Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, July 18, 2015

በካናዳ ጀርመናዊው የገደላት ሰብለ ከአንድ አመት በኋላ በመኖርያ ቤቷ ተቀብራ ተገኘች

በካናዳ ጀርመናዊው የገደላት ሰብለ ከአንድ አመት በኋላ በመኖርያ ቤቷ ተቀብራ ተገኘች
(ክንፉ አሰፋ ቶሮንቶ) ሰብለ (ሚሚ) ዲትሪች ለመጨረሻ ግዜ የታየችው እ.ኤ. አ. ጁላይ 10 2014 (ባለፈው አመት) ነበር። የሶስት ልጆች እናት የነበረች የዚህች ኢትዮጵያዊት በድንገት መሰወር ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖ ሰንብቷል። ለአመት የጠፋችው ይህች ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሴት በህይወት እንደማትኖር በርካቶች ቢጠረጥሩም፣ ማንንም ሳታማክር በድብቅ ወደ ሃገርዋ ገብታለች የሚሉ አልጠፉም። አለም አቀፍ ፖሊስ በአለም ዙርያ ፍለጋውን ተያያዘው።
በካናዳ ኪችነር ከተማ ቫንኮቨር ድራይቭ የተገኘው አጽም ግን የሁሉንም እንቆቅልሽ ፈታው። ሰብለ ህይወትዋ አልፏል። የሶስት ልጆችዋ አባት የነበረው ጀርመናዊው ስቴፋን ዲትሪች ገድሎ እዚያው መኖርያ ቤታቸው እንደቀበራት ፖሊስ ጠቁሟል። በፖሊስ እና በሰለጠኑ ውሾች ጥቆማ የተገኘው የሰብለ አስከሬን በቶሮንቶ ኮርነርስ ኮምፕለክስ ለጥናት ተልኮ የተገኘው ውጤት ሰብለ በሰው እንደተገደለች ተረጋግጧል። ዋናው ተጠርጣሪም ጀርመናዊው ባለበትዋ ነው።
በመጀመርያ ደረጃ የግድያ ወንጀል የተከሰሰው የሚሚ ባለቤት ስቴፋን ዲትሪች ፍርድ ቤት ቀርቦ በሰጠው ቃል ጉዳዩ በጀርመን ሃገር እንዲታይለት ጠይቋል። በእለቱ ኢትዮጵያውያን ፍርድ ቤቱን አጥለቅልቀውት ነበር።
ሰብለ ዲትሪች ተገድላ ከተሰወረች ከአመት በኋላ የቀብር ስርዓትዋ እለተ አርብ (ጁላይ 18) በካናዳ ቅዱስ ፓውሎስ ቤተ ክርስትያን ተፈጽሟል። በቀብሩ ላይ ወላጅ እናትዋን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።
ስቴፋን ዲትሪች የአዞ እንባ እያነባ ምስጢሩን ለአመት ከደበቀው በኋላ መኖርያ ቤቱን ለመሸጥ ማስታወቅያ አውጥቶ ነበር። ይህ ድርጊቱ የፖሊስን ጥርጣሬ እንዳጎላው ግልጽ ነው።
ሰብለ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነበረች። የቤተ ክርስትያኑ ዘማሪም ናት። ባልዋ ዲትሪችም እንደዚሁ። ከጀርመን ሃገር ወደ ካናዳ ከተዘዋወሩ በሁዋላ እጅግ በጣም የተደላደለ ኑሮ እንደነበራቸው ይነገራል። ሰብለ ከኢትዮጵያውያን የቤተ-ክርስትያን ሰዎች በተለይ ከፓስተሮች ጋር የምታደርገው የአገልግሎት ግንኙነት ግን ለስቴፋን ዲትሪች እንዳልተመቸው የሚመሰክሩ አሉ። ይህም ቢሆን ክቡር ነብስን ለማጥፋት ምክንያት ሊሆን አይችልም። …. ስቴፋን ዲትሪች ሰብለን ለምን ገደላት? ገድሎስ ለምን ቤቱ ቀበራት? ይህንን ከፍርድ ቤቱ ሂደት የምናየው ይሆናል።
የሰብለ እናት የካናዳ የመኖርያ ፈቃድ አግኝተው የመጡ ሲሆን ሶስት ልጆቹን እሳቸው እንደሚንከባከቧቸው ከካናዳ መንግስት መረጃ አግኝቻለሁ።


No comments:

Post a Comment

wanted officials