Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, December 27, 2016

ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን በሶማሌ ድንበር በኩል ከሃገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ



በሶማሌ ክልል ድንበር አቋርጠው ከሃገር ሊወጡ የነበሩ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ማክሰኞ ገለጸ።
የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) በበኩሉ የመንን ጨምሮ ከተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት መውጫን አጥተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ድርጅቱ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገር ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ እያለ ማክሰኞ ማለዳ በጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭነው በሶማሌ ክልል ድንበርን አቋርጠው ለመውጣት የሞከሩ 105 ኢትዮጵያውያን በቁጥርር ስር ሊውሉ መቻላቸውን የክልሉ ፖሊስ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
በጸጥታ ሃይሎች ከተያዙት መካከል 24ቱ ሴቶች ሲሆኑ ከሁለት የጭነት ተሽከርካሪ ሾፌሮች መካከል አንደኛው አምልጦ በፍለጋ ላይ መሆኑ ታዉቋል።
ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣትን ተከትሎ መንግስት በድንበር አካባቢ ጥብቅ የተባለ ቁጥጥር ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና አሁንም ድረስ በጎረቤት ሶማሊያ ኬንያ እና ሱዳን በኩል ወደ ተለያዩ ሃገራት የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ በተያዘው የፈረንጆች አመት ብቻ 90ሺ ኢትዮጵያውያን ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመን መሰደዳቸውን የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጸው ድርጅቱ በማላዊ እስር ቤቶች ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ይገልጻል።
እንዲሁም ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ዕልባት ባለማግኘቱ ሳቢያ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ችግሩን ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ትምህርታዊ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በሞዛምቢክ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በጉዞ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የትራፊክል አደጋ ደርሶባቸው ከ15 የሚበልጡት ህይወታቸው ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።
ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ወጣቶች በመሰደድ ላይ መሆናቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment

wanted officials