Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, December 10, 2016

ለጋራ በጎነታችን ቅድሚያ እንሥጥ (የአማራ ታጋዮችን በሚመለከት የትኩረት መስመር )



በአሁን ሰዓት በትግሉ ዙሪያ፤ በጋራና በግል ባለን አመለካከት፣ በግልጽና በሕቡዕ በሚደረጉ ክንውኖች፣ በሀገር ቤትና በውጪ ሀገር ባለው እንቅስቃሴ፣ የተለያዩ ክስተቶች የተለያየ ትርጉም እየያዙ፤ ትግሉ በአንድነት ከመጓዝ ይልቅ ወደ ኋላ የተንሸራተተ ይመስላል። በርግጥ ባድ ሕዝባዊ ትግል፤ ወደፊትና ወደኋላ፤ ባለበት መርገጥና ቀን መቁጠር ያለ ነው። ራቅ ብለው ድምሩን ሲመለከቱት ግን፤ አቅጣጫው ወደ ፊት መሆኑን ማየት ይቻላል። ስለዚህ አሁን ረጋ ባለ መንፈስ፤ ለጋራ በጎነታችን ቅድሚያ በመፕጠት፤ በጥሞና መደማመጥ ይኖርብናል።
በሁሉም ወገን ያሉትን የመስማሚያ ነጥቦች እንመልከት። የአማራውን ተጨባኝ ሁኔታ ሁላችንም በትክክል ተረድተናል። በጎንደር ኅብረት ዙሪያ የተሰባሰቡትም፣ በጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር ዙሪያ የተሰባብሰቡትም፣ በዳግማዊ መላ ዐማራ ሕዝብ ድርጅት ዙሪያ የተሰባሰቡትም፣ በቤተ ዐማራ ዙሪያ የተሰባሰቡትም፣ በከፋኝ ዙሪያ የተሰባሰቡትም፣ በግል ጥረት የሚያደርጉትም እንዲሁ፤ ሁላችንም ይህ ዋናው ጉዳያችን መሆኑን እናውቃለን። ጠላታችን የትግሬዎች ቡድንም ይሄንን እንደምናውቅ አጠናቆ ያውቃል። ሁላችንም በአንድ መሥራት እንዳለብን እናውቃለን። ጠላት ይህ እንዳይሆን ሌት ተቀን በቻለው ሁሉ እየሞከረ ነው። እኛ ደግሞ ይህን በማኮላሸት፤ ዋናውን ግባችንን ማሳካት አለብን።
በከፍተኛ ትኩረት ትግሉን ከትግሬዎች ቡድን ሰርጎ ገቦች መጠበቅ አለብን። አዎ! የትግሬዎች ቡድን ትግሉ እንዳይጠናከር፣ አንድነታችን ገሃድ እንዳይሆን፣ ተጨባጭ ድርጊቶች እንዳይከሰቱ የሕልውናው ተልዕኮ ነው። አዎ! ገንዘብ ከፍሎ ሆድ አደሮችን ማሰማራቱ ግልጽ ነው። እነዚህን ለይቶ አውጥቶ በጠላትነት በመፈረጅ ተገቢውን ማድረግ ግዴታችን ነው። እናም፤ ባንድ በኩል የታጋዩን ወገን ማጠናከር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጠላትን ኃይል ማመንመን የትግል ሀ፣ ሁ፣ ነው።
እስኪ ክዚህ አንጻር አሁን ያለንበትን የትግል ጎራ እንመልከት! አንድ አማራ ሆነን፣ አንድ ጠላት በላያችን ላይ ሰፍሮ፣ በአንድነት መታገል አስቸግሮናል። ይህ ትግል፤ ትልቁን ከትንሹ፣ ጤነኛውን ከበሽተኛው፣ ሀብታሙን ከደሃው፣ የተማረውን የመማር ዕድል ካላገኘው፣ በአንድነት አሰባስቦ፤ ለአማራው ሕልውና የጠራ ትግል ነው። የዴሞክራሲ ቅንጦት፣ የቦታ መካለል ፍላጎት፣ የጦረኝነት ስሜት፣ ወይንም የሌሎችን የበላይነት ለማግኘት የተጠነሰሰ ሴራ አይደለም። ታዲያ በየጎራችን ተቀምጠን፤ እኔ ያልኩት ካልሆነና የኔን የማይቀበል ሁሉ አማራ አይደለም፤ በሚል ጋቢ በየጎራችን ተሸፋፍነናል። አንድ ከኛ የተለየ ሃሳብን ሆነ ግለሰብ፣ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ የግለሰቦች ስብስብ፤ በመሽቀዳደም ወያኔ ወይንም የወያኔ ቅጥረኛ በማለት፤ ሌሎችን ያለ ምርጫ ወደ ጠላት ሰፈር እንዲበረግጉ እያደረግን ነው። ለምን?
የቤተ አማራ ወጣቶችን ወያኔ ያቋቋማቸው፤ በረከት ስምዖን የፈጠራቸው፤ እያልን መረጃ በማናቀርብበት ሁኔታ እንወነጅላለን። በቤተ አማራዎችም ዘንድ፤ በአንድነት ስም እንታገል የሚሉትን ሰዎች፤ የአማራ ጠላቶች በማለት ፈርጀዋል። በክፍለ ሀገር ደረጃ በማኅበር ስም የተደራጁትን ጎጠኞች፤ እኒህ በተገልባጭ ደግሞ ሌሎችን ዘረኞች በማለት፤ መለያየቱን ሙያ አድርገነዋል። ለምን?
ባደባባይ መወነጃጀሉስ ለምን ይሆን? በጽሑፍ ባደባባይ ስለሰፈረ፣ በሬዲዮ ስለተነገረ፣ በሜዲያ ስለተለጠፈ፤ ሁኔታው እኛ በፈለግነው መንገድ ይሄድልናል የሚል እምነት ኖሮን ነው? ወይስ አድራጊና ፈጣሪ፣ የትግሉ ሹፌርና አውታንቲ እኔ ብቻ ነኝ የሚል ባለቤትነት ካባ ለብሰን ነው? አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ ያለው ቴክኖሎጅው ነው። ባሁን ጊዜ ማንም የፈለገውን ለብዙዎቹ ማድረስ የሚችልበት ጊዜ ላይ ነን። ዜና ማሰራጫ አውታሩ ለሁላችንም ዝርግ ነው። እናም እያንዳንዳችን ዜና አቅራቢ፣ አስተላላፊ፣ አዳማጭና ሃሳብ ሠጪ ነን። በተለይ በውጪ ተቀምጠን፤ ሌሎች በሀገር ቤት በሕይወታቸው እየከፈሉ ያሉበትን ትግል፤ እንደ መዝናኛና ጊዜ ማሳለፊያ፤ እንዲህ ሆነ ለማለት ብቻ የአምስት ደቂቃ ትኩረት በመሥጠት፤ አዛዥ ናዛዥ ሆነናል። ቁጥር ሳይሆን የሰው ሕይወት የሚያልፍበት መሆኑን በጥሞና አልያዝነውም። እናም ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መንገድ መያዛችንን የተረዳነው ስንት እንደሆን መገመቱ አዳግቶኛል።
አሁንም ይህ የአማራው የራሱን ሕልውና ለመጠበቅ የሚያደርገው ትግል፤ ከላይ እስከታች ያለን የአማራ ልጆች ጠለቅ ያለ ምርምር ማድረግ ያስፈልገናል። በውስጣችን መደረግ ያለባቸውን ባደባባይ ማውጣቱ ማንን ለመጥቀም ነው? በቅርብ መነጋገር የሚችሉ ሁለት የአማራ ሰዎች ለምን በአደባባው ይዘላለፋሉ። እኔም ከዚህ ጥፋት ነፃ አይደለሁም። ተነግሮኛልም። ተምሬበታለሁ። አሁን የአማራን ስም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሁሉ፤ የውስጥ ግንኙነት ጀምረዋል። አንባቢ እርስዎም የዚህ አካል ይሁኑ። በድርጅቶቹ መካከል፤ የመወነጃጀል ሥራው ረግቦ፤ የመተዋወቅ ሥራ የጀመሩት ይቀጥሉ፤ ያልጀመሩት ይጀምሩ። ለዚህ ብዙ ረዳቶች አለን። ትግሉ የሁላችን በመሆኑ፤ ትግሉ የሚሳካውም፤ ሁላችንን አካቶ በኅብረት ሲሆን ነው። አንድነት መታጋል ያለብን፤ እኔ ስለፈለግሁ ሳይሆን፤ መታገያ ጉዳዩና ሊከተል የሚፈለገው ግብ አንድ ስለሆነ ነው።
ሌላው አስከፊ ክስተት ደግሞ፤ ዋናው ጠላት እያለ የጎንዮሽ ሌላ ጠላት የምናበጅበት ሂደት ነው። አዎ! የአማራው ጠላት የትግሬዎቹ ቡድን ብቻ አይደለም። ነገር ግን፤ አሁን አማራው ተፋጦ ያለው ከዚህ ወገንተኛ አምባገነን ቡድን ጋር ነው። ሌሎቹ አሁንም በአማራው ላይ የሚያደርጉትን መርሳቴ አይደለም። አሁን ግን ጠላታችንና ወገናችንን እያጠፋ ያለው ይሄው ወንጀለኛ ፀረ-አማራ ቡድን ነው። ስለዚህ ከአማራው ድርጅት ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከሌሎቹ ድርጅቶች ጋር እያደረግን ያለውንም ንትርክ ማቆም አለብን። ጉልበታችን፣ ጊዜያችንና ንብረታችን ውጤታማ በሆነው ትግል ላይ መዋል አለበት እንጂ፤ በማይረባና አድካሚ በሆነው የየግላቸው አጀንዳ ካላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር መሆን የለበትም። የሌሎች መድረክ የኛ ካልሆነ የሚል ጩኸት፤ ጯሂው የጩኸቱን መልዕክት አለማወቁን ያስረዳልና፤ ራሳችንን ለትዝብት አንጣል። በርግጥ ይህ በግለሰቦች እንጂ፤ በማንም በአማራ ስም በሚንቀሳቀስ ድርጅት፤ በድርጅት ደረጃ ሲፈጸም አላስተዋልኩም። ሆኖም ግለሰቦች ባሁን ጊዜ በጀርባቸውን መወከላቸው መስካሪ አያሻውምና፤ ጠንቀቅ!
አክባሪያችሁ
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

አርብ፤ ሕዳር ፳ ፫ ቀን፤ ፳ ፻ ፱ ዓመተ ምህረት  ( 12/2/2016 )

No comments:

Post a Comment

wanted officials