ ንፅሕና መድፈር፣ መኖሪያ ቤቶችን እና ሰዎችን ማቃጠል፣ እነዚህ ሁሉ ኬንያ ውስጥ እንደ ወንጀል ነው የሚቆጠሩት። እና ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም አያስፈልግም ነበር፤ ዓቃብያነ ሕግ ራሳቸው ጉዳዩን ሊከታተሉት ይችሉ ነበር። »
ኦሽዋንግ እንደሚሉት፣ አይ ሲ ሲ የምስክሮችን ደህንነት ለመከላከል እና የሁከቱ ሰላባዎች ፍትሕ ይኖራል ብለው እምነት እንዲያድርባቸው ሲል የተጠርጣሪዎቹ ኬንያውያን ስም ዝርዝር እንደቀረበለት ተጠርጣሪዎቹን በዚያን ወቅት ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር ማዋል ነበረበት። ይህን አለማድረጉን ስህተት ነው ያሉት ኦሽዋንግ አሁን ተጠርጣሪዎቹ ወይም የተከሰሱት ሰዎች በአነፃራቸው የምስክርነት ቃል የሚሰጡት ሰዎች ተከላካዮች ሆነው መቅረባቸው የምስክሮች መካላከያ አውታርን ትርጉም አልባ ከማድረጉ ጎን የኬንያ ድህረ ምርጫ ሰለባዎች በፍትሑ ላይ እምነታቸው በየቀኑ እየቀነሰ እንዲሄድ ምክንያት ሆኖዋል ሲሉ ኦሽዋንግ ወቅሰዋል።
አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን
Source DW
No comments:
Post a Comment