By SEBAT KILO (ዳኝነት መኮንን)
ጥቅምት 2002 ዓ.ም፤ ከፍተኛ በራስ መተማመን የሚታይበት የ23 ዓመት ወጣት ኦሮሞ ብሔረተኛ፤ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን የፖለቲካ ንቅናቄ ከዐርባ ዓመታት በላይ የመራውን እና አቅሙ ተዳክሞ ሳይቀር መንፈሳዊ ልዕናውን ያላጣውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን በግሩም ቋንቋ እና ባልተለመደ ቀጥተኝነት፣ ያለ ምኅረት እና ያለ ማመንታት በመተቸት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ራሱን አስተዋወቀ፤ ወጣቱ የድርጅቱን የውስጥ ክፍፍል፣ የአመራር ችግር፣ የፖለቲካ እና የወታደራዊ ድል ማጣት ከደረደረ በኋላ የግንባሩን መሞት አወጀ፤ የኦሮሞ ብሔረተኝነትን ተቋማዊ ንጉሥ አንገቱን ቀላው። ጽሑፉ በኦሮሞ ብሔረተኞች ዘንድ ብቻ ሳይኾን በፓን ኢትዮጵያውያንም ዘንድ ጥዝታ ፈጠረ፤ አንጫጫ። ታዋቂው ፈላስፋ መሳይ ከበደ ለጽሑፉ መልስ ሰጡ። ወጣቱ ጊዜ ሳያባክን ምላሹን ወረወረ። ክርክሩ የኢትዮጵያውያን “ኢንተርኔት” መነጋገሪያ ኾነ፤ የትዊተር አራዶች እንደሚሉት “ኢንተርኔቱን ሰበረው”። ጃዋር ሲራጅ መሐመድ ብጉር ከማውጣቱ በፊት ፖለቲካን ሲያደቅ የኖረ ቢኾንም በዚህ ጽሑፉ እና ከመሳይ ከበደ ጋራ ባደረገው ክርክር ያደባባይ ሰው ኾኖ ተወለደ። ነገር ግን ከዚህም በላይ ጃዋርን ‘ያፈመመው’ ምርጫ 2002ን በሚመለከት በአልጀዚራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቱባ ሰውዬ አቶ በረከት ስምዖን በተቃራኒ ኾኖ ባደረገው ክርክር ባሳየው ብቃት ነው። የመንግሥት ደጋፊዎች ሳይቀሩ የ24 ዓመቱ ጎረምሳ አቶ በረከትን በዝረራ እንደረታ ላለመመስከር አልተቻላቸውም።
ጃዋር መሐመድን ለመጀመርያ ጊዜ የተዋወቅኹት በዚያ ወቅት ነበር። ጃዋር ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በምኖርበት አገር ቋንቋ የአዲሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ “ገን ስሊንገር” ኾኖ ነበር፤ ትኩስ፣ ፈጣን፣ እንደ ታታሪ ንብ ብዝ ብዝ የሚል እና በየቦታው በሹክሹክታ ጥያቄዎች የሚነሱበትም ነበር። ጠርጣራ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኞች፦ “የዚህ ልጅ ፍላጎት ምንድነው?” ሲሉ . . . . ፓን ኢትዮጵያኒስቶች፦ በተስፋ “ልጁ የኦሮሞ ኦባማ ሊኾን ይችላል?” ሲሉ . . . የኦሮሞ ብሔረተኞች ደግሞ፦ “ጃዋር ከጠላቶቻችን ጋር ብዙ እያመቻመቸ ነውን?” ይሉ ነበር . . . ሁሉም በየቦታው መላምት ይወረውራል። ጃዋርን ብዙ ጊዜ በስልክ እና በግንባር አግኝቼ ተጨዋውተናል። ግን እነዚህ መስተጋብሮች “ጃዋር ጓደኛዬ ነው” ከማለት ያለፈ ስለ ፖለቲካዊ ፍላጎቱ ከተንሾካሿኪዎቹ የተሻለ እውቀት አልሰጠኝም። ይኹንና ይህን እመሰክራለሁ፦ ጃዋር ከሌሎች ዲሲ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች የተለየ ተክለ ሰብእና ነበረው። ከብዙ ቡድኖች ጋር ለመነጋገር እና ለማድመጥ ዝግጁ ነበር። የኦሮሞ ብሔረተኛ መኾኑ ጥርጥር ባይኖረውም፤ በዚህ አረፋ ውስጥ ራሱን የደፈቀ አልነበረም።
ከዚያ ጃዋር ዲሲን ለቆ መኖሪያውን በሜኔሶታ እና ኒውዮርክ እያፈራረቀ አደረገ። የግራጁዌት ስኩል ፍጋትን እና ጠንካራ የፖለቲካ እንቅስቃሴን አጣመረ። እንደ ብዙ ኢትዮጵያውያን ይኼኛውን ጃዋር የተከታተልኹት ከሩቅ በሶሻል ሚዲያ ነው። አንዳንድ ማኅበራዊ ሳይንቲስቶች ዲጂታል ዱዋሊዝም የተባለ ሐሳብን ያስተጋባሉ። በዚህ ሐሳብ መሠረት የሰዎች የኦንላይን እና የኦፍላይን ተክለ ሰብእና የተለያየ ሊኾን ይችላል፤ አንዳንዶቻችን በዲጂታል ዓለም ያዙኝ ልቀቁኝ ባይ፤ ሙርጃ ለስላሽ ጽንፈኞች (abrasive) ነን፤ ኦፍላይን ባለ መስተጋብር ግን በተቃራኒው ለስላሶች እና አመቻማቾች እንኾናለን። ምሁራኑ ለዚህ ዱዋሊዝም የተለያዩ መንስኤዎችን ያቀርባሉ። መንስዔዎቹ ምንም ይኹኑ ዲጂታል ተክለ ሰብዕናን “በክህደት ባይኾንም በጥርጣሬ መመልከት ይበጃል” ብዬ በሶሻል ሚዲያ የማየውን ጃዋር በተመለከተ አጠቃላይ የግምገማ ፍርድ ልሰጥ አልቸኮልኩም። ነገር ግን አንድ ነገር ግልጽ ነበር። የሶሻል ሚዲያው ጃዋር ዲሲ በአካል ካገኘኹት ጃዋር በተለየ በራሱ የአይዲዮሎጂ ሰፈር (ideological enclave) የከተመ ነው፡፡ ይኼኛውን “የሜንጫው”ን ጃዋር “አወዛጋቢ” የሚለው ቃል እንኳን በሚገባ አይገልጸውም። ይኹንና ጃዋር “የእነርሱ” ብቻ ኾኖ በሌሎች ዘንድ “ስምና ዝናው” ቢያቆለቁልም የፖለቲካ ኀይሉ (power) ግን ጨምሯል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በኦሮሞ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመንግሥት መዋቅር ውጭ የጃዋርን ያህል ኀይለ-ግናኔ ያገኘ የለም፤ የኦሮሞ ፈርስት ንቅናቄ መሪ፣ የጎምቱ የኦሮሞ ኢንቴሌክቹዋል ሕይወት ማዕከል የኦሮሞ ስተዲስ አሶሲዬሽን ፕሬዝዳንት፣ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሊቀመንበር፣ የኦሮሞ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ኢ-መደበኛ አፈቀላጤ።
ጃዋርን የሰባት ኪሎ ፊት ለፊት ተጋባዥ ላደርገው ስወስንም ይህን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለውን ጉልህ ቦታ እና ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ባለፉት ሦስት ወራት ጃዋርን ሁለት ጊዜ በስልክ አግኝቼው ከአራት ሰዓት በላይ የቆየ ቃለ ምልልስ አድርጌያለሁ። የልጅነት ታሪኩም ይኹን የአሁኑ የፖለቲካ ተሳትፎው ለማወቅ ጉጉት የሚያጭር ነው። ከጃዋር ጋራ በብዙ ሐሳቦች አልስማማም። የእርሱ ፖለቲካ የእኔ ፖለቲካ አይደለም። የእርሱ እሴት የእኔ እሴት አይደለም፤ ይኹንና ሲያወራ እጅግ ቀልብ የሚስብ፣ ብዙ ያነበበ እና ያሰላሰለ፣ ለዓላማው ጽናት ያለው፣ ለተቀናቃኞች የሚያስቸግር፣ ለወዳጅም የቤት ሥራ የኾነ ሰው መኾኑን መካድ አይቻልም። በእነዚህ ሁለት ቃለ ምልልሶች፣ ጃዋር አንዳንዴ አስቆጥቶኛል፤ አንዳንዴ አስደምሞኛል፤ አንዳንዴ አስቆኛል። ሳልጠይቅ ያለፍኳቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ተጨማሪ 10 ሰዓት ቢሰጠኝ እንኳ የሚበቃኝ አይመስለኝም። ቃለ ምልልሱን ከድምጽ ወደ ጽሑፍ መልሼ ሳነበው “ወይኔ እዚህ ጋ ሸወደኝ” ያልኩባቸው በርካታ ቦታዎች አሉ። ጽሑፉን ያነበቡ የሰባት ኪሎ ጓዶቼ አንዱ “አረ ይኼ ሰውዬ ጭልጥ ብሎ የፍራንሲስ ፉኩያማ ተከታይ (ፉኩያሚስት) ኾነ” ሲል፣ ሌላው “እንዴ ሰውየው ኤድመንድ በርክን መመጥመጥ ጀመረ እንዴ” ሲል ሌላው ደግሞ “አቤት ወገብ፣ አቤት መተጣጠፍ” ሲል ፈገግ አሰኘኝ፤ ከጥያቄዎቼ አንዱ “መለስን ትመስላለህ?” የሚል ስለነበር። አንባቢዎቼ፦ ይኼን ቃለ ምልልስ ኮምኩማችሁ ስለ ጃዋር ከሰባት ኪሎ ጓዶቼ የተሻለ የተጨበጠ መረጃ እንደምታገኙ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ይኸው . . . .
(ዳኝነት መኮንን)
ልጅነትና ፖለቲካ
ስለተወለድክበት እና የልጅነት ዘመንህን ስላሳለፍክበት ስለ ድሙጋ ትንሽ አውጋኝ።
በርግጥ ድሙጋ ያደግኹበት እና ራሴን ያወቅኹበት ከተማ ነው፤ በቅርቡ እናቴ እዚህ መጥታ ስትነግረኝ፤ የተወለደኩት ቤተሰቦቼ ይኖሩበት ከነበረ ዲማ ከሚባል ስፍራ ነው፤ ሰኞ ገበያ የሚባል ቦታ ነው፤ ቤተሰቦቿ ጋር ሄዳ ወለደችኝ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ድሙጋ መጣን፤ እና እዚያው አደግኹ። በአርሲ እና ሐረርጌ ድንበር አካባቢ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነች፤ ድሮ የኦነግ ወታደራዊ ንቅናቄ ካምፕም በአካባቢው ነበር፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ቡና ነው፤ በጣም ብዙ ውኃ አለ በአካባቢው፤ ከደጋ አርሲ የሚመጡ ወደ 27 የሚኾኑ ወንዞች አሉ፤ ትልልቅ የመንግሥት የቡና እርሻዎች አሉ፤ የተለያየ ዐይነት እና ቅይጥ የኾነ ባህል የሚታይባት ከተማ ነች። ከኦሮሞ ጎሳዎች ውስጥ ከነምሳ ቀነንዴ የሚመጡት የአፈንቀሎ ጎሳዎች በብዛት አሉ፤ በአካባቢው ደግሞ የአርሲ እና የኢቱ ጎሳዎች አሉ፤ ከሰላሌ ከሸዋ የመጡ የእናቴ ዘመዶች እና ወደዛ ፈልሰው ያሉ አሉ፤ አማራዎች አሉ፤ ኤርትራውያን ሁሉ ያሉባት እና በብዙ ባህሎች ስብጥር የተዋበች ከተማ ነበረች – ያኔ እኔ ሳድግ።
ድሙጋ እስከ ስንተኛ ክፍል ተማርክ?
ድሙጋ ሰባት ጨርሼ ወደ ስምንት ስሻገር ወደ አሰላ ተዛወርኩ፤ ከዚያ በኋላ አሰላ ሁለት ዓመት ተማርኩ። ስምንተኛ ክፍል እያለሁ ከትምህርት ቤት ተባርሬ ነበር።
በምን ተባረርክ?
የፖለቲካ ሱስ ነዋ፤ እዚያ እያለሁ ሰልፍ አስወጣኹባቸው፤ በእነዚሁ ሰዎች ላይ፤ እዚያ እያለሁ የኾነ እንዲሁ ዐይነት እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። በማሳደሜ ምክንያት ስምንተኛ ክፍልን እንዳለ ዘግተው ሁላችንንም ከትምህርት ቤት አባረሩን። የተዘጋው ታህሳስ ወር ላይ ይመስለኛል፤ ከዚያ እኔ ወደ አሳላ መጣሁና መማር ጀመርኩ።
ይህ የመጀመርያው የፖለቲካ ተቃውሞህ ነው?
ለመጀመርያ ጊዜ ተማሪዎችን አሰልፌ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰድኹት የስድስተኛ ከፍል ተማሪ እያለሁ ነበር። ስምንተኛ ክፍል ላይ ስደርስ አንድ የኦሕዴድ የምሥረታ በዐል ነበር፤ በዚያ በዐል ላይ እኛ የኦነግን መዝሙር ዘመርን። እና በዚያው ተባረርን፤ ይኼ እንግዲህ በ1992/3 ዓ.ም መኾኑ ነው።
የአሰላ ቆይታህ እና የፖለቲካ ተሳትፎህስ ምን ይመስል ነበር? ስለ አሰላስ የሚሰማህ ምንድን ነው?
ድሙጋ ማለት ትንሿ ድሬዳዋ ማለት ናት፤ ብዙ ዐይነት ሰው ያለባት፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ የተጋጋለ፤ አኗኗሩም ሞቅ ያለ ነው። አሰላ ስትመጣ በተቃራኒው ቀዝቃዛ ነው፤ አሰላም እንደ ድሙጋ የባልህ ስብጥር የሚታይበት ከተማ ነው። ይኹን እንጂ ማኅበረሰቡ ወግ አጥባቂ ነው፤ እኛ ደግሞ ስንናገር ምላሳችን ለቀቅ ለቀቅ ይላል፤ በአኗኗሩ ደግሞ ሰብሰብ ብለህ በጨዋ መኖር አለብህ፤ ከዚያ ጋራ መዋሃድ መጀመርያ ላይ ስደርስ ፈተና ኾኖብኝ ነበር። እኛ ጋ እንግዲህ ‘እርስዎ’ የሚባል ነገር የለም፤ አንቱ የሚባል ነገር የለም፤ ማንም ይኹን ማን ሁሉም አንተ ነው፤ እና አንድ ጊዜ ክፍል ውስጥ የሂሳብ አስተማሪ ሂሳብ እየሠራ እያለ የስሌት ስህተት ይፈጥራል፤ “ቲቸር እዚያ ጋ ተሳስተኻል፤”አልኩት። ዞሮ “ማንን ነው የምትልው? ከዚህ ከእኔ ጀርባ ሌላ ሰው አለ እንዴ?” እያለ ይጠይቀኛል። ከዚያ እኔ “አንተን እኮ ነው የምልህ” ስለው ጆሮዬን ይዞ ዳይሬክተሩ ጋ ወሰደኝ። ከዚያ ዳይሬክተሩ “በምን ተጣላችሁ?” ብሎ ሲጠይቀኝ “እኔ ምን አውቃለሁ . . . ሂሳብ ስሌት ላይ ተሳስተኻል ስለው” ብዬ ሳልጨርስ ዳይሬክተሩ በሳቅ ሞተ። ዳይሬክተሩ አረማ ስለተማረ ባደግኹበት ባህል ውስጥ አንቱታ እንደሌለ ያውቃል። ከዚያ በኋላ አንቱ ለሚለው ምላሴን ወፈር ማድረግ ጀመርኩ፤ እርሱ አንዱ ተግዳሮት ነበር። ስምንተኛ ከፍል ካቶሊክ ትምህርት ቤት ነው የተማርኹት፤ ከዚያ በፊት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት እማር ነበር፤ ከእናቴ ቤተሰቦች እና ዘመዶች ጋራ፤ ለእኔ በጣም ደስ የሚል እና ለየት ያለ ጊዜ ነበር ያኔ። በአጠቃላይ ስምንተኛ ክፍል የነበረኝ ጊዜ ደስ የሚል ነበር። ዘጠነኛ ክፍል እንደገባሁ ደብቄ የተቀመጥኹት ፖለቲካ እንደገና አገረሸብኝ፤ ማደራጀት ጀመርን፤ የምማርበት ትምህርት ቤት ጭላሎ ነበር፤ ፖለቲካው ሳይጀመር የተማሪዎች ክበብ በሚባለው ውስጥ መሳትፍ ጀምሬ ነበር፤ በማኅበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ተማሪዎችን ማነቃቃት እና ማደራጀት ላይ ተሳትፎ አደርግ ነበር፤ ከዚያ በባሌ ደን ጉዳይ ላይ ተቃውሞ እንዲሰማ አደረግን፤ ትልቅ ሰልፍ ተደረገ፤ እዚያ ያሉት የአስተዳደር አካላት ማስጠንቀቂያ ሰጡኝ፤ ሲረዱኝ የነበሩ ሰዎች “አሁንም ከዚህ ከተባረርክ አስቸጋሪ ነው የሚኾነው፤ ስለዚህ ትምህርት ቤቱን ልቀቅ እና ወደ አዳማ ሂድ” ተባልኩ፤ አዳማ ሄድኩ እዚያ 10ኛ ክፍል ገባሁ፤ ዐሥረኛ ጨርሼ ወደ ዐሥራ አንደኛ እንዳለፍኩ ነው ወደ ሲንጋፖር የመጣሁት። አዳማም በጣም በተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ በአጠቃላይ በምሥራቅ ሸዋ፣ በምዕራብ ሐረርጌ እና በአርሲ አካባቢ በውስጥ በመንቀሳቀስ አደራጅ ነበር፤ በፖለቲካ ብቻ ሳይኾን በባህል ጉዳይ ላይ፣ መሠረተ ትምህርት በማስፋፋት ጉዳዮች ላይ እሳተፍ ነበር፤ አዳማ እያለሁ። በስፋት አክቲቪስ የነበርኹት አዳማ ነው ማለት ይቻላል።
ጃዋር በእስያ፤ ባህል እና ፖለቲካ
ወደ ሲንጋፖር የሚያስጉዝህን ስኮላርሺፕ እንዴት አገኘህ? የሲንጋፖር ቆይታህስ እንዴት ነበር?
ዩናይትድ ዎርልድ ኮሌጅ የሚባል የትምህርት ተቋም አለ። ያኔ እኔ ስሄድ ዐሥር ትምህርት ቤቶች ነበሩት፤ ይኼው ኮሌጅ ከየአገሩ ተማሪዎችን እያመጣ ያስተምራል፤ እንደ ‘ፕሪፓራቶሪ’ ዐይነት ነገር ነው፤ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ያስተምራሉ፤ ግን ተጨማሪ አድቫንስድ ኮርስም ይሰጣል፤ 10ኛ ክፍል ጨርሰው ጥሩ ነጥብ ያላቸውን ልጆች እና በትምህርት ቤት ውስጥም በአመራር ደረጃ አክቲቭ ከኾኑ ተማሪዎች ውስጥ አንድ አንድ ተማሪ ዕጩ አድርጋችሁ አቅርቡ ይባላሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች፤ ዳይሬክተሩ እና መምህራን ዕጩ አድርገው ያቀርቡኻል፤ ከዚያ ከሁሉም ትምህርት ቤቶች የተሰባሰቡ ተማሪዎች ተወዳድረው ይጣራ እና የመጨረሻዎቹ 25 ተጠራን። ይኼን ዩናይትድ ዎርልድ ኮሌጅ እነ ሪቻርድ ፓንክረስት እና ሪታ ፓንክረስት የሚያስተዳድሩት ነው፤ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታወቅ ድርጅት ነው፤ 25ቱ ተማሪዎች ለኢንተርቪው ቀረብን፤ የጽሑፍ ፈተና ነበር፤ እኔ ፈጽሞ የማልፍ አልመሰለኝም ነበር፤ እንግሊዝኛ አልችልም ነበር፤ ሌሎቹ ተማሪዎች እንግሊዝኛውን እንደውኃ ያንቆረቁሩታል፤ ማታ ላይ አልፈኻል ተብሎ ሲነገረኝ ደነገጥኹ። ቀን ላይ ከቃለ ምልልሱ እና ከጽሑፍ ፈተናው ውጪ አንደኛው መስፈርት አገር መምረጥ ነበር፤ አሜሪካ፣ ኢንግላድ፣ ጣልያን፣ ኖርዌይ እና ካናዳ . . . እኔ ግን ከአንድ እስከ ሰባት ካሉት አማራጮች ዐይቼ መጨረሻ ላይ ያለውን ሲንጋፖርን መረጥኹ።
ለምን?
ዐየህ . . . ድሙጋ እያለሁ እንግሊዝኛ ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፤ በጊዜው ምንም ዐይነት የእንግሊዝኛ ጋዜጣ አልነበረም፤ ዕቃ የሚጠቀለልበት ጋዜጣ ብቻ ነበር፤ ስትሬት ታይምስ የሚባል ባለቀለም ጋዜጣ አግኝቼ ሳነብ ሲንጋፖር የሚል ዐየቼ ነበር። እኔ ሲንጋፖር በዚያ ሰዓት ኤዥያ ውስጥ ያለች መኾኗን አላውቅም ነበር፤ አውሮፓ ውስጥ ያለች ከተማ ናት ብዬ አስብ ነበር፤ ከዚያ ሲንጋፖርን ካርታ ላይ ማፈላለግ ጀመርኩ፤ በዚያ ወቅት ሳርስ የሚባል በሽታ ተነስቶ ነበር፤ የሚያውቁኝ ሰዎች “የወፍ በሽታ ያለበት አገር አትሄድም፤ ለመሞት” አሉኝ። ይኹን እንጂ ከሲንጋፖር ጉዞ አልቀረኹም፤ ሲንጋፖር ሄጄ ሁለት ዓመት ተማርኩ።
የባህል ልዩነቱ ድንጋጤ ምን ይመስል ነበር?
ከብዙ አገራት የመጣን 17 ተማሪዎች ነበርን። የባህል ልዩነቱ እጅግ ሰፊ ነበር፤ ከዚያ በተጨማሪ የአገሩ ሰው ከእኛ ጋራ አይማርም፤ አስተማሪዎች ደግሞ አብረውን አይኖሩም፤ በዚህም የተነሳ ደንጋጤው ከባድ ነበር፤ ትምህርቱ በጣም ከፍ ያለ እና ደረጃውን የጠበቀ ነበር፤ የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይኾን ተግባራዊ ትምህርትም እንማራለን፤ በተለይ ስለ ባህል ‘ሴንሲቲቪቲ’፣ ስለ ባህል ግጭት ማኔጅመንት፣ ብዙ ነገር ትማራለህ፤ ጥሩ የለውጥ ጊዜ ነበር፤ በዚያ ላይ የራስህን ቋንቋ መማር ይፈቀድልኻል፤ እንዲያውም እሱን የበለጠ እንድታዳብረው ትበረታታለህ፤ እኔ እዚያ አፋን ኦሮሞን ነበር የተማርኩት፤ ለመጀመርያ ጊዜ አፋን ኦሮሞ የተማርኩት እኔ ነኝ፤ ያም በራሱ የሚያጓጓ እና የሚመስጥ ተግዳሮት ነበር። ያኔ ዓለማቀፍ አክቲቪዝም ውስጥ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ውስጥ (ለምሳሌ የሲሪላንካን ግጭት በመሸምገል)፣ የወጣቶች ተነሳሽነት ውስጥ እሳተፍ ነበር፤ ወደ ቤልጂየም ሄጄ‘ክላሽ ኦፍ ሲቪላይዜሽን’ዐይነት በስደተኛው እና በነባሩ መካከል ያለውን ግጭት የማጥራት እና የመሸምገል እና ኮንፈረንስ የማዘጋጀት ዕድል ነበረኝ፤ እንዲሁም ካናዳ በስረ-ቀዬ (indigenous) ሕዝብ እና በሌላው ማኅበረሰብ መካከል ያለውን . . . በተለያዩ አገሮች በካምቦዲያ፣ በላዖስ፣ እና በሌሎችም አገሮች በብዛት ተጉዤ ነበር፤ ያ ወቅት ለእኔ በጣም የለውጥ የሚባል ጊዜ ነበር። ወደ ብዙ አገሮች እሄድ ነበር፡ ማሌዢያ እዚያው በር ላይ ስለኾነ በየሁለት ሳምንቱ እሄድ ነበር፤ ታይላንድ እንሄዳለን፤ ሕንድ እና ኔፓል ጭምር እሄድ ነበር፤ ከዚያ ውጪ አውሮፓ ኔዘርላንድስ ለኮንፈራንስ ሄጄ ነበር፤ ካናዳም እንዲሁ። የወጣቶች ተነሳሽነት አስባባሪ ኾኜ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሄጄ ነበር፤ ኤዥያ ውስጥ ግን የቀረኝ አገር ያለ አይመስለኝም።
ብዙ ጊዜ ስንጓዝ “መንገድ ላይ ያለሁት፤ ወደ ቤቴ ስለምመለስ ነው” በሚል መንፈስ ነው። ቤት ብዙ ጊዜ ማጣቀሻ ነጥብ (ሪፈረንስ ፖይንት) እናመስታወት ነው፤ በጉርምስናህ ከአገር ወደ አገር ስትጓዝ አንተ ውስጥ ከቀረው የአገር ቤት ማንነት፣ ባህል እና ፖለቲካ ጋራ እያነጻጸርክ እና እያወዳደርክ ትለካ ነበር?
ከባህል አንጻር ስታየው፤ በተለይ እኔ ካደግኹበት ጋራ እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚቀርበው ማሌዢያ ነው ማለት ይቻላል፤ እስከ አሁንም ድረስ ባላገር (ኢንዲጂኒየስ) ናቸው፤ በርግጥ ቅኝ ተይዘው ነበር፤ ነገር ግን የነበረው የቅኝ አገዛዝ የደች ዐይነት ቅኝ አገዛዝ ነው፤ በኋላ ላይ የእንግሊዞች በተወሰነ ደረጃ።
መሳይ ከበደ ‘ካልቸራል ዲስሎኬሽን’ የሚለው ችግር ያልተንሰራፋበት ሞደርኒቲ አላቸው?
ብዙ የባህል ጥፋት አይታይበትም። የሕዝቡ አስተሳሰብ እና የማኅበራዊ ሕይወቱ እኩልነትን ያማከለ (ኢጋሊቴሪያን) ነው፤ በጎሳ የተያያዘ ነው፤ ሰው ይረዳዳል፤ የተለየ ነው። እኔ ባደግኹበት ከትምህርት ቤት ስትመጣ ምሳህን የትኛውም ሰው ቤት ውስጥ ትበላለህ፤ ማሌዢያ እንደዚያ ዐይነት ነገር ታያለህ። ወደ ችግሩ ስትመጣ ደግሞ በተለይ ሲሪላንካ የብሔር ግጭቱን፣ ፖለቲካውን ስታየው ከእኛ አገር ጋር ይመሳሰላል፤ የዚያን ጊዜ ታሚል ታይገሮች ከጦርነት ወደ ሰላም የመጡበት አካባቢ ነው፤ ያኔ ነበር ኮንፈረንስ ያዘጋጀነው። የነበረውን ውጥረት በተወሰነ ደረጃም ቢኾን ታየዋለህ። እኔ ሳድግ ደግሞ በኦነግ እና በሕወሓት መካከል ጦርነት ስለነበረ፤ ያንን ታያለህ፤ ከኤዥያ በጣም ብዙ የምንማረው ነገር አለ፤ ሁሉም አገራት የተለያየ የእድገት መንገድ ተጠቅመው የሚሄዱት፤ ለምሳሌ፦ ታይላንድን እና ማሌዢያን ብታነጻጽራቸው ጎረቤታሞች ናቸው፤ የሚከተሉት የኢኮኖሚ መንገድ በጣም ይለያያል። የባህል ዕድገቱን ስትመለከተውም ልዩነት ይታያል፤ ታይላድ በኢኮኖሚ እድገት የጀመረችው አሜሪካ ቬትናምን በምትደበድብበት ወቅት ነበር፤ የዚያን ጊዜ የአሜሪካ ወታደር እንደ ቤዝ አድርጎ ይጠቅምባት ነበር። ያን ተጠቅመው ኢኮኖሚያቸው ማደግ ችሏል፤ ግን ባህላቸው ሙሉ ለሙሉ ነው የተደመሰሰው። መጥፎ መጥፎ የምዕራብ ባህል ገብቶ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ኢ-እኩልነት የሚታይበት ዕድገት የተፈጠረበት ኾኗል። በጣም የተበከለ ዐይነት ባህል ነው የምታየው ታይላንድ ውስጥ። ማሌዢያ ግን በጣም ግትር የኾኑ ብሔረተኛ መሪዎች ነበሯቸው፤ ከነጻነት በኋላ የመጡት። እነ ቱኩዋንደራህማን የሚባሉ፤ ቢያንስ በኤሊት ደረጃ ስምምነት ስለፈጠሩ የውጭውን ኩባንያ ተጽዕኖ ቀንሰው በብዛት በራሳቸው ችሎታ አደጉ፤ ባህሉ ባለበት ተጠብቆ ከዘመናዊነት ጋራ እየተብላላ የራሱን ዘመናዊነት እየፈጠረ ተራመደ። ኢምፖርትድ የኾነ ዘመናዊነት ሳይኾን፣ እዚያው የተፈጠረ እና ያደገ ዘመናዊነት ስለኾነ የባህል መናጋት አደጋን በጣም መገደብ ተችሏል። የኢኮኖሚ ዕድገቱን ኢኮኖሚስቶች እኩልነትን ለመለካት የሚጠቀሙበትን ጂኒ ኮፊሸንትን ብትመለከት ማሌዢያ ከታይላንድ በብዙ ይለያል። ታይላንድ ውስጥ የማይሸጥ ነገር የለም። ሰው ሲሸጥ ታያለህ፤ ይህ በማሌዢያ አይታሰብም።
እዚያው ጎረቤት ላዖስ የሚባል አገር ስትሄድ ደግሞ፤ እስከ አሁን ኮሚኒዝም ነው፤ እስከ አሁን የራሽያ መኪና ነው የሚነዱት፣ እስከ አሁን ድረስ ባንዲራ ሲወጣ እና ሲወርድ ዝግ ብለህ ካላቆምክ በጥፊ ትመታለህ። እዚያው ጋ ደግሞ ቬትናሞች በከፍተኛ የኢኮኖሚ ፍጥነት ሲሄዱ ታያለህ፤ እዚያው ጋ ደግሞ ማሌዢያ በተረጋጋ ፍጥነት ስተጓዝ ትመለከታለህ፣ እዚያ ጋ ደግሞ ታይላንድ ምስቅልቅሉ ወጥቷል፤ እዚህ ጋ ደግሞ ላዖስ የሚባል ልክ ይኼ . . ድሮ በሠርቶ አደር ጋዜጣ የምታያትን ዐይነት ኢትዮጵያ ታያለህ።
መለስ ዜናዊ ስለ ኤዢያ ሞዴል ብዙ ይናገር ነበር፦ አንድ እርሱ ያላገኘው እኔ በቅርብ ያስተዋልኩት ምን መሰለህ፦ የኤዢያ ሞዴል የሚባል ነገር የለም። ሁሉም አገሮች የየራሳቸው የኾነ ሞዴል ነበራቸው፤ ሁሉም አገሮች የየራሳቸው በጎና መጥፎ ነበራቸው፤ እኔ ያኔ ማሌዢያ ውስጥ በአውቶብስ እና በባቡር እያንዳንዱን ገጠር እየዞርኩ እመለከት ነበር፤ ገበሬ ቤት እያደርኩ። እና እንደ አገር ማድረግ ያለብህም ማድረግ የሌለብህም ብዙ ነገሮች ትማራለህ።
ስለሲሪላንካ ስታነሳ ከኢትዮጵያ ጋራ የሚመሳስል የፖለቲካ ችግር እንዳላቸው አንስተሃል፤ አንዳንድ ጊዜ ተመሳሳይ የሚመስሉ ችግሮች የተለያዩ መንስዔዎች አሏቸው። እስቲ ስለ መንስዔ እናውራ። የመንግሥት (ስቴት) ጭቆና እና ጭፍለቃ ከእኛ ጋር ይመሳሰላል። የብዙኀን እና ውህዳን ስብጥሩን እና የኀይል ሚዛኑን ከውጭ ሲመለከቱት ግን የብዙኀን አምባገነንነት ችግር ይመስላል።
እንግዲህ እዚያ አገር ያሉት ሁለት ዋና ዋና ብሔሮች ናቸው፤ ታሚል እና ሲንሃሊዝ የሚባሉ። ሲንሃሊዝ የሚባሉት ሰባ በመቶ የሚኾኑ ይመስለኛል፤ ታሚሎች 15 በመቶ ይኾናሉ፤ በሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ነው የሚኖሩት። በኮሎኒያሊዝም ጊዜ እንግሊዞቹ ታሚል ‘ማይኖሪቲ’ ስለነበረ ሥልጣን ላይ አቆይተውት ነበር። እነርሱን ተጠቅመው ነው ብዙኀኑን ሲገዙ የነበሩት። ከሥልጣን ሲወርዱ ግን ሥልጣኑን ‘ለማጆሪቲው’ አስተላልፈው ነው የሄዱት። ወደ ሥልጣን የመጡት ደግሞ የታሚል ልዩ ጥቅም አለ ብለው ስለነበር ያንን ለመጨፍለቅ ስለፈለጉ ብዙ ርምጃዎችን ወስደዋል።
ወደ እኛ ስንመጣ ከማሌዥያ ጋር ላነጻጽርልህ፤ የማሌዢያን ቅድመ ቅኝ ግዛት ማኔጅመንት ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የሲሪላንካ ታሚሎች ቅኝ አገዛዝ ጋራ ሥልጣናቸውን አጡ። ታሚሎች በዚያ ጊዜ ብዙ ስለተማሩ ሰፊውን ልዩነት ለማመጣጠን የሲንሃሊዝ ልሂቃን ታሚሎችን በመጨቆን ወደኋላ የማስቀረት ርምጃ መውሰድ አለብን አሉ፤ እና ቋንቋቸውን ከትምህርት እና ከአገልግሎት እንዲወጣ አደረጉት፤ ታሚሎች እንግሊዝኛ ስለሚናገሩ እና ሲናሊዞች ስለማይናገሩ እንግሊዝኛንም ጭምር ከለከሉ፤ ስለዚህ ታሚሎች የባህል ጭቆና፣ የቋንቋ ጭቆና እና ኢኮኖሚያዊ መገለል ደረሰባቸው። ይኼ እንግዲህ በ1960ዎቹ በደንብ እየተብላላ የመጣ ነው። የታሚል ፓርቲዎች ልክ እኛ ጋ እንደሚታየው በሰላም እየሞከሩ አልኾነላቸውም፤ እያለ እያለ ወደ ጦርነት ሄዱ። የማሌዢያን ስንወስድ ደግሞ የቻይና ሰፋሪዎች (እንግሊዞች ያመጡዋቸው የቻይና የጉልበት ሠራተኞች ነበሩ) ብዛታቸው 10 ፐርሰንት ያህል ነው፤ ከእንግሊዞች ጋራ የቅኝ ግዛት ወኪል በመኾን የኢኮኖሚ አውታሩን ተቆጣጠሩት። እንግሊዞች እነርሱን ከማላዮች ጋር ለማጋጨት ሞክረው ነበር፤ የማሌዢያ ብሔረተኞች ግን የቻይናውያን ተጽዕኖ እንዲቀጥል አደረጉ። ያንን የበላይነት ለመስበር በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት ጦርነት ውስጥ መግባት ስላልፈለጉ ቱንኩ የሚባለው ሰውዬ “ኢንላርጂንግ ዘ ፓይ” ቲዎሪ ይዞ መጣ።
እንግሊዞች የነበራቸው ሀብት እንዳለ ይወረስና ለማሌዢያውያን እንዲተላለፍ ይደረጋል፤ የቻይኒዞቹ እንዳለ አይነካም፤ ኢኮኖሚው በሚያድግበት ጊዜ የቻይኖቹ እንዳለ እየቀጠለ የማላዮቹ ግን በስፋት ማደግ አለበት፤ ቻይናዎቹ ምንም የሚያጡት ነገር የለም፤ ይህ ሁሉ ሲኾን የቻይኒስት ኮሚኒስት ፓርቲ እንቅስቃሴ ነበር፤ እነሱም ቡኖ የሚባል ፓርቲ ፈጠሩ፤ ቻይና በዚህ መልክ ጣልቃ ትገባ ነበር፤ ይሁንና ያንን ሁሉ መቆጣጠር ችለዋል። ሲሪላንካ ውስጥ ያንን ማድረግ አልቻሉም፤ ውጥረቱ በጣም እያየለ የታሚል ብሔረተኛነት እያደገ በመጣ ቁጥር እርሱን ለመስበር ያላደረጉት ነገር የለም፤ በተለይ የሰላማዊ ፖለቲካ ምህዳሩን በዘጉት ቁጥር፣ ባህሉ እንዳያድግ መንገዱን እየዘጉት በሄዱ ቁጥር፣ እየጠነከ እየጠነከረ መጣና ፓራብካሃራን የተባለ አንድ ጎረምሳ (ያኔ 19 ዓመቱ ነበር) የዐማፂ ቡድን ፈጠረ፤ ዓለምን ያንቀጠቀጠ ዐማፂ፤ አገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ፈራረሰች። አሁን ታሚሎች ተሸነፉ ምናምን የሚባለው ነገር እንዳለ ኾኖ፣ በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ቁስል በምንም በምንም ሊጠገን የሚችል ዐይነት አይደለም። እኔ ያኔ እዚያ በነበርኩበት ወቅት ሰላም ሰፍኖ ነበር፤ ሁለተኛው ዙር ጦርነት አልተከፈተም፤ ከሲሪላንካ ከሁለቱም ቡድኖች ወደ መቶ ምናም የሚኾኑ ወጣቶች ይዤ ወደ ሲንጋፖር መጣሁ፤ የመጡት ከኖርዝ ነው፤ ከዚያ አግኝተናቸው ወደ ሦስተኛ አገር እንዲሄዱ አደረግን። በዚያ ጊዜ የነበረው ውጥረት እጅግ በጣም አደገኛ ነበር። ይኹንና ከሦስት ሳምንት በኋላ በነበረን የመፍትሄ አማራጭ በማግባባት ሥራ ማቀራረብ ቻልን።
ወደኛ ልምጣ። እኔ ሳድግ ሕወሓት ሲያደርግ የነበረው የኦሮሞ ብሔርተኝነትን በሐይል ለመጨፍለቅ የሚውስዳቸው ርምጃዎች (በርግጥ እኛ ሕጻናት ነበርን፣ ርምጃ የሚወሰደው ግን በአባቶቻችን፣ በታላላቅ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ ነበር) እያጠነከረው በመጣ ቁጥር ብሔርተኝነቱ ሥር እየሰደደ፣ ጽናቱም ሥር እየሰደደ ሄደ። እዚያም በታሚል እና በሲንሃሊዝ መካከል እዚህም ደግሞ በኦሮሞ እና በሕወሃት መካከል ያለው ልዩነት በጣም ያሻከሩት ብሔረተኝነትን ለመጨፍለቅ የተወሰዱ ርምጃዎች ናቸው። የፖለቲካዊ የአመራር ብልሹነት አደጋ ከፍተኛ ነው፤ ልዩነትን ማጥፋት አትችልም፤ ልዩነትን ግን ማኔጅ ማድረግ ትችላለህ፤ የመንግሥት አስተዳደር ጥበብን የምር በሚባል መልኩ ከተጠበብክ ምንም ዐይነት ጦርነት ያለበት አገር ቢኾን መልሰህ ለመገንባት ዕድሉ አለህ፤ የፖለቲካ አመለካከቶችን በተለይ የማኅበራዊ እና ባህላዊ መሠረት ያላቸውን የፖለቲካ አመለካከቶች ጨፍልቄ ለውጥ አመጣለሁ ማለት አይቻልም።
ጃዋር ስለ መለስ ዜናዊ
መለስ ዜናዊ ሲንጋፖርንን ምሳሌያደርጋል። በዚያ እኮ ጭፍለቃ ነበር።
በጣም የተሳሳተ ምሳሌ ነበር። ሲንጋፖር ውስጥ በግልጽ ብሔር አይደለም የተጨፈለቀው። ታርጌቱ ኮሚዩኒስቶች ነበሩ። ሊኩዋን ኮሚዩኒስቶችን እና ለእነርሱ ያዝናሉ የሚላቸውን ደርምሶ እና ጨፍልቆ አምባገነን ኾነ፤ ግን መጀመርያ ሥልጣን ሲይዝ የቋንቋ እና የብሔርን ጥያቄን ፈታው፤ በሲንጋፖር ውስጥ ያሉ ቋንቋዎች በሙሉ የሥራ ቋንቋዎች ናቸው፤ ትንሽም ሕዝብ የሚናገራቸው ጭምር፤ በርግጥ ተፎካካሪዎቹ ማሌ እና ቻይኒዝ ናቸው፤ በይፋም የሚታወቁ ናቸው፤ እንግሊዝኛ የሥራ ቋንቋ ነው። ጭፍለቃው በሁሉም ብሔረሰቦች አባላት ላይ ያነጣጠረ ‘እኩል’ ነው። ከሁሉም ብሔረሰብ ደግሞ ወደ ሥልጣን እና ወደ ኢኮኖሚው አውታር በማስገባት ነው በዚያው ለመቆየት የሚያስችል ዕድገትን ያመነጨው እና አምባገነንነትን መገንባት የቻለው። እኛ ጋ ግን መለስ ሲሞክር የነበረው 95 በመቶ ያለውን ብሔረሰብ ጨቁኖ እና እንዳለ ወደ ጎን ገፍቶ ልማታዊ ኢኮኖሚ /ልማታዊ መንግሥት ነበር፤ አሁንም እንደምታየው ፈነዳ።
አንድ የሳይኮሎጂ ክስተት አለ፤ ዘ ካሚሊዮን ኢፌክት የሚሉት። አንዳንድ ጊዜ ሳናውቀው የምናጠናውን ሰው መምሰል እንጀምራለን። መለስን ጠንቅቀህ ያጠናህ ተመራማሪ እንደሆንክ አውቃለሁ፣ ጠላትን በማወቅ የሂሳብ ስሌት እርሱን መስሏል የሚሉህ አሉ።
(ሳቅ). . . . የስቶኮልም ሲንድረም እንዳይሉት እንጂ . . . . ባላንጣን በደንብ ማጥናት አስፈላጊ ነው፤ መለስ በሁላችንም ላይ አሉታዊም አዎንታዊም ተጸእኖ አለው፤ በተለይ በእኛ ትውልድ ላይ፤ ምክንያቱ ሌላውን ድምጽ በሙሉ ጸጥ አድርጎ የእርሱ ድምጽ ብቻ ይሰማ ስለነበር ነው። ከእኛ በፊት ለነበሩ ሰዎች ግልጽ ላይኾን ይችላል፤ ለእኛ ግን ግልጽ ነው። በእኛ ሕይወት ውስጥ እንደ መንፈስ በየቦታው የተንሰራፋ ነበር። ካድሬዎቹ የሚናገሩት ቋንቋው ሳይቀር የእርሱን ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የሚናገራቸው ነገሮች እና ሥራ ላይ የሚውሉት ነገሮች ይለያዩ ነበር። ከሕጻንነቴ ጀምሮ እርሱ ስለ ዲሞክራሲ ያወራል፤ በተቃራኒው ግን ሰው ይጨፈጨፍ ነበር። ስለዚህ ፖለቲካውን ለማወቅ አፉ ብቻ ሳይሆን እጁ የሚያደርግውን ማጥናት ግዴታ ነው። ቶሎ ነው የገባኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ ዲስኩሩን እና ሥራውን አጠና ነበር።
መለስ ታክቲሻን ነው እንጂ ስትራቴጂስት አይደለም፤ በታክቲክ ጎበዝ ነበር፤ ስማርት ነው፤ ጥሩ አንባቢ ነው፤ ፖለቲካል ‘ሰርቫይቫል’ ነው፤ ሞተ ስትለው ይተርፋል። እና የእርሱን ታክቲኮች ማጥናት ወሳኝ ነበር፤ ለእኔ ብቻ ሳይኾን በእኔ ዕድሜ ላሉ የኦሮሞ ወጣቶች የለየለት አምባገነን ነበር፤ እርሱን ማሸነፍ አስፈላጊ ነበር፤ እርሱን ለማሸነፍ ብቻ ሳይኾን፤ እርሱ በዚያ አገር ላይ ያመጣውን ጥፋት እና ጉዳት ለማወቅ የእርሱ የፖሊሲ መርኾዎች መነሻቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፤ ይኼ የኤዢያን ሞዴል የሚለውን፣ ልማታዊ መንግሥት የሚለውን፣ ከሌላ አገር እየተቀበለ አምጥቶ የሚዘራውን። እኔ ደግሞ እነዚያን እርሱ ተማርኩባቸው የሚላቸውን አገሮች እየሄድኩ ለማየት ዕድሉ ነበረኝ። ባጋጣሚ እርሱን አግኝቼ ኢንተርቪው አድርጌው ነበር።
እርግጥ የእርሱን ስትራቴጂ ስታጠና ተጽዕኖ ይኖርብኻል፤ ነገር ግን ክሱ ‘ጃዋር መለስ ኾነ’ የሚል ከኾነ ትልቅ ችግር ነው (ሳቅ)። አይዲዮሎጂካል ልዩነቶች አሉን። በርግጥ አንዳንድ ጠንካራ ነገሮች አሉት። ግን ያለውን ጠንካራ ነገር ለመጥፎ ተጠቀመበት። ከመለስ ጋር በተገናኘ ያለኝ ትልቁ ቁጭት ባጠፋው ነገር ላይ ብቻ አይደለም፤ ሊያደርጋቸው እየቻለ አገሪቱን ያሳጣት ዕድሎች በርካታ ናቸው። የተለየ ችሎታ እያለው አጥፊ ነው። እርሱ ሥልጣን ላይ በወጣ ጊዜ ትልቁ ውጥረት የነበረው በኦሮሞ እና በአማራ ልሂቃን መካከል ነበር። እንደ ሦስተኛ ወገን ሆኖ የሽምግልና፣ የማስታረቅ እና የማቀራረብ ሥራ ሊሠራ ይችል ነበር። የአማራም ኾነ የኦሮሞ ልሂቅ ከትግራይ ልሂቅ ጋራ ቢዋጋም የችግሩ መንስዔ የከረረ አልነበረም።ዋናው የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ከአማራ እና ከኦሮሞ ልሂቅ ግጭት ጋር የተያያዘ ነበር። ያንን ችግር ለመፍታት ዕድል እንስጥ የሚባልበት ልዩ አጋጣሚ ነበር። የመንግሥት አስተዳደር ጥበብን ተጠቅሞ (በተለይ ያለውን የመናገር እና የመጻፍ ችሎታ ተጠቅሞ) እነዚህን ሁለት ማኅበረሰቦች፣ ለረጅም ጊዜ ያላቸውን የፖለቲካ ልዩነት ክፍተቱን የማጥበብ እና አገር የመገንባት ዕድሉ ቀላል አልነበረም። እርሱ ግን የድሮው አዙሪት ውስጥ ገብቶ ወደዘረፋው እና የራሱን ብሔር የበላይነት ወደመገንባት ሄደ። ያንን ባያደርግ አማራውም ያዳምጠው ነበር፤ ኦሮሞው ያዳምጠው ነበር፣ ሌላውም ማኅብረሰብ ያዳምጠው ነበር፤ አገርን ለመለወጥ የነበረው ዕድል ከምናብ የላቀ ነበር፤ ያንን ዕድል ግን በተቃራኒ ለመጥፎ ተጠቀመበት። ሁለቱን ማኅበረሰቦች ከማቀራረብ ይልቅ ሕይወቱን በሙሉ ያሳለፈው በማለያየት ነው፤ ዛሬም ከእርሱ በኋላ የቀሩት ቅራሬዎች ምንድን ነው እየተጠቀሙ ያሉት?
ሁለቱን ማኅበረሰብ እኮ ቢያቀራርቡት ትግራይ አይጎዳም፤ በማቀራረብ ግን ዘላቂ የኾነ ሚና ሊኖረው ይችል ነበር፤ ዘላቂ የኾነ የሠላም አምጪ ችግር ፈቺ (ሸምጋይ) የመኾን ዕድል ይኖረው ነበር። በምትኩ እርሱ ምን አደረገው የእርሱን የትግራይ የበላይነት የመገንባት ስትራተጂ የሁለቱን ማኅበረሰቦች ማጋጨት ላይ ተንጠላጠለ፤ በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል በነበሩት ፍርሃቶች ላይ ሽብልቅ፤ በነበሩት ቁስሎች ላይ ጨው እየነሰነሰ ቀጠለ። እርሱ ልማታዊ ሞዴል ሲል የነበረውን በማጠናበት ወቅት እነዚህ አካሄዶቹ እንቆቅልሽ ኾነውብኝ ነበር። እነዚህ ነገሮች በእኔ ስትራቴጂክ አስተሳሰብ ላይ የራሳቸው የኾነ ሚና ነበራቸው፤ ይኹንና በአብዛኛው በተቃራኒው መሥራቱ ላይ ነበር ያተኮርኩት እንጂ እርሱን በማስመሰል እና በመገልበጥ ላይ አይደለም ያተኮርኩት።
ኢትዮጵያን የሚመራው ማነው? ማስወገድስ ይቻላል?
ብዙ ግዜ ሳዳምጥህ ያለው የትግራይ ገዢ መደብ ማስወገድን ቀለል አድረገህ ታየዋል፤ በመጻዒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕወሓት ዙርያ የተኮለኮለውን በጥቅም የተሳሰረ ቡድን ከጥያቄው ማውጣት እና ማስወገድስ ቀላል ነወይ? ሌላ የእርቅ እና አገር የመገንባት ዕድል አያልፈንም?
በጣም ቀላል ነው፤ ይኼ እኮ ከቲዎሪም አልፈልን በተግባር እያሳየነው ያለነው ነገር ነው። ሕወሓትን ማስወገድ ለእኛ ትውልድ በጣም ቀላል ነው፤ ምክንያቱም በውስጡ ነው ያደግነው፤ ገና ሥልጣን ሲይዙ ጀምሮ እነርሱ በቀረጹት ትምህርት ውስጥ ነው ያለፈነው፤ የእኔ እና ያንተ እኩዮች በዚያ ሥርዐት ውስጥ ነው የሚሠሩት፤ ሕወሓትን ለመጣል ትልቁ ዕድል እነርሱ ከሚያውቁን የበለጠ እኛ እነርሱን ማወቃችን ነው። ሁለት ተነጻጻሪ ወይም ተፎካካሪ ሐይሎች ለመሸናነፍ የሚኖራቸው የኢንፎርሜሽን ሐይል የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፤ እኛ ሕወሓትን በጣም እናውቃለን፤ እነርሱ ግን ስለ እኛ ምንም የሚያውቁት ነገር የላቸውም፤ አንድ ይኼ ነው። ሁለተኛ፦ የሕወሓትን ድክመት እና ጥንካሬ እናውቀዋለን፤ ስስ ብልቱን እናውቀዋለን፤ ሕወሓት አንደኛ ሕዝባዊ መሠረት የለውም፤ ሁለተኛ ሥሩን በሚቆርጠው ዛፍ ላይ ቁጭ ብሎ የሚንደላቀቅ ወጠምሻ ነው። ሕወሓቶች ቁጭ ያሉት በብአዴን እና በኦሕዴድ ላይ ነው፤ ሌላ ምንም ምትሃት የለም። ይኹንና ቀን ከሌት የብአዴን እና የኦሕዴድን መሠረት ሲገዘግዙ ነው የሚውሉት። ሃምሳ በመቶ የሚኾነውን ሥራ ላንተ የሚሠሩልህ እነርሱ ናቸው፤
እኔን እንቅልፍ የሚነሳኝ ሕወሓትን መጣል የሚለው አይደለም፤ የኦሮሞ ወጣቶች ቢገፉት ይጥሉታል፤ ነገር ግን ቅዠት ኾኖ እኔንም አንተንም የሚያሳስበን ከዚያ በኋላስ የሚለው ነው። እነርሱን የማውረዱ ሂደት ሌላ የተሻለ ሲስተም ለመገንባት ዕድል መክፈት መቻል አለበት፤ እኔ የማምነው አንድን ሥርዐት ስትንደው ጎን ለጎን ከዚያ የተሻለ ሥርዐት እየገነባህ መሄድ መቻል አለብህ በሚለው ነው። ያንኑ ዐይነት ተመሳሳይ ሥርዐት በትንሳኤ እንዳታስነሳው መጠንቀቅ አለብህ። አሁን እኮ ሕወሃቶች የመጨረሻ ወፍረዋል፤ በገንዘብ ጭምር ወፍረዋል፤ ደንቆሮዎች እና ትዕቢተኞች ስለኾኑ ሲወድቁ ላይህ ላይ ነው የሚወድቁት። እኔ የገበሬ ልጅ ነኝ፤ ሁሌ የገጠር ምሳሌ ነው የምሰጠው፤ ዛፍ ስትቆርጥ ዛፉ ወደ አንተ ላይ እንዳይወድቅ አስቀድመህ ርግጠኛ መኾን አለብህ፤ ሕወሓትን መጣል ከባድ የሚያደርገው ከዚያ በኋላስ የሚለው ነው፤ የእኛ ትውልድ ዋና ሥራ መኾን ያለበትም ይኼው ነው። ያ ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው።
የሶርያ ትምህርት . . .
የሕወሓት አወዳደቅ የትግራይ ሕዝብን ይዞ እንዳይወድቅ መጥንቀቅ አስፈላጊ ነው፤ እየተጫወቱ ያሉት ጨዋታ እጅግ አደገኛ ነው። የአሳድ ቤተሰቦች የተጫወቱትን የሚመስል ጨዋታ ነው እየተጫወቱ ያሉት፤ የአላዋይቶች ጉዳይ እያየነው ነው። ካልተጠነቀቁ ያንኑ እንጠቅማለን ብለው የሚሉትን ማኅበረሰብ ይጎዳል። ማንም ይኹን ምን ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ብሔረሰብ መጎዳት ለኢትዮጵያም ኾነ ለአጠቃላዩ የምሥራቅ አፍሪካ መልካም አይደለም። የአንድን ብሔረሰብ የበላይነት እናስወግድ ስንል የአንድን ብሔረሰብ ውድመት መመኘት አይደለም። ያ እንዳይመጣ መጠንቀቅ አለብን፤ ስለዚህ እነዚህ በጣም ውስብስብ የኾኑ ጉዳዮች፤ ብዙ ሐሳብ፣ ብዙ አእምሮ፣ ብዙ ስትራቴጂ እና ብዙ ፕላን የሚጠይቁ ናቸው፤ ድኅረ ሕወሓት ኢትዮጵያ ምን ዐይነት መኾን አለባት? ከሕወሓት በኋላ ምሥራቅ አፍሪካ ምን መምሰል አለበት? የሚለው ነው እንቅልፍ የሚነሳኝ። አንተንም፤ ሁላችንንም – እንጂ ሕወሓትን ማስወገድ የዚያን ያህል ውስብስብ ኾኖ አይታየኝም።
የሚገርመው ሕወሃትን ስለማወቅ አንተ የምትለውን ኢዴፓ ዙሪያ የነበሩ ወጣቶች ከ15 አመታት ይሉት ነበር። ሕወሓቶች በአሁኑ ሰዓት ሥር የሰደደ ሕዝባዊ መሠረት አይኑራቸው እንጂ፤ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ከጎናቸው የሚቆሙ የብአዴን እና የኦሕዴድ ሰዎች መኖራቸው እሙን ነው፤ ከዚያ ሌላ የፓርቲ አባላት ያልሆኑ የተለያዩ ብሔር ልሂቃን እነርሱ ዙሪያ ተስብስበዋል። ተሞክሮና የፖለቲካ ሳይንስ የሚጠቁሙት እንደ እነዚህ ዐይነት ቡድኖች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሥልጣን ላይ ያለውን ቡድን እንደሚጠብቁ እና እንደሚከላከሉ ነው። በኢትዮጵያ የእነዚህ ቁጥር ከፍተኛ አይደለም ወይ? ሕዝባዊ መሠረት የሌላችው አምባገነኖች በእንደዚህ ዐይነት ልሂቃን ርዳታ ይቆያሉ።
ይኼ ያልከው ጉዳይ ችግር ይፈጥር የነበረው ከዐሥር ዓመት በፊት ቢኾን ነበር፤ አሁን አይደለም፤ ያኔ ሕወሃት ጮማ እየበላ ለእነርሱ ፍርፋሪ ነበር የሚሰጣቸው። አሁን እነርሱ ፍርፋሪውን በልተው በትንሹ መጠርቃት ጀምረዋል፤ ሕወሃት ደግሞ ይኼን ነገር እያየ ያለው “እነዚህ ሰዎች በዚህ ፍርፋሪ እንደዚህ እየተጠናከሩ ከመጡ እኮ ይቺን ጮማ ሊቀሙኝ ይችላሉ” ብሎ ነው፤ ስለዚህ ፍርፋሪውን እየቀነሰባቸው ነው። ይኼን እንደ አንድ አስፈላጊ ስትራቴጂ ማየት አለብን፤ ሁለተኛ፦ መለስ በነበረት ወቀት ሕወሓት በኦህዴድ እና በብአዴን ይፈራ ነበር። አሁን ያሉትን አመራሮች ከምንም አይቆጥሯቸውም፤ “አንተ” እያሉ የሚያናግሯቸው ናቸው፤ አባታቸው የለም። የኦሕዴድም ኾነ የብአዴን ባለሥልጣን ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋራ በጋራ ቁጭ ብለው የመለስን ሌክቸር ሲያደምጡ የነበሩ እንጂ ከመካከላቸው መምህር አልነበርም፤ ያም አስፈላጊ ነው፤ ወደ ጥቅማቸው ስንመለስ ግን ሕወሓት ትግሉን የሚረዳ አንድ ነገር እያደረገ ነው። ኦሕዴድ እና ብአዴን ከተጠናከሩ ለእኛ አደጋ ናቸው ብለው ስለሚፈሩ በኩርኩም መምታቱን አጧጡፈዋል፤ አሁን ባለፈው ሁለት ዓመታት ያደረጓቸውን ወሳኝ የስትራቴጂ ስህተቶች ታያለህ። ኦህዴድ እና ብአዴን ለሕወሃት እና ለትግራይ ሕዝብ ብድር መክፈል አለባቸው የሚል ቲዮሪ ይዘው መጡ፤ ኻያ ምናምን ዓመት ኦሮሚያ ውስጥ ተወልጄ ነው ያደግኹት የሚለውን አንድ ኦሕዴድ “አይ ትግራይ ውስጥ ነው የተወለድከው” የሚል በጣም የሚያገል ዘመቻ አደረጉባቸው። ኻያ አምስት ዓመት የተናገሩትን ታሪክ ሰርዘው አዲስ እንዲጽፉ እና የሕዝብ ተቀባይነታቸውን እንዲያጡ አደረጓቸው። ብአዴኖች ደግሞ ለረዥም ጊዜ ከሕወሓት ጋራ አጋር ኾነን ደርግን ጥለን ነው የመጣነው ነበር የሚሉት። እውነታም አለው፤ ሙዚየም ሁሉ አላቸው ባህር ዳር ላይ። አሁን በቅርቡ ለኀይለማርያም ደሳለኝ የብአዴን 35ኛ ምሥረታ ላይ እንዲያቀርብ ጽፈው የሰጡት ንግግር “የሕወሓት ታጋዮች ሲታገሉ፤ የአማራ ሕዝብ ስንቅ እና ትጥቅ አቀብሎ ነበር” የሚል ብአዴንን ለማዋረድ እና ሚናውን ዝቅ ለማድረግ የተሠራ ፕሮፖጋንዳ ነበር፤ ይኼ በእነዚህ መካከል ምን ይፈጥራል?
ይኼ ብቻ አይደለም፤ ሕወሓት ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያገኙት የኢኮኖሚ ድርሻ እና የብአዴን እና የኦሕዴድ ሰዎች የሚያገኙት ድርሻ ሰማይ እና ምድር ነው፤ የተወሰኑት ባለሥልጣናት ዳታ አለኝ። አንድ የብአዴን ባለሥልጣን የሚያገኘውን ከፍተኛ የኾነ “ኪራይ” አዲስ አበባ ውስጥ የአንዱ ክፍለከተማ ጸሐፊ የኾነ የሕወሓት አባል ያገኘዋል፤ ከብአዴኑ ሊቀመንበር የበለጠ ንብረት አለው። እርሱ ቁጭ የሚለው ከሕወሓቱ ባለሥልጣን ጋራ ነው፤ የዚህ ባለሥልጣን የበታች – በታች – በታች የኾነ ሰው ግን ከእርሱ የበለጠ ኢኮኖሚ ሲያጋብስ ይመለከተዋል።
ውጥረቱንና ተቃርኖውን በግለሰብና በቡድን ከፍዬ ላስቀምጥልህ። በባለስልጣናት ደርጃ (ለምሳሌ በአዲሱ ለገሰ እና በአባይ ጸሐዬ፣ በአባይ ጸሐዬ እና በአባዱላ) መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ልዩነት ተመልከት። ይኼ ወደ መካከለኛ ደረጃ ሲሄድ የክፍል ጓደኞች የነበሩ፣ ከ2000 በፊት አብረው ስኒ ሲደረድሩ የነበሩ ካደሬዎች አሁን በኢኮኖሚ ደረጃቸው ፍጹም ተለያይተዋል። ሕወሃቱ አለቃ ከመኾን አልፎ ኦህዴዱ/ብአዴኑ ታክሲ ሲጠብቅ መኪና እየነዳ በአጠገቡ ሲያልፍ አቧራ አልብሶት ይሄዳል።
በቡድን፦ የእኔ ክልል እና ማኅበረሰብስ ለአገር የሚያበረክተው ድርሻ ምን ያህል ነው? የሚለው ጥያቄ እያደገ ነው። አሁን ኦሮምያ ውስጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በኦሕዴድ ተሳትፎ እንደሚደረግ ሕወሃቶችም ኾኑ ሌሎቹ በደንብ የሚያውቁት ነው። ይኼንን ያደረጉት ብሔረተኛ ስለኾኑ አይደለም፤ ጥቅማቸው ከኦሮሞ ጥቅም ጋራ የተሳሰረ ስለኾነ ነው፤ የብአዴን ጥቅም በደንብ አልተሠራበትም እንጂ በቀጥታ የሚያያዘው እና የሚተሳሰረው ከአማራ ገበሬ ጥቅም ጋራ ነው። የግል እና የጋራ ጥቅም የት ጋራ ነው እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉት የሚለውን በደንብ ማጥናት እና መገንዘብ አስፈላጊ ነው፤ የኦሕዴድ አባላት በሙሉ ጥቅማቸው ከሕዝባቸው ጋራ የተሳሰረ መኾኑን አሁን በደንብ ተገንዝበዋል።
ይህን ነገር በሌላ በኩል እንመልከተው። እንዳንተ አባባል ጮማ በሉ የሕወሃት ቡድን ላለፉት 25 ዓመታት ራሱን በደንብ አደልቧል፤ ራሱን ያደለበ ቡድን ደግሞ ይህን ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚያስችል ‘ሪሶርስ’ እና ቁርጠኝነት አለው። ደቡብ አፍሪካን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል። የሕወሃት ልሂቃን የችግሩ መፍቻ አንድ ቁልፍ ካልሆኑ ሰበብ የለውም? የሕወሓት ካልሆነ ደግሞ የትግራይ ልሂቃን አዎንታዊ ሚና ወሳኝ አይደለም?
በጣም አስፈላጊ ውስብስብ ጥያቄ ነው። በፊት ከትግራይ ልሂቃን ውስጥ ተራማጅ የኾነ ቡድን ማግኘት ይቻላል፤ ካልኾነ ደግሞ ሞደሬት የኾነ አንጃ (ፋክሽን) ከሕወሃት ውስጥ ሊበቅል ይችላል የሚል ተስፋ ነበረኝ፤ ሁላችንም ነበረን፤ ያ ተስፋ አሁን ጨልሟል፤ ምክንያቱም፦ አንደኛ ተራማጅ ተብለው የሚታሰቡት ተጠቅልለው ወደዚያው ገብተዋል፤ ሞደሬቶቹም እንዲሁ፤ በተለይ ከመለስ ሞት በኋላ። እነ ስዬ እና ሌሎቹ፤ ከገብሩ በስተቀር ወደዚያ ተመልሰዋል፡፤ ከመመለስም አልፈው የኢኮኖሚ ተቋዳሽ ኾነዋል፤ የትግራይ ልሂቅ እና የሕወሃት ጥቅም አንድ ላይ የተሸመነ ነው። ልዩነታቸውም እንደ መርፌ የቀጠነ ነው። ያ የሚሰነጠቅ አይመስለኝም። ለእኛም ቢኾን አራት መቶ ሰው ሲጨፈጨፍ አንድም የትግራይ ልሂቅ ወጥቶ “አረ ይኼ ግድያ ትክክል አይደለም” አለማለቱ ከእነርሱ ውስጥ ሊወጣ የሚችል ተራማጅ ይኖራል ብለን ብንከራከር የሚሰማን ወገን እንዳናገኝ ያደርጋል።
ወደ ህወሃቶች ስንሄድ፦ ከመሠረቱ ጋራ እየተዋጉ ነው፤ ስለዚህ ለውጥ በሚመጣበት ጊዜ . . በጣሙን ይፈረካከሳሉ . . . ይበታተናሉ። ምናልባት “ጫናው እየበረታ እና እየጨመረ በመጣ ቁጥር በወታደራዊ ክንፉ ያሉት ጄኔራሎች እና ሌሎች የፖለቲካ ክንፉን ወደ ጎን ገፋ አድርገው ከሌላው ጋራ ይተባበሩ ይኾን?” የሚል ሊኖር ይችላል። ነገር ግን እስከ አሁን እያየን ያለነው ተቃራኒውን ነው።
የኦሮሞ ተቃውሞ እና የልሂቃን ፉክክር
የኦሮሞ ተቃውሞ የሌሎች የፖለቲካ ኀይሎችን እገዛ እንደሚሻ ከዚህ በፊት ለሚዲያ ተናግረኻል፤ ከሌላው ልሂቅ ጋራ፣ ከሌሎች የፖለቲካ ሐይሎች ጋራ እንዴት መተባበር ይቻላል? የተለያየ ጥቅም በማሳደድ ዐይን ለዐይን መተያየት ያልቻሉትን የአማራ እና የኦሮሞ ልሂቃንን በምን የጋራ ጥቅምና እሴት ዙሪያ ማቀራረብ ይቻላል? አማካኝ መመዘኛው የት ጋር ነው ያለው?
ለእኔ ከአማካኝ መመዘኛው፦አንዱ የአንዱን ሕልውና መገንዘብ ነው፤ ሕልውና ሲባል እንደ ባሕላዊ ማኅበረሰብ፣ እንደ ፖለቲካ ማኅበረሰብ፣ የራሱ ማንነት እና የራሱ ሕልውና ያለው ማኅበረሰብ እንዳለ መገንዘብ ነው። የተለያዩ ዐይነት ፍላጎቶች እንዳሉም መገንዘብ ያስፈልጋል፤ እነዚህን ነገሮች እንዳሉ እንቀበላቸው ማለት አይደለም፤ እንዳለ “እንካ ውሰድ – እንካ ወስድ” ሳይኾን በትንሹ አበበ እንደ አበበ እንዳለ፤ በአካል ያለ አንድ ሰው ነው፣ በእኔ ቁጥጥር ስር አይደለም፤ በራሱ መቆም ይችላል ብዬ መቀበል መቻል አለብኝ። ማንነትን መቀበል መቻል አስፈላጊ ነው፤ አንዱ ይኼ ነው። ሁለተኛ፦ ደግሞ ዳኝነት የራሱን ጥቅም እና ፍላጎት በራሱ አንጥሮ ማውጣት የሚችል መኾኑን መቀበል አስፈላጊ ነው፤ ከዚህ ተነስተን እንግዲህ ከፍ ወዳለ ማኅበራዊ ደረጃ ስንወስደው ኦሮሞ እንደ ኦሮሞ ሕዝብ መኖሩን፤ አማራ እንደ አማራ ሕዝብ መኖሩን ግንዛቤ መውሰድ አለብን፤ ወይም ማንኛውም ቡድን በመረጠው መንገድ እና መልክ፤ የትኛውም የፖለቲካ ማኅበረሰብ ደግሞ የራሱ የኾኑ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች እንዳሉት መረዳት ያስፈልጋል፤ ከዚያ በኋላ እነዚህ ማኅበረሰቦች ለረጅም ጊዜ አብረው ከመኖራቸው የተነሳ በመሀል ቁርሾዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነዚያን መገንዘብም አስፈላጊ ነው፤ በጣም ሳያስጮኹ እና ሳያጋንኑ መኖራቸውን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፤ ያ ቅድመ ኹኔታ ይመሰልኛል፤ የአንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ሕልውና የሚረጋገጠው የራሳችን የሚሉት ማንነት እና ፍላጎት ተሟልቶ መገኘት ነው።
የግለሰብ ነፃነትና እኩልነት ጽንሰ ሃሳብን የቡድን መብት መጋገሪያ እያደረከው ነው?
አዎ። ይህን ከተቀበልን በኋለ እነዚህ የተለያዩ ማንነቶች በእንዴት ያለ መንገድ አንድ ወደመኾን ሊመጡ ይችላሉ የሚለውን ማሰብ ይቻላል፤ “የጋራ የኾነ የሚጋሩት ጥቅም መሠረት አድርገው፤ የጋራ ማንነት፣ የጋራ ጉዞ እንዴት ማድረግ እንችላለን?” የሚለው ላይ መነጋገር የሚቻለው ከዚያ የጋራ መሠረት ላይ ስንነሳ ነው፤ ሳስበው ወደዚያ መግባት የሚቻል ይመስለኛል፤ ብዙ ጊዜ የሚነሳው የአማራ እና የኦሮሞ ጉዳይ ነው፤ የአማራ እና ኦሮሞ ጉዳይ ሰዉ ዝም ብሎ ውስብስ ያደርገዋል እንጂ በጣም ቀላል ነው።
እነዚህ ሁለት ማኅበረሰቦች ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን አሁን በቅርብ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ እንደሚያሳየው ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በጋራ በጦርነት እና በሰላም፤ በመተባበር እና በመጋባት የኖሩ ማኅበረሰቦች ናቸው፤ ሁለት ትላልቅ የኾኑ ማኅበረሰቦችም ናቸው፤ ከዚህ የተነሳ ትልቅ የኾነ ዕምቅ አቅም አለ፤ ይኼ አዲስ የተጋባ ማኅበረሰብ አይደለም፤ ለ700 ዓመታት ሲጋጭ እና ሲተባበር የኖረ ማኅበረሰብ ነው። የፖለቲካ ትብብር ለመፍጠር ከዚህ ውስጥ አማራጭ መንገድ መገንባት ይቻላል። ግጭት የመፍታት መፍትሄ መገንባት እና ማምጣት ይቻላል። የእውቀት ክምችት፣ የልምድ ክምችት፣ በእውቀት የዳበረ ልምድ አለን።
ሕወሃቶች ደጋግመው የሚናገሩት ነገር አለ፤ “እኛ ከመሀከላቸው ከወጣን ኦሮሞዎች እና አማራዎች ይጫረሳሉ።” ይኼ የማይረባ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ሕወሓቶች ከመምጣታቸው በፊት ኦሮሞ እና አማራ ሲጣላም ሲተባበርም የኖረ ሕዝብ ነው። ሲጣላም በራሱ ጊዜ ነው የተጣላው፤ ሲታረቅም በራሱ ጊዜ ነው የታረቀው። በሕወሓት ሸምጋይነት አይደለም የተጣላውም የታረቀውም። ይኼ ለረጅም ዓመታት አብሮ ተጣልቶም ተፋቅሮም የኖረ ማኅበረሰብ አንድ ባዕድ አስታራቂ ነኝ ብሎ መሀሉ ላይ ሲገባ “ኣላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል ነው፤” ንፍጥ ነው እየለቀለቀ ያለው ሕወሓት። የሕወሓት ከእነዚህ ሕዝቦች መካከል መግባት ጊዚያዊ ችግር ሊፈጥር ይችላል፤ መሀል ላይ ኾኖ ወዲያ እና ወዲህ እየገፋቸው ነው ያለው፤ የኦሮሞ እና የአማራ ልሂቅ የየራሱን ፕሮፖጋንዳ መንፋቱን ትቶ ሕወሓትን ከመሀከል ለማስወጣት ፊት ለፊት በጋራ ሊጋፈጣቸው ይገባል፤ ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት ሲገጣጠሙ ክምችቱን ሰብሰብ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። በዚህ መገደድ ይዘውት የሚመጡት ልምድ ጥንት በጋራ የሸመኑት ብቻ ሳይኾን መጪውንም በጋራ ለመሸመን የሚያስችል ነገር እንዳለ ለማወቅ እንዲገደዱ ያደርጋቸዋል ማለት ነው። ያኔ ሲገደዱ ይዘውት የሚመጡት መፍትሄ እውነተኛ ወዳጅነት፣ እውነተኛ ትብብር እና የመጨረሻ መፍትሄ ሊኾን ይችላል።
ስለ ብሔር ማኔጅመንት የተጻፉ አዳዲስ ቲዎሪዎች “የተለያዩ ብሔሮች ባሉበት አገር ላይ አንድ ወጥ የኾነ አገር መፍጠር አይቻልም” ሲሉ ያትታሉ። ከኔሽን ስቴት – ስቴት ኔሽን እየተባለ ነው ያለው፤ ሁሉም የራሱ የኾነ ፖለቲካል ማኅበረሰብ አለው፤ ግን ሁሉም የጋራ የኾነ ይኖረዋል፤ ከዚያ ያልፍና በጊዜ ብዛት እርስ በርሳቸው ሲፋጠጡ አንዱ ገኖ የሚታይበት ሳይኾን በመዋጮ የሚገነባ የጋራ ማንነት ወደመገንባት ይሻገራሉ። የጠየቅኸኝ ትንሹን መመዘኛ ነው፤ ነገር ግን ከዚያ አልፎ መሀከልን ለመገንባት ቴክኒካል ነገሮች አሉ፤ ከሌሎች አገሮች ብዙ መማር እንችላለን፦ ለምሳሌ ከሕንድ።
ስለ ታሪካዊ በደል ብዙ ጊዜ ይነሳል፤ ሲነሳም በዋነኛነት የሚነሳው ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ነው፤ ያለፉትን መቶ ሃምሳ ዓመታት ከማየት አልፈህ ወደ ሰባት መቶ ዓመታት ለማየት ለምን መረጥህ? ብዙ ጊዜ የታሪክ ምእራፍ የምንምርጠው ለፖለቲካ አቋማችን ጠበቃ እንዲኾንልን ነው።
አሁን ላለው ፖለቲካዊ ልዩነት እና ንትርክ ምክንያት የሚኾነው ምኒልክ ነው፤ ነገር ግን ለግንኙነት የሚኾን መፍትሄ ስትፈልግ “ከምኒልክ በፊት ምን ነበር?” ብሎ መጠየቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚያ በፊት የነበረው በስፋት መጠናት እና መጻፍ ያለበት ነው፤ ከዚያ በፊት የአቢሲኒያ መንግሥት አለ፤ ዘመናዊ መንግሥት አልነበረም፤ በአጠቃላይ ጆግራፊክ የኾነ ግንኙነት ነበር፤ አማራው በመንግሥት ደረጃ፣ ኦሮሞው ለመንግሥቱ የሚገዛ ኾኖ ግንኙነቱን የጀመረው ከምኒልክ በኋላ ነው፤ ለዚያ ነው እዚያኛው ላይ ትኩረት ሳደርግ የነበረው፤ ያኛው አውድ አስፈላጊ ነው፤ በጣም አስፈላጊም ነው፤ ያ ማለት ግን ከምኒልክ በፊት የነበረው አስፈላጊነቱ አናሳ ነው ማለት አይደለም፤ ይኼንን ማጥናት የጀመርኩት ዛሬ አይደለም፤ ስታንፈርድ እያለሁ ወደ ኦክስፎር ሄጄ ነበር፤ እዚያ በነበርኩበት ወቅት የነበረኝን ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ያሳለፍኩት ፓሮኪያል ፓርቲ ፖለቲክስ ሳጠና ነበር፤ ግን ትኩረት ሳደርግበት የነበረው ቅድመም ኾነ ድኅረ ምኒልክ፣ ወይም ደርግ አሊያም ኢሕአዴግ የሚባል ነገር አልነበረም፤ ከ13ኛው እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የማኅበረሰብ አደረጃጀት ነበር። የመሐመድ ሐሰን መጽሐፍ የሚመስጠኝ፦ አንደኛ ያኔ የዚያን ጊዜ ያጠናኋቸውን ስለሚያስታውሰኝ ነው፤ መጽሐፉ ሁለት ነገሮችን ይዳስሳል። የኦሮሞ ባህል የሚለውን ነገር ግልጥልጥ (ዲሚስቲፋይ) ያደርገዋል፤ ከዚያ አልፎ ደግሞ ግንኙነቱ የሚነሳው ድኅረ ምኒልክ ብቻ ነው የሚለውን ሐሳብ በመጣል ከዚያ በፊት ብዙ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች እንዳሉ ያሳያል።
ድኅረ ምኒልክ የራሱ የኾነ ሚና አለው፤ ቅድመ ምኒልክ የነበረው ኹነት ደግሞ ድኅረ ምኒልክን ለመፍጠር የነበረው ሚና አለ፤ ድኅረ ሚልክ የነበረው ሚና ግን ቀላል አልነበረም፤ ምክያቱም ጠንካራ የኾነ የፖለቲካ ማኅበረሰብ እና የፖለቲካ ግንኙነት ፈጥሯል፤ ከዚያ በፊት የነበረው በየጊዜው የሚቀያየር እና የሚለዋወጥ ነበር። ከ13ኛው እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ግጭት እና ትብብር ቀላል እና ያልተወሳሰበ ነበር፤ ለውጡም ፈጣን ነበር፤ ይኼ ነው የሚባል ለረጅም ጊዜ የቆየ የበላይነትም ኾነ ትብብር አልነበረም። አንዱ የበታች – ሌላው የበላይ የሚባል ነገር ለማግኘትም አትችልም። የመጨረሻ ብለህ የምትለው ቁርሾም የሚሰጥ አይደለም። ፖለቲካዊ ልዩነት ሊፈጥር አልቻለም፤ ምክንያቱም በትናንሽ ደረጃ በተበታተነ መንገድ የሚታይ ስለኾነ፤ ለምሳሌ ሸዋ ያለው የአማራ ስቴት እዚያ አካባቢ ካሉት ጋር ነው የሚጋጨውም የሚተባበረውም፤ ጎጃም ያለው አማራ እዚያው አካባቢ ካለው የወለጋ ኦሮሞ ጋራ ነው የሚተባበረውም የሚጋጨውም፤ ጎንደር ያለው ደግሞ ከወሎ ኦሮሞዎች ጋራ ነው የሚያደርገው፤ በዚያ ጊዜ የነበረው ጠንካራ ወደሚባል ደረጃ ያደገ አልነበረም።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በአጠቃላዩ የዓለም ክፍል ቋሚ የኾነ የኢምፔሪያሊዝም መስፋፋት አይዲዮሎጂ የተከሰተው በ19መቶ ክፍለ ዘመን ነው፤ ከምኒልክ መምጣት በፊት በዝቅተኛ ደረጃ የነበሩት ግጭቶች እና ቁርሾዎች በአካባቢ እና በዙሪያቸው የሚከሰቱ እና የሚደርቁ ነበር፤ ይኹንና በዚያ የኢምፔሪያሊዝ የመስፋፋት ዘመን በቦታው ላይ የሚቀመጠው ምኒልክ እንኳ ባይኾን ለምሳሌ፦ ጦና ቢኾን ከዚያ ሊያመልጥ የሚችልበት ምንም ዐይነት አጋጣሚ የለም፤ በዚህም ምክንያት ድኅረ ምኒልክ የራሱ የኾነ ወሳኝ ሚና ነበረው። ይኼ ለመለስ ዜናዊም ይሠራል፤ ይኼ በምኒልክ ተክለ ሰብእና እና በመለስ ሰብእና ምክንያት የኾነ አይደለም። በጣም አስፈላጊ የኾነ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሽግግር በተከሰበት ሰዓት ነው እነዚህ ሰዎች ወደ ሥልጣን የመጡት። እነርሱ የወሰዷቸው ርምጃዎች ለአሁኑ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ የራሳቸው የኾነ ተጽዕኖ ነበሯቸው።
መለስን ስታነሳ . . . ሕወሃት የኦሮሞን ልሂቅ አይንቅም ነበር፤ አሁን ግን ንቀት አምጥቷል ብለኻል፤ አሁን መናቅ የጀመረውን ምኑን ነው? ለምንድን ነው?
ሕወሃቶች የኦሮሞን ሕዝብ አያውቁትም። በዚያ ወቅት ክብር እንኳን ባይኖር የኾነ ትውታ (deference) ይታይ ነበር። ሥልጣን እና ሀብት ሳያደልባቸው በፊት ልጆች በነበሩበት ጊዜ ኮሚኒስቶች ነበሩ፤ ተራማጅ ግለሰቦች ነበሩ፤ እነ መለስ፣ እነ ስብሃት፣ እነ አባይ የኢትዮጵያ ተራማጅ ንቅናቄ አንድ አካል ነበሩ። ከአማራው ልሂቅ ጋራ ጦርነት ውስጥ ስለነበሩ ጥላቻዎች እና ቁርሾዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከኦሮሞው ልሂቅ ጋራ ግጭትም ስለሌላቸው ሥልጣን እስኪይዙ ድረስ ተራማጅነታቸውም አላለቀም ነበር፤ ማርክሲስታዊ ጨዋነት ነበራቸው። ነገር ግን ሥልጣን ከያዙ በኋላ . . . ሀብት እያካበቱ በሄዱ ቁጥር አይነኬ ኾኑ፤ “እኛ ማን ይደርስብናል፤ እንዲህ እየዘረፍነው፤ እንዲህ እያደረግነው ጸጥ የሚለው ሰው ሁሉ ምንም አያመጣም!” የሚል ዕብሪት ውስጥ ገቡ፤ ራሳቸው የሚንቀሳቀሱበት የኾነ ኹነት ፈጠሩና ያንን ኹነት እውነት ነው ብለህ አመኑት፤ ደህና ደህና ኦሮሞዎች፣ ጠንካራ የኾኑትን በሙሉ ወይ በግድያ ወይ በስደት ታባርራቸዋለህ፤ አማራውንም ታባርረዋለህ፤ ከዚያ ከጎንህ የሚቀረው ማነው? በእውቀት ብቃት የሌለው፤ በትምህርት ትጋት የሌለው ልፍስፍሱ! እና ሕዝቡን እንዳለ በዙርያህ በከበበህ አቅመ ቢስ ልክ ትመዝነዋለህ። ኦሮሞን በኦሕዴድ ልክ መመዘን ጀመሩ። ኦሕዴድ ከውስጥ ራሱ ተመትቶ ተመትቶ ከላይ የቀረውን ቅራሪውን ነው ማነጻጻር የጀመሩት፤ “እንዴ ይኼ ጠላ አይደለም፤ አይረባም፤”አሉ።
አሁን ግን ከንቀት ወደ ፍርሃት እየሄዱ ነው። አሁን እጅግ በጣም አስፈላጊ የሚባለው የሽግግር ወቅት ላይ ነን። ስትንቀው የነበረ ዝኾን አንድ ቀን ሲነሳ ግዝፈቱን ታየዋለህ፤ አሁን ወደ ክብር ከመሄድ ይልቅ ወደ ፍራቻ እና ጥላቻ ውስጥ እየገቡ ነው፤ አሁን አባይ ጸሐዬ የሚናገረውን፣ ጌታቸው ረዳ የሚናገረውን ሌሎች በሶሻል ሚዲያ ያሉት የእነርሱ ልጆች የሚናገሩትን ስትመለከት የምናየው ይኼን ሽግግር ነው፤ የኦሮሞ ልጅ አንድ ጊዜ ተነስቶ ሲያንቀጠቅጣቸው ያ ንቀት በድንገት በአንድ ምሽት ወደ ፍርሃት እንዲሻገሩ አደረጋቸው፤ ይህ ፍርሃት ከጥፋታቸው ከመመለስ ይልቅ ጥፋታቸውን ለማጠናከሪያ ወደ ጥላቻ እየተለወጠ ነው። ይህ ደግሞ የሚወስዷቸውን ርምጃዎችም ያከፋል፤ ምላሹም የዚያኑ ያህል መጠኑ የጨመረ ይኾናል።
በነገራችን ላይ አንድ ደጋግሜ እየተናገርኩ ያለኹት እና የኦሮሞ አመራርም እየተናገረ ያለው ነገር በሁለት ወር ውስጥ የኦሮሞ ወጣቶች እና ገበሬዎች ክልሉን ሲያርበደብዱት፤ ነጻ ሲያወጡ አንድ ትግረዋይ አልተነካም፤ አንድ እንኳ! የኦሮሞ ወጣቶች ማሳየት የፈለጉት የእናንተም ሲቪሊያን ቢኾኑ በሰላም ይኖራሉ የሚለውን ነው፤ የኦሮሞ ልጆች ይኼን ከምናቤ ውጪ በኾነ መንገድ አረጋግጠውልኛል።
የኦሮሞ ተቃውሞ ሲነሳ ማስተር ፕላኑ ላይ ያተኮረ ነበር፤ አሁን ግን ከኩርማን ጥየቃ(minimalism) ወደ ስንዝር ፍለጋ(maximalism) የተሸጋገረ ይመስላል።
የዛሬ ሁለት ዓመት ጥያቄው አስቀድሞ እንደተነሳ ቢመልሱት ኖሮ ይቆም ነበር። በቀላሉ ሊያቆሙት የሚችሉትን ነገር እምቢ ብለው ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ዕብደት ውስጥ ገብተዋል። ከሕዝቡ ጋራ ደም ተቃቡ፤ ከዚህ በኋላ ጥያቄው ተቀይሯል፤ ተለውጧል፤ ያ ብቻ አይደለም፤ የማስተር ፕላኑንን ጥያቄ ከልብ አልመለሱትም፤ ማስተር ፕላኑን ያወጣው ሕወሃት ነው፤ የፌዴራል መንግሥት በሚለው ስም! የኦሕዴድ ተሳትፎም አልነበረም፤ የኦሮሞ ተሳትፎ አልነበረም፤ ይኼ ፕሮፖጋንዳ አይደለም፤ ኦሕዴዶች በቴሌቪዥን የተናገሩት ጉዳይ ነው። ያ ብቻ ሳይኾን ማስተር ፕላኑ እንደ ጥያቄ ይነሳ እንጂ የኦሮሞ ገበሬ እያለ የነበረው “የመሬት ዝርፊያ፤ የመሬት መቀራመት ይቁም!” ነው። ማስተር ፕላኑ ይኼን የመሬት ንጥቂያ እና ዝርፊያ ተግባራዊ ለማድረግ የወጣ ነው። የመሬት ቅርምቱ በስፋት ቀጥሏል። የመሬት ቅርምቱ እስካልቆመ ድረስ ትግሉ መቀጠሉ ደግሞ ግዴታ ይኾናል ማለት ነው። ከእንግዲህ በኋላ በኦሮሞ ማኅበረሰብ እና በሕወሓት መካከል የነበረችው በጣም ቀጭን ገመድ ነበረች፤ ያቺ ገመድ አሁን ብጥስጥሷ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ ኦሮሞ እነርሱ መፍትሄ ይሰጡኛል ብሎ አይጠብቅም።
እንበልና ተቃውሞው ውጤታማ ኾነ። በአብዮት ከሚወድቁ መንግሥታት በኋላ የሚመጡት መንግሥታት ተቋማዊም ኾነ ሌላ መፍትሄ ለማምጣት ሲቸገሩ ብቻ ሳይኾን ችግሩን የበለጠ ሲውሳስቡ እና አንዳንዴ ቀድመው ያልተገመቱ አዳዲስ ችግሮች (unintended consequences) ሲቀፈቅፉ ይታያል፤ ከዚህ አንጻር የለውጥ ሐይሎች የሚባሉት በሚመጣው የለውጥ ሂደት ውስጥ ድርሻቸው ምን ይኾናል? መጻዒውን የሕዝብ ድልስ ማነው ሊመራው የሚችለው? በምን መንገድስ ነው ተቋማዊ እና መዋቅራዊ መፍትሄ ማምጣት የሚቻለው?
አሁን አንተ ያነሳኸውን ጥያቄዎች ማንሳት ብቻ ሳይኾን መልስ መፈለግ ወሳኝ ነው። ከሌሎች አገሮች የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ ከራሳችንም ስህተቶች የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ። አንተ ያነሳኸው የአምባገነንነት ወይም ሌላ ትላንት ከነበረው ያልተለየ አወቃቀር ይመጣል ወይስ አይመጣም ለሚለው፤ በአንዳንድ አገሮች ስኬታማ በኾነ መንገድ የተሠሩ ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ፤ ከአረብ ስፕሪንግ ውስጥ ስኬታማ የኾነውን ቱኒዚያን ብትወስደው፤ በምሥራቅ አውሮፓ፣ ኤዢያ እና ላቲን አሜሪካ አካባቢ ስኬታማ የኾነ ሽግግር የተደረገባቸው ልምዶች አሉ፤ እነዚያን ልምዶች ቀረብ ብሎ ማጥናት እና ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው፤ አንዱ እኔ የማየው፦ የትግሉ ሂደት አሁን ያለውን አምባገነንነት ለማውረድ ዲዛይን የሚደረግበት መንገድ ሌላ አምባገነን እንዳይተካ ሊያደርግ ይችላል። ብቸኛ አውራ ፓርቲ፣ ብቸኛ የኾነ ግሩፕ እንዳይወጣ የምታደርግባቸው ዘዴዎች አሉ፤ ከዚያ ውስጥ ትግሉ በራሱ በአንድ የኾነ ቡድን ተጠልፎ እንዳይቀር በተለያየ መንገድ የተቀናጁ ሲቪክ ማኅበራት ትልቅ ሚና ሊኖራቸው ይገባል፤ የእነዚህ ሲቪክ ማኅበራት በየሰፈሩ እየተጠናከረ መምጣት የፖለቲካውን አካሄድ ቅርጽ ያስይዘዋል፤ በአንድ ምሽት የሚያድግ አምባገነንነት የለም፤ ሥልጣንን በማጠናከር እና የበላይነትን ለማሳየት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሚያድግ እንጂ። እንዲህ ያለውን የፖለቲካ ሥርዐት ገና ከእንጭጩ ለመቅጨት ሥልጣኑ ሳይፋፋ ራሱ እየተሸበበ እና ልጓም እየተያዘበት እንዲመጣ፤ እንዲሁም ከዚያ የሥልጣን ማጠናከር ወደ አምባገነንነት እንዳይቀየር ገድቦ ሊይዘው የሚችለው ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት መኖር እና መጠናከር ነው፤ ሲቪል ማኅበራት ማለት አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት በሕግ አሉ የሚላቸውን ዐይነት ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን አስደናቂ የኾኑ መንግሥት ሊመለከታቸው ያልቻለ የሲቪክ ማኅበራት አሉን፤ በማኅበራዊ መዋቅሩ ላይ መሠረት አድርገው የሚገነቡ፤ እነዚህን ከሥር ከመሠረት መገንባት አስፈላጊ ነው፤ የፖለቲካ ስትራቴጂው እና የትግሉ ዋና አካል እንዲኾኑ አድርጎ ማስኬድ ያስፈልጋል፤ እየተደረገም ነው።
ሁለተኛው ከቱኒዚያ የምንማረው ደግሞ አምባገነንነትን ስታስወግድ ማኅበራዊ ውሉም አብሮ ማለቅ አለበት፤ ሦስት ምዕራፎች ማለፍ አለበት፤ የመጀመርያው፦ የአገር ግንባታ የሚባለው ነው፤ ኢትዮጵያ እስካሁንም የአገር ግንባታ ሂደት ላይ ናት፤ ሁለተኛው ዲሞክራታይዜሽን ሲኾን፤ ሌላኛው ደግሞ ተፎካካሪ ወይም ተገዳዳሪ ፖለቲካ ነው። ዲሞክራሲ የምንለው ተገዳዳሪ ፖለቲካ ሲኖር ነው። አንድ አገር እንዴት ነው የአገር ግንባታ አልጨረሰም የሚባለው? የመንግሥቱ ተቀባይነት በተወሰነው የሕዝብ ክፍል የተረጋገጠ ነገር ግን በአብዛኛው ሕዝብ ደግሞ ተቀባይነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከኾነ ያ አገር ገና ግንባታውን አልጨረሰም ማለት ነው። ከዚያ ያንን የጨረሰ ከኾነ ወደ ዲሞክራታይዜሽን ይሸጋገራል። ዲሞክራታይዜሽን የሕግ የበላይነት ተግባራዊ የሚኾንበት ሂደት ውስጥ የሚያስገባ ነው፤ ከዚያ ደግሞ ዲሞክራሲ። እኔ ሳስበው ብዙ ጊዜ ችግሮች የሚፈጠሩት፤ የአገር ግንባታ ሳይጠናቀቅ ዘሎ ወደ ዲሞክራሲ ለመግባት በሚደረገው ጉዞ ነው። ምክንያቱም ገና ሰርተህ ያልጨረስኸው የጨዋታ ሕግ ስላለ። አገር ግንባታን የማጠናቀቅ ሂደት እና ወደ ሦስተኛው ምዕራፍ መሸጋገር፣ ሁለተኛውን እና አንደኛውን ምዕራፍ እንዲጣመሩ ማድረግ ይቻላል፤ እንዲቆላለፉ ልናደርጋቸውም የምንችልም ይመስለኛል። ግን ምንድን ነው፤ ያረጀውን መንግሥት በማውረድ ሂደት ሙከራ ውስጥ የፖለቲካ ውሉ፣ የማኅበራዊ ውሉ እና የጫዎታው ሕግ በአንድ ላይ ተጣምረው እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል። ቱኒዝያ ውስጥ (ለረጅም ጊዜ ልክ እኛ አገር በብሔር እንደሚያጋጨን) እዚያ የሚጋጩት በአይዲዮሎጂ ነበር፤ አምባገነኑ መንግሥት ሴኪዩላሪስቶች እና ኮንሰርቫቲቮችን እያጋጨ ነበር ሥልጣን ላይ የቆየው፤ በ2003 ፓሪስ ላይ ስምምነት ፈጥረው፤ ከ2003 እስከ 2011 ድረስ ሲስተሙን ለመቀየር በጊዜ ሂደት የማኅበራዊ ውሉ፣ የፖለቲካ ውሉ እና የጨዋታው ሕግ እንዲጣመር አደረጉት፤ ከዚያ ቤን አሊ ሲወድቅ የማኅበራዊ ስምምነት ውላቸውን አወጡት፤ ያ ኮንትራት ደግሞ ሁለት ሦስት ጊዜ እየወደቀ እየተነሳ በጊዜ ተፈትኗል፤ እንደመጡ አብላጫ የነበረው የወግ አጥባቂው ቡድን ነበር፤ ነገር ግን ኮንትራቱ ስለማይፈቅድላቸው በዚያ ምርጫ ሲኩላሪሶቶቹ በምርጫ እንዲሳተፉ አደረጓቸው፤ ወደ ዲሞክራታይዜሽን የሚወስደውን ሂደት በቀላሉ መዝለል ቻሉ።
ግብጽ ላይ ግን ስህተት ሠሩ። መንግሥቱን ካወረዱ በኋላ የማኅበራዊ ውሉን ከማምጣት ይልቅ፣ ወደ የጫዎታው ሕግ የሚያስገባውን የአገር ግንባታ ሂደት ከመቀበል ይልቅ፤ ከአምባገነንነት በቀጥታ ወደ ተገዳዳሪ ፖለቲካ ገቡ። የጨዋታ ሕግ ሳይኖር፣ የገበያ ዋጋ ሳይተመን፣ ግዢው ውስጥ ነው የገቡት ማለት ነው። በቀጥታ ወደ ምርጫው ሲገቡ ምንድን ነው የኾነባቸው፤ በርግጥ ኀይል የነበረው ወግ አጥባቂ የኾነው የሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን ነው፤ እነርሱ ምርጫው አሸነፉት፤ መከላከያው መታቸው፤ ከዚያ አብዮት ተፈጠረ። ወደነበሩበት ተመለሱ፤ ወደ ሙባረክ ዘመን ሄዱ፤ አንድ የኾነ ቦታ ለመድረስ አቋራጭ መጠቀም ማየት አልብኝ ካልክ ብዙ ነገር እንዲያመልጥ ያደርግኻል፤ መንገድ ላይ የምትረሳቸው ነገሮች ይኖራሉ፤ ተመልሶ ማንሳት ግድ ይላል፤ እና ግብጾች ምንድን ነው ያደረጉት፤ ከምዕራፍ አንድ እመር ብለው ምዕራፍ ሦስት ውስጥ ገቡ። ምዕራፍ ሦስት ላይ ሲደርሱ ምዕራፍ ሁለት ላይ ምንም ስላልተሠራ ባዶ ነው፤ የጫዎታው ሕግ እና የማኅበራዊ ውል ስለሌላ ትልቅ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅ ተፈጠረ። ያለ ጠንካራ ማኅበራዊ ውል እና ያለ ጠንካራ የጫዎታ ሕግ የማኅበራዊ ምስቅልቅ ፈጽሞ የማይቀር ይኾናል፤ የደኅንነት መዋቅሩንም ይበጣጥሰዋል፤ የፖለቲካ ኹኔታውንም ያናጋዋል።
ሁለተኛው፦ በልሂቃን እና ምሁራን ደረጃ፦ የማኅበራዊ ውሉ እና የጫዎታው ሕግ አሁኑኑ መገንባት አለበት፤ ተባብረን ሄደን ይኼን ሰውዬ እንናደው ብቻ ሳይኾን፤ ለነገው ምን እንገነባለን የሚለውን ከአሁን መጀመር አለብን፤ ከላይ ጣሪያውን ታስረዋለህ፤ ከሥር በሲቪክ ማኅበራት ጥሩ መሠረት ታስቀምጥለታለህ፤ ከላይ ደግሞ እንዳያፈስ ጥሩ ጣርያ ትገነባለታለህ፤ ከዚያ ምሰሶው ይጠናከራል ማለት ነው፤ በዚያ መልኩ መሄድ ያስፈልጋል።
ዳያስፖራውስ….
የዳያስፖራው ሚና በተመለከተ በተለይ ሁለት ሚና ሊኖረው ይችላል፤ ነጻ በኾነ ኹኔታ ውስጥ ስላለ የማኅበራዊ ውሉን በምሁራን ደረጃ እና በፖለቲካ ደረጃ ሚዲያውን እና ያሉትን ነገሮች ሁሉ ተጠቅሞ ማሳደግ ይችላል፤ ብዙ ነገሮችን ሊጨርስ ይችላል፤ ልክ አሁን አንተ እንደምትሠራው፤ አሁን አንተ እያደረግህ ያለኸው ነገር እስካሁን ሳወራ የነበረውን ነገር ነው። እኔን እና ሌሎች ሰዎችን ኢንተርቪው በማድረግ ማኅበራዊ ዉሉ እንዲያድግ እና እንዲሰፋ ሚዲያው ትልቅ ሚና አለው፤ የኮሚኒቲዎች መሰባሰብ እና የመሳሰሉት ነገሮችም እንዲሁ። መሠረት እና ውኃ ልክ ማስቀመጥ ላይም ሚና አላቸው። በመሬት ላይ ላሉ አሰባሳቢዎች እና ለሚዲያ ጥሩ ግብአት በመኾን ያገለግላሉ። ለምሳሌ በአቅማችን ያደርግናቸውን ነገሮች ብታይ፦ ከእያንዳንዱ ቀበሌ ድምፆችን እናሰማ ነበር፤ በእያንዳንዱ ቀበሌ ኦኤምኤን አገልግሎት ይሰጣል፤ ከላይ ላሉት የፖለቲካ ሰዎች የምንሰጠውን ያህል ከሥር ላሉትም እየሰጠን ኀይላቸው እንዲጠናከር እናደርጋለን፤ ያሉንን ግብአቶች እንሰጣቸዋለን። በዚያ መልኩ ዲያስፖራው ሲቪክ ማኅበራቱን በማጠናከሩ ረገድ ትልቅ ሚና መጫዎት ይችላል፤ በማበረታታት፣ በማጠናከር፣ በመደገፍ እና በማደራጀት።
የኦሮሞ ጥቅም አስጠባቂ ቡድን ማነው? ዴሞክራሲ በሌለበት አገር ሁሉም እየተነሳ የሕዝብ ወኪል ነኝ ይላል።
ኦሮሞው ጥሩ ወኪል አለው፤ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ግልጽ በኾነ ኹኔታ የኦሮሞን ውክልና የራሱ አድርጓል፤ አገር ቤት ናቸው፤ ከውጪ እየተሰጣቸው ያለ ተቀባይነት አለ፤ በሕወሃትም ኾነ በዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲው ዘንድ የኦሮሞውን ውክልና በመውሰድ ረገድ የኦፌኮ ድርሻ ከፍ ያለ እንደኾነ ግልጽ ነው። በኦሮሞ ስም ኾነው መደራደር የሚችሉ ናቸው፤ በመሬት ላይ አሮሞን የሚወክሉ ናቸው። ሌላው እዚህ ያሉት የአድቮኬሲ ሥራ መሥራት ይችላሉ፣ እያንዳንዱ ኦሮሞ የኦሮሞን ውክልና ይወስዳል ብዬ ነው የማስበው። ሜምፊስ ያለው የኦሮሞ ኮሚዩኒቲ የኦሮሞን ጥቅም ማስጠበቅ ይችላል፤ በዚያ መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። ነገር ግን በአገር ውስጥ ኦፌኮ ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ ያለው ድርጅት ነው። ኦሮሞ አንድ ብቸኛ ፓርቲ አለው፤ እርሱም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ነው። ያ ስብስብ እና ጥንካሬ ዋነኛው ስኬት ነው። ጥሩ አመራር አላቸው፤ ያ አመራር ሕዝቡን ይወክላል፤ ከዚህ ደግሞ ድጋፍ ይሰጣቸዋል፤ ውጪ ደግሞ የዲፕሎማሲ ሥራ በተለያዩ መልኩ እየተሠራ ነው።
በሲቪክ ማኅበራት ደረጃ እያጠናከርን ስንሄድ ማኅበራዊ ኮንትራቱን እንዲሻሻል፤ እንዲያድግ፣ እንዲጠናከር እና እንዲለወጥ እያደረግን ስንመጣ የራሳቸው ወኪል የኾኑ መሪዎችን ማፍራታችን የማይቀር ይኾናል፤ የለውጥ ወኪል የኾኑ አካላት በጊዜ ሂደት ተቀባይነትን በማግኘት ይወጣሉ፤ የፖለቲካ ካፒታላቸውን በእጃቸው በማስገባት እና ራሳቸውን በማሳደግ የለውጥ ወኪሎች በራሳቸው ሰዓት መውጣታቸው አይቀርም። ትኩረት ማድረግ ያለብን የማያቋርጥ ለውጥ ተግባራዊ እንዲኾን ማድረጉ ላይ መኾን አለበት። የማያቋርጥ ዝግመተ ለውጥ፤ እና ኹኔታው ባለበት ተግትሮ እንዳይቀር ማድረግ፤ በየጊዜው መግፋት፤ ስትገፋው ያ ለውጥ ይመጣል፤ ይኹንና የኦሮሞን ውክልና በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ስናስብ የኦሕዴዶችን ሚና ዝቅ ያለ ግምት ልንሰጠው አንችልም፤ እኔ እና አንተ አይደለንም አገር የምናስተዳድረው፤ ማን እንደሚያስተዳድርም ላናውቅ እንችላለን፤ ቢሮክራሲው ውስጥ ያሉት ብዙ ሰዎች እንዲለወጡ ተደርገው፣ መጀመርያ ከዚህ አምባገነን ሥርዐት ነጻ ከወጡ በኋላ እንደገና ተሠርተው አስተዳደር ውስጥ የሚሳተፉበት ዕድል ሁሉ አለ። መጪውን ጊዜ ያለ እነሱ ማሰብ የሚቻልም አይመስለኝም፤ እና ያንን ሁሉ ስሌት ውስጥ እያስገቡ ማየቱ አስፈላጊ ይመስለኛል።
በምዕራብ ሸዋም፣ በምሥራቅ ሸዋም፣ በኦሮሞ ተዋቃውሞ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከስም ዝርዝሩ ውስጥ ከፊሉ የአማራ ስም ያላቸው ናቸው፤ ይህ ጉዳይ ከማንነት ጥያቄም አልፎ ጉዳዩ የመሬት ጥያቄ መኾኑ ያሳያል የሚሉ ሰዎች አሉ፤ አንተ ይኼን እንዴት ታየዋለህ?
ጥያቄውን የኢትዮጵያ ጥያቄ ብለህ ብትለው ስህተት አይደለም፤ ምክንያቱም ጥያቄው የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው። እንዴት ስትል፤ የመሬት ዝርፊያ እየተካሄደ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰማንያ ምናምን በመቶ የሚኾነው ገበሬ ነው፤ ሕይወቱ ከመሬት ጋራ የተያያዘ ነው፤ ያለችው ብቸኛ ሀብት ደግሞ መሬት ብቻ ናት። ያቺ ትንሽ መሬት ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የለችም፤ ልጆቹ መሬት መውረስ አይችሉም፤ ምክንያቱም እንውረስ ቢሉ ለመኝታ የሚኾን ቦታ አያገኙም። አባት ለልጆቹ እንኳን ቆራርሶ መስጠት የማይችላትን መሬት ነው መንግሥት እየነጠቀ እና እየዘረፈ ያለው፤ እና ከዚያ ጋራ በርግጥ ከአዲስ አበባ ጋራ ከመቅረቡ ጋራ ተያይዞ ቀጥተኛ ተጠቂ የኾነው ኦሮሞ ኾነ እንጂ፣ በዚያ ያለው አማራ ቢኾን ልዩነት የለውም፤ አዋሳን ለማስፋፋት በሚል ከዚያ አካባቢ እየተፈናቀለ ያለው የሲዳማ ሕዝብ ቀላል አይደለም። ወደ አማራ እንሂድ፣ ለምለም የኾነው የአማራ መሬት ያለው መተማ አካባቢ ነው፤ መተማ አካባቢ ያለው ገበሬ ተፈናቅሏል፤ ወልቃይት እና ጠገዴን እንውሰድ፤ ሌላኛው ለምለም የአማራ ክልል ነው፤ ተቆርሶ ተወስዷል፤ ታሪካዊ የኾነ ገዳምን የማፍረስ ትልቅ ስጋት አለ፤ በአጠቃላይ በገበሬ ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው። በኢትዮጵያ መሠረት ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው። የኢትዮጵያ መሠረት የቢዝነስ መደብ አይደለም፤ የቢዝነስ መደብ የለም፤ የኢትዮጵያ መሠረት የአገልግሎት ሰጪ ተቋም አይደለም፤ የኢትዮጵያ መሠረት ግብርና ነው፤ እነርሱ አሁን እንደሚቀደዱት ይኼ” መካከለኛ ገቢ” ካላቸው ተርታ እያሉ እንደሚሉት አይደለም፤ ይኼ እነርሱ የሚያወሩት የመሃይም ወሬ ነው። ራሳቸውን እንዴት እያሞኙት እንደኾነ ጨርሶ አልገባቸውም፤ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ገበሬው ነው። ኀይለሥላሴ የተፈናቀለው ገበሬውን ሲነካ ነው፤ ምክንያቱም ገበሬውን ስትነካ መሠረቱን ታናጋዋለህ፤ በቀለ ገርባ ተወዳጅ የኾነበት ምክንያት ከምንም ነገር በላይ የመሬት ጉዳይ ይዞ ስለተነሳ ነው። ብዙ ሰዎች እስር ቤት የገባው በሌላ ነገር ይመስላቸዋል፤ እስር ቤት የሄደው፦ በምርጫው ላይ ከማንም በበለጠ ስለ መሬት ሲናገር የነበረው እርሱ ስለኾነ ነው፤ ከዚያ አልፎ ደግሞ አምነስቲዎች የታሠረ ሰው ዐሳየን ሲሉት ምን አደረገ? ገጠር ይዟቸው ሄዶ የተፈናቀለ ሰው አሳያቸው፤ የታሠሩት ሰዎች የታሠሩበትን ዋና ምክንያት ማየት አለባችሁ ብሎ። እሥረኞቹ ምልክቶች ናቸው፤ ምክንያቶች አይደሉም፤ ዋናው ምክንያት መሬት ነው፤ ለዚያ ነው ለሥርዐቱም ዋነኛ አደጋ የኾነበት።
ይኼ ከግብርና ውጪ በሚተዳደረው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ አለው? አዎን! ባለፉት ዐሥር ዓመታት የጤፍ ዋጋ ወደ አንድ ሺህ ፐርሰንት ያህል ጨምሯል፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለምንድነው በዚህ ያህል መጠን የጤፍ ዋጋ ሊጨምር የቻለው ብሎ መጠየቅ መቻል አለበት። ለምንድን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ እህል የተወደደው? ለምን?! የአንድ ሠራተኛ ደሞዝ አንድ ሺሕ ብር ኾኖ የጤፍ ዋጋ ሁለት ሺሕ ብር የኾነው ለምንድን ነው? የከብቶች ዋጋ በዚህ ደረጃ የናረው ለምንድን ነው? ምክንያቱ ከግብርና ጋራ ስለሚያያዝ ነው፤ ገበሬው በሁለት መልኩ ነው እየተጠቃ ያለው፤ አንዱ መሬቱ እየተነጠቀ ኢ-ምርታማ ለኾነ ነገር እየዋለ ነው፤ ድንጋይ መኮልኮያ ኾኗል፤ ሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ድንጋይ ነው የተኮለኮለው እንጂ ምንም ምርታማነት የለም፤ ምንም ዐይነት ገቢ አያስገኝም፤ አንድ እሱ አለ።
ሁለተኛው፦ ገበሬው ባለችው መሬት የነፍስ ወከፍ ገቢውን ከፍ እንዳያደርግ አድርገውታል፤ ማዳበሪያን ከውጪ የሚያስመጣው አማልጋሜትድ ነበር፤ ገብረየስ ቤኛ ይባላል። ይኼ ሰው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ደርግ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ሲወርስ የእርሱን ኩባንያ አላደረገውም፤ በተወዳዳሪነት ትንሽ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ይደረግም ነበር፤ ይሸጡ ነበር፤ ሕወሃት ምን አደረገ? ልክ እንደመጡ እነዚህ ዘጉና በአንድ ካምፓኒ ስር አስገቡት፤ ማዳበሪያ የሚያስመጣው አንድ ኩባንያ ነው፤ ዋጋውን የሚተምነው እርሱ ነው፤ ገበሬው ገንዘብ ቢኖረው እንኳ መግዛት አይችልም፤ በብድር ነው የሚሰጠው፤ ይኼን ብድር የሚሰበስበው ማነው? የመንግሥት ወኪል ነው፤ የልማት ወኪል (ዲኤ) እየተባለ የሚጠራው ነው፤ ዋጋው የማይነቃነቅ ነው፤ ልትደራደርበት አትችልም፤ የገበያ ሕግ የለውም፤ በየጊዜው ይጨምራል፤ ታህሳስ በመጣ ቁጥር ከወለድ ብድር ትከፍላለህ፤ አንድ ገበሬ አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ገዝቶ ያለምንም ጥርጥር ምርቱ ይጨምርለታል፤ ግን ያን ምርት ሸጦ ነው መልሶ የሚከፍለው። ከመለሰው ላይ በቂ ትርፍ ቀርቶ ለዓመት የቀለብ ፍጆታ የሚኾን አይተርፈውም፤ ከዚያ ምን ይሉኻል፤ የግብርና ምርት ዕድገት አሳየ ይሉኻል፤ እነርሱ አደገ ይላሉ፤ እውነታው ግን ወድቋል። በርግጥ ባለፉት ኻያ አምስት ዓመታት የታረሰው መሬት ጨምሯል፤ የነፍስ ወከፍ ገቢው ግን ቀንሷል፤ ይኼ ለገበያው ወድነት ሚና አለው። ይኼ ብቻ አይደለም። ድሮ አንድ ሰንጋ ገበሬው ከገጠር ይዞ ይመጣና ድሙጋ ይሸጡታል። የድሙጋ ነጋዴ የሚቀጥለው ከተማ መቻራ ላይ ይሸጠዋል፤ የመቻራው ገለምሶ ያደርሰው እና ከገለምሶ አዳማ፤ የአዳማው አዲስ አበባ። በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ የገንዘብ ልውውጥ ይደረጋል፤ ገበያ አለ። አሁን ምን አደረጉ መሰለህ? ኮፕሬሽን በሚል ከገበሬው ላይ በቀጥታ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ወይም ወደ ውጪ ላኪዎች ይገዟቸዋል። ቦረና ላይ ሄጄ ያየኹትን ልንገርህ፦ ከየአቅጣጫው የሚመጣውን ምርት የሚሸጥበት ጉምሩክ የሚባል ትልቅ ገበያ አለ። እዚያ ከብት ይሸጥ ነበር፤ ከአዋሳ እና ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡት ከዚያ ገዝተው አዲስ አባባ አድርሰው እንደዚያ ነበር የሚሸጠው። የሰንጋ ንግድ ድሮ በጣም የታወቀ ነው፤ በውስጡ ብዙ ሰዎች ይተዳደሩበት ነበር፤ አሁን የሰንጋ ንግድ የሚባል ነገር የለም። ምክንያቱም ኮርፖሬሽኖቹ ነጥቀዋቸዋል። እዚያ በቅርብ ያለ የሸዋ ገበሬ ደግሞ በሬውን ነድቶ አምጥቶ ይሸጠው ነበር። ያ አሁን ላይደገም ጠፍቷል። አሁን ኮርፖሬሽኖቹ (ሁለት ሦስት ኩባንያዎች ናቸው) ሄደው ከገበሬው ላይ አፍነው የሚገዙት። ዋጋውን የሚተምኑለት እነርሱ ናቸው፤ አዲስ አበባም የሚሸጡ እነርሱ ስለኾኑ ዋጋውን የሚተምኑት እነርሱ ናቸው።
ባለፈው የከብት ዋጋ ቀነሰ ተብሎ ሲነገር ነበር፤ ለምን መሰለህ? በድርቁ ምክንያት ገበሬው ከብቱ ከሚሞት መንግሥት የፈጠረውን ሥርዐት በጣጥሶ በቀጥታ ወደ ገበያ ይዞት ወጣ፤ ለዚያ ነው ዋጋ የወደቀው። ለምንድን ነው እዚህ ዝርዝር ውስጥ የምገባው? ይኼ ገበሬውን የማፈናቀል፤ ገበሬውን የመዝረፍ ኹኔታ የገበያ ንረቱ ላይ ያለው ሚና ቀላል አለመኾኑን ለማሳየት ነው፤ ጥያቄው የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው የሚል ሐሳብ የሚያነሱ ሰዎች በዚህ ረገድ ትክክል ናቸው፤ እንዲያውም ገፋ አድርገው ሊሄዱበት ይገባል። ገበያው ላይ ከፍተኛ ጫና አምጥቷል፤ ስለዚህ የአድዓ በርጋ ገበሬ ጥያቄ አዲስ አበባ የሚኖረው የሸምሱ ጥያቄ ነው፤ የሄለን እና የኅሊና ጥያቄ ነው፤ ምክንያቱም በእርሷ ደሞዝ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እየፈጠረ ስለኾነ። በዚያ መልኩ ቅርጽ መስጠቱ አስፈላጊ ነው።
ስለስሞች በተነሳው ላይ ዋናዋና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሦስቱ ሸዋዎች ናቸው። ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምሥራቅ ሸዋ፤ በተለይ ሁለቱ ሸዋዎች። መሬት እየተቀሙ ያሉትም እነርሱ ስለነበሩ ከፍተኛ ንቅናቄም የተደረገው እዚያ አካባቢ ነው። የሚገርመው ከዐጼ ምኒልክ በኋላመንግስት እዚያ አካባቢ የተዋጋውለመጀመርያ ጊዜ ነው። እነዚህ ሰዎች ጦርነት ልትከፍትባቸው የሚገባ ሰዎች አይደሉም፤ በየቀኑ በበራቸው ላይ የምታልፍ ሰዎቸ ናቸው። ሕወሃት የፈጸመው ትልቅ ስህተት (ደርግ እንኳ በሩ ላይ ከማንም ጋራ ተዋግቶ አያውቅም) በበራቸው ላይ ጦርነት ማድረጉ ነው፤ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ በቤተመንግሥት ደጃፍ ላይ ጦርነት የተካሄደው ዛሬ ነው። ይህ ሕዝብ ደግሞ መቼው የሚተው ሕዝብ አይደለም። እኔ ጠንቋይ አትበለኝ እንጂ የሕወሃቶች መቀበሪያ አምቦ እና ግንደ በረት እንደሚኾን ምንም ጥርጥር የለም።
የኦሮሞ ተቃውሞ የሕዝብ ነው?
እስቲ ስለፖለቲካል ኢኮኖሚ እናውራ። የአዲስ አበባ ሰፈሮች ፈርሰው ደኻ ከተሜ መፈናቀል ከጀመረ አረፋፍዷል። የኦሕዴድ ሰዎች የኦሮሞ ገበሬ እያፈናቅሉ ለአዲስ አበባ ልሂቅ መሬት ሲቸበችቡ ከርመዋል። አሁን ጫጫታው የመጣው ኦሕዴዶች የጀመሩትን ሕወሃቶች በከፍተኛ ደርጃ ለመግፋት ስለፈለጉ አይደለም? በኦህዴድ እና በሕወሃቶች መካከል የሚደርግ የጥቅም ግጭት በሕዝብ ጥያቄ ስም መጣ እንጂ በእውን የሕዝብ ጥያቄን ያነገበ ጩኸት አይደለም የሚል ትንተና የሚሰጡ አሉ። የሕዝብ ጥያቄ ከኾነ ለምን ኦሕዴዶች ያለተጠያቂነት የገበሬ መሬት እየነጠቁ ሲቸበችቡ አልተነሳም?
በአጠቃላይ አክቲቪዝም እስኪጀመር ድረስ ከእውነታ የመገንጠል ኹኔታ ነበር፤ የኢትዮጵያ አክቲቪዝም በጣም አይዲሎጂካል ኾኖ ከዕለት ተዕለት ሕይወት ጋራ ያልተሳሰረ ስለነበረ አሁን አንተ የምትለውን እውነት ብዙ የሚገነዘብ አልነበረም። ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ ዲሞክራሲ አለ ወይ፣ ነጻ ሐሳብ አለወይ? በሚለው ጉዳይ ላይ የመጠመድ ነገር ነበር፤ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ አማካይ የምትላቸው ቶላዎች፣ አዝምብጤዎች፣ ሐጎሶች እና ኦጁሎዎች አልነበሩም። የአክቲቪዝም ሕይወት እኮ ችግር ውስጥ ነበር። አንዱ ስንል የነበረው፦ አክቲቪዝሙ ማውራት እና መነጋገር ያለበት ስለ ዳቦ እና ስለ ቅቤ መኾን አለበት ነበር። ያ አንዱ ችግር ይመስለኛል። ሁለተኛው ኦሕዴዶች ሲያፈናቅሉ ተቃውሞ አልነበረም ወይ? በደንብ ነበር፤ ዶክተር መረራ እኮ በ2005 ምርጫ ላይ እና ከዚያም በፊት ሲናገር የነበረው ይኼንኑ ነው፤ አክትቪስቶቹም መቶ በመቶ ትኩረት ሰጥተው አያድርጉት እንጂ እንደ ዋና ጉዳይ ያዩት ነበር። በተግባር ዛሬም ቢኾን እኮ መሬቱን ከገበሬው እየነጠቀ የሚሰጠው ኦሕዴድ ነው። ከብሔርተኝነት አልፎ አንዱ ሕወሓት እና ኦሕዴድ የተጣሉበት እንደ ፖሊስ ኾነው በሚሰጧቸው ትዕዛዝ ነው፤ ይኼ የመጣው ደግሞ ከ2001 እ.ኤ.አ ከተማ ማስፋፋት የሚሉት የኢኮኖሚ መመሪያ ሲመጣ ነው። ኦሕዴዶች ሲያደርጉ የነበሩት ምንድነው፦ ያንን ትዕዛዝ ማስፈጸም ነው፤ ሲያስፈጽሙ በመሀከል ቆርሰው ይወስዳሉ። ኮሚሽን ነበር የሚያገኙት። ከሁሉም ብሔሮች በደላልነት ሀብታም የኾነ ስንት የምናውቀው ሰው አለ። ሕወሓቶች ይኼንን ኮሚሽን መከልከል ፈለጉ፤ ለምን ኮሚሽን እንክፈል የሚል መጣ። አንድ የሰበታ ከንቲባ የታሰረበት ጉዳይ አለ። ትዕዛዝ እምቢ አይልም፤ ግን ኮሚሽን መከፈል ነበረበት። ለአንድ የሕዋሓት ሰው መሬት እንዲሰጥ ሲባል እምቢ አላለም፤ ኮሚሽን ጠየቀ፤ “እንዴት አባክ” ብሎ ሽጉጥ አወጣበት። ያኛውም ታጥቋል ሽጉጥ ተማዘዙ። ይኼ በጣም አስፈላጊ መኾኑን የምታየው፤ የኦሕዴድ ካድሬዎች የእነርሱ ጥቅም ከሕዝቡ ጥቅም ጋራ የተሳሰረ መኾኑን ያዩት እንዲህ ዐይነቱ ችግር ወስጥ እየገቡ ሲመጡ ነው። ከዚያ በፊት ምን እየተከናወነ እንደኾነ አልገባቸውም። መሬት ተላልፎ እየተሰጠ እንደኾነ አልተረዱትም። ሲስተማቲክ በኾነ መንገድ የመሬት ሽግግር እየተከናወነ እንደበነበር አልተረዱትም። አሁን ምን ማለት ጀመሩ፤ ኮሚሽንም ተከልክለን፣ከሕዝባችንም ነጥቀን፣ እንዴት ይኾናል የሚለው መጣ። ያኔ ነው ከትግሉ የተቀላቀሉት።
ሕወሓት ላይ የሚነጣጠርበት ምክንያት ይኼን ኮሚሽን የሚሠሩት ሰዎች በተጨባጭ ብዙ ጊዜ ተይዘው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ወይም ከኢሕአዴግ ቢሮ ተላከ በሚባል ደብዳቤ በቀጭን ትዕዛዝ እነዚህ ሰዎች ተፈትተው ሌላ ቦታ ይሾማሉ። ሸዋ ላይ የተከሰሱት አርሲ ላይ ሄደው አስተዳዳሪ ይኾናሉ። አርሲ ላይ የተያዙት ሐረርጌ ላይ ሄደው አስተዳዳሪ ይኾናሉ። ይኼ ምንድን ነው የሚያሳይህ፧ ሥርዐቱ እነዚህን ሰዎች ይፈልጋቸዋል። ከፍ ባለ ደረጃ ስትመለከተው ደግሞ፦ ምን እየተደረገ ነው? አማራም፣ ጉራጌም ማንም መሬቱን በኮሚሽን ይሽጥ ማንም ምንም ያድርግ፤ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ ነው ይኼ ነገር እየሄደ ያለው። መሬት ከኦሮሞ ገበሬ ተነጥቆ ለትግራይ ነጋዴ እየተሰጠ ነው፤ እየተላለፈ ነው። “እነዚህ የትግራይ ነጋዴዎች እነማን ናቸው?” ብለህ ፕሮፋይል ስትመለከት፤ ከዚህ በፊት ወታደር የነበሩ፤ በከተማው ውስጥ ሰላይ የነበሩ ሰዎች፣ በ1990ዎቹ ከሚሊተሪ ከወጡ በኋላ የኮንትሮባንድ ንግድ አጧጡፈው ከሶማሌ እና ከጂቡቲ ያለ ቀረጥ ዕቃ አስገብተው ገንዘብ ያካበቱ ናቸው፤ ይኼን ገንዘብ ምን ማድረግ ጀመሩ፤ ከጋምቤላ እና ከደቡብ እንዲሁም ከኦሮምያ መሬት ወስደው አበባ ተከሉ፤ እርሻ አረሱ፣ ቡና አመረቱ። ከዚያ በተጨማሪ አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ለምሳሌ ወደግል ተዛውሯል። ይኼ የሀብት ዝውወር የተደረገው ሕገወጥ በኾነ መንገድ ባካበቱት ሀብት ነው። ይህን ያካበቱትን ገንዘብ በተጨማሪ ኢንቨስት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለው አሰቡ። መቀሌ እንዳይሄዱ አልኾነላቸውም፤ ምክንያቱም ሩቅ ነው፤ ስለዚህ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የትግራይ ቋሚ ሰፋሪዎችን መፍጠር አለባቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ኬፕታውንን መሥራት ፈለጉ። ይኼ ኬፕታውን የት ይኹን? በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ። ለምን? ምቹ ነው፤ ሜትሮፖሊታን ነው፤ ምናልባትም ለመጪው ጊዜም አስተማማኝ የኾነ ሥፍራ ነው።
ስለዚህ እንደ እኔ ላለው አክቲቪስት የትኛው ነው የበለጥ አስፈላጊው እና ትኩረት የሚያሻው? የገበሬው መጎዳት! ይኼ የገበሬው መጎዳት ደግሞ መሬቱ ወደየት ነው እየተሸጋገረ ያለው የሚለውን እንድታስብ ያደርግኻል። የአጭር እና የረዥም ጊዜ ፖለቲካዊ ተጽዕኖውስ ምንድን ነው? ይኼ አንድ ሐጎስ የሚባል ግለሰብ ስለወሰደው ጉዳይ አይደለም፤ ቋሚ የኾነ የአንድ ብሔር የበላይነት እየተፈጠረ ነው። ወደፊት የሚፈጥረው የማኅበራዊ ክፍፍል እና ምስቅልቅል ይዞት የሚመጣው የኢኮኖሚ የበላይነት እና የበታችነት ችግር በጣም አደገኛ ከመኾኑ የተነሳ ማስቆም መቻል አለብህ።
ኢትዮጵያ ባለፉት 11 ዓመታት በርካታ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ዐይታለች። ከእነዚህ ውስጥሦስቱን ብዙ ሳናጋንን ምሁራን ‘ሜጀር ፕሮቴስት’ የሚሉትን ስያሜ ልንሰጣቸው እንችላለን፤ ምርጫ 97 ፣ የሙስሊም ተቃውሞ እና የኦሮሞ ታቃውሞ።በአንተ አረዳድ የእነዚህ ተቃውሞች አንድነት እና ልዩነት ምንድን ነው? እነዚህ ተቃውሞዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነጻነት በመደበኛ ሕጎችና የተቋማት የሥራ አካሄድ ተጨፍልቆ ባለበት ጊዜ የተፈጠሩ ወይም የተጋጋሉ ናቸው። ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ይህን ጭፍለቃ በጎን ለማለፍ የሞከሩ ሚዲያዎች ተቃውሞውን በማስፋፋት በኩል ያላቸውን ሚና እንዴት ትመለከተዋለህ፤ ለምሳሌ የኦኤምኤን እና የኢሳት።
እነዚህ ሦስት ንቅናቄዎች፣ በነገራችን ላይ እነዚህን ከማየታችን በፊት ከዚያ በፊት የነበሩትን ሁለት የተማሪ እንቅስቃሴዎች ማየት ተገቢ ነው። የ1993ቱ የተማሪዎች ዐመጽ ለ2005ቱ ንቅናቄ መወለድ ምክንያት ነው። እርሱ የተቃውሞ መጀመርያ ነው፤ ሁለተኛው፦ እ.ኤ.አ 2002 ኦሮሞ ተማሪዎች ያስነሱት ተቃውሞ ነው፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ በ2004 አዲስ አበባ ወደ አዳማ ይሂድ የተባለውን መዝግብልኝ፤ የ2005ቱን የአዲስ አበባ እንቅስቃሴ መዝግብልኝ፤ የ2006ቱ ከምርጫ በኋላ ኦነግ ከሕወሓት ጋራ ተጣልተው ነበር እርሱን ያዝ፤ ከዚያ የ2011ዱ የሙዝሊም እንቅስቃሴ አለ፤ ከዚያ የ2014- 15 እና16 የኦሮሞ ተቃውሞ፤ የእነዚህን የጊዜ ሂደት መገንዘብ አለብን፤ ምንድን ነው አስፈላጊነቱ? እነዚህ ተቃውሞዎች በስፋትም፣ በጥልቀትም፣ በስትራቴጂ ውስብስብነትም እየጨመሩ ነው የሄዱት፤ ምንም እንኳ የተለያየ ዓላማ ይዘው ቢሄዱም አንዱ ከአንዱ ልምድ እየቀሰመ ነው የመጣው። የሙስሊሞቹ እንቅስቃሴ በጣም መጠቀስ ያለበት ነው፤ ምክንያቱም፣ ዐመጽ ዐልባ ተቃውሞን በኢትዮጵያውያን ዐይን ውስጥ ያስገባው እርሱ ነው፤ ይኼንን በአግባቡ ክሬዲት ልንሰጠው ይገባል። በጣም ውስብስብ እና ሸዋጅ የኾነ ጥያቄ ስለነበረ ያንን ይዘው ለመሄድ ጠንቃቃ መኾን ነበረባቸው፤ ከፍ ያለ ዲሲፕሊን የሚጠይቅ እንቅስቃሴ ነበር። ከፍ ያለ ራስን የመግዛት፣ ከፍ ያለ ውስብስብነትን የሚጠይቅ እንቅስቃሴ ነበረ፤ ብዙ ሰዎች መልሱ አልተመለሰም ምናምን ይላሉ፤ ግን መቶ በመቶ ውጤታማ እና ስኬታማ የነበረ እንቅስቃሴ ነው። ከዚያ በፊት የነበሩ ተቃውሞች ነበሩ፤ ግን በዲሲፕሊን፣ በመጀራጀት እና በመሰጠት የተካሄደው ይኼኛው ነው።
የኦሮሞ ተቃውሞ ከዚህኛው የተማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ። አጠቃላይ ኹኔታውን በመመልከት እና ግንኙነት በመፍጠር እና በመሳሰሉት። የ2014ቱ የኦሮሞ ተቃውሞ የራሱ የኾኑ ውስንነቶች ነበሩት፤ ግብ ማስቀመጥ ነበረበት፤ በጣም ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፤ የ2015ቱ ግን ከዚህ በፊት ከነበሩት እንቅስቃሴዎች በሙሉ ልምድ ስለቀሰመ ውስብስብነቱም ከፍ ያለ ነው፤ ማቀናጀቱም በጣም የተለየ ነው፤ ተማሪውን እንደ አቀጣጣይ ተጠቀመ፤ ከዚያ በኋላ በፍጥነት በተሳካ ኹኔታ ወደ ገበሬው መሸጋገር ቻለ፤ በተለያየ አቅጣጫ ራሱን ወደ ሁሉን አቀፍ ተቃውሞ አሳደገ፤ ይኹንና ይህን ስኬት የተቀዳጀው ከዚህ በፊት በአገሪቱ በነበሩት እና በተካሄዱት ተቃውሞዎች ምክንያት ነው፤ ይኼኛው ለኦሮሞ ትራንስፎርማቲቭ ነው፤ በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ በሥነ-ልቡና እና በፖለቲካ ወሳኝ ነበር። እጅግ በጣም ወሳኝ ከሚባሉት አንዱ። ወደ 1960ዎቹ ይዞን የሚጓዝ ወሳኝ ማይል ስቶን ነው። ለምን? አንድ፦ ፖለቲካዊ አንድነት (ዩኒቲ ኢን አክሽን) የሚለውን አሳየ፤ እያንዳንዱ ገጠር ተቀናጅቶ። ሁለተኛው፦ አንድ ንቅናቄ ስኬታማ ለመኾን ካለው ነባራዊ ኹኔታ መነሳት ይኖርበታል የሚለው ቲዎሪ በገዳ ሳይኮሎጂ ላይ የተመሠረተ ስለኾነ ከፍ ባለ አመራር ሳይኾን በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኙ የማኅበረሰቡ ወኪሎች የጎንዮሽ ግንኙነቶች ተግባራዊ በማድረግ ይህን ቴሲስ ተጠቅሞ በኦሮሞ ልሂቅ ላይ የነበረውን ፍርሃት ሙሉ ለሙሉ አሸነፈ። በእያንዳንዱ የኦሮምያ ቀበሌ ውስጥ ፍርሃት ሞቶ ተቀበረ። አሁን ካንተ ጋራ ሳወራ የማገኛቸው ምስሎች አሉ፤ ሰላሌ ውስጥ የወታደር ካምፕ አለ፤ ትልቅ የወታደር ካምፕ፤ ካምፑ ፊት ለፊት ሰው ሰልፍ እየወጣ ነው። ፍርሃትን ማሸነፍ ችሏል።
ሌላኛው መገንዘብ ያለብን እና መመዝገብ የሚገባን ጉዳይ፦ መንግሥታት ሲያደርጉት የነበረው “ኦሮሞ ከተነሳ ከአገር ያባርራችኋል፤ ይፈጃችኋል፤”የሚለውን ነገር ወኃ ደፋበት። ብዙ ከተሞች ነጻ ወጥተዋል፤ ገበሬው ተቃውሞ አድርጎ መግባት ይችል ነበር፤ ሙሉ ለሙሉ ነጻ አውጥተው ለመውሰድ የወሰኑበት ምክንያት፣ ነጻ በኾነ የኦሮሞ መሬት እያንዳንዱ ሰው ደኅንነቱ እና ሰላሙ ይጠበቃል፤ ኦሮሞ አውሬ አይደለም፤ ኦሮሞ ከእናንተ ጋር ጠብ የለውም፣ ኦሮሞ ከእናንተ ጋራ አይደለም ችግሩ ከመንግሥት ጋራ ነው፤ መንግሥት አባረን ነጻ በወጣ የኦሮሞ መሬት እያንዳንዱ በሰላም እና በደኅንነት ይኖራል የሚለውን አረጋገጠ። የሌላ ሰውን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ሕይወቱን ያጣ ሰው አለ፤ ኦሕዴዶች እና ሕወሃቶች የብሔር ግጭት ለማስነሳት ባደረጉት ሙከራ ከበው የሰውን ንብረት እና ሕይወት ለማዳን የሞቱ የኦሮሞ ልጆች አሉ፤ ሌላኛው አስፈላጊ ነገር፦ ድሮ ሰው ይቃወማል፤ ከዚያ አገር ጥሎ ይሸሻል፤ 2004 ላይ የነበሩ ልጆች በሙሉ የሉም። የታሠሩትም ከእስር ቤት ወጥተው ለዚህኛው ትግል ተዘጋጁ እንጂ ሌሎቹ የሉም፤ አሁንስ? 50ሺሕ ሰዎች እስር ቤት ውስጥ ናቸው። 50ሺሕ ሰው እስር ቤት እያለ ሰው እየሸሸ አይደለም፤ ሞቶም እንኳ “አንወጣም” ይላል።
የጃዋር የግል የፖለቲካ ጉዞ
የአደባባይ ሰው እንደመሆንህ ይህን ጥያቄ ሳልጠይቅህ ማለፍ አልችልም። መምህር መኾን እንደምትፈልግ፤ ትግሉን ማገዝ እንጂ ፖለቲከኛ መኾን እንደማትፈልግ ተናግረኻል፤ በቅርብ የሚያውቁህ ሰዎች ግን በዚህ አያምኑህም፤“ጠቅላይ ሚኒስትር የመኾን ፍላጎት አለው”ይሉኻል።
(ሳቅ). . . . ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኛ የተሰማውን ሁሉ እና የሚፈጽመውን ሁሉ እየተናገረ የሚሄድ ሰው በጣም ትንሽ ከመኾኑ የተነሳ ሰው አያምነውም፤ ያ ነው በጣም አስቸጋሪው ነገር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር የመኾን ፍላጎት ቢኖረኝ ኖሮ አሁን እየሠራሁ ያለኹትን ሥራ መሥራት አይጠበቅብኝም። አብዛኞቹ የምሠራቸው ነገሮች “ፖለቲካል ሱሳይድ” ናቸው እንደምታየው። እኔ የተግባር ሰው ነኝ፤ ራሴንም እንደ ወታደር ነው የምመለከተው። እውነቱን ከነገርኩህ፦ ፍቅሬ ትግል ነው፤ ፍቅር ያለኝ የመናገር ዕድል ለተነፈጉት ድምጽ ኾኖ ከመገኘት ነው፤ ለስትራቴጂ ፍቅር አለኝ፤ ለማስተማር ፍቅር አለኝ። ይኼን የምለው ሌላ የተደበቀ ዓላማ ስላለኝ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዜዳንት ወይም ሌላ የመኾን ፍላጎት ቢኖረኝ ያለምንም ገደብ በአደባባይ እናገረዋለሁ። ልጅ እያለሁ፦ አምስተኛ ከፍል ስማር አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍል አስተምር ነበር፤ ስምንተኛ ክፍል እያለሁ የአስተማሪ እጥረት ስለነበር ሂሳብ እና ሌሎች የትምህርት ዐይነቶችን ለአምስተኛ ክፍሎች አስተምር ነበር፤ ማስተማርን በጣም ነው የምደሰትበት፤ መጻፍ፣ መናገር፣ እውቀትን ማካፈል ያስደስተኛል። እኔ በጣም ትንሽ ኢትዮጵያውያን ሊያገኙት የሚችሉትን ዐይነት ትምህርት ነው ያገኘኹት። በዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት የተደረገብኝ እና ምርጥ የሚባሉ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የተላክሁ ሰው ነኝ፤ ያገኘኹትን እውቀት ለሌሎች እንዳይደርስ ማድረግ አግባብ ነው ብዬ አላስብም፤ ከራሴም ማንነት ጋራ፣ ከፍላጎቴም ጋራ ስታየው አብሮ አይኼድም፤ ለእኔ የአንድ አገር ማኔጀር መኾን ደባሪ ነገር ነው። ለምሳሌ ዛሬ ለውጥ ቢመጣ እና የተረጋጋ ዲሞክራሲ ቢፈጠር እኔ በምናቤ የምስለው ምንድነው? እናንተ ጋዜጣ ላይ ይጻፋል፤ ሚዲያ ይኖረናል፤ እንጽፋለን፣ የመሪዎች ተቋም ይኖረናል፤ አስተማሪዎችን እና ጋዜጠኞችን እናሰለጥናለን፤ ወደ ታዋቂ እና ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች የሚላኩ ታማሪዎችን እናዘጋጃለን፤ የእኔን የመጨረሻ ሕልም ከጠየቅኸኝ፦ እኔ በጣም ጠንካራ የኾነ መሪዎችን የሚያፈራ ተቋም መገንባት ነው የምፈልገው፤ በቁስ አካላዊ እውቀት ብቻ ሳይኾን፣ እምቅ የኾነውን የማኅበረሰቡን ኹኔታ አውቀው የመመርመር እና የመተንተን ብቃት ኖሯቸው በሚሠማሩበት በየትኛውም ሞያ ችግር ፈቺ መኾን የሚችሉ ልጆችን ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ መመልመል ነው የእኔ ሕልም። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ዶክተር – ዶክተር ብቻ አይደለም፤ ከዚያ ያለፈ ብዙ ሚና አለው፤ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋራ ስታመዛዝነው በጣም ትንሽ ከመኾናቸው የተነሳ ብዙ ሚና የመወጣት ሐላፊነት በእነርሱ ላይ ይጫናል፤ መጻፍ እፈልጋለሁ፤ ብዙ ጀምሬ ያልጨረስኳቸው . . . ገና ብዙ ነገሮች አሉ፤ አክቲቪዚሙ በሥራ ስለወጠረኝ ነው፤ ገና ወደ ትምህርት መመለስ እፈልጋለሁ። በአዲስ አበቤዎች ቋንቋ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አይመቸኝም፤ ከሙዴ ጋራ አይሄድም።
የሕዝብ ወኪል ነኝ ብለው በማኅበረሰቦች መካከል ግጭት የሚቀሰቅሱ የግጭትና መራራቅ (polarization) ነጋዴዎች በርካታ ናቸው። አንተ በተነሳህ ቁጥር ስለ ሜንጫ ይነሳል፤ “ኢትዮጵያውያን ከኦሮምያ ይውጡ”ም ይጠቀስብኻል፤ አንተ የሐረር ልጅ ነህ፤ በድሙጋ እና በሐረር መካከል ያለውን ልዩነትም ልታሳየኝ ሞክረኻል፤ “ሜንጫ ቡጢ አይደለም፤ ሜንጫ የፖለቲካ ሃይልን ለመግልፅ የምንጠቀምበት የተለመደ ተኪ ቋንቋ አይደለም፤ ‘ሜንጫ ነው” በሚል ያዳልጥኻል ለሚሉ መልስህ ምንድን ነው?
እኔ ቲዮረቲካል አይደለሁም፤ ኦፕሬሽናል ነኝ፤ በምሠራቸው ሥራዎች ውስጥ ሰዎች ሊመዝኑኝ እና ሊፈርዱኝ ይችላሉ፤ ዳያስፖራ ከመጣሁ 10 ዓመቴ ነው፤ አክቲቪዝም ከጀመርኩ ደግሞ 15 ዓመቴ ነው፤ ሥራዬ በራሱ ይናገራል፤ አዳልጦኻል ብሎ ለሚል ሰው ማረጋገጫ የማቀርብበት ምክንያት የለኝም። እኔ ትክክል ነበርኩ አይደለሁም ብዬ ለማንም ምክንያት ልሰጥ አልችልም፤ የእኔ የየቀኑ ሥራ፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ ለማንኛውም ሰው ጀስቲፋይ ለማድረግ በራሱ በቂ ነው። ራሴን በዚህ መንገድ መግለጽ አይጠበቅብኝም፤ ምን አደረግኹ – አላደረግኹ ብዬ። ምክንያቱም፦ ማፍረስ የሚፈልግ ሰው ሁሌም ቢኾን አቃቂር ማውጣት እና ጸጉር መሰንጠቁን አያቆምም፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ኾነ ኦሮሞያ ውስጥ በተጨባጭ ምን ዐይነት ዓላማ እንዳለኝ በተግባር እያሳየኋቸው ነው። ስለዚህ በሥራ እና በተጨባጭ እየሠራኹ ለማሳየው ነገር ተመልሼ ራሴን “ትክክል ነበርኹ-አልነበርኹም” እያልኹ ሁልጊዜ መልስ የምሰጥበት ነገር አይታየኝም፤ ምክንያቱም፦ የእኔ ሥራ በተጨባጭ ማየት የማይፈልጉ ሰዎች ካሉ ችግሩ የእኔ ሳይኾን የእነርሱ ነው።
No comments:
Post a Comment