በሽብርተኝነት ተከሶ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ ፀኃፊ አቶ በፍቃዱ አበበ በትናንት ሀምሌ 15/2007 ዓ.ም በልደታ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት የመከላከያ ምስክሮቹን አሰምቷል፡፡ ከአምስቱ የመከላከያ ምስክሮች መካከል አራቱ የአርባ ምንጭ ፖሊስና ደህንነቶች በፍቃዱ አበበ ላይ በሀሰት ከመሰከሩ የተሻለ ጥቅም እንደሚሰጣቸው ቃል ገብተውላቸው እንደነበር ገልጸው መስክረዋል፡፡
ከአመት በፊት አንድነት ፓርቲ በአርባምንጭ ያደርገው በነበረው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተሳትፈሃል ተብሎ ከድንጋይ ማንጠፍ ማህበር የተሰናበተ አንድ ወጣት ‹‹በፍቃዱ አበበ ለግንቦት ሰባት እየመለመለ ይልካል፡፡ እኔንም መልምሎኛል ብለህ ከመሰከርክ ወደ ስራህ እንመልስሃለን›› እንዳሉትና እሱም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በሀሰት ሳይመሰክር መቅረቱን ገልጾአል፡፡ በተጨማሪም ሌላ ወጣት በፍቃዱ ላይ ምስክር ሆኖ ከቀረበ የሚፈልገውን እንዲሚያደርጉለት ቃል ተገብቶለት እንደነበር ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ይህ ወጣት የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ ልደታ ፍርድ ቤት ድረስ መጥቶ የነበር ቢሆንም በፍቃዱን እንደማያውቀውና በሀሰት መስክር መባሉን እንደሚገልጽ ለአቃቤ ህጉ በመናገሩ ሳይመሰክር እንዲመለስ መደረጉን አስረድቷል፡፡
አቶ በፍቃዱ ተጨማሪ ምስክሮችን ለማሰማት እንዲሁም የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ በሀሰት መስክሮብኛል ያለው ግለሰብ ለአርባ ምንጭ ፖሊስና ለልደታ ፍርድ ቤት የሰጠው ቃል እንዲቀርብለት በመጠየቁ ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ለነሀሴ 21/2007 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡ አቶ በፍቃዱ አበበ በመከላከያ ምስክርነት የጠራቸው ግለሰቦች እንደታሰሩበትና ለምስክርነት የመጡትም ሲጉላሉበት እንደሰነበቱ መግለጹ ይታወቃል፡፡
No comments:
Post a Comment