Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, February 3, 2015

ከአረብ ሃገር ተመላሾች መሬታችን በመነጠቃቸው ሰርተው ለመኖር አለመቻላቸውን ተናገሩ ፡፡

ከአረብ ሃገር ተመላሾች መሬታችን በመነጠቃቸው ሰርተው ለመኖር አለመቻላቸውን ተናገሩ ፡፡

ጥር ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ፣ ሰሜን ወሎና ባቲ አካባቢዎች የሚኖሩ ከስደት ተመላሽ ወጣቶች ባሰሙት ቅሬታ፤ ከአረብ ሃገር ወደ ሃገራችሁ ግቡ የሚለውን የገዢው መንግስት ቅስቀሳ በመስማት ስራቸውን ጥለው ወደ ሃገር ቤት ቢመጡም፣  ከስደት በፊት ጥረው ግረው ያለሙትን ቦታ በኢንቨስትመንት ስም ለባለሃብቶች ተሰጥቶ በማግኘታችው አብዛኛው ወጣቶች ተመልሰው ሲሄዱ ሌሎች ደግሞ ለችግር ተዳርገዋል።
1 መቶ 80 ቅሬታ አቅራቢ ወጣቶች  በአካባቢው አመራሮች በወረዳ ደረጃ ጸድቆ የተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እያለ ያለሙት መሬት ለሌላ ባለሃብት ከእጃቸው ተነጥቆ መሰጠቱን ገልጸዋል።   ባለስልጣናቱ «መሬቱን የሰጠናችሁ እኛ ነን መንጠቅ እንችላለን፡፡» እንዳሉዋቸው የሚገልጹት ከስተደት ተመላሾች፣   ከመንግስት ጋር ጦርነት የምናነሳበት ጉልበት ስለሌለን እንደገና ስደትን አማራጭ አድርገናል ይላሉ፡፡
የ5 ልጆች አባት የሆነው ከስደት ተመላሽ አርሶ አደር ባለው ጥንድ መሬት ቤተሰቡን ለማስተዳደር እንደማይችል በመረዳቱ ሀገሩን ጥሎ ለመሰደድ እንደተገደደ ይናገራል፡፡ «እንኳን እኔ ልጆቸንም ወደ ስደት በመውሰድ ለማሰማራት አስቤያለሁ፡፡»  በማለት በደረሰበት ምሬት ቤተሰቡን ይዞ ለመሰደድ እንደተገደደ ተናግሯል፡፡
መሬቱን በማልማት ውሃ አውጥቶ በውሃ መሳቢያ ሞተር በመጠቀም ጥሩ ኑሮ በመኖር ላይ እያለ ፤ወደ አካባቢው ለኢንቨስትመንት ተጋብዘው ለመጡ ባለሃብቶች   የቤተሰቡን ጉሮሮ ይሞላበት የነበረውን መሬት አሳልፎ  እንዲሰጥ መገደዱን የሚናገረው አርሶ አደር፤ ሲጠቀምበት የነበረውን ቦታ አለስልሶ እና አስተካክሎ ለምርት ስራ ለማዋል ከሁለት አመት በላይ ቢፈጅበትም ያለምንም የማካካሻ ክፍያ ሁሉንም ከስደት ተመላሽ አርሶ አደር ልቀቁ መባላቸው እንዳሳዘነው ተናግሯል፡፡ይህ በመሆኑም እንደ ሁለተኛ ዜጋ ከሚመለከታቸው መንግስት ጋር ከመኖር ይልቅ ስደትን የመረጡት ወጣቶች በርካታ መሆናቸውን በምሬት ተናግሯል፡፡
መሬቱን የተረከቡት ባለሃብቶች አዲስ ቴክኖሎጂ እና ምርጥ ዘር እንደሚያቀርቡ ተነግሮ ስራ ቢጀምሩም፤ የተጠበቀውን ያላቀረቡ ሲሆን  ቋሚ ተክል ባለመትከላቸው ለአካባቢው ማህበረሰብ ያቀርቡታል የተባለው የፍራፍሬ አቅርቦት በወሬ ብቻ መቅረቱን አርሶአደሮቹ ይናገራሉ፡፡አሁን ወጣቱ ተስፋ በመቁረጥ ስደትን አማራጭ አድርጎ እንደያዘ ተናግረዋል፡፡  ሃገርህ ግባ ሲባል የተሻለ ነገር ለማግኘት ሁሉም ተሰባስቦ ቢመጣም እዚህ ግን ምንም አማራጭ አላገኘም፡፡መሬቱ በዚህም በዚያም ተወርሶ ሲያገኘው ከስደት የተመለሰው፣ ሌሎችን በመጨመር ተመልሶ እንደሄደ ቅሬታ አቅራቢዎች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
በሃገራችን ሰርተን እንለወጣለን የሚል  ሃሳብ እንደሌላቸው የሚናገሩት ወጣቶች ሃገራቸው በጥቂት ባለሃብች በመወረሯ እዚህ መስራት እንደማንችል አይተናል፡፡መልካም አስተዳደር በሌለባት ሀገር መስራት ካልተቻለ ስደትን እንደመፍትሄ እንቆጥራለን በማለት  ለዘጋቢያችን በዝርዘር ተናግረዋል፡፡
ወጣት ከስደት ተመላሾችን በመደራጀት ቦታ ተሰጥቷቸው የተሻለ በማልማት ራሳቸውን እየለወጡ ነው´ በሚል በየጊዜው በገዥው መንግስት ሚዲያዎችና ጋዜጦች የሚዎጡ ዘገባዎች ስህተት ናቸው  በማለት የሚቃወሙት ከስደት ተመላሾች ፤ ቦታ በማዘጋጀት አደራጅተው የሚያከፋፍሉት ለገዢው ፓርቲ አባላት፣ ለአመራር ቤተሰቦች፣ለጓደኞቻቸውና ለመሳሰሉት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስደተኞችን ለመመለስ ከአለም ወጣቶች ማህበር የተገኘውን የእርዳታ ድጋፍ የመንግስት አመራሮች ተሻርከው ቀምተውናል የሚሉት ተመላሾች፣ ” ለመቋቋሚያ የተላከልን ገንዘብ በትክክል አልደረሰንም ወደ ቤተሰብ ስንሄድ ይሰጠን ከነበረው አንድ ሺህ ብር እንኳን  አንድ መቶ ብር በመቀነስ ዘጠኝ መቶ ብር ብቻ ነው የሰጡን፡፡ ከሁሉም ስደተኛ ኪስ የወሰዱትን ገንዘብ ለምን አገልግሎት እንደሆ ባልታወቀ ሁኔታ ለግል ጥቅማቸው አውለውታል” በማለት ይናገራሉ፡፡
በርካታ ወጣቶች አሁንም ከወሎ፣ከኦሮምያ ዞን ፣ከሰቆጣ እና ከትግራይ ጠረፋማ ወረዳዎች በየቀኑ ወደ አረብ ሃገራት በህገ ወጥ መልኩ እንደሚሰደዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials