በኢትዮጵያ አጋጥሟል የተባለን የኢኮኖሚ መዳከም ተከትሎ የሃገሪቱ የዋጋ ግሽበት በተያዘው ወር ከአምስት ነጥብ ስድስት ወደሰባት በመቶ ከፍ ማለቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሃሙስ አስታወቀ።
የአለም ባንክ ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለው የውጭ ንግድ ገቢ መቀነስና የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማሽቆልቆል በኢትዮጵያ ዋጋ ግሽበት ሊያስከትል ይችላል ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
ባንኩ ሲሰጥ የቆየውን ትንበያ ተከትሎ የሃገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ ምክንያት የዋጋ ግሽበቱ ከፍ ሊል መቻሉን በሪፖርቱ አመልክቷል።
ባለፈው ወር 3.4 ተመዝግቦ የነበረው የምግብ የዋጋ ግሽበት በተያዘው ወር ወደ 6.1 ማሻቀቡም ታውቋል።
በሃገሪቱ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ሰሞኑን ሪፖርቱን ያወጣው የአለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግስት አፋጣኝ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ካላደረገ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ሊዳከም እንደሚችል አሳስቧል።
በተያዘው በጀት አመት መንግስት ይመዘገባል ብሎ የነበረው የ11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ስምንት በመቶ አካባቢ የቀነሰ ሲሆን፣ በሃገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ውጥረትና የውጭ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆል በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጫና ማሳደሩን የአለም ባንክ ይገልጻል።
የመንግስት ባለስልጣናት በአዲሱ የፈረንጆች አመት ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ በ11.4 በመቶ እንደሚያድግ ቢገልጹም፣ የአለም አቀፉ ሞኒተርኒንግ ፈንድ (IMF) ዕድገቱ በአምስት በመቶ አካባቢ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ተንብዮአል።
ኢትዮጵያ አጋጥሟት ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ንግድ ገቢ ችግር ለመቅረፍ ከፖሊሲ ማሻሻያዎች በተጨማሪ የብር የመግዛት አቅም መቀነስ እንዳለበት የአለም ባንክ አሳስቧል።
ይሁንና የብሄራዊ ባንክ ሃላፊዎች ባንኩ ያቀረበው ሃሳብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል በሚል ጥያቄውን እንደማይቀበሉት ምላሽ መስጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ከ36 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ለኢኮኖሚ እድገቱ ማነቆ ሆኖ መገኘቱንና ሃገሪቱ ያጋጠማት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈታ እንደማይችል በመግለጽ ላይ ናቸው
No comments:
Post a Comment