Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, July 5, 2015

በእስር ስትጉላላ የከረመችው የሰማያዊ ወጣት ምስጋና አቀረበች

ወይንሸት ሞላ የሰማያዊ ፓርቲ ካፈራቸው ትንታግ ታጋዮች አንዷ ናት። ለወራት ወያኔ በሃሰት ከሶ ሲያንገላታት ከርሟል፣ እነሆ ከእስር ተፈታ “ትግሉ ይቀጥላል!” ትለናለች።
Woyinshet Molla, Semayawi party member
ወይንሸት ሞላ
ምስጋናዬ ይድረሳችሁ!
ኢህአዴግ አይ ኤስ የተባለውን አራጅ ቡድን እናውግዝ ብሎ ራሱ ሰልፍ ከጠራ በኋላ ሰልፉ ሳይጀመርና እኔም መስቀል አደባባይ ሳልደርስ መስቀል አደባባይ ተገኝቼ እንደበጠበጥኩ በሀሰት ተከስሼ በታሰርኩባቸው ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች ድጋፋችሁን ለሰጣችሁኝ ወገኖች ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ባልተገኘንበት አስረው፣ በሀሰት አስመስክረውብን፣ ወህኒ ቤት ሲያወርዱን ሞራላችን የሚሰበር፣ ወደኋላ የምንል ቢመስላቸውም እኛን ግን ይበልጡን እንድንጠነክር አድርጎናል፡፡
ወትሮውንም ወደ ትግሉ ስንገባ መስዋዕትነት እንደምንከፍል አውቀን ነው፡፡
በእስር ላይ እያለሁ ብዙ አሳዛኝ ነገሮች ተከስተዋል ነገር ግን ውድ ወንድማችን ታጋይ ሳሙኤል አወቀን ቀጥቅጠው መግደላቸው ከሁሉም በላይ ያሳዘነኛል። በኢትዮጵያ ታሪክ በተመሳሳይ ሁኔታ ግድያ የተፈጸመባቸው ታጋዮችን ለማግኘት ተቸግሬያለው። ሳሙኤል አወቀ የተገደለው በህሊናውና እና በማሰቡ ብቻ ነበር። ፍፁም ሰላማዊ ለሃገሩ እና ለወገኑ የሚጨነቅና ለባህልና ሃይማኖት ትልቅ ክብር ያለው ኢትዮጵያን የሚወድ ጀግና ነበር። ስለዚህ ተኪ የሌለው ታጋይና የትግል ጓደኛዬ በመሰዋቱ በጣም ተጎድቻለው።
እኔም በእስር ላይ ያሳለፍኩት ስቃይ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነበር ግን ይህንን ልተወው ምክንያቱም ከዚህ በላይ ህይወቴንም ጭምር አሳልፌ ለመስጠት የወሰንኩበት የነፃነት ትግል ውስጥ ስለገባሁ የእስር ቤት ስቃይ የማይጠበቅ መከራ አይደለም።
የሳሙኤል አወቀ ድምጽ ከመቃብሩ ይጮሀል፤ ትግሉ ይቀጥል ትግሉን አፋፍሙት ይለናል፤ አደራ ይለምነናል። ዛሬ አንድ ወጣት በኑሮ ስኬታማ ለመሆን ብዙ አመራጮች ስለሚኖሩት ራስን ለነፃነት ትግል መስዋዕት ለማድረግ ፈታኝ የሆነበት ጊዜ ነው። ግን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት የሚያስገርፍ እና ለእስር የሚዳርግበት፣ ዜግነታችን ውርደት የሆነበት ጊዜ ላይ በመሆናችን በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ብሄራዊ እርቅን ያማከለ አንድነት የግድ አስፈላጊ ነው።
ወትሮውንም ወደ ትግሉ ስንገባ መስዋዕትነት እንደምንከፍል አውቀን ነው፡፡ ፈጣሪ ከፈቀደው ሞትም ቢሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ነፃነት የሚጠየቀውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆኔን እንድትረዱኝ እፈልጋለው።
ትግሉ ይቀጥላል!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ወይንሸት ሞላ

No comments:

Post a Comment

wanted officials