Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, December 15, 2016

ከፋሲለደስ ጎንደር ለ ጀግናዋ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ለ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ



ከፋሲለደስ ጎንደር ለ ጀግናዋ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ለ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ


የእናት ነገር ሆኖብኝ ላለፉት አመታት ሰርክ ስለናቴ አስባለሁ፤ ስለሷ መንፈሰ ጠንካራ ማንነት ለመመስከር አንደበቴ ይደነቃቀፋል። የኔ የምንግዜም ጀግና፤ ልጅን ተንከባክቦ ማስተማርና ልጆቿን እንደሷ የሀገር ፍቅርን ከህዝብ መወገንን ፅናትን በአግባቡ ያስተማረችና የተወጣች እንደሆነች እኔ ልጇ ምስክር ነኝ።
እስርንና መከራን ለመቀበል መዘጋጀት ሞትን ከመጋፈጥ በላይ እንደሚከብድ ብትረዳም ለመቀበል ያልሰነፈች ብርቱ፤ የእናትነት ፍቅሯን ብቻ ሳይሆን የሷን ፅኑ የሀገር ፍቅርን ያጋባችብኝ፤ ዘመኗን ሙሉ ከበዳዮች ያልወገነች ናት እናቴ። ይህንን ማለቴ እናቴ ስለሆነች አይደለም ስለሷ ልፋትና ጥንካሬ መመስከርን የሷን እውነትና የአላማ ፅናት የሚያቁ ሰነፎች መድፍር ሲሳናቸው ባይ እንጂ።

በሀገሬ ሰማይ መታሰር፤ መንገላታትን ስቃይን ለህዝብ እንዲነገርና እንዲታወቅ አጨብጫቢና አዳማቂ ሊኖር እንደሚገባ አልጠፋኝም፤ ዋጋን ቀድመው የከፈሉ እየከፈሉ ያሉ ፊተኞች፣ ከሰልፉ በስተመጨረሻ በደረሱ ሲካዱ ሲዘነጉ ማየትም አይገርመኝም፤ ጥንካሬሽን መመስከር በሚያባንናቸው ልፋትና ጥረትሽ ተገቢውን ክብርና ቦታ ባይሰጠውም፤ ለኔም ሆነ ለጀግና ወዳዶቹ እስታሁንም የጠንካራ ሴትና እናት ምሳሌ እንደሆንሽ ቀጥለሻል። አንቺ ፅኑ ነሽ አቃለሁ፤ ለሀገር ፍቅር የመታመን ዕዳሻ እስርና ስቃይን እያስከፈለሽም ቢሆንም ጥንካሬሽ እያየሽ ባለው መከራም ሆነ መዘንጋት አይፈረካክስም።



እማዋያሽ በዚህ ጨቋኝ ስርዓት ስር ለመኖር ማንነቷ የተገነባት አስተዳደግ የበቀለችብት ጀግና አብቃይ ምድር እሺኝ አይላትም፡፡ እንደ ማንም እናት ሰቆቃን መቀበል ምርጫዋም አይደለም፤ በተመቸ ቤትና በሞቀ አልጋ ላይ ከልጆቿ ጋር ማሳለፍን አትጠላም፤ ከዚህ በላይ ግን ለሀገሯ የታመንችለት የእውነት እዳ ያስጨንቃታል። ከሴትነቷ በላይ የገዘፈዉ ልበ ሙሉነቷ ጭቆናን ለመቀበል እንቢኝ እንድትል አርጓታል፡፡
እናቴ በሰው በላዎች ከትግራይ በበቁል እንክርዶች መከራን ስትቀበል ክህደትን ደግሞ ከታሪክ ተሻሚ ታጋዮችነን ባይ ቢከፈላትም፤ እሷ ግን የገዛ አጋሮቻቸዉን አሳልፈው በመስጠት በሰው በላዎቹ ካስበሉ ክህደት መገለጫቸው ከሆኑ አንዳች አትጠብቅም፤ የእድሜ ልክ የእስር ቅጣትን ወንበዴን አገልጋይ ከሆነ ፍርድቤት ቢበየንባትም የመንፈስ ልዕልናዉ ግን መቼም አይፈርስም።

እናቴ ብትካጂም፤ ዘመን ሲፈቅድ አዋቂዎችና አስተዋዮች ወደ አደባባዩ ሲመጡ የካዱሽ ክህደታቸው ሲጋለጥ ውርደትን በህዝብ ፊት መጎናፀፋቸው አይቀርም፤ በእውነተኞቹ ዘንድ አንቺም በልፍታሽ ትወደሻለሽ፤ እነሱም በሀሰትና በክህደት በተሞላ ተግባራቸው ይሸማቀቃሉ፡፡

እናቴ በጣም ናፍቀሽኛል፤ በጣም፡፡ ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? ስቃይሽ የከፈልሽው መከራ.. አንቺ እኮ ሰው በሰው ላይ እንደውም ለሴት ክብር ባላው ማህበረሰብ ውስጥ እንደመብቀላችን፤ በእናትና በሴት ላይ ፈፅሞ ይደረጋል ተብሎ የማይታመን በደል ተፈፅሞብሻል፤ ከሁሉም ከሁሉም ልጅነቴን የምናፍቅባቸው ያለስስት የጠባሁት ጡቶችሽ በዱላ ተደብድበዋል እስታሁንም እያሰቃየሽ ነው። ህመም ነው ለኔ እልፍ በደል ቢፈፀምብሽም ከሌላው ስቃይሽ ይህንን ሳስብ ሆድ ይብሰኛል አቅም አልባነቴ ጎልቶ ይሰማኛል። ይህን ስቃይ ያቀመሱሽ ከምን ተፈጠሩ ብዬ ሁሉ እንድጠይቅ ያረገኛል።

እናቴ እወድሻለሁ!!

እጅግም ናፍቀሽኛል!!

አምላካ ካንቺ ጋር ይሁን ዘንድ ምኞቴ ነው ፤ የሰዉንማ እያየን ነው

ምንም አይረባሽም።

አምላክ ይሁንሽ እምዬ!!

በጣም ናፍቀሺኛል ፥ እወድሻለሁ!!

ልጅሽ ፋሲለደስ ጎንደር

No comments:

Post a Comment

wanted officials