Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, July 17, 2015

በኬንያ ወህኒ ቤት ኢትዮጵያዊው ሞተ





በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከደላሎች ጋር እንደሚሰራ ብዙዎች በምሬት ይገልጻሉ
‹‹ወተትና ማር ታፈልቃለች››ወደሚሏት ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር በተለይ ከደቡብ ኢትዮጵያ በመነሳት በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ በመግባት ረዥሙን ጉዞ ለመያያዝ ራሳቸውን በሚያዘጋጁበት ቅጽበት እየተያዙ ወህኒ የሚወርዱ ወጣቶች ቁጥር በኬንያ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ በኬንያ ለመቆየት፣ስራ ለመስራት አልያም የሽብር ተግባር ለመፈጸም የመጡ እንዳልሆኑ ቢታወቁም በአገሪቱ ፖሊሶች እየተያዙ ‹‹ወደ ኬንያ በህገ ወጥ መንገድ ገብታችኋል በሚል ክስ››ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ ይደረጋሉ፡፡በአብዛኛው ገንዘቡን የሚከፍሉበት አቅም የሌላቸው በመሆኑ የገንዘብ ቅጣቱ በእስራት ይለወጥባቸዋል፡፡
በወህኒ ቤቶቹ የሚፈጸምባቸው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እነርሱነታቸውን እንዲጠሉ የሚያደርግ በመሆኑም ዕድል አግኝተው እንኳን ቢወጡ ጤነኛ ሆነው ለመቀጠል ይቸገራሉ፡፡እናም በዛ ያሉ ወጣት የአእምሮ በሽተኛና ጎዳና ተዳዳሪ ኢትዮጵያዊያንን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡
45 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተወላጆች አገር ውስጥና ኬንያ በሚገኙ ሰው አዘዋዋሪ ደላለሎች ሰንሰለት አማካኝነት በአጭር ቀናቶች ውስጥ ጆሃንሰበርግ እንደሚያደርሷቸው ተስፋ ተገብቶላቸው እያንዳንዳቸው ለደላሎቹ 90.000 የኢትዮጵያ ብር ከፍለው ናይሮቢ እንደደረሱ በፖሊሶች እጅ ይወድቃሉ፡፡
ወጣቶቹ በፖሊስ መያዛቸውን የተረዱት ደላሎችም አድራሻቸውን በማጥፋት ይሰወራሉ፡፡ከኬንያ ፖሊሶች ጋር በቋንቋ መግባባት ባለመቻላቸውም ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የስምንት ወራት እስራት ተብኖባቸዋል፡፡እስራታቸውን እንደፈጸሙ ደግሞ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ፡፡
ለቤተሰቦቹ መሪር ሐዘን እንዳይን ስሙን የማልጠቅሰው ወጣት በወህኒ ቤቱ የቅጣት ግዜውን በማሳለፍ ላይ እንዳለ በጽኑ በመታመሙ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡በወገናቸው ሞት መሪር ሐዘን የደረሰባቸውና የእነርሱም ዕጣ ፈንታ በእስር ቤቱ እስከቆዩ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን በመረዳታቸው ቀሪዎቹ እስኞች የርሃብ አድማ በመምታት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል፡፡
የወጣቶቹ የርሃብ አድማ ዋነኛ አላማ ‹‹ወገናችን ይድረስልን፣የታለብንን እስር ወደ አገር ቤት በመመለስም ቢሆን እንድንጨርሰው ይሁን››የሚል ነው፡፡በቅርቡ ሰዎችን በማዘዋወር ስራ ተሰማርታ ነበረች የተባለችን ሴት ከነረዳቷ ወደ አገር እንድትመለስ መደረጓን የኢትዮጵያ መንግስት ያሳወቀ ቢሆንም በኬንያ ተቀምጠው አገር ውስጥ በሚገኙ ደላሎች አማካኝነት ዝውውሩን የሚፈጽሙ ብዛት ያላቸው ህገ ወጦች በናይሮቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመስራት ኢምባሲው በሚጠራቸው ስብሰባዎች ፣በሚያዘጋጃቸው የእርዳታ ጥሪዎች ዳጎስ ያለ ብር በመስጠትና ቦንድ በመግዛት አቻ እንዳልተገኘላቸው የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ኢሲኦሎ ካውንቲ 89 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለመጠየቅ የርሃብ አድማ ቢመቱም የኬንያ ፖሊስ የአንድ አመት የእስራት ግዚያቸውን ሳያጠናቅቁ እንደማይለቃቸው አስጠንቅቋቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials