Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, December 19, 2016

የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር፤ የበሔራዊ አጀንዳ እጦት ነው። (ክፍል አንድ) በጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ አመጽ ሲነሳ ይህ የመጀመርያው አይደለም። በተደጋጋሚ የተነሱ ሕዝባዊ ቁጣዎች፤ በስርዓቱ ጨካኝ እርምጃ፤ ቢዳፈኑም ሁሌም ውስጥ ለውስጥ እየተንቦገበጉና፤ እየተብላሉ፤ ጊዜና አጋጣሚ ጠብቀው መነሳታቸው አልቀረም። ዛሬም በኦሮምያ፤ በአማራና፤ በቆንሶ የምናየው ይህንኑ ነው። ሕዝቡ በሶቱን በአደባባይ ይገልጻል ውጭ ያለው የሃገር ተቆርቋሪው ዜጋ፤ የወገኖቹን ችግር ከአድማስ እስከድማስ ያስተጋባል። ምንም ህሊና በሌላቸው ግለሰቦችና፤ የወሮበላ ቡድን የሚመራው አገዛዝም፤ ለሁሉ ነገር መልሱ እስራት፤ ድብደባና፤ ግድያ በመሆኑ፤ ሕዝቡን ማሰቃየትና፤ የሃገሪቱን ብርቅዬ ዜጎች ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሎበታል። ተው የሚለው ያጣው ይህ ግፈኛ አገዛዝ፤ ላለፉት 25 ዓመታት፤ ይህን የግፍ አገዛዙን ሊቀጥል የቻለው፤ በጥንካሬው ሳይሆን፤ በተቃዋሚው ደካማነት መሆኑ በተደጋጋሚ ቢነገርም፤ መልዕክቱ አድማጭ ያገኘ አይመስልም። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ከአመታት በፊት “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚለው መልእክታቸው ዛሬም ወቅታዊና ያልታሰበበት ጥያቄ ነው።
ደግመን ደጋግመን የምናየው ነገር፤ ሃገራችን ያጣቸው፤ በበቂ ሁኔታ ተደራጅቶ፤ ብሔራዊ አጀንዳ ቀርፆ ትግሉን አቅጣጫ የሚያሲዝ የፖለቲካ ሃይል ነው። በጊዜያዊ አጀንዳ፤ በግዚያዊ “ድል” የሰው ሃይልና ገንዘብ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ የብርቅዬ ወጣቶች ሕይወት ሲጠፋ እያየን ነው። በየጥጉ ጮዋሂው በዝቶ፤ አድማጭ ለመጥፋቱ፤ የማህበራዊ ሚድያዎች ምስክር ናቸው። ላለፉት 42 ዓመታት፤ ወያኔ በሃገራችን የተከለውን የመርዝ ችግኝ ለመንቀል ከፍተኛ ትግል ቢደረግና ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢከፈልም፤ የትግሬ ብሔርተኝነት፤ የአማራ ብሔርተኝነት፤ የኦሮሞ ብሔረተኝነት፤ ወዘተ፤ ከሁሉም በላይ ደግም ጽንፈኛ አመለካከቶች እያደጉና እያበቡ ሲመጡ አየን እንጂ፤ መስዋዕትነቱ የምንፈልገውን ፍሬ እያፈራ አይደለም። ከዚህም አልፎ በኢትዮጵያዊነት ስም፤ ዘረኝነት በአደባባይ ሲደሰኮር፤ “እረ ተው የሚለው ሰው ቁጥርም” ማነሱን የምንመስክርበት አደገኛ ወቅት ላይ ደረስናል።
የ1966 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) የፈነዳው አብዮት፤ አስተባባሪና መሪ ድርጅት በመጣቱ፤ ወታደራዊ መንግስት፤ ስልጣኑን ዘርፎ ለ17 ዓመታት ሲያስረን፤ ሲደበድበን፤ ሲያሳድደንና ሲገድለን ኖረ። በስንት ውድ ኢትዮጵያውያን ሕይወት መስዋእትነት፤ ፋሽስታዊው ደርግነ በማስወገድ የተገኘው ሕዝባዊ ድልም፤ ብሔራዊ አጀንዳና፤ ኢትዮጵያዊ ራእያ ባጡ ጥቂት ወሮበሎች ተነጥቆ፤ ላለፉት 25 ዓመታት ስንታሰር፤ ስንደበደብ፤ ስንሳደድና፤ ስንገደል ኖረናል፤ አሁንም እየሞትን ነው። ይህ ከታሪክ ባለመማራችን የከፈልነው ከፍተኛ ዋጋ ነው። ዛሬም ትምህርት አልወሰድንም፤ ዛሬም ብሔራዊ አጀንዳ ቀርጾ ሕዝቡን ከዳር እስከዳር የሚያነቃንቅ ሃይል አጥተን፤ በምናያቸው “የአካባቢ ሕዝባዊ አመጾች” እና ንቅናቄዎች እየተኩራራን፤ ‘ወያኔ ሊወድቅ ነው አለቀለት’ እያልን በውሸት እራሳችንን እናሞክሻለን። በእኛው ስህተት ትግሉ ረጅምና መራራ ሆንዋል። ወያኔ ጠንካራ ሆኖ አያውቅም፤ ፈተናችን ጠንካራ ተፎካካሪ አለማግኘቱ ነው። ወደ ኋላ ተመልሼ፤ በተለይ ተቃዋሚው ስለተጎናጸፋቸው ድሎች፤ ስለፈተናውና ስለችግሮቹ ብናገር፤ ስድስት መጽሐፍት ይወጣዋል። ዛሬ ካለው ነገር ልነሳና፤ እየተጓዝን ያለንበትን አቅጣጫ፤ እንዲሁም ስር ነቀል ለውጥ ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብን ያለችኝን ላካፍል።
ከብዙ አቅጣጫ የሚነሳው ጥያቄ፤ በተለይ የትግራይ ሕዝብ ለምን ዝም አለ የሚል ነው። ለጥያቄው መልስ የሚሰጡት ጥያቄውን ያነሱት ሰዎች በመሆናቸው፤ ለእነሱ ምቹ የሆነው መልስ፤ የትግራይ ሕዝብ “የማይነሳው”፤ ከአገዛዙ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው የሚል ነው። ከዚህ ድምዳሜ በመነሳት፤ ይህንኑ አመለካከታቸውን፤ የተቀረው ሕዝብ ላይ ለመጫን፤ ባገኙት አጋጣሚና፤ በተለይም በየማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ ይለጥፋሉ። ሌላው ቀርቶ “በጋዜጠኝነት ሙያቸው አንቱ ተባልን” ብለው የሚገምቱ ግለሰቦች ሳይቀሩ፤ ሳሞራ “ትግሬና ወያኔ አንድ ነው” ብሏልና ከፈለጉ ትግራይን ይዘው ይሂዱ በሚል አሳሳች አመለካከት፤ ወያኔ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንድንሄድ ግፊት ሲያደርጉ፤ ‘ተው እንዲህ አይደለም’ የሚላቸው እንኳን አላየሁም። “ትግሬ ዝም አለ” እያሉ ሳንባቸው እስኪድክም የሚጮሁ ዜጎች ግን፤ አዲስ አበባ ለምን ዝም አለ፤ ወላይታ፤ ጉራጌ፤ሽዋ፤ ወሎ፤ ወዘተ ለምን ዝም አለ ሲሉ አንሰማቸውም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት፤ የትግራይ ሕዝብ፤ ይህንን ስርአት ለመጣል፤ ከሌላው ሕዝብ የተለየ ምንም ሃላፊነት የለበትም። ወያኔ ለሚፈጽመው በደልና ግፍ ተጠያቂው የወያኔ አመራር፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ ናቸው። ሳሞራ “ትግሬና ወያኔ አንድ ነው” ብሏል፤ ስለዚህ ሳሞራ ልክ ነው የሚሉን ሰዎች፤ ብአዴን የአማራን ሕዝብ እወክላለሁ ስላለ፤ ብአዴን የአማራን ሕዝብ ይወክላል ብለው ያምናሉ ወይ ብለን ለመጠየቅም እንገደዳለን። አቶ ተክለሚካኤል አበበ የተባሉ ጽሃፍ “የኛ ነገር፤ ትግሬን መነጠል፤ ሐሳዊ-ኢትዮጵያዊነት ነው” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሁፋቸው “ትናንትናና ዛሬ ሕወሀት/ኢህአዴግ፤ ነጋሪት ጎስሞ፤ አዋጅ ነግሮ፤ የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የፈጠረ አማራ ነው ሲል፤ ያንን ስንቃወም የኖርን ሁላ፤ አሁን ደግሞ መልሰን የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ፈጣሪ ትግሬ ነው ስንል፤ ለሕወሀት/ኢህአዴግ የአመታት ዘመቻ እጅ ብቻ ሳይሆን፤ እግርም እየሰጠን ይመስላል፡፡” ያሉት፤ ለሁላችንም የሕሊና ደውል ሊሆን ይገባዋል።
ለምን ይህ ወይም ያኛው ብሔር/ብሔረሰብ አልተነሳም ከማለታችን በፊት፤ በኦሮምያና በአማራ ክልል የተነሱት ንቅናቄዎች ጥያቄያቸው ምንድ ነው ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። በአማራ ክልል፤ በወልቃይትና ጠገዴ ማንነት ጥያቄ ዙርያ ንቅናቄ ከመንሳቱ በፊት፤ በኦሮምያ አካባቢ የአዲስ አበባን መስፋፋት አስመልክቶ በተነሳው ተቃውሞ የተጀመረው ንቅናቄ ላይ፤ በዙዎቸ “በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፍ ሃይሎች” ጥያቄውን ሲያጣጥሉና “ጠባብነት” ነው፤ የአዲስ አበባ መስፋፋት ምን ችግር አለው ሲሉ አንብበናል፤ ሰምተናል። በ2016 መጀመርያዊች ላይ በአማራ ክልል ንቅናቄው ሲነሳና እያደገ ሲመጣ ነው፤ በኦሮምያና በአማራ ክልል ያለው ንቅናቄ እንደ “የጋራ ትግል” እየተቆጠረ የመጣው። ዛሬ በኮንሶ ያለውንም ንቅናቄ ስናይ፤ ንቅናቄው የተነሳው ከኮንሶ መሬት ጋር በተያያዘ ነው። ይህም በመሆኑም ነው፤ ከነዚህ ከሶስት ክልሎች ውጭ፤ በተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች ሕዝባዊ ንቅናቄ የማናየው። ብዙዎች፤ በተለይ “ወያኔ አለቀለት” በሚል ስሜት ውስጥ ያሉ ሰዎች ያልጠየቁት እና ያላዩት ነገር፤ የወልቃይትና ጠገዴ ጥያቄ ቢመለስ፤ የትግሉ አቅጣጫ ምን ይሆናል? የኦሮምያ ክልል ጥያቄስ ቢመለስ ትግሉ ወዴት ሊሄድ ይችላል? የሚለውን ነው። ነውጡ በመነሳቱ ብቻ እርካታ አግኝተው፤ ሊመለሱ የሚገባቸውን ጥያቄዎች የዘነጉ በዙዊች ናቸው። ለመሆኑ፤ የወያኔ ጥንካሬውና ድክመቱ ምንድነው? የተቃዋሚውስ ድክመትና ጥንካሬ ምንድነው? ወታደሩ፤ ፖሊሱ፤ አጠቃላይ የፀጥታው መዋቅር በወያኔ ቁጥጥር ስር ሆኖ፤የተቃዋሚው ጎራ፤ ሕዝቡን ከጥግ እስከጥግ ሳያስተባብር፤ ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ ይችላል ወይ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ካለ፤ መልሱን እስካሁን ያስነበቡን ስዎች ያሉ አይመስለኝም።
ወያኔና ሻዕብያ፤ ከዚያድ ባሬ ከወሰዱት ተመክሮ፤ “አማራ” ላይ ያነጣጠረ ትግል አድርገው ነው “ስኬታማ የሆኑት” እኛም ትግሉን በፀረ “ትግራይ” ላይ ካደረግን “ስኬታማ” እንሆናለን የሚል አመለካከት ካለ፤ ትግሉ፤ ሕዝቡ ወደ ሚፈልገው ትክክለኛ አቅጣጫና፤ የምንፈልገውን ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት ለመግንባት ወደሚያስችል መንገድ የሚሄድ አይመስለኝም። ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ትግል ያህል፤ ብሔራው አጀንዳውን “ፀረ ትግራይ” ለማድረግ በትጋት የሚሰሩ ጽንፈኞች ለመኖራቸው ሶሻል ሚድያው በግልጽ ያሳብቃል። “ትግራይ ሁሉ ቆዳው ሲፋቅ ወያኔ ነው” የሚለው ደካማና አደገኛ አመለካከት፤ መለስ ዜናዊ ባንድ ወቅት “የኦሕዴድ አባል ሁሉ ቆዳው ቢፋቅ ኦነግ ነው” ከሚለው እኩይና ደካማ አስተሳሰብ የተለየ አይደለም። ማንም ሕዝብ፤ የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ፤ሌላው ሕዝብ ሲጎዳ ደስተኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ ሕሊናችን በጠባብነት እንዲዳክር መፍቀድ ነው። ትግሬ ሁሉ አመለካከቱ አንድ ነው ካልን፤ አማራ ሁሉ ኦሮሞ ሁሉ ወዘተ አመለካከቱ አንድ ነው ብለን እናምናለን ማለት ነው፤ ይህን ከተቀበልን ደግሞ ስለነዚሀ ብሔሮችም የሚባለውን መጥፎ ነገር ሁሉ እንቀበላለን ማለት ነው። ይህን ካመንን ደግሞ፤ ‘ነጭ ሁሉ አዋቂና ብልህ ነው፤ ጥቁር ሁሉ ደንቆሮና ወንጀለኛ ነው” የሚለውንም መላ ምት የምንቀበል ልንሆን ነው ማለት ነው። የሰው ልጅ “በዘሩ ያስባል” የሚል አመለካከት የለኝም። በነገሬ ላይ “የትግራይን ሕዝብ” በሌላው ሕዝብ ለማሰጠላትና፤ “እኛና እነሱ” የሚለውን ጎራ ለማስፋፋት፤ የወያኔ አባላት የሚሰሩበት ስትራተጂ ነው። የትግራይ ክልል ተጠቅሟል ወይስ አልተጠቀመም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ከመሆን አያልፍም። በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ፈቃድ ሽዋ ቀና በቅርቡ “የትግራይና የህወሀት የበላይነት ጥያቄ – ዕውነቱ ውሸቱና ማስፈራሪያው” በሚል ርዕስ ባሰነበበን ጽሁፍ በሚገባ ገልጾታል። የትግራይ ክልል ተጠቃሚ ሆንዋል፤ ፋብሪካዎች መከፈታቸው፤ የአግልግሎት ሰጭ እንዱስትሪዎች መስፋፋታቸው፤ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፤ የዘመናዊ እርሻ መስፋፋት፤ እነዚህ ሁሉ ለትግራይ ክልል የስራ እድል ፈጥረዋል። እነ ኤፈርት፤ እና ትልማ፤ የትግራይን ክልል ለመጥቀም እየሰሩ ነው፤ እነዚህ ድርጅቶች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከማንኛውም የንግድ ተቋማት በበለጠ፤ ከባንኮች ገንዘብ የማግኘት እድል አግኝተዋል፤ ያለቀረጥ እቃ ከውጭ ያስገባሉ፤ ተገቢውን ቫትም ሆነ የገቢ ታክስ አይከፍሉም፤ ይሁ ሁሉ ለትግራይ ክልል ትልቅ ጥቅም ነው። የትግራይ ክልል አልተጠቀመም ብዬም አልከራከርም። ግን የትግራይ ሕዝብ ለዚህ ተጠያቂ ነው ወይ? ፋብሪካ ሲከፈት አትክፈቱ ማለት አለበት? መንገድ ሲሰራ አትስሩ ማለት አለበት? ይህንን እያንዳንዱ ሰው ይመልሰው። የትግራይ ክልል ተጠቀመ ማለት፤ ትግሬ ሁሉ ተጠቀመ ማለት እንዳልሆን ይሰመርልኝ፤ ይህ ቢሆን ኖሮ፤ አዲስ አበባ በትግራይ ችግረኞች ተጥለቅልቆ ባላየን ነበር። ይህ ቢሆን ኖሮ መቀሌ “አፓርታይድ” ተብሎ የተሰየመ መንደር ባላስተናገደች።
ቀጣዩ ጥያቄ የትግራይ ክልል ከሌላው ክልል በተሻለ መልኩ ነጻነት አለው ወይ? ሕዝቡስ በሰላም ወጥቶ የመግባት እድሉ ከሌላው ክልል የተሻለ ነው ወይ? የሚል ነው። በእኔ እምነት ለዚህ መልሱ የተሻለ አይደለም የሚል ነው። እንደውም የትግራይ ክልል ከሌላው በበለጠ መብቱ የተረገጠና፤ ነፃነቱን የተነፈገ ለመሆኑ ብዙ መረጃዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ ትግራይ ውስጥ የግል ጋዜጦች እንኳን አይገቡም። በትግራይ ውስጥ ምንም ዓይነት ተቃዋሚ እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድለትም። በግንቦት 1991 (አውሮፓ አቆጣጠር) ወያኔ በትረ መንግስቱን ሲጨብጥ፤ ሃገር ውስጥ “በሕጋዊ መንገድ” ለመንቀሳቀስ ከገቡት ድርጅቶች መካከል፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ህብረት (ኢዲህ) አንዱ ነበር። ለዑል መንገሻ በትግራይ ሕዝብ የተወደዱና የተከበሩ በመሆናቸው፤ ትግራይ ክልል በዙ ደጋፊ አፍርተው ነበር፤ ይህ ያሰደነገጠው ወያኔ በርካታ የኢዲህን አባላት በማሰር፤ በማፈን፤ ንብረት በማቃጠል፤ የድርጅቱን ደብዛ ከትግራይ እንዲጠፋ አድርጓል። በርካታ ሕብረ ብሔር ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ባደረጉት ሙከራ፤ በስርዓቱ ያጋጠማቸውን ችግር በተደጋጋሚ መግለጫ አውጥተውበታል። ዛሬም አረና ትግራይ የተባለው ድርጅት ምን አይነት ማነቆ ውስጥ እንዳለ የምንሰማውና የምናየው ነው። ትግሬዎች ወያኔ ላይ ስላላቸው ተቃውሞ ሲነሳ፤ የማይነሳው፤ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን) ስለሚባለው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ከግንቦት ሰባት ጋር ግንባር ፈጥሮ ወያኔን እየታገለ እንደሆነ በቻ ሳይሆን፤ ወያኔን በትጥቅ ትግል ከሚፋለሙት በብዛትም በትጥቅም የበለጠ መሆኑን በተደጋጋሚ ተገልጽዋል፤ ታድያ የእነዚህ የትግሬ ታጋዮች መስዋእትነት አይቆጠርም? ሞላ አስገዶም የተባለው የድርጅቱ መሪ ለወያኔ እጁን ሲሰጥ፤ “ዘር ከልጓም ይስባል” ተብሎ ሲተች፤ በእኔ እምነት፤ ከሞላ የበለጠ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ጉዳት ያደረሰውና አሁንም በማደርሰ ላይ ያለው ሰለሞን ተካልኝ የተባለ ሙዚቀኛ፤ በዘር ልጓሙ እንዴት አልተመዘነም? ዛሬ ወያኔን የሚደግፍ ሁሉ ትግሬ ብቻ ነው ካልን፤ እነ አባዱላ፤ እነ ተፈራ ዋልዋ፤ እነ ሙክታር፤ ወዘተ በምን የዘር ሂሳብ ነው የሚሰሉት?
በእኔ እምነት ትልቁ ችግር ብሔራዊ አጀንዳ አለመኖሩና ሕዝቡን በብሔራዊ አጀንዳ ስር እንዲነሳ አለማድረጉ ነው። ከጥቂት ጊዜያት በፊት፤ የአዲስ አበባን ህንጻ ያንቀጠቀጠው የሙስሊሙ ማህበረሰብ የት ገባ? ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል። ችግራችን፤ አፈንጫችን ሲመታ ዓይናችን አለማልቀሱ ብቻ ሳይሆን፤ ልባችን አለመድማቱም ጭምር ነው። ከ 1993 እሰክ 1996 (አውሮፓ አቆጣጠር) በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ሬድዮ ላይ እሰራ በነበረበት ጊዜ፤ በዋሽንግተን አካባቢ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላትን የማነጋገር እድል አጋጥሞኝ ነበር። በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የስብአዊ መብት ጥሰት የነበረበት ወቅት ነበር፤ እነዚህን መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም እንዲወስዱ ስንጠይቅ፤ የሚነግሩን ገለልተኛ እንደሆኑ ነበር። እንዳውም አንዳንዶቹ፤ ከወያኔ ጋር በቁርኝት ይሰሩ ነበር። የሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደ አንድ ማህበረሰብ የተነቃነቀው፤ ወያኔ በቀጥታ በሙስሊሙ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት በፈጸመው ወንጀል ነው። ይህን የማነሳው ጣት ለመጠቆም አይደለም፤ ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ስለማይ ነው። አንዱ ሲነካ ሌላው እንዲነሳ፤ የአንዱ ጉዳት የእኔም ጉዳት ነው እንድንል፤ የሚያስተባብር ሃይል የለንም። በግንቦት 1997 የአዲስ አበባ ነጋዴዎች አድማ አድርገው በነበረበት ጊዜ (በወቅቱ አዲስ አበባ ነበርኩ)፤ እኔና ጓደኞቼ ባለታክሲዎቹም እንዲያድሙ ለማስተባበር ስንሞከር፤ የሰጡን መልስ፤ “እኛ ስናድም ማን አገዘን?” የሚል ነበር። ያኔ የነበረው “የብሔራዊ አጀንዳ እጦት” ዛሬም ድረስ መቀጠሉ፤ ‘ለዚህ ተግባር ብቃት ያላቸው የተቃዋሞ መሪዎች አሉ ወይ’ ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ትልቁ ችግር፤ የአማራው ጥቃት፤ የኦሮሞ ጥቃት፤ የክርስቲያኑ መጠቃት፤ የሙስሊሙ መጠቃት ሆኖ እንዲሰማን የሰራነው ስራ የለም። ሁሉም “ለየእራሱ” ነው የሚጮኸው። የኦሮም ብሔራዊ ኮንግረስና ሰማያዊ ፓርቲ አብረን መስራት ጀምረን ካሉ ወራቶች አልፈዋል። ዛሬ ግን መግለጫ ከመስጠት ባሻገር የፈየዱት ነገር ምን እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም። ውጭ የምንገኘውም፤ ያለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ብሔራዊ መልክ እንዲይዝ፤ ሃገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሃሳብም ይሁን በገንዘብ ለማገዝ በቂ እርዳታ እያደረግን አይደለም። እንዲተባበሩም ለማድረግ፤ መጀመርያ እኛ እራሳችን እዚህ መተባበር አለብን። እዚህም ቢሆን ላለፉት 25 ዓመታት በዲፕሎማሲው በኩል ምንም ስራ አልሰራንም ማለት ይቻላል። ያለንን የፖለቲካ ካፒታል ልንመነዝረውና ጥቅም ላይ ልናውለው አልቻልንም። ብዙ ጊዜ ችግራችን፤ ከሃገር ፍቅር የበለጠ፤ የድርጅትና የቡድን ፍቅር ማየሉ ይመስለኛል። ዛሬም “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” ማለት ግድ ይላል። በተሰባበረ አጀንዳ ወጣቱ አይለቅ፤ ብሔራዊ አጀንዳ ሊኖረን ይገባል፤ ዘረኝነት ከየትም አቅጣጫ ይምጣ ሊወገዝ ይገባል። “ጥሩ አማራ የሞተ አማራ ብቻ ነው” የሚለው የመከነ ወያኔያዊ አስተሳሰብ አደገኛና በታኝ ነው ብለን ካመንን “ጥሩ ትግሬ የሞተ ትግሬ ብቻ ነው” የሚለውን የመከነና የደከመ አስተሳሰብ ባንድ ድምጽ ልናወግዝ ይገባል። እንዲህ ዓይነት የተሳሳቱና ከፋፋይ አስተሳሰቦች፤ ትግሉ በሔራዊ አቅጣጫ እንዳይዝ የሚያደርጉና፤ ሃገራችንን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ነው። በዙ ጊዜያችንን የምናባክነው፤ ሃገር ውስጥ ያለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በማራገብ ነው። አስትዋጾአችን ከዚህ የተሻለ መሆን አለበት፤ ትግሉ ብሔራዊ አቅጣጫ እንዲይዝ፤ ብሔራዊ አጀንዳና እስትራቴጂ ለመቀየስ መስራት ይኖርብናል። አለዚያ፤ ልክ እንደ 2005 ምርጫና ነውጥ፤ ወያኔ ትግሉን ለጊዜውም ቢሆን ሊያዳፍነው ይችላል። ይህ ሁላችንንም እንቅልፍ ሊነሳ የሚገባ ነገር ነው። በቅርቡ በወያኔ፤ ጎንደር ውስጥ የታፈነችው ወጣት እንዳለችው፤ “እነሱ ሃገር ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሰሩ፤ እኛ ሃገር ለማዳን ሌት ተቀን መስራት እንዴት ያቅተናል?”

No comments:

Post a Comment

wanted officials