Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, December 9, 2016

በተለይ ለኦሮሞ ልሂቃን የተላከ ማስታወሻ – ከነፃነት ዘለቀ


No automatic alt text available.
መድሓኒት ከምን እንደሚሠራ አለማወቃችን በጄ እንጂ ብዙ ፈዋሽ መድሓኒቶች የሚቀመሙት ከመርዝና ብዙም ከማንወዳቸው ነገሮች ነው፡፡ ግን መዳን ስላለብን ሃኪምና ዐዋቂ እንድንወስዳቸው የሚመክሩንን የሚቀቡም ሆኑ የሚዋጡ መድሓኒቶች አለማመንታት እንወስዳቸዋለን፡፡ በቤታችንስ ስንቶቻችን ነን የገዛ ሽንታችንን የምንጠጣ? አዎ፣ መድሓኒት ነው ከተባለ የጅብ ጉበትም ይበላል፤ የአህያ ወተትም ይጠጣል፡፡ ዋናው ከሚያሰቃየን ደዌ መፈወሱ ነው፡፡ “ምንም ቢያስቀዝን ጮማ” ብሎ ነገር በጭንቅ ወቅት አይሠራም፡፡ አሁን ያለንበት ሀገራዊ ድባብም እንዲሁ በጣም አስጨናቂና አሳሳቢ ነው፡፡

ልዩነትን ስናሽኳልለው “ልዩነት ጌጥ ነው” እንላለን፡፡ ግን ልዩነት የብልቃጥ መርዝ ነው፡፡ የብልቃጥ መርዝ ደግሞ እንደያዥው ነው፡፡ ከተፈለገ በመርዝነቱ ሰውን መጨረስ ራስንም ማጥፋት ይቻላል፡፡ ካስፈለገም ወደመድሓኒትነት ለውጦ ትክክለኛ መጠኑንና የአቀማመም ቀመሩን በጠበቀ ሁኔታ ወደ ፈዋሽ መድሓኒትነት መለወጥ ይቻላል፡፡ ምርጫው ሁለት ነው፡፡ አንድም ልዩነትን በጌጥነት ለመጠቀም ቀመሩን ማወቅና ውበትን መላበስ አንድም በመርዝነት መጠቀምና መተላለቅ፡፡

አስተሳሰብ ወደፊት እየመጠቀ እንጂ ወደኋላ እየተጎተተ ሊሄድ አይገባም፡፡”በምኒልክ የደነቆረ ዕድሜ ልኩን በምኒልክ ይምላል” እንዲሉ ሆኖብን እንጂ የሀገራችን ልሂቃንና ተማርን የምንል ወገኖች ሁሉ አስተሳሰባችን ዘመንንና ወቅትን የዋጀ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ቢያንስ ቢያንስ ከነሲንጋፖርና ከነማሌዥያ ተርታ በተሰለፈች ነበር፡፡ ነገር ግን በማይማዊ እልህ እግር ከወርች ታስረን ያልተገባ ፉክክርና የማያሸንፉት ጦርነት ውስጥ ገብተን እኛንም ሕዝባችንንም አገራችንንም የኋሊት ሽምጥ ስናስጋልብ እንገኛለን፡፡ ዛሬ አደጉ በሚባሉ ሀገሮች ውስጥ የሰው መሠረታዊ ፍላጎቶች ተሟልተው አንድም የሚራብና የሚጠማ የሚታረዝም ሆነ ካለመጠለያ የሚኖር ዜጋ የለም፡፡ ካላፈርክ በነፃ ብፌ በሚበላባቸው ምግብ ቤቶች፣ በነፃ በሚታደርባቸው አዳራሾችና በነፃ በሚለበስባቸው ቤተ-አልባሳት በመሄድ ራስህን አንደላቅቀህ ማኖር ትችላለህ፡፡ ድህነት ሲባል በእኛና በነሱ መሥፈርት የተለያዬ ነው፡፡ ይህን ግን መንግሥታችንን ጨምሮ ብዙዎቻችን አናውቅም፡፡ እኛና ሀገራችን ሊናገሩት የሚዘገንን የድህነት አረንቋ ውስጥ ልንገኝ የቻልነው እንግዲህ በቅድሚያ የአስተሳሰብ ድሆች በመሆናችንና ያንንም ተከትሎ በየጊዜው በሚከሰት የርስ በርስ ግጭት በምናጠፋው የሰው ሕይወትና የሀገር ሀብት ውድመት ሳቢያ ቁልቁል ስለምንጓዝ ነው፡፡

አሁንስ? እያሳለፍነው የምንገኘው መከራና ስቃይ አስተምሮናል? በውጪ ሀገራት በስደትም ይሁን በትምህርት ምክንያት ስንሄድ ከምናየው የሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰብኣዊ ሕይወት ምን ትምህርት ቀሰምን? እነዚህ ሕዝቦች ርሀብንና የርስ በርስ ቅራኔን እንዴት ፈትተው አሁን ወደሚገኙበት የዕድገት ደረጃ ደረሱ? ለመሆኑ በነሱ ሀገር አሁን በቀን ስንት ጥይት ይጮሃል? ስንትስ ሰው በገዛ መንግሥታቸው ጥይት እንደቅጠል ይረግፋል? እንደሰው ከማያያቸው ባዕድ-መሰል መንግሥት ከተላቀቁ ስንት ዘመን አለፋቸው? የልዩነታችን መሠረትና መንስኤው ምን ይሆን?

ባላምባራስ ጓንጉል ድፋባቸውና ቀኛዝማች አዝብጤ መሸሻ የዛሬ መቶ ዓመት አንዳች ጥፋት አጥፍተው ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሤ ጠንክር ጉዲሣና የደርጉ ሊቀ መንበር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ፈይሣ ያዘዟቸው ወታደሮች ደግሞ እነስንሻው መኳንንትን፣ እነለጥይበሉ ማንደፍሮህን፣ እነአበጋዝ ይማምን፣ እነሐጎስ ገመቹን፣ እነሸንቁጥ ለሊሣን… ገድለዋል፡፡ መበደልና መበዳደል ማኅበራዊ ክስተት እንጂ ለአንድ ዘውግና ለአንድ ሀገር ብቻ የሚተው ብርቅዬ ነገር አይደለም፡፡ ባለፉ ዘመናት ማን ማንን በጣም በደለ በሚል አላስፈላጊ እንካስላንትያ ውስጥ መግባት ካላስፈለገ በስተቀር ሁሉም ተበዳድሏል፤ ሁሉም ተሰዳድቧል፤ ሁሉም ይቅር ለእግዜር ተባብሏል፡፡ በጊዜ ሂደት ሁሉም ተቀያይጧል፤ ሁሉም አንድ፣ አንዱም ሁሉም ሆኗል፡፡ ያለፈን ታሪክ እያሞሰኩ ባለፈ ሕይወት አሁን መኖር ምን ዓይነት ውድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ከእኛ በላይ የሚያውቅ ከቶ ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ዘመን የለዬለትን መገደልንና መሞትን ለ‹ዕድለኛ› ሟች እንደመልካም አጋጣሚ እንቁጠረውና በርሀብና በዕርዛት በቁም መሞትን የመሰለ በዓለማችን ፊት የሚያሰቅቅ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ለዚህ የበቃነው ደግሞ የቤት ውስጥ ቀጋው ወያኔ ሳይረሳ በተባባሪነት በቆሙ በውጪ ሀገራት በተለመደው አገላለጽ በርገር እየቆረጡ በሞቀ ቤታቸው ውስጥ በሰላም በሚኖሩ ወገኖቻችን ነው፡፡

ይህ አካሄዳችን መለወጥ አለበት፡፡ መለወጥ ያለበትም አሁን ነው፡፡ መድሓኒት መዋጥ አለብን፡፡ መድሓኒት ሲዋጥ መረረኝ ጣፈጠኝ የለም፡፡ መድሓኒት በተፈጥሮ መራራ መሆኑን እናውቃለን – ጣፋጭ እንኳን ቢሆን በሥነ ልቦናችን መራራ እንደሆነ ስለምናስብ ጥፍጥናው በምሬት ይተካና እየጎመዘዘን እንውጠዋለን፡፡ ስለዚህ ስለኛ ብቻ ብለን ሳይሆን ስለልጆቻችንና ስለመጪው ትውልድ ብለን ቢመረንም በፈዋሽነቱ ወደር የማይገኝለትን ፍቱን መድሓኒት መርጠን አሁኑኑ እንዋጥ፡፡ ጊዜ የለም!

“እግዜር ሲቆጣ ሽመል አይቆርጥም፤

ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም፡፡” እንዲሉ ሆኖብን እስካሁን ድረስ ጥቃቅን ነገሮችን በምክንያትነት እየደረደርን ላለመግባባት ስንግባባ ቆይተናል፡፡ ይህ ሂደት ግን እኛን አልጠቀመንም ብቻ ሣይሆን ሕዝባችንን ከመኖር ወዳለመኖር እየለወጠው ነው – እስካሁን ኖረ ከተባለ ሊያውም፡፡…

ልክ እንደዐማራው ሁሉ ኦሮሞም በጣም ሰፊና ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ሰፊነትና ታላቅነት የሚገለጽባቸው ባሕርያት አሉ፡፡ ከነዚህም ጥቂቶቹ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው የሚሸፍኑት የቦታ ስፋት፣ በሕዝብ ቁጥር ያላቸው አብላጫነት፣ በብሔራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የተማረ የሰው ኃይል ብዛት፣ ጎላ ብለው የሚታዩት ባህላዊና ሥነ ልሣናዊ የዘዬ ልዩነቶች ወዘተ. ለሰፊነታቸው በዋቢነት ሊጠቀሱ ሲችሉ ለታላቅታቸው ደግሞ ኢዮባዊ ትግስታቸው፣ ተቻችሎ የመኖር ችሎታና ብቃታቸው፣ በተራ ወፍ ዘራሽ ስብከት ያለመወሰድ ዝንባሌያቸው፤ በቋንቋ፣በባህል፣ በሃይማኖት፣ በጋብቻና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ክሮች በፍቅርና በውዴታ መተሳሰራቸው ወዘተ. ከብዙው በጥቂቱ ሊወሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ኦሮሞ ያልገባበት የኢትዮጵያ ግዛት የለም – አለ ከተባለም ጥቂት የኤርትራና የትግራይ ሥፍራዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲወራ እሰማለሁ፡፡ የኦሮሞ ዘር ያልገባበት ኢትዮጵያዊ የዘር ሐረግ በፍጹም የለም፡፡ እያንዳንዳችን ከአባታችን ተነስተን ወደኋላ ብንቆጥር አብዛኞቻችን የኦሮሞ ስም ለማግኘት እስከ ሰባት ትውልድም መሄድ ላያስፈልገን ይችላል – የዐማራ ወይ የሌላ ስም ለኦሮሞ እንደሚሰጥ ግን ልብ አድርጉ! እናም በለየለት ሁኔታ “ገመቹ” ወይም “ረጋሣ” ዓይነት ስም በትውልድ ሐረጋችሁ ፈልጉ ማለቴ እንጂ በሌሎች ስሞችማ ኦሮሞ በሽበሽ ነው – ጋዲሣ የሚባል አማራም ስለማውቅ ይህ አሰያየም ለሁሉም የሚሠራ እንጂ ለኦሮሞው ብቻ እንዳልሆነ ይያዝልኝ (በብዙ ምዕተ ዓመታት የረጂም ጊዜ ተራክቦ ኦሮሞው በአማራው ውስጥ፣ አማራውም በኦሮሞው ውስጥ ቀልጠዋል)፡፡ “ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ይገነጠላል” ለሚለው የመነቸከ ቀልድ ኦሮሞዎችን ራሳቸውን ጨምሮ ብዙ ዜጎች “ቅርንጫፍ እንጂ ግንድ ሊገነጠል ይችላል ወይ?” የሚል ትክክለኛ መልስ የሚሰጡበት አንደኛው ምክንያት ይሄው የኦሮሞዎች ሁሉንም የመሆን ተፈጥሯዊ ጠባይ ነው፡፡ በአዲሱ የወያኔ ዘፈን ካልጨፈርን በስተቀር የኢትዮጵያ ትልቁ መለያም የሕዝቧ የደም ትስስር ነው – ለዚህም እኮ ነው እንደወያኔና ደቀ መዛሙርቱ ሤረኛ አጠራር “የኢትዮጵያ ሕዝቦች” ሣይሆን “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ሲባል ከውስጠ-ውሳጤያችን ጀምሮ አንዳንዶቻችንን ደስ የሚለን!

ኦሮሞ እንደትግሬ ወይም እንደጽዮናውያን በጣም የተቀራረበ ጎሣዊ አስተሳሰብና ዘውጋዊ ትስስር የለውም ፤ ዐማራም እንዲሁ ነው ወይም ቢያንስ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እንዲሁ ነበር፡፡ ብዙኃት ተጋሩን ወደዚህ እጅግ አስቀያሚ የጎሠኝነት ስሜት ለማድረስ ሕወሓት የወሰዳቸውን እርምጃዎችና በዚያም ሳቢያ ያደረሰውን ዕልቂት፣ በተጋሩና በተለይም በዐማሮች መካከል የነዛውን የጥላቻ መርዝና የዘመናት ፕሮፓጋንዳ ስናስብ ጥፋትን ዘርቶ ዕልቂትና ውድመትን ለማዝመር ከባድ አለመሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ግን በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህን ሁለት ሕዝቦች – ኦሮሞንና አማራን – እየገፉ ወደ ደምና አጥንት ጅረት ሊከቷቸው ሌት ተቀን በመትጋት ላይ የሚገኙ ይመስላል – እንደኔ ደግሞ ጨለማው ሊነጋ የተቃረበ ይመስለኛልና ከዚህ በኋላ ይህ እንደውሻ አጥንትና ዘር እያነፈነፉ መጠራራትና ለጥፋት መሰማራት ሊያከትም ጫፍ ላይ ደርሷል እላለሁ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ጉዳይ ግን አንድን ማኅበረሰብ ጊዜ ይፍጅ እንጂ ሸረኞችና ተንኮለኞች በቀደዱት የጥፋት ቦይ መክተት የሚቻል መሆኑን ነው፡፡

ውድ ወገኖቼ! አሁን ጊዜ የለንም፤ ዐማራና ኦሮሞ ወደ ዐማራነትና ኦሮሞነት ለይቶላቸው ከመዝቀጣቸው በፊት እንድረስላቸው፡፡ ልድገመው – ኦሮሞና ዐማራ ወደ ኦሮሞነትና ወደ ዐማራነት በአራዶቹ አገላለጽ ከመሸብለላቸው በፊት ቀድመን ካልደረስንላቸው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከታሪክ መዝገብም ተፍቃ ትጠፋለች፤ ይህ ሰይጣናዊ ትንቢቴ እውን እንደማይሆን በአንድዬ ብተማመንም “ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር” ይባላልና የሆነው ይሁን በሚል እጃችንን አጣጥፈን መቀመጡ ከእስካሁኑ የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ትላልቅ ምሠሦዎች ሦስት ናቸው፤ አንደኛው ሳይወድ በግዱ አዝምሟል – የጊዜ ጉዳይ ነው እንዳዘመመም አይቀርም፤ ሁለቱ ግን እስካሁን ደህና ነበሩ – በብዙ የንፋስ ንፅውፅውታ እየተመቱም ቢሆን በጽናት እንደቆሙ እስከቅርብ ዓመታት ዘልቀው ነበር፤ ከአሁን በኋላ ግን አስጊ ነው፤ የጽናታቸውም ምክንያት ሳይደግስ አይጣላምና (a blessing in disguise) በአካባቢና በሕዝብ ብዛት የበላይ እንደመሆናቸው ሁሉንም ወደ አንድ ለማሰባሰብና በአንድ ጠባብ ሥነ ልቦናዊ ቦይ እንዲፈሱ ለማደረግ ባለመቻሉ ነው – እነዚህን ዘውጎች በትናንሽ ነገዶች ሣይቀር ለመበጣጠቅ ሳይሞከር ቀርቶ ሣይሆን ለመሠሪዎች ተንኮል ምቹ አልነበሩም፡፡ ቀስ በቀስና በጊዜ ሂደት ግን የማይቻል ነገር የለምና እነዚህ ሕዝቦች ወደተዘጋጀላቸው የጥበት መንገድ ሊገቡ ይችላሉ፤ አዝማሚያዎችም በግልጽ እየታዩ ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ አምላክ በቅርብ ጣልቃ የሚገባው፡፡ ደስ ይበለን – ጣልቃ ይገባል!…(እውነቴን ነው የምላችሁ ማን እንዲህ በል እንደሚለኝ አላውቅም፤ግን እውነቱ ይሄውና ይው ነው – በቅርብም ኢትዮጵያን የሚያድን ተዓምር እናያለን፡፡ ታሪክም ለዚህ ምሥክሬ ው፡፡)

ኦሮሞ ሰፊ ነው፡፡ የሸዋ ኦሮሞ አለ፡፡ የወለጋ ኦሮሞ አለ፡፡ የአርሲ ኦሮሞ አለ፡፡ የባሌ ኦሮሞ አለ፡፡ የወሎ ኦሮሞ አለ፡፡ ባጭሩ የሌለ ኦሮሞ የለም፡፡ “ኦሮሞ ታዲያ ከየት ነው የሚገነጠለው?” ብለን ስንጠይቅ ችግሩ ከሕዝብ ሣይሆን ከሌላ ሆኖ እናገኘዋን፡፡ ያ “ሌላ” ነገር ደግሞ በዋናነትም ባይሆን በመለስተኛ አጫፋሪነትና በዕቅድ አስፈጻሚነት ልሂቅ ተብዬውን ሀገር አጥፊና ሀገር አልሚ ይይዛል፡፡ የተማረ ሰው ለልማት ቅርብ የመሆኑን ያህል ለጥፋትም በጣም የቀረበ ስለመሆኑ በተለይ ያሳለፍናቸው 42 የመከራና የስቃይ ዓመታት በግልጽ ይናገራሉ፡፡ ልሂቅ ሀገር አጥፊና አልሚ አልሁኝ? ራሳችንን እንመርምር፡፡

ኦሮሞን እገነጥላለሁ ብሎ የተነሣ ወገን ካለ ዕብድ ነው፡፡ እርግጥ ነው አማራጭ ሚዲያ ባለመኖሩ ምክንያት በተወሰኑ በሞኖፖል በተያዙ የሚዲያ አውታሮች የተወሰነ ግርግርና ጊዜያዊ የልብ መሸፈት መፍጠር ይቻላል፡፡ እውነቱ ሲገለጥ ግን ሁሉም አቅል ይገዛል፡፡ እስከዚያውና እንደ እውነቱም ከሆነ ግና “mob” የምንለው ነገር በጣም መጥፎ ነው፡፡ ክርስቶስን ያሰቀለው ሞብ ነው፡፡ ብሩተስን ያሰቀለው ሞብ ነው፡፡ በሞብ ምክንያት ብዙ ሀገሮች ፈርሰዋል፤ ተፈጥረዋልም፡፡ በሞብ ምክንያት እጅግ ብዙ ንጹሓን የዓለም ዜጎች ለሰይጣን ጭዳነት ተዳርገዋል፤ አሁንም ድረስ፡፡ በሞባዊ እንቅስቀሴ ወቅት ምክንያትና ሎጂክ እሥር ቤት ይገባሉ፤ ይገረፋሉ፤ በጭካኔም ይታረዳሉ፡፡ ስለሆነም “ሞብ አያስፈራም፤ ሞብ አገር አይበትንም፤ ሞብ አገር አያስገነጥልም ….” አልልም፡፡ ብዙ መጥፎ ውሳኔዎችና መጥፎ ድርጊቶች በሞብ ጊዜ – በስሜት ግልቢያ ወቅት – ይከናወናሉ፡፡ በነዚህን መሰል መጥፎ ድርጊቶች ወቅት የሚከሰቱ የክፋትና የውድመት ተግባራት ለከፍተኛ ጸጸት የሚዳርጉና ብዙዎቹም የማይቀለበስ አሉታዊ ጠባሳ የሚያኖሩ ናቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ – የነብር ጣቱ – ትኩስ ኃይል እንደመሆኑ አዲስ ነገርን የማየት ጉጉት አለው፡፡ መሠሪዎች ይህን ኃይል ተጠቅመው ታሪክን ቢያንሻፍፉና ቢያጣምሙ በሀገር ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ – ይህን እስኪበቃን አይተናል፤ እያየንም ነውና ለኛ አዲስ አይደለም፡፡ ስለሆነም ምራቅ የዋጡ የማኅበረሰቦቻችን አባላት ብዙ ይጠበቅባቸዋል – ከየጎሣው ያሉ አባቶችና እናቶች ዝም አይበሉ፡፡

ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ የተለያዩ አስተሳሰቦች እንዳሉ ማንም ይገነዘባል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት አቋም ያላቸው የኦሮሞ ልሂቃን መኖራቸውም የማይታወቅ አይመስለኝም፡፡ ጥሪየ እነዚህ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም ልጆቼ ወደኅናሊቸው እንዲመለሱና የጋራ ሀገር እንዲኖረን በጋራ ትግል እንዲሠለፉ ነው፡፡ ከስሜት የወጣ የሰከነ ትግል እስካልተደረገ ድረስ የጠላት መሣሪያ እንደሆኑ ዕለተ ምፅዓትን እየተሰቃዩ መጠበቅ ነው – ተነጣጥሎ ደግሞ ነፃነት ዕርም ናት፤ አትገኝም፡፡ ከእልህ ወጥተን ወደ አመክንዮ እንግባ፡፡ ሥልጣን እንደሆነች ወንበሯ አንዲት ናት፡፡ ያቺን ወንበር ደግሞ ማንም ይያዛት ግን አንዲት እንደሆነች ዓለም ታልፋለች እንጂ እንኳንስ ሺህና ሚሊዮን ሁለትም አትሆንም፡፡ ለሚራኮትባት ሁሉ ብትሆን ደስታውን ባልቻለችው – ስገምት፡፡ ግን ካንድ በላይ ቢቀመጡባት ትሰባበራለችና አትችልም፡፡ ታዲያ ለዚህች አንዲት ምሥኪን ወንበር ይህን ያህል ሕዝብ በውጪና በሀገር ውስጥ በጎሣና በዘር፣ በሃይማኖትና በወንዝ ልጅነት ጎራ ለይቶ አበሳውን ማየቱ ለጤና ነው ትላላችሁ? አቅል እንግዛ እንጂ! “ሀበሻ ዱሮውንም…” ከሚል ትችት መውጣት አለብን – ሀበሻነትና ሀበሻዊ ማንነት በራሱ አጠያያቂ ቢሆንም፡፡

ትናንት በኦኤምኤን – በዐዋጅ ብከለከልም በድብቅ – አንድ ልዩ ዝግጅት ተከታትያለሁ – ባማርኛ፡፡ በዚህ ዝግጅት አወያዩ ደጀኔ ጉተማ ለጠየቀው አንድ ጥያቄ ጃዋር መሀመድ የሰጠው መልስ እንዲህ ነበር – “የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ከሩዋንዳ ጋር የሚመሳሰል አይመስለኝም፡፡ እንደኔ የዚህች አገር መፃዒ ዕጣ-ፋንታ ከዩጎዝላቪያና ከሶቭየት ኅብረት ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡” የመልሱ ጥቅል ይዘት እንዲህ ነበር፡፡

በጣም ገረመኝ፡፡ ከዚህ አባባል ብዙ ነገር መገንዘብ ይቻላል – “የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው”፤ ጃዋር ምን ማለት እንደፈለገ ብቻ ሣይሆን ምን እንዲሆንለት እንደሚፈልግ ሣይቀር ወደየትም የጥንቆላ ቤት መሄድ ሳያስፈልገን በቀላሉ መረዳት አይከብድም – ከዚያ ይሰውር እንጂ፡፡ በነገራችን ላይ ከሁለትና ከዚያ በላይ ዘውጎች የምትወለዱ ወገኖቻችን ልዩነቶቻችንን ለማጦዝና የሆነ ዓላማ ለማሣካት ከምትሞክሩ ይልቅ የሁለት ቤት አባልነታችሁን የማይገሠስ ወርቃማ ዕድል በመጠቀም ሕዝቦችን ለማስማማትና ለማዋሃድ ብትጥሩ በታሪክም በትውልድም ትከበራላችሁ፡፡ ሰዎች ክፉ ከሆኑ ፣ በሀብትና በሥልጣን ሱስ ከተለከፉ፣ በእርኩስ መንፈስ ከተነዱና ጤናማ ኅሊናቸውን በሆነ ኃይል ከተነጠቁ … ልዩነትን ለክፉ ዓላማ መጠቀም ይችላሉ – እንደ አብነት ጎጃሜዎቹን መለስ ዜናዊንና ገብሩ አሥራትን(የአሁን እሱነቱን አይደለም!)፣ ኦሮሞውን አዲሳለም ባሌማንና ወሎየውን ሼህ አላሙዲንን መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ ልዩነትን በተለይም በራስ ውስጥ የሚገኝን የሁለትነት ልዩነት በጎ ላልሆነ ዓላማ መጠቀም ከኩነኔዎችና ከክፋቶች ሁሉ የበለጠ መጥፎ ተግባር ነው፡፡ በኔ ውስጥ ያለውን አንዱን ማንነት በኔ ውስጥ በሚገኝ ሌላ ማንነት ብደበድበው፣ ደብዳቢውም ተደብዳበውም እኔ ራሴው ነኝና በየትኛውም መለኪያ ልክ አልሆንም ብቻ ሣይሆን ትልቁን የወንጀል ፍርድ ያስበይንብኛል – ራስን መግደል ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ነውና! እነጀዋርም የዚህ ሾተላይ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ “እኔ ‹ንጹሕ‹ አማራ ነኝ” የሚልና ሙሉ በሙሉ “እኔ ‹ንጹሕ› ኦሮሞ ነኝ” የሚል ሰው (ደግነቱ በየዋህነት እንዲህ የሚል ቢኖርም ከእውነት ግን ሊኖር አይችልም እንጂ) ይህን ዓይነት ስህተት ቢሠራ ንስሃ አለው – አለማወቁና አለኝ የሚለው “ንጹሕ” የኦሮሞ ወይም የአማራ ደም መጠነኛ አዘኔታና አመክሮ ሊያስገኝለት ይችል ይሆናል፤ እነጀዋር ግን ሕዝብን አንድ ለማድረግ ማድረግ ከሚጠበቅባቸው መልካም እንቅስቃሴ ውጪ ለመለያየትና ክፍፍል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉ አይደለም እግዚአብሔር ሰይጣን ራሱ ይታዘባቸዋል – መሬቱ የተደላደለላቸው ኅብረትንና ስምምነትን ለመፍጠር ብቻ ነውና ሁለቱንም ሆነህ ወደ አንዱ ብታዳላ ማዳላትህን ማንኛውም ወገን በፀጋ ሊቀበለው አይገባም – ነግ በኔም እኮ አለ! ለምሣሌ እኔ የጉራጌ ደም እያለብኝ በጉራጌ ላይ ከዘመትኩ ጤናየ ተቃውሷል ማለት ነውና የሀኪም ክትትል በእጅጉ ያስፈልገኛል፡፡ ምን ማለት እንደፈልግሁ በተለይ የሁለት ዘውጎች ውጤት የሆናችሁ ዜጎች በደንብ የገባችሁ ይመስለኛል፡፡

ለማንኛውም የዚህ ንግግር አንድምታ (implication) ኦሮምያ የሚባል በታሪክ የሚታወቅ አንድ ሀገር ኖሮ፣ አማሪያ የሚባል ራሱን የቻለ ግዛት ኖሮ፣ ከፊቾ የሚባል፣ ሃዲያ የሚባል፣ ጠምባሮ የሚባል፣ ጌዲዮ የሚባል፣ ከምባታ የሚባል፣አፋር የሚባል…. ራሳቸውን የቻሉና በተባበሩት መንግሥታት መዝገብ ውስጥ እንደነፃ ሀገር ተመዝግበው የሚኖሩ “የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት” ኖረው በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በሕወሓት የአፓርታይድ አገዛዝ ሥር ያሉትን “ነጻና ፌዴራል መንግሥታት” በቅጡ የማያስማማ ሁኔታ ከተፈጠረ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሩዋንዳ ዓይነት የዘር ፍጅት ሣይሆን እንደቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረትና ዩጎዝላቪያ “ኢምፓየሪቱ” ትበታተናለች የሚል አስተያየትና ቅድመ ትንበያ ነው ጆሃር የሰጠው – “ህልም እልም” ብያለሁ ጆሃር፡፡ ይቺ የፈረደባት ኢምፓየር ደግሞ ስንቶች የኦሮሞ ነገሥታትና መሣፍንት ወያኔ ወደ ሥልጣን እስከመጣበት እስከ 1983ዓ.ም ድረስ ሲገዟትና ሲነዷት እንደነበሩ መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ ዕንቆቅልሽ ምን አውቅልህ፡፡ (ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሣ ምነው ሰሞኑን ፀጥ አልክ? ኧረ ብቅ በል!)

እንደኔ እንደኔ ኢትዮጵያ መጥፎ ዕድል ከገጠማት የምታመራው ወደ ራሺያና ወደ ዩጎዝላቪያ ሣይሆን ወደ ሶማሊያና ሦርያ እንዲሁም ወያኔዎች በጭካኔያቸው ቀጥለው የትግራይን ሕዝብ መከታና ደጀን በማድረግ ሌሎችን መጨፍጨፋቸውን አባብሰው ከገፉበት ጉዟችን በቀጥታ የሚያመራው ወደ ሩዋንዳ ነው – ማንም ሲያምረው ይቅር እንጂ ኢትዮጵያ ወደ ራሺያ ሊያስኬዳት የሚያስችል ታሪካዊ መደላድልም ሆነ ማኅበረሰብኣዊ ዝግጅት የላትም፤ እውነትና ትንቢት ይለያያሉ ወንድሞቼ፡፡ ይህን መጠራጠር ቂልነት ነው፡፡ በመሠረቱ እኔ የፖለቲካ ሣይንስ ተማሪ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን “የኢትዮጵያ ሁኔታ እየከፋ ከመጣ የምንሄደው ወደ ዩጎዝላቪያ ነው ወይንስ ወደ ሩዋንዳ?” ተብዬ ብጠየቅ መልሱ እጅግ በጣም ቀላልና እርሱም ወደ ሩዋንዳ መሆኑን ማስረዳት አይቸግረኝም፡፡ ይልቁንስ “አይመጣምን ትተሸ ይመጣልን ባሰብሽ” ነውና ነገሩ ጤነኛ ነኝ የሚል ዜጋ ሁሉ ይህን ነገር አሁኑኑ ይጨነቅበት፡፡

ብዙ ስናገር መዋል እንደሌለብኝ አውቃለሁ፡ አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን ከገባችሁበት ወረተኛና ከፋፋይ የባዕዳን አስተሳሰብ ባፋጣኝ ውጡ፡፡ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ከሞላ ጎደል በእኩል ደረጃ ተረግጠው የሚኖሩባት የምስኪኖች ሀገር ናት፡፡ መበታተን የሚባል ቃል ያለው በልሂቃን ምናብ ውስጥ እንጂ በእውን ምድር ላይ የለም፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታች ወርዶ ማየትና ኑሮውን እየኖሩ የሚፈልገውንና የማይፈልገውን ማጥናት ይገባል፡፡ የሚሻው አምባነኖችን በአምባገነኖች መተካት ወይም እንደዶሮ ተገነጣጥሎ ለየብቻው መኖርን ሳይሆን እፎይ ብሎ በአንድነትና በነፃነት የሚኖርባትንና ሰብኣዊ መብቶች የሚከበሩባትን የጋራ ሀገር መፍጠር ነው፡፡ በጥቃቅን ታሪካዊ ቁርሾ ምክንያት ትልቅ ሀገር አትፈርስም፡፡ ብትፈርስ ደግሞ ማንም ከማንም በልጦ የማይጠቀምባት ወይም የማይጎዳባት የጃርት መፈንጫ ትሆናለች እንጂ በላም አለኝ በሰማይ በሚገነቡ ትናንሽ መንግሥታት ውስጥ ማንም አፄ በጉልበቱ ከኮልኮሌዎቹ ጋር የሚዘባነንባቸው ብጭቅጫቂ ሀገራት አይመሠረቱም፡፡ ይህ አስተሳሰብ ህልም ነው፡፡

ባንዴራን በሚመለከት ሕዝብን ባናወናብድ መልካም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንደነበረችና እንደነገሩም ቢሆን አሁንም እንዳለች የማንቀበል ከሆነ እንደእስካሁኑ ሁሉ ስምምነቶችና ድርድሮች ሳይጀመሩ እያለቁ ዕዳችን ይቀጥላል፡፡ ይህም ሁኔታ ለጋራ ጠላቶቻችን ምቾትንና እፎይታን እየፈጠረ የግፍ አገዛዙ – እንደሰውኛ አስተያየትና ግምት – ማብቂያ የሌለው ይሆናል፡፡ አዲስ ነገር እየፈጠርን ሕዝብን በተለይም ወጣቱን ውዥንብር ውስጥ አንክተት፡፡ ችግራችን የእራፊ ጨርቆች ቁጥር ማነስ ወይም መብዛት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ለዘመናት የገዙ የኦሮሞ ነገሥታት ያውለበልቡት የነበሩት የትኛውን ባንዴራ እንደነበረ ታሪክና የታሪክ ሰዎች ቀርተው መሬቱም ያውቃል፡፡ ከዚህ ከኢትዮጵያዊነት አኩሪ ነጥብ አንጻር ራስ አሊ ሚራህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አባት ነበሩ – “የኢትዮጵያን ባንዴራ እንኳን የአፋር ሰው ግመሎቻችንም ያውቃሉ” ብለው የተናገሩት ዘመናትን ተሻጋሪ በሳል ንግግር አሁንም ትኩስ እንደሆነ አለ፡፡ ከርሳቸው እንማርና ከታሪክ ተወቃሽነት እንዳን፡፡ የወረት ፍቅር ወረት ነውና ያልፋል፡፡ ስካርም ምን ጊዜም ስካር ነውና በስካር ወቅት የምናደርጋቸው አንዳንድ አልባሌ ነገሮች ለትዝብት እንዳይዳርጉን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ወረትም ስካርም ቢያልፉም ጠባሳ ትተው እንጂ እንዲሁ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከብዥታ እንውጣና ወደ እውነቱ እንቅረብ፡፡ እውነት እንደፀሐይ ጨረር በቀጥታ ሲያዩት ቢያጥበረብርም አማራጭ የለንምና ትውልዳችንን ማዳን ከፈለግን ከልቦለድ ዓለም ባፋጣኝ እንውጣ፡፡ ወያኔ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን በቀላሉ እየጨፈለቀ ለጊዜውም ቢሆን ትንሽ ፋታ ያገኘ የመሰለው በኦሮሞና በአማራ ልሂቃን ዕርዳታ ነው – በተለይም በኦሮሞዎቹ፡፡ ችግሩን ቀን ይፈታዋል፡፡ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን እነሱ ምቹ ቦታ ተቀምጠው ሕዝብን የሚከፋፍሉና ልብ ለልብ እንዳይገናኝ ለማድረግ ልዩነትን የሚዘሩ ክፉ ሰዎች አሉ፡፡ ከናዝሬት አዲስ አበባ በደቂቃዎች ውስጥ በኅብረት ጉዞ መድረስ እየተቻለ በኬኒያና በደቡብ ሱዳን ዞረው በሊማሊሞና በግራካሱ በኩል ወደ ፊንፊኔ ለመግባት የሚቋምጡ ኃይሎች እንዳሉ በበኩሌ አውቃለሁ፡፡ ማንም ግን ብቻውን ተጉዞ አራት ኪሎ ይቅርና ቃሊቲም ይሁን ሰንዳፋ አይደርስም፡፡ የዐዋቂ አጥፊ አንሁን፡፡

ቋንቋና ባህልን በተመለከተ ማንኛውም ዜጋ የራሴ ነው የሚለውን ቋንቋና ባህል ማሳደግና ለትውልድ ማስተላለፍ መብቱ ብቻ ሣይሆን ግዴታውም ነው፡፡ ስለሆነም የዚህን ሰፊ ሕዝብ ቋንቋና ባህል ማክበርና ጥቅም ላይ ማዋል የኦሮሞ ብቻ ሣይሆን የሌሎቻችንም ሁሉ የውዴታ ግዴታ ነው፤ የኦሮሞው ብቻም ሣይሆን – የጋራችን ሀብታችንን አማርኛን ሳንዘነጋ – የሁሉም ዘውግና ነገድ ቋንቋ ማደግና መበልጸግ አለበት፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ በተለይ ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ እንጂ አለልክ የሚኮፈሱበት ወይም ሌሎችን ለመናቅና ለማናናቅ የሚጠቀሙበት የግል ዕቃ እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው – አንተ ቶሎሣ ባጋጣሚ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋህ ሆነ፤ ማነህ አንተ ወንድሜ አቻምየለህ ደግሞ ዐማርኛ ሊሆንብህ ተገደድህ ልበል፡፡ እናሳ? ወደንና ፈቅደን ባልሆንነው ነገር ዝንታለሙን የቋንቋ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀን መኖር አለብን? እንደግ እንጂ! ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ኦሮምኛን/አማርኛን መናገር ባይችል እንኳን የኦሮሞነትን/የአማራነትን ማንነት መላበስ ይከብደው እንደሆነ እንጂ የኦሮምኛን/የአማርኛን የባለቤትነት ይዞታ የመጋራት ያልተሸራረፈ መብት አለው – ሁሉም ቋንቋ የሁሉም ነው – ቋንቋ የሰው ነው፤ ባለቤት አልባ የሆኑ ነገሮች ውስጥ ቋንቋ የመጀመሪያው ነው – ባለማወቅና በሞኝነት ግን ሰዎች በቋንቋ ምክንያት ብዙ ሲነታረኩ ይስተዋላል፡፡ ለምሣሌ እንግሊዝኛ አሁን ባለቤት የለውም፡፡ አማርኛም በኢትዮጵያ የዚያኑ ያህል ነው፡፡ በሂደት ደግሞ ሁሉም ቋንቋዎች ወደዚህ ደረጃ ሊደርሱ ይገባል ወይም መድረስ አለባቸው፤ ይህ የኔ ምኞት ነው – ምናልባትም በተግባር ሳይታይ ዓለማችን ቅርጽዋን የምትቀይርበት ከንቱ ምኞት፡፡ ለማንኛውም አንዱ የሌላውን ልሣን ሲያውቅና ሁሉም የሁሉንም ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን ማንም እየተነሣ “የኛ ቋንቋ የናንተ ቋንቋ” የማለት ሥልጣን የለውም፡፡ የኔ ያንተ፣ ያንተም የኔ ይሆኑና አንደኛው የግጭት መንስኤ ይወገዳል፡፡ መሆን ያለበት እንደዚያ ነው፡፡

በቋንቋ አርበኝነት የሀገርም ሆነ የግለሰብ ዕድገት አይመጣም፡፡ የሥነ ልሣንን ህገ ተፈጥሮ እንወቅ፡፡ በሥነ ልሣን ልደትና ሞት የሚጠቀሱ መሠረታዊ አላባውያን አሉ – በጉልበትና በዐዋጅ፣ በዕብሪትና በጥላቻ ግን አንድ ቋንቋ አያድግም፤ አይጠፋምም፡፡ ስለዚህ ትልቁ መፍትሔ ወደ ኅሊና መመለስ ነውና ከጥላቻ መንፈስ መውጣትም ነውና በፍቅር ማዕበል ውስጥ እየዋኙ ሰውን በሰውነቱ ብቻ ዜጋን በዜግነቱ ብቻ መቀበልና ተፈቃቅዶ አብሮ መኖርም ነው በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ እናተኩር፡፡ ኦሮሞና አማራ ትግሬና ጊሚራ የመጣው የዛሬ ስንት ዓመት ገደማ ነው፤ ሰው ግን ሲፈጠር አንድ ብቻ ነበር – ከዚያ ሔዋን ተጨመረችና ሁለት ሆኑ፤ ቀስ ብሎ ደግሞ እኛ ተጨመርንና ሰባት ቢሊዮንን አለፍን፤ ሰው በዛ ነገር በዛ፡፡ እናም ግዴላችም “ፍቅር ካለ ዘጠኝ ቂጣ ለባልና ሚስት ይበቃል” ይባላልና ፍቅር ይኑረን፡፡ ፍቅር ካለን የሚጎድለን ነገር አይኖርም፡፡ ፍቅር ከሌለን ግን አለን የምንለው ብዙ ነገር ሁሉ የኛ አይደለም – በዪና ቀማኛ ይታዘዝበታልና፡፡ መደማመጥንና መግባባትን ያድለን፤ ሰላም፡፡

ከነፃነት ዘለቀ (nzeleke35@gmail.com)

No comments:

Post a Comment

wanted officials