Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, July 23, 2015

ህወሓት በፈጠራቸው ድርጅቶች ውስጥ ተኩኖ ህወሓትን ማዳከም አርበኝነት ነው!

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ለኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶቹ አባላት የሚከተለው መልዕክት ማስተላለፍ ይሻል።
Patriotic Ginbot 7 Movement for Unity and Democracyህወሓት ጥቂት አባላትና ደጋፊዎች ይዞ ታላቂቷን ኢትዮጵያ ለማንበርከክ እና ሀብቷን ለመመዝበር እናንተን መጠቀሚያ ያደረጋችሁ መሆኑን የምታውቁት ነው። እናንተ አባል የሆናችሁባቸው ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ የተባሉ ድርጅቶች የራሳቸው ድርጅታዊ ነፃነት የሌላቸው የህወሓት አገልጋዮች መሆናቸው እነሱ ራሳቸው የሚነግሯችሁ ከመሆኑም በላይ እናንተም በዕለት ተዕለት ተግባራችሁ የምትታዘቡት ሀቅ ነው። እነዚህ ድርጅቶች ህወሓትን ለማስደሰት ሲሉ የራሳቸውን ሕዝብ የሚያስሩ፣ የሚገድሉ፣ የሚዘርፉ፣ ከቀየው የሚያፈናቅሉ፣ መኖሪያ ቤቱን የሚያስፈርሱ መሆናቸው እናንተም እየተሳተፋችሁበት ያለ ሥራ ነውና የምታውቁት ነው። “አጋር ድርጅቶች” የሚል ስያሜ የተሰጣችው አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊ እና ኢሶዴፓ “አጋር” ሳይሆን የህወሓት ጀሌዎች መሆናቸው እናንተም እኛም የምናውቀው ነው። እናንተ አባል የሆናችሁባቸው ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ፣ አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ የተባሉ አድርባይ ድርጅቶች ባይኖሩ ኖሮ ህወሓት ለ24 ዓመታት ኢትዮጵያዊያን እየገደለና እያሰረ፤ እየዘረፈ በውሸት ምርጫና በውሸት ዲሞክራሲ ስም ፍጹም የሆነ ዘረኛ፣ ከፋፋይ፣ አምባገነናዊ ሥርዓት በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያሰፍን ባልቻለም ነበር። ህወሓት በኢትዮጵያዊያን አናት ላይ እንዲፈነጭ እናንተ አባል የሆናችሁባቸው ድርጅቶች አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው።
ይህ ብቻም አይደለም። እናንተ አባል ሆናችሁ ድጋፍ ባታደርጉላቸው ኖሮ እነዚህ አድርባይ ድርጅቶች ባልኖሩም ነው። ስለሆነም ህወሓት በኢትዮጵያዊያን አናት ላይ እንዲፈነጭ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ ልጆቻችሁ እና የልጅ ልጆቻችሁ በሎሌነት እንዲያድጉ፤ ጥቂቶች በልጽገው ብዙሃኑ እንዲደኸዩ እናንተ በግል አስተዋጽዖ አድርጋችኋል።
ብዙዎቻችሁ እነዚህ አድርባይ ድርጅቶችን የተቀላቀላችሁት በኑሮ ግዴታ፣ በትዕዛዝ፣ በአማራጭ እጦት ሰበብ፣ የሰብዓዊ ተፈጥሮችን አካል በሆነው የመንፈስ ደካማነት ምክንያት እንደሆነ፤ ድርጅታችሁ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰው በደል እያያችሁ ህሊናችሁ እንደሚቆስል እናውቃለን። አንዳንዶቻችሁ ውስጣችሁ እያነባ እጆቻችሁ ኢፍትሀዊ ተግባር እንደሚፈጽሙ እናያለን። ኢህአዴግ እንደማፊያ ድርጅት መግባት እንጂ መውጣት የማይቻልበት ሆኖ እንዳገኛችሁት እናውቃለን። “ይህንን ድርጅት ከለቀቅኩ የሚጠብቀኝ እስር፣ አልያም ሥራ ማጣት ነው። ያኔ ምን ይውጠኛል? ትዳሬ፣ ልጆቼ፣ ወላጆቼ እንዴት ይሆናሉ?” የሚል ስጋት እንዳለባችሁ እንገነዘባለን። ህወሓትን በመርዳት ያቆማችሁት ሥርዓት እንኩዋንስ ለሌላው ለእናንተም ከፍርሃት ነፃ ሊያደርጋችሁ አለመቻሉን እናውቃለን። ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7፣ እናንተ ያላችሁበት አጣብቂኝ ቀላል እንዳልሆነ ይገነዘባል። በዚህም ምክንያት ይህንን ጥሪ ለእናንተ ያቀርባል።
ሀገራዊና ሕዝባዊ ስሜት ያላችሁ፤ ለራሳችሁና ለቤተሰቦቻችሁ ክብር የምትጨነቁ፣ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ሎሌነትን ሳይሆን ክብርን ማውረስ የምትፈልጉ የኢህአዴግ እና የአጋር ድርጅቶቹ አባላት ሆይ! አባል የሆናችሁባቸውን ድርጅቶች ሳትለቁ፤ ኢህአዴግም ሆነ አጋር ድርጅቶቹ ውስጥ እያላችሁ ለህሊናችሁ፣ ለልጆቻችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁና ለሀገራችሁ የምትሠሩበት መንገድ ተመቻችቶላችኋልና ተጠቀሙበት።
የአገራችን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ እንደሚያስተምረን አርበኝነት ሁለት ዓይነት ነው። አንዱ በገሀድ፣ በግላጭ፣ በውጊያ ሜዳ የሚታይ አርበኝነት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ፣ በጠላት ጉያ ውስጥ ተኩኖ፣ ጠላትን መስሎ የሚደረግ አርበኝነት ነው። ሁለተኛው ዓይነት አርበኝነት በተለምዶ “የውስጥ አርበኝነት” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በተግባርና በውጤት ከአደባባይ አርበኝነት በምንም የማይተናነስ የጀግንነት ሥራ ነው። የውስጥ አርበኛ፣ አርበኛ ነው። የውስጥ አርበኛ ገድሉ በታሪክ የሚወደስ፣ በአርዓያነቱ የሚጠቀስ የሀገሩ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።
የኢህአዴግ አባላት ሆይ የውስጥ አርበኛ የመሆን እድላችሁን አታስመልጡ!
ዛሬ በምንገኝበት ሁኔታ የውስጥ አርበኝነት ማለት ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ፣ አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊ ወይም ኢሶዴፓ ውስጥ ሆኖ ህወሓትን ማዳከም ማለት ነው። በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ቀንደኛ የህወሓት ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንዳሉ ይታወቃል። የውስጥ አርበኞች ተግባር እነዚህ ከህወሓት በላይ ህወሓት ሆነው እናንተ በወገናችሁ ላይ በደል እንትድፈጽሙ የሚያደርጓችሁ፤ ለህወሓት ባርነት መገዛትን መታደል እንደሆነ አድርገው የሚሰብኩ ቀንደኛ ባንዳዎችን መቆጣጠር ነው። የውስጥ አርበኛ ማለት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ሆኖ ሥርዓቱ የሚያዳክሙ ተግባራትን የሚሠራ ጀግና ማለት ነው። የውስጥ አርበኛ ማለት በሕዝብ ላይ በደል የሚሠራን ሥርዓት በአሻጥር የሚያሽመደምድ ብልህ ዜጋ ማለት ነው። የውስጥ አርበኛ ማለት አለቆቹን እየሰለለ፣ ራሱ የተሳተፈበትም ቢሆን የሥርዓቱን እቅዶች ለታጋዮች አሳልፎ የሚሰጥ ባለውለታ ማለት ነው። የኢህአዴግና “የአጋር” ድርጅቶች አባላት በውስጥ አርበኝነት በመሳተፍ ለህሊናችሁ፣ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ውለታ መሥራት ትችላላችሁ።
የህወሓትን ዓላማ የማይደግፉ የህወሓት አባላት እንዳሉም እናውቃለን። ለእነሱም ህወሓት ውስጥ ሆኖ ህወሓትን ማዳከም ትልቅ የውስጥ አርበኝነት እንደሆነ ማስገንዘብ እንወዳለን። የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዳይ ከዘር በላይ መሆኑ የሚረዱ፤ እነሱ ለራሳቸው እንዲሆን የሚፈልጉት ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም የሚመኙት መሆኑን የተረዱ የህወሓት አባላት የኢፍትሃዊነት ምንጭ የሆነው ድርጅታቸውን በማዳከም ላይ የመልካም ዜግነት አክሊል መቀዳጀት ይችላሉ።
በህወሓትና ህወሓት የፈጠራቸው ድርጅቶች ውስጥ የምትገኙ ወገኖቻችን ፈልጋችሁ አግኙን፤ ደህንነታችሁ በተጠበቀ መጠን በዘረኛ ድርጅት ውስጥ ሆናችሁ ዘረኝነትን፤ በፋሽስት ድርጅት ውስጥ ሆናችሁ ፋሺዝምን መዋጋትና ከህሊናችሁ ጋር ታርቃችሁ መኖር ትችላላችሁ። ይህን ስትሰሩ እኛ ከናንተ ጋር ነን። ይህንን ስትሠሩ እኛና እናንተ ለጋራ ዓላማ የምንሰራ ጓዶች እንጂ ጠላቶች አንሆንም። ሥርዓቱን በማዳከም ረገድ የምትወስዱት ተጨባጭ እርምጃዎችን ማየት እንፈልጋለን። እኛን ማግኘት ከባድ አይደለም፤ ፈልጋችሁ አግኙን። ተባብረን አገራችን ከህወሓት ፋሽስታዊ ዘረኛ አገዛዝ ነፃ እናውጣ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment

wanted officials