Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, July 28, 2015

ፕ/ት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችንና የሰብአዊ መብት ተማጋቾችን ማሰሯን በአደባባይ ነቀፉ

ሐምሌ ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
U.S. President Barack Obama delivers remarks at the African Union in Addis Ababa, Ethiopia July 28, 2015. REUTERS/Jonathan Ernst
አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ " በዲሞክራሲያዊ ምርጫ" የተመረጠ ነው ብለው መናገራቸውን ተከትሎ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ተቃውሟቸውን ባሰሙ ማግስት፣ ይህንን ንግግራቸውን የሚቃረን ንግግር በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተገኝተው አድርገዋል። ፕሬዚዳንቱ ስለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ በመጀመሪያው ቀን የተናገሩትን ላለመድገም ጥንቃቄ ያደረጉ ሲሆን፣ ምርጫውን በተመለከተ ያነሱት ብቸኛ ጠንካራ ጎን ያለ ብጥብጥ ተጠናቋል የሚለውን ነው። ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እንቅስቃሴ መገደቧን የምትቀጥል ከሆነ የህዝቦቿን እምቅ ሃይል መጠቀም አትችልም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ባለፈው ምርጫ ተቃዋሚዎች በነጻነት የምርጫ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ ገደብ ተጥሎባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል። ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም አገሪቱ ብዙ እንደሚቀራት ማመናቸው ጥሩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ ፣ የጉብኝታቸው አላማም በጓደኝነት ቀርቦ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። በአዳራሹ ውስጥ በተሰባሰቡ አፍሪካውያን ጭብጨባ የሚቋረጠው ንግግራቸው በአብዛኛው በአፍሪካ መሪዎች ላይ አነጣጥሯል። ከአፍሪካ በዲሞክራሲ ግንባታ የተመሰገኑት ቦትስዋና፣ ቤኒን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮንና ናይጀሪያ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው በምሳሌነት የተጠቀሱት ደግሞ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ቡሩንዲ ናቸው። በብዙ የአፍሪካ አገሮች የዜጎች ነጻነት ይገፈፋል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ "ዲሞክራሲ በየወቅቱ የሚደረግ የተለመደ ምርጫ አይደለም ብለዋል። "ጋዜጠኞችንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እስር ቤት ውስጥ አስቀምጠህ ዲሞክራሲ አስፍኛለሁ ብትል፣ ዲሞክራሲያው የስም እንጅ የተግባር አይደለም" ያሉት ኦባማ፣ "ለጸጥታ ብለን ነጻነትን የምንሰዋ ከሆነ፣ ከሁለቱም ሳንሆን እንቀራለን" በማለት በጸረሽብር ትግል ስም የሚደረገውን የመብት ገፈፋ ነቅፈዋል። "የአፍሪካ መሪዎች፣ በተለይም ገንዘብ ካገኙ በሁዋላ ስልጣን ለምን እንደማይለቁ አይገባኝም" የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መሪዎቹ የጻፉትን ህገመንግስት እንደማያከብሩ፣ የጨዋታ ህጉን ጨዋታው መሃል ላይ እንደሚቀይሩት" በማንሳት በሰፊው ተችተዋል። "የስልጣን ገደብ ሊኖር ይገባል፣ ማንም የእድሜ ልክ መሪ ሊሆን አይገባም" የሚሉት ባራክ ኦባማ፣ እኔ ከሌለሁ አገር ይፈርሳል የሚሉ መሪዎች፣ አገራቸውን አለመገንባታቸውን ሊያውቁት ይገባል ብለዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials