Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, December 25, 2016

በምስራቅ አፍሪካ ለምግብ እርዳታ ከተጋለጡት ግማሽ ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ተመድ ገለጸ


ኢሳት 
ኢትዮጵያን ጨምሮ በጎረቤት ሶማሊያና ኬንያ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡ ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ።
በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ወራቶች በሃገሪቱ ያለው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ ሊሄድ የሚችል በመሆኑን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስፍሯል።
በተለይ በኢትዮጵያ ከአንድ አመት በፊት ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ ዕልባት ሳያገኝ በቅርቡ ያጋጠመው አዲስ የድርቅ ክስተት በሃገሪቱ ያለውን ችግር የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል ተሰግቷል።
በሶስት ሃገራት ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ የምግብ ዋጋ ንረትን ያስከትላል ተብሎ የተገመተ ሲሆን በአደጋው በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳትም እንደሚሞቱ የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያ አመልክቷል።
በአለም ምግብ ፕሮግራም የአስቸኳይ ጊዜ ማቋቋሚያ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ዶሚኒክ በርገን በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና፣ ኬንያ ያጋጠመው የዝናብ እጥረት ለደርቁ አደጋ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለችግሩ ተጋልጠው የሚገኙ ወደ ስድስት ሚሊዮን ሰዎችን ለመደገፍ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚያስፈልግ ሲሆን ከ20 የሚበልጡ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ለመደገፍ ጥረት እየደረጉ መሆኑ ታውቋል።
በሶማሊ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና፣ የደቡብ ክልሎች ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የመለክታል።
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድርቁ እየተባባሰ እንዳይሄድ አፋጣኝ ርብርብ ካላደረጉ የተረጂዎች ቁጥር በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
መንግስት በበኩሉ አደጋው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንዲጋለጡ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።
ችግሩ ዕልባት ባለማግኘቱ 9.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የቅርብ ክትትል የሚፈልጉ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials