Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, December 12, 2016

በቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት ቃጠሎ አደጋ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው 37 ተከሳሾች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸመባቸው ገለጹ







ኢሳት (ኅዳር 26 ፥ 2009)

በቅርቡ በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ ከነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው 37 ተከሳሾች በእርቃናቸው የመገረፍና የተለያዩ የሰብዓዊ ስቃዮች እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ለፍርድ ቤት አቤቱታን አቀረቡ።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሾቹ ላይ የቀረበውን አዲስ ክስ ለመስማት በተሰየመ ጊዜ ተከሳሾቹ የቀረበባቸው “የእሳት ቃጠሎ አስነስታችኋል” ክስ የውሸት ክስ ነው ሲሉ ለዳኞች መግለጻቸው ታውቋል።

አቤቱታቸውን ለችሎቱ ያቀረቡት እነዚሁ ተከሳሾች እየተደረሰብን ነው ካሉት ስቃይና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲጠበቁ በገለልተኛ አካል ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የክስ ሂደቱ መደመጥ በጀመረበት ዕለት የመናገር እድል ያገኙ አንድ ተከሳሽ በእርቃኑ መግረፉንና በግዳጅ ቃል እንዲሰጥ መደረጉን በምሬት ለችሎት አስረድቷል።

በህይወት ስለመቆየታችን ዋስትና የለንም ሲሉ የተናገሩት ተከሳሾቹ ሰውነታቸው ፎቶ እንዲነሳና የሚናገሩትም ለማስረጃነት ተቀርጾ እንዲቀመጥላቸው ለችሎቱ ጠይቀዋል።

37ቱ ተከሳሾች ከወራት በፊት በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ የነበረውን የእሳት አደጋ እንዲነሳ በማድረግ ከ20 ለሚበልጡ እስረኞች ሞት ምክንያት ናቸው የሚል ክስ ቀርቦባቸው ይገኛል።

ይሁንና ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ የውሸት መሆኑንና ነገም ሌላ ሴራ ተሰርቶ እነሱ ናቸው ሊባል እንደሚችል አስታውቀዋል።

በእስር ቤቱ የእሳት ቃጠሎ አደጋ በደረሰ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎችና እማኞች ከእሳቱ አደጋ በፊት በቃጠሎው ወቅት የጥይት ተኩስ ሲሰማ ማርፈዱን በወቅቱ ለኢሳት መገለጻቸው ይታወሳል።

በእለቱ ያለመሳሪያ በጥበቃ ላይ የነበረ አንድ የጸጥታ አባል የታጠቁ የእስር ቤቱ ሰራተኞች በእስረኞቹ ላይ ሲተኩስ መመልከቱንና በማግስቱ አርሱና ሌሎች ባልደርቦች ወደ እስር ቤቱ ቅጥር ግቢ እንዲገቡ ተደርጎ እንደነበር አዲስ ስታንዳርድ ለተሰኘ መጽሄት እማኝነቱን ሰጥቷል።

የሟች ቤተሰቦች በበኩላቸው የተረከቡት አስከሬን በጥይt መመታቱን ማረጋገጥ እንደቻሉ ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት ለእስረኞቹ ከእሳት አደጋ ለማምለጥ ሲሞክሩ በመጨናነቅና በመረጋገጥ ህይወታቸው አልፏል ሲሉ ማስተባበያን ሰጥተዋል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ 37ቱ እስረኞች ከግንቦት ሰባትና አልሸባብ ታጣቂ ቡድን ጋር በመመሳጠር በእስር ቤቱ አባላትን ሲመለምሉና የእሳት ቃጠሎ አደጋ እንዲደርስ አድርገዋል ሲል በቅርቡ ክሱን መስርቷል።

ይሁንና ተከሳሾቹ እሳቱን በምን ሁኔታ እንዳስነሱትና ተያያዥ መረጃዎችን በዝርዝር ከመግለፅ ተቆጥቧል።

የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከሙስና ጋር በተያያዘ ለእስር ተደርጎ የሚገኝ አንድ ዜጋው ከ37ቱ መካከል ውስጥ እንደሚገኝና የጤንነቱ ሁኔታ አሳስቦኛል ሲል ስጋቱን ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል። የተከሳሾቹን ጉዳይ መመልከት የጀመረው ፍርድ ቤት ለታህሳስ 14 ፥ 2009 አም ተለዋጭ ቀጠሮን መስጠቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials