በመላዉ የአዲስ አባበ ፖሊስ ጣቢያዎች በአዲስ ምልምልነት ስራ ይጀምራሉ ተብለዉ በዝግጅት ላይ ያሉት ፖሊሶች ከ 3 ወራት በፊት በአፋጠኝ ስልጠናዎችን መዉሰዳቸዉን እና በእያንዳንዱ ወረዳ ከ 40 እስከ 80 ፖሊሶች መመደባቸዉን ከዉስጥ ምንጮች ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሊነሳ ይችላል ተብሎ የሚሰጋውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለማስቆም በተሻለ ታማኝነት ያገለግላሉ ተብለው በአገዛዙ እምነት የተጣለባቸው ለእነዚህ አዳዲስ የፖሊስ ምልምሎች ሞቅ ደመቅ ያለ አቀባበል እንዲደረግ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ የወረዳ ፖሊስ ቢሮዎች በሙሉ ትዕዛዝ መተላለፉንና ወረዳዎቹም በታዘዙት መሰረት ስፖንሰሮችን ሲያፈላልጉ ቆይተዉ በነገዉ እለት ዕሁድ ድግሱን ለማብላት በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ታዉቋል።
ከነገ ዕሁድ ጀምሮ ስምርት ውስጥ ከሚገቡት አዲስ ምልምሎች በተጨማሪ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስተዳደር ሌሎች ተጨማሪ አዳዲስ የፖሊስ አባላትን በከፍተኛ ፍጥነት በማሰልጠን ወደ ስራ ለማሰማራት እንቅስቃሴ ላይም እንደሚገኝ የዉስጥ ምንጮች አያይዘው ሲገልፁ፤ስልጠናዎችን ወስደዉ ስራ ለመሰማራት ከተዘጋጁትም ሆነ ለስልጠና እየተመለመሉ ካሉት የፖሊስ አባላት ከ95 ፐርሰንት በላዮቹ ሙያዉን ፈልገዉት እና አምነዉበት አይደለም ሲሉም ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ካሉ በርካታ ነባር ፖሊሶች መካከል በተለይ በአዲስ አበባ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ በየወረዳው በትንሹ ከ50 በላይ ፖሊሶች የስራ መልቀቂያ ያስገቡ ሲሆን፣ መልስ የሚሰጣችሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ ነዉ የሚል መልስ እንደተሰጣቸውና በዚህም የተነሳ በርካቶች ያለዉዴታቸዉ በስራዉ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ። የስራ መልቀቂያ ያስገቡ ፖሊሶች በእጃቸው ምንም መሣሪያ እንዳይይዙ መታገዳቸዉን እና አንዳንዶች ሰበብ ተፈልጎባቸዉ እንደታሰሩም የደርሰን መረጃ ያመለክታል። ነባር የፖሊስ አባላት በሥራቸው ላይ ደስተኛ እንዳይሆኑ ካደረጋቸው ምክንያቶች ከፍሉ በብሄር ልዩነት የሚደገረዉ አድሎአዊነት እና በተደጋጋሚ የሚነሳው የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ እንደሆነ እና በተለይ የህዝባዊ እንቢተኝነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ መንግስት በፖሊሶች ላይ እምነት እያጣ ከመሆኑ የተነሳ በፈጠረባቸዉ ከፍተኛ ጫና የተነሳ ስራቸዉን ለመልቀቅ መወሰናቸዉን በርካታ ፖሊሶች ይናገራሉ።
በተያያዘ ዜና በአገሪቱ ውስጥ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት የሥልጣን ዕድሜው እያጠረ መምጣቱ ያሳሰበው የህወሃት አገዛዝ አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችን ውሎ አበል እየከፈለ ለብቻቸው ለመሰብሰብ ውስጥ ለውስጥ ጥሪ ማስተላለፉ ለማወቅ ተችሎአል።
ህወሃት የኦሮሞ ተወላጆችን ለይቶ በጠራው ስብሰባ ላይ ለያንዳንዱ ተሰብሳብ የከተማ ቦታና ገንዘብ ለመስጠት እንዳሰበ በማስረዳት ሊነሳ የሚችለውን ህዝባዊ አመጽ እንዲዋጉ ማግባባት ተቀዳሚ ፍላጎቱ እንደሆነ ታውቆአል።
ህወሃት ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ስብሰባና ቃል ስለሚገባላቸው የከተማ ቦታና ገንዘብ በተመለከተ የትንሳኤ ሬዲዮ ተጨማሪ መረጃ በማሰባሰብ ለአድማጮቹ እንደሚገልጽ በቅዲሚያ ያስታውቃል።
No comments:
Post a Comment