Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, July 22, 2015

ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጠ

ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጠ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ የወሰነው የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በምስክርነት እንዲያቀርብ ለሀምሌ 29/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሀምሌ 13/2007 ዓ.ም ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው የመከላከያ ምስክር እንዲሆኑ ፍርድ ቤቱ ወስኖ የነበር ቢሆንም ይገኙበታል ለሚባሉት ማረሚያ ቤቶች በተለይም ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚላከው ማዘዣ ዘግይቶ በመላኩ እንዳልደረሰለት ገልጾ ለዛሬ ሀምሌ 15/2007 ለምስክርነት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም አቶ አንዳርጋቸው ዛሬም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ለምን እንዳላቀረበ የተጠየቀው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ማዘዣው እንደደረሰው ገልጾ ነገር ግን ማዘዣው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተብሎ መፃፍ ሲገባው ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተብሎ በመፃፉ አቶ አንዳርጋቸውን ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጾአል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ማዘዣው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተብሎ ተፅፎ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሀምሌ 29/2007 ለመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት 10 ግለሰቦች መካከል ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝታችኋል የሚል ክስ የቀረበባቸውና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት እንዲመሰክሩላቸው የጠሩት አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ማንዴላ ጥላሁን፣ አቶ አንሙት የኔዋስና አቶ አሰፋ ደሳለኝ ናቸው፡፡


No comments:

Post a Comment

wanted officials