Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, July 15, 2015

የተገደሉት የመድረክ አባላት ቁጥር 5 ደረሰ

የተገደሉት የመድረክ አባላት ቁጥር 5 ደረሰ

– መድረክ ባወጣው መግለጫ ከ2007 ምርጫ በሁዋላ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተገደሉ የመድረክ አባላት ቁጥር 5 ደርሷል። የኢህአዴግ አገዛዝ በደቡብና ኦሮምያ የሚፈጽማቸው ድብደባዎችና እስራቶች መጨመራቸውንም መድረክ ገልጿል። በከፋ ዞን በግንቦ ወረዳ በአድዮ ካካ ምርጫ ክልል በጎጀብ ምርጫ ጣቢያ የመድረክ ምርጫ ታዛቢ/ወኪል ሆነው የሠሩት አቶ አሥራት ኃይሌ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድብደባ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የገለጸው መድረክ፣ ድብደባው የተፈጸመው ጎረቤቶቻቸውና ቤተሰባቸው ወደ ገበያ ሄደው በነበረበት ወቅት ነው። አቶ አስራት ቦንጋ ከተማ 01 ቀበሌ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን እያሉ ከረፋዱ በ4፡00 ሰዓት ላይ ወደ ቤታቸው በመጡና ለጊዜው ማንነታቸው በትክክል ተለይቶ ባልታወቁ ሰዎች ጭንቅላታቸውን ተመትተው ራሳቸውን ከሳቱ በኋላ በተለያዩ የሰውነት አካሎቻቸው ላይ ዘግናኝ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። አቶ አስራት ወደ ጅማ ሆስፒታል ተወስደው በመታከም ላይ እያሉ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ ም ህይወታቸው ማለፉን መድረክ ገልጿል።
medrek logo
የቃለሕይወት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ የሆኑት የአቶ አሥራት፣ ሰኔ 30 ቀን ወደ መኖሪያቸው ቦንጋ ከተማ አስከሬናቸው የተመለሰ በሆንም፣ የቤተክርስያኑ አባላት ሲቀበሩ በቆዩበት የቀብር ቦታ ላይ የቀብር ሥነሥርዓታቸው እንዳይፈጸም ከኃላፊነታቸው ውጭ በጉዳዩ ጣልቃ በገቡትና የካፋ ዞን አስተዳዳሪ የአቶ አስራት መኩሪያ ወንድምና በከተማው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ የሆኑት ቄስ መምህር ታፈሰ መኩሪያና በግንቦ ወረዳ ባለሥልጣናትና ፖሊሶች ተከልክሎ መቆየቱን ገልጿል። ይሁን እንጅ ሕዝቡ ባቀረበው አቤቱታ ረቡዕ ሃምሌ 1 ቀን 2007 ዓ ም የሟቹ አስከሬን መቀበሩን መድረክ አክሎ አስታውቋል። በካፋ ዞን የመድረክ ተወካይ የሆኑት አቶ አድማሱ አምቦና ሌሎች የዞኑ የፓርቲው አመራር አባላት ሁኔታውን ተከታትለው መረጃ እንዳያስተላልፉ በቢሮ ውስጥ እያሉ ከቢሮአቸው እንዳይወጡ ቢሮው በወታደርና በታጣቂዎች ተከቦ መቆየቱንና ስለሟቹ ማንነትና ስለግዲያው ሁኔታ የማጣራት ሥራ ለማከናወን የተቻለውም የቀብር ሥነሥርዓቱ ተፈጽሞ በመድረክ ጽ/ቤት ላይ ተደርጎ የነበረው ከበባ ከቆመ በሁዋላ መሆኑን ደርጅቱ አስታውቋል። በኦሮሚያ በሁለት አባላት፣ በትግራይ በአንድ አባል እናንዲሁም በደቡብ በአንድ አባል ላይ ተማሳሳይ ግዲያዎች መፈጸማቸውን የፖለቲካ ድርጀቱ አስታውሷል። በዚሁ ዞን በፈለገሰላም ወረዳ በጨታ ምርጫ ክልል በቦባ ቀበሌ የመድረክ የምርጫ ታዛቢ ወኪል የነበሩት አቶ ገረመው ቆዲ፣ የምርጫው ቀስቃሾች የነበሩት አቶ አሥራት ሻውአኖ፣ አቶ ገረመው ጋንአቾ እና የሾላይ ቀበሌ ታዛቢ ወኪል የነበሩት አቶ ገዛሃኝ ገንቢ እንደዚሁም በዴቻ ወረዳ ጭሪ ምርጫ ክልል የሚታ ቀበሌ ታዛቢ ወኪል የነበሩት አቶ ተክሌ ቆጭቶ ከሚያስፈሊጋቸውና ከአቅማቸው በላይ የሆነ ማዳበሪያ እንዲገዙ በቀበሌው አመራሮች ታዘው ትዕዛዙን ለመፈጸም ባለመቻላቸው ተይዘው እንዲደበደቡና እንዲታሰሩ ተደርጓል።
በቤንች ማጂ ዞን ሸዋ ቤንች ወረዳ ደግሞ አቶ መኮንን ሚቱስ፣ አቶ ማሙር ሁሌት፣ አቶ ሉቃስ አለሙ፣ አቶ ቶሳ ሳቁያብ፣ አቶ ዘለቀ ታቹያብ፣ አቶ ሐሰን ዴሪያብ፣ አቶ ተስፋዬ ወ/የስ፣ አቶ ሳሙኤል ቸሪቲ፣ አቶ መላኩ ታርሳ፣ አቶ መንግስተ ሾዳ፣ አቶ ኬሪቲ ቡጢያብ፣ አቶ አድነው ወ/የስ እና አቶ አብርሃም ሳሙኤል የሚባሉ የመድረክ አባላት መስከረም ሲሲ በሚባል ቀበሌ ውስጥ ባለው ፖሊስ ጣቢያ ከአራት ቀን እስከ ሁለት ሳምንታት ያህል ጊዜ ታስረው ከቆዩ በኃላ ተለቀዋል፡፡ ባሎቻቸው እቤት ውስጥ ያልተገኙ 12 ሚስቶች ታስረው ከቆዩ በኃላ እንደተፈቱ ፓርቲው አስታውቋል። በሸኮ ልዩ ወረዳ የፉዥቃ ቀበሌ ነዋሪና የመድረክ የምርጫ ታዛቢ የነበሩት አቶ ደርጀር ዲኩ እና አቶ ፀጋዬ ፉርጃ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ። ደቡብ ኦሞ ዞን በማሊ ወረዳም እንዲሁ አቶ ታገሰ ቡርዝጋ፣ አቶ ቦት ቦርታ እና አቶ ነጌ ደምቤ የሚባሉ የመድረክ አባላት ለመድረክ ቅስቀሳ አካሄዳችሁ ነበር በሚል ውንጀላ ታስረዋል፡፡ በዚሁ ወረዳ የኩንታር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 26 አርሶ አደሮች የመድረክ ደጋፊና ቀስቃሾች ስለነበራችሁ የእርሻ መሬታችሁን ልቀቁ በመባላቸው በቀበሌው አመራር አባላት የእርሻ መሬታቸውን ተነጥቀዋል፡፡
በጋሞጎፋ ዞን በካምባ ወረዳ ደግሞ በመድረክ በኩል በምርጫው ወቅት የምርጫ ጣቢያ ወኪል/ታዛቢዎች ሆነው የሠሩት አቶ ግዛ ግብሳ እና አቶ ገጦሬ ገባሌ የተባሉ የግብርና ኤክስተንሽን ሠራተኞች ከሚያዚያ ወር 2007 ጀምሮ ከሥራና ከደመወዛቸው የታገዱ ሲሆን፣ አቶ ሕዝቃኤል ፋንጌ እና መምህር አቴ አይሳ የተባሉት የመድረክ የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ደግሞ የየካቲት ወርና ከሚያዚያ ወር 2007 ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያለው ደመወዛቸው በሥራ ላይ እያሉ ታግዶ ይገኛል፡፡ በወረደው ውስጥ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ በርካታ የመድረክ አባላትና ደጋፊ የሆኑ አርሶ አደሮችም ከአቅማቸው በላይ እንዲገዙ የተመደበባቸውን ማዳበሪያ በወቅቱ አልገዙም በሚል ሰበብ እስከ 1000 ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እየተጣለባቸው እንዲከፍሉ ተገደዋል ሲል ፓርቲው አስታውቋል።
በኦሮሚያ በጉጂ ዞን ዋመና ወረዳ አቶ ሮባ ገልቹ፣ በቦረና ዞን መልካ ሶዳ ወረዳ አቶ ጠደቻ አሬሮ፣ በምስረቅ ሻዋ ዞን ሞጆ ወረዳ አቶ ዝናቡ ዳምጤ የሚባሉ የኦፌኮ/መድረክ አባላት በየወረዳዎቻቸው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ታስረው ይገኛሉ፡፡ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ደግሞ አቶ አሸናፊ ነጋሽ፣ አቶ ለሚ እንዳለማው፣ አቶ ባብሣ ገመዳ፣ አቶ ጉዳታ ቢራ፣ ወ/ሮ ወይንሸት፣ አቶ እሸቱ ዲማ፣ አቶ አንበሳ ያኢ፣ አቶ ታምሩ ቁምቢ፣ አቶ ቀነኒ ደሜ እና ወ/ሮ ደምበልቱ ዳሜ የተባሉ የመደረክ አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ 10 አርሶ አደሮች መኖሪያ ቤቶች በቀበሌው አመራሮች እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ግንደበረት ወረዳ የኦፌኮ መድረክ አደራጅና በምርጫው ወቅት የመድረክ ቀስቃሽና ተዘዋዋሪ ታዛቢ የነበረው ተማሪ ጉቱ ሦሬም በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት ያልተፈቀደ ስብሰባ አካሄደሃል በሚል መሠረተብቢ ክስ በጸጥታ ኃይሎች ተደብድቦ ታሥሮ እንደሚገኝ ፓርቲው የላከው መግለጫ ያመለክታል። ከምርጫ 2007 በሁዋላ የተገደሉ የተቃዋሚ ድርጅት አባላት 6 ደርሷል።
ምንጭ – ኢሳት

No comments:

Post a Comment

wanted officials