በአገራችን የመንግሥትን ሥልጣን በሕዝቦች ፍላጎትና ምርጫ ሣይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ የተቆጣጠረዉ የህወሐት አገዛዝ ለዓመታት ለዘለቀዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዲሞክራሲ፣ የእኩልነትና የነፃነት ጥያቄዎች ተገቢዉን መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎቹን በማንሣት የሚታወቁትንና ሕዝብ የሚቀበላቸዉንና የሚከተላቸዉን የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፣ የሕዝብን ድምፅ በሰላማዊ መንገድ በማንፀባረቅ የሚታወቁ ጋዜጠኞችን፣ ወጣት ተማሪዎችን፣ በአጠቃላይ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ንፁሃን ዜጎችን በጅምላ ማሠር፣ ከአገር እንዲሰደዱ ማድረግና በወገንተኛ ወታደሮቹ አማካይነት መፍጀት የዘወትር ተግባሩ ማድረጉ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች የተሰወረ አይደለም፡፡ ራሱን የኢትዮጵያ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉ ይህ ሕወሐት-መራሽ የዘራፊዎች ቡድን ሰሞኑን ደግሞ ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት በታየዉ የሥርዓቱ የግፍና የስቃይ እርምጃዎች ባለመደናገጥና ተስፋም ባለመቁረጥ የአገዛዙ መሪዎች ከዛሬ ነገ ወደልቡናቸዉ ተመልሰዉ እንደሰዉ በማሰብ ሕዝቦቻችን ለሚጠይቋቸዉ ፍትሃዊ ጥያቄዎች ከሞላ-ጎደልም ቢሆን መልስ ይሰጡ ይሆናል በሚል አርቆ አስተዋይነት የተመላበት እምነት በሰላማዊ ትግሉ ዉስጥ በትዕግሥት፣ በድፍረትና በቆራጥነት ፀንተዉ የቆዩትን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ መሪና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ለእስር የመዳረጉን አስደንጋጭ ዜና ሰምተናል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና በብዙዎች ዘንድ እንደሰላማዊ ትግል ተምሳሌት ተደርገዉ ከሚታዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪዎች አንዱና ዋነኛዉ መሆናቸዉ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የእኚህ መሪ በአዉሮፓ በተደረገና በኢትዮጵያ ጉደይ ላይ በተነጋገረ ይፋዊ ስብሰባ ላይ ተሣትፈዉ ወደሚወዱት አገራቸዉና ወደሚያከብሩትና ወደሚታገሉለት የአገራቸዉ ሕዝብ ሲመለሱ ገና አገር ዉስጥ ከመግባታቸዉ ታፍነዉ መታሠር የሚያሣየዉ ተደጋግሞ የተገለፀዉን የአገዛዙን መሪዎች ፍፁም አረመኔነትና ለሕዝብ ስሜት ደንታ-ቢስነት ብቻ ሣይሆን በኦሮሚያ፣ በአማራና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች እየተካሄደ ያለዉ የሕዝቦች የነፃነት ትግል ተስፋ ያስቆረጣቸዉና የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ያሣጣቸዉ የመሆኑን እዉነታ ነዉ፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለፀዉ የሕወሐት መሪዎች ፍላጎት ላለፉት ሃያ-አምስት የግፍና የስቃይ ዓመታት ሲያደርጉ እንደቆዩትና አሁንም እያደረጉ እንዳሉት የኢትዮጵያን ሕዝብ በጠመንጃ ኃይል አስገድዶ በባርነት መግዛትና አገሪቱን እንደግል ንብረታቸዉ በፈለጉት መንገድ መቆጣጠር ይህ ፍላጎታቸዉ በታጋይ ኢትዮጵያዉያን የሞት ሽረት ትግል ምክንያት የሚሣካላቸዉ መስሎ ካልታያቸዉ ደግሞ አገሪቱን እንዳልነበረች አድርጎ በማጥፋት የዘረፉትን ቁጥር ስፍር የሌለዉ የአገር ሃብት ይዘዉ ለእነሱና ለቅርብ ቤተሶቦቻቸዉ ይስማማናል በሚሉት የዓለም ክፍል ቀሪ ዕድሜያቸዉን ማሣለፍ ነዉ፡፡ አሁን በዶ/ር መረራ ላይ የተወሰደዉ የጭካኔና የተስፋ መቁረጥ እርምጃም የሚያሣየዉም ይህንኑ የገዢዉን ቡድን ወደጥፋት የመሄድ አዝማሚያ ነዉ ብለን እናምናለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግን የተጠየቀዉን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል አገራቸዉን ከወያኔዎች የግፍ አገዛዝ ነፃ አድርገዉ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመመሥረት ዉጭ ሌላ አማራጭ የላቸዉም፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነዉ በዶ/ር መረራና በሌሎችም ታጋይ ኢትዮጵያዉያን ላይ የተወሰደዉና እየተወሰደም ያለዉ የጨቋኝ ገዢዎች የጭካኔ እርምጃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊወገድ የሚችለዉ፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ዋነኛ ተልዕኮም ይህን የሕዝቦቻችንን የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ ለመመለስ ይቻል ዘንድ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚረዱ ቅድመ-ሁኔታዎችን ከወዲሁ ለማመቻቸትና እስከአሁን በተበታተነ መልክ እየተካሄዱ ያሉትን የነፃነትና የዲሞክራሲ እቅስቃሴዎች አስተባብሮ ወደ አንድ ጥላ ሥር በማምጣት ትግሉን ለሚፈለገዉ ዉጤት ማብቃት ነዉ፡፡ ስለሆነም የዶ/ር መረራንም ሆነ የሌሎች ታጋይ ኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ መሪዎችንና ታዋቂ ጋዜጠኞችን ማለትም የእነ በቀለ ገርባን፣ አንዳርጋቸዉ ፅጌን፣ ኦልባና ሌሊሣን፣ አንዱዓለም አራጌን፣ እስክንድር ነጋን፣ ተመስገን ደሣለኝን፣ ኮ/ል ደመቀ ዘዉዱንና ሌሎችንም ስማቸዉን ዘርዝረን የማንዘልቀዉን በሺዎች የሚቆጠሩ የፍትህ፣ የነፃነት፣ የዲሞክራሲና የእኩልነት ጥያቄዎች ግንባር ቀደም አራማጅ ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ህልም ዕዉን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን አገራችንና ሕዝቦቻችን የደረሱበት የችግርና የስቃይ ደረጃ ደግሞ ዝም ብለን መግለጫ በማዉጣት ብቻ የምናልፋቸዉ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ያየነዉ ነዉ፡፡ ስለዚህ:-
1. ይህ የጥቂቶች የአገዛዝ ሥርዓት በሕዝቦቻችን የተባበረ ክንድ ተወግዶ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና እኩልነት በአገራችን እንዲሰፍን የምትፈልጉ ወገኖች ሁሉ በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የተጀመረዉን ትግል በመቀላቀል የነፃነት ትግሉን ተጠናክሮ እንዲቀጥል የየበኩላችሁን እንድታደርጉ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
2. ሕወሐት መራሹ የኢትዮዽያ መንግሥት አገርን ከጥፋት ለመታደግ ዶ/ር መረራንም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ በአስቸኩዋይ ፈትቶ የፖለቲካ ሜዳዉን የኢትዮዽያ ጉዳይ ለሚመለከታቸዉ ኃይሎች ሁሉ ክፍት በማድረግ ሁሉም ወገኖች የሚሣተፉበትና ዉስብስብ ለሆኑት የአገራችን ችግሮች የጋራ መፍትሔ መፈለግ የሚያስችል አገር አቀፍ ጉባዔ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች አበክረን እናሳስባለን።
3. ሕወሐት መራሹን የጥቂቶች አገዛዝ ሥርዓት በተለያዩ መንገዶች አቅፋችሁና ደግፋችሁ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ጫንቃ ላይ ተደላድሎ እንዲቀመጥ አስተዋፅኦ በማድረግ የምትታወቁ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አባላትና በዕድገትና በሥልጣኔ የዳበራችሁ መንግሥታትም በዚህ ታሪካዊ ወቅት ኢትዮዽያንና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ከአደገኛ ጥፋትና ትርምስ ለማዳን ይቻል ዘንድ እስከዛሬ ስታደርጉት እንደነበረዉ ከጨቋኙ የሕወሐት ሥርዓት ጋር ሣይሆን ከነፃነት ናፋቂዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጎን እንድትቆሙና በሕወሐት በሚመራዉ የኢትዮዽያ መንግሥት ላይ ጫና እንድታደርጉ ልናሳስባችሁ እንወዳለን፡፡
ፍትህና ነፃነት ለሁሉም ሕዝቦች!!
የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ
የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ
No comments:
Post a Comment