Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, July 9, 2015

ጥቂት ስለአርበኞች ግንቦት 7 ተዋጊ አርበኛ ሃና – ከጋዜጠኛ መሳይ መኮንን


ጥቂት ስለአርበኞች ግንቦት 7 ተዋጊ አርበኛ ሃና – ከጋዜጠኛ መሳይ መኮንን



የርዕዮትን: የማህሌትንና የኤዶምን ከህወሀት ማጎሪያ እስር ቤት ነጻ መሆን ውስጤ የፈጠረውን ደስታ እያጣጣምኩ እያለ ድንገት በትዝታ አምስት ወራት ወደ ሁዋላ ሄድኩኝ- -ከኤርትራ በረሃ:: ይህቺን ኢትዮጵያን ከህወሀት እስር ቤት ነጻ ለማውጣት ብረት ያነሳችውን እህታችንን ላስተዋውቃችሁ::

አርበኛ ሀና ትባላለች:: የ23 ዓመት ወጣት ናት:: የአርበኞች ግንቦት 7 ተዋጊ ወታደር ስትሆን በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሳትፋለች:: በኤርትራ በረሃ ስማቸው ከጀግንነት ጋር ከሚነሳላቸው አርበኞች መሃል ሀና ግንባር ቀደም ናት:: ስሟ በአርበኞች መንደር ገኖ ይነሳል::
………አንድ ጊዜ ላይ እንዲህ ሆነ::

ሀና የምትገኝበት ወታደራዊ ክፍል ግዳጅ ይሰጠዋል:: እስከ 30 የሚጠጋ አርበኛ የሚገኝበት ይህ ቡድን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ በመግባት በአንድ የህወሀት ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ፈጽሞ የመመለስ ግዳጅ ተሰጥቶት ይሰማራል:: ሀና መትረየሷን ታጥቃለች:: ጠዋት ከመነሻቸው ወደ ኢላማ ቦታው ገሰገሱ:: እንደታቀደው ድንገተኛ ጥቃቱ ተሰንዝሮ የታሰበውን ጉዳት አድርሰው ወደ ካምፓቸው ሊመለሱ እያለ ድንገት በህወሀት ሰራዊት ይከበባሉ:: ምን ይደረግ? ብዙ ቁጥር ያለውንና እስከአፍንጫው የታጠቀውን የህወሀት ሰራዊት መክቶ ወደ ካምፕ መመለስ ከባድ ሆነ:: የዚህን ጊዜ ነበር አንድ ጀግና ታሪክ የሰራችው:: ….ሀና::

መትረየሷን መተረች:: ገዢ መሬት ያዘች:: ቦታዋን አስተካከለች:: ….እሷ መስዋዕት ሆና የትግል ጓዶቿን ልታስመልጥ ወሰነች:: ምሽት እየመጣ ነው:: ጓዶቿ ተስናበቷት:: ዳግም በህይወት እንደማያገኟት ታወቃቸው:: …እሷ መትረየሷን ወደ ህወሀት ሰራዊት ለቀቀችው:: ለጓዶቿ ሽፋን በሚሰጥ ስልት አስካካችው:: …ፍልሚያው በአንዲት ሀና እና በህወሀት ሰራዊት መሃል ሆነ:: የሀና መትረየስ ያስካካል:: ጓዶች በዚያ ሽፋን ወደ ጦር ካምፓቸው እየተመለሱ ነው:: የሀና የመትረየስ ድምጽ እየራቃቸው ነው:: እነሱ ይተርፉ ዘንድ አንድ አርበኛ መስዋዕት መሆን ግድ አለ:: በተሰጣቸው ግዳጅ ውጤታማነት እየተደሰቱ የሃናን መስዋዕትነት እያወደሱ ከካምፓቸው ምሽት ላይ ደረሱ:: በአርበኞች መንደር ህይወት እንዲህ ናት:: ታጋይ ይሰዋል:: ትግል ይቀጥላል::

…እኩለ ሌሊት ከመድረሱ በፊት ነው:: ጭው ካለው የኤርትራ በረሃ አንድ ሰው ወደ አርበኞቹ መንደር ከኢትዮጵያ ድንበር አቅጣጫ ይገሰግሳል:: በርቀት የተመለከቱት የሌሊት የካምፕ ተረኛ ዋርዲያዎች(ጠባቂዎች) መሳሪያቸውን አስተካክለው ጣት ከቃታ አገናኝተው ወደ ካምፑ እየገሰገሰ ያለውን ሰው ይጠብቃሉ:: ውድቅት ሌሊት ስለነበር ማንነት መለየት አልተቻለም:: የሚገሰግሰው ሰው እየቀረበ ሲመጣ ዋርዲያዎቹም ኢላማቸውን አስተካክለው እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጁ:: ….ሰውዬው ቀረበ:: ሴት ናት::ሃና:: ዋርዲያዎቹ አላመኑም:: የዕለቱን የይለፍ ቃል ጠየቋት:: መለሰችላቸው:: ደክሟታል:: ተአምር የሚያሰኘው ከዚይ የህወሀት ሰራዊት ከበባ ማምለጧ አይደለም:: ሁለት የጦር መሳሪያዎችንም ማርካ ተሸክማለች:: ከሷ መትረየስ ጋር ሶስት:: ዋርዲያዎቹ በሚያዩት ነገር ተደንቀዋል:: በአርበኞች መንደር ስለ ሃና እርም ወጥቷል:: ጉድ ተባለ::

….ሃናን በአካል ሳገኛት በጣም ቁጥብ ነበረች:: ብዙ አትናገርም:: ታሪኳን እንድታጫውተኝ ያደረኩት ጥረት አልተሳካም:: ሲበዛ ዝምተኛ ናት:: ጀግና አይናገርም::
…ሃና ከሰሞኑ ውጊያዎች በአንዱ እንደተሰለፈች እገምታለሁ:: ልብን በኩራት በሚያሞቀው ጀግንነቷ ሁሌም አስታውሳታለሁ:: የጣይቱ ልጅ!!!!!

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44915#sthash.NPj8jfDG.dpuf

No comments:

Post a Comment

wanted officials