Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, July 29, 2015

ኦባማ የአፍሪካን ገዢዎች እያዋዛ ደቆሳቸው ! ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም



ኦባማ የአፍሪካን ገዢዎች እያዋዛ ደቆሳቸው !
ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም
ሐምሌ/2007
ኦባማ በአፍሪካ ኅብረት ያደረገው ንግግር ብዙ ጥያቄዎችን መልሷል፤ የኦባማ ጉብኝት ያስከተለው ጫጫታ ሁሉ መልስ አገኘ፤ የሰው ልጆች በመሀከላቸው ምንም ዓይነት የአድልዎ ልዩነት ሳይደረግባቸው በሰውነታቸው ብቻ በተፈጥሮ ያገኙትን ክብራቸውንና መገሣቸውን አስከብረው መኖር እንዳለባቸው በአጽንኦት ተናገረ፤ ዛሬ የአሜሪካኑ ፕሬዚደንት ያደረገው ንግግር ከፕሬዚደንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ እስከፖሊሶች፣ መርማሪዎችና አዛዦቻቸው፣ እስከጦር ኃይሉና አዛዦቻቸው፣ አስከዓቃብያነ ሕግና ዳኞች፣ እስከወህኒ ቤት ጠባቂዎችና አዛዦች በየሥልጣን ተዋረዱ ላይ ሆነው የኢትዮጵያውያንን የሰውነትና የዜግነት እኩልነት አፈራርሰው በጎሣ መሠረት ላይ ሊበታትኑት የሚሞክሩትን በኃይለኛ ቃላት ከመሬት በታች ከቶአቸዋል፤ ማሰብና ማስተዋል የጎደለው፣ ከአፍንጫ የራቀ አመለካከት የሌለበት፣ አገርን የሚያጠፋ፣ ከሰውነት ጎዳና የሚያወጣ የድንቁርና መንገድ መሆኑን ገልጧል፡፡
ኦባማ የኢትዮጵያን ገዢዎች ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ገዢዎች በሙሉ አላግጦባቸዋል፤ በሥልጣን ላይ ሙጭጭ በማለታቸው፣ በሙስናቸው፣ በአፈናቸው፣ ልክ ልካቸውን ሲነግራቸው እፍረታቸውን ውጠው ያጨበጭቡለት ነበር፤ የአፍሪካ ገዢዎች ሕጉን እንደፈለጉ የሚጠመዝዙትን መሳቂያ አድርጓቸዋል፤ በአዳራሹ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች የኦባማን ንግግር በማድነቅ በጭብጨባና በጩኸት ይገልጹ ነበር፤ ለወግ ብቻ የሚደረግ ምርጫ የዴሞክራሲ መግለጫ አይሆንም አለ፤ ዴሞክራሲ ነጻና ትክክለኛ ምርጫን፣ ሀሳብን በነጻነት መግለጽን፣ በነጻነት መደራጀትንና መሰብሰብን ያካትታል፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድረጅቶችን ማገድና መገደብ ለዴሞክራሲ እንቅፋትና ለእድገት ጸር ነው፡፡
አገዛዞች ነጻነትን በማፈናቸው ሁለት ዋና ዋና የማኅበረሰብ ዓምዶችን ማለትም ደኅንነትንና ሰላምን ያጣሉ፤ ሰላምና ደኅንነት ሰጠፋ ማኅበረሰቡ የጉልበተኞች መጫወቻ ሆኖ ይደናበራል፤ ይህ አደገኛ ጉዞ ነው፤ መልካም አስተዳደር ከሰፈነ ሽብርተኛነት የሚበቅልበት መሬት አያገኝም፤ ሰዎች ሁሉ በሰውነታቸውና በዜግነታቸው እኩልነት ሰብአዊ መብቶቻቸው ሁሉ ከተከበሩላቸው ወደኃይል እርምጃ የሚወስደውን መንገድ የሚከተሉበት ምክንያት የለም፤ እድገት የነጻነትና የዴሞክራሲ ውጤት ነው፤ ነጻነት የሰው ልጆች ሁሉ ዓላማ ነው፡፡
ማንም ቢሆን ከሕግ በታችና ለሕግ ተገዢ መሆን አለበት፤ ሕገ መንግሥቱን ለእሱ እንደሚበጀው እያደረገ በመተርጎም በሥልጣን ላይ መቆየት አይቻልም፤ ሊፈቀድም አይገባም፤ በአጠቃላይ አባማ በአፍሪካ ኅብረት በአደረገው ንግግር የአፍሪካ ገዢዎችን ሁሉ ቁስላቸውን በአልኮል ሲያጥብላቸው እየለበለባቸው ተመልክተውታል፤ አዳምጠውታል፤ አንዳንዶቹም እያፈሩ አጨብጭበውለታል፡፡
የዚህ ንግግር የመጨረሻው ግብ ያልገባቸው የአፍሪካ ገዢዎች ክፉ ነገር ይጠብቃቸዋል፤ በሽብርተኛነት መነገድ መልኩን ሊለውጥ ነው፤ ካላወቁበት የማያውቁት ሽብር ቤታቸውን ይጠርግላቸዋል!

No comments:

Post a Comment

wanted officials