Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, December 13, 2016

በኮንሶ ዞን በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያንያት ዛሬም ድረስ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳልሰፈነ ነዋሪዎች ገለጹ

54 ብሄር ብሄረሰቦች በአንድ ክልል እንዲጨፈለቁ በተደረገበት ደቡብ ክልል ነዋሪ የሆኑ የኮንሶ ማህበረሰብ አባላት ላለፈው አንድ አመት ያነሱት የመብት ጥያቄን ተንተርሶ የህወሃት አገዛዝ የሚፈጽምባቸው ግዲያ፤ እስርና እንግሊት ተጠናክሮ መቀጠሉንና በዚህም ምክንያት የማህበረሰቡ አባላት የኑሮና የሠላም ዋስትና አስከፊ ደረጃ  ላይ መድረሱን ነዋሪዎች  ገልጸዋል።
ህዝብ ያነሳውን የመብት ጥያቄ በሃይል ለመደፍጠጥ በዞኑ ውስጥ የተሠማሩ የመንግሥት ታጣቂዎች በሚወስዱት የሃይል እርምጃ አብዛኛው ነዋሪ እራሱን ከጥቃት ለማዳን ቤት ንብረቱን ሜዳ ላይ በትኖ  ወደ ጫካ እንደተሰደደ  እንደሚገኝ የገለጹ  እነዚህ ነዋሪዎች እንደሚሉት የመንግስት ታጣቂዎች በሚያደርሱባቸው ግፍና መከራ ምክንያት ተቃውሞ ያሰማሉ የሚባሉ ወንዶች  ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው በእስርና  በድብደባ  እየተሰቃዩ  እንደሚገኝ ፤ በተፈጸመባቸው ድብደባ የተነሳ የአልጋ  ቁራኛ የሆኑም ሰዎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ አስረድተዋል። የመንግሥት ታጣቂዎች እየወሰዱ ካለው የሃይል እርምጃ በተጨማሪም የክልሉ ማህበረሰብ የወፍጮ፤ የውሃና የህክምና የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኝ እንደተከለከለም ይነገራል። ህብረተሰቡን ለመጉዳት ሆን ተብሎ እንዲቋረጡ በተደረጉ አገልግሎቶች ምክንያት ከፍተኛ ችግር እየደረሰ እንደሚገኝ  በተለይም የወፍጮ ቤቶችን በማዘጋት አገልግሎት እንዳይሰጡ መደረጉ ህዝቡ ለምግብ ፍጆታ የሚሆነውን እህል ኋላ ቀር በሆነው ባህላዊ የድንጋይ ወፍጮ ለመጠቀም እንዲገደድ እያደረገው መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል። ህዝብ ለማሸማቀቅ በስፍራው የዘመቱ ታጣቂዎች እንዲቋረጥ ያደረጉትን አገልግሎቶች በአንዳንድ የገጠር መንደሮች ለመስጠት በሞከሩት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደተወሰደ በተለይም ወፍጮ ቤቶች ምንም አይነት አገልግሎት እንዳይሰጡ ወፍጮዎቹን ለማስነሳት የሚያገለግሉ  መዘወሪያና መሰል ክፍሎችን ፈትተው እንደወሰዱባቸው ነዋሪዎች በምሬት ገልጸዋል።
ሌላው ህዝቡ እንዳያገኝ እየተደረገ  ያለው ማህበራዊ አገልግሎት የንጹህ ውሃ አገልግሎት ሲሆን በቀበሌ ከተሞች አካባቢ የቧንቧ ውሃ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ተደርጎአል። በገጠር የሚገኙት በእጅ እየተዘወረ  አገልግሎት የሚሰጡ የጉድጓድ ውሃ  እንዳይጠቀሙ መከልከሉን የሚናገሩት ነዋሪዎች ህዝብ ምንጭ ወርዶ  ውሃ እንዳያገኝም መታገዱን አክለው ገልጸዋል። በዚህና  በሌሎች እየተፈጸሙባቸው ባሉ በርካታ  በደሎች በመማረር የመንግስት ሰራተኞችና  ሙሁራን ሳይቀሩ ወደ ጫካ  መሸፈታቸውን ነዋሪዎቹ ለትንሳዬ  ጨምረው ገልጸዋል።
የኮንሶ ተወላጆቹ አክለው እንደተናገሩት ምንም እንኳን  በዞኑ የሚገኝ አንድ በዞኑ መስተዳደር ሥር የሚተዳደር ሆስፒታል ለጊዜው  የሚሰጠውን አገልግሎት ያላቋረጠ ቢሆንም  የመንግስት የጤና  ተቋማት ግን ስራ  ካቆሙ መሰንበታቸውን ገልጸዋል። በወረዳው ያሉት 11 የጤና  ጣብያዎችና በገጠር የሚገኙት የጤና ኬላዎች ሙሉ በሙሉ ዝግ መሆናቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች ከየካቲት ወር 2008 ማለትም የኮንሶ ህዝብ ጥያቄውን አንግቦ አደባባይ ከወጣበት ጊዜ  ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ።
በኮንሶ ወረዳ  ከ164ፖሊሶች መካከል  11 ፖሊሶች ብቻ ስራቸውን እየሰሩ ሲሆን ሌሎች በርካቶች ትጥቅ  መፍታታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸ ዛሬ ድረስ ህዝብ መግደልና  ማሰሩ እንደቀጠለ ትንሳኤ  ያናገራቸው እነዚሁ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
በአካባቢው ህዝብ እርስ በእርስ እንዲጋደልና  እንዲጋጭ ሆን ተብሎ  እንደሚሰራ  የሚገልጹት ነዋሪዎች ይህም ህዝብን በህዝብ ላይ በማጋጨት የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ  አቅጣጫ  ለማስቀየር እንደሆነ  ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
እንደነዋሪዎቹ ገለጻ  የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ በርካታ የኮንሶ ተወላጆች በአሁን ወቅት በየእስር ቤቱና  በየማጎሪያው ስፍራ በውሃ  ጥምና  በረሃብ እንዲሁም በሌሎች ኢሰብአዊ የእስረኛ  አያያዝ እየተሰቃዩ  መሆናቸውን ያስረዳሉ። ለዚህም  ከ250 በላይ የሚደርሱ ዜጎች በፖሊስ ጣቢያ  ታስረው የሚገኙ ሲሆን  ዞኑ ውስጥ በሚገኘው ኮሌጅ ግቢ ከ400 በላይ ታሳሪዎች እንዲሁም በሌሎች በርካታ  ስፍራዎች ደግሞ ከ1000 በላይ የሚደርሱ የኮንሶ  ተወላጆች የመንግስት ሰራተኞች ምሁራንና ተማሪዎች ታስረው እንደሚገኙ ነዋሪዎች ለትንሳኤ  አረጋግጠዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials