Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, December 11, 2016

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ አራዘመ



ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቦ የነበረው የአሜሪካ መንግስት፣ ማስጠንቀቂያውን በድጋሚ አራዝሟል፡፡ የኢንተርኔት እና የሞባይል ስልክ አገልግሎቶች በመላ ሃገሪቱ ያለ ማስጠንቀቂያ እንደሚቋረጡ እና ሙሉ በሙሉ እንደሚዘጉ የገለጸው የአሜሪካ መንግስት ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ ይህ ሁኔታም አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቹን የመርዳት አቅሙን እንደሚፈታተነው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ አትቷል፡፡


የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎቹ በሀገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ አደጋ እንዳይገጥማቸው ሲል ባራዘመው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ላይ፣ ዜጎቹ ከሰላማዊ ሰልፎችና ሰዎች በብዛት ከሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ አሳስቧል፡፡ እንደዚሁም የደህንነታውን ሁኔታ በንቃት እንዲከታተሉ እና የሚንቀሳቀሱባቸውን አካባቢዎች ያለማቋረጥ እንዲከታተሉ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በጽኑ አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችን ለመበተን የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ በቀጥታ ሊተኩስ እንደሚችል የገለጸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው ላይ አስጠንቅቋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ሊካሔዱ የታሰቡ ሰልፎች ድንገት ወደ ሁከት ሊቀየሩ እንደሚችሉ ስጋቱን የገለጸው የአሜሪካ መንግስት፣ ዜጎቹ ይህን ከግምት በማስገባት እንዲንቀሳቀሱ እና ከፍ ሲልም ኢትዮጵያን ለቅቀው የሚወጡበትን የአደጋ ጊዜ ዕቅድ ከወዲሁ እንዲያዘጋጁ መክሯል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ከዚህ በፊት ጥቅምት 11 በኢትዮጵያ ላሉ እና ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ዜጎቹ የጉዞ ማስጠንቀቂ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ትላንትና በድጋሚ የወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያም የጥቅምት 11ዱን የጉዞ ማስጠንቀቂያ የሚተካ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከተሎ የተፈጠረው ሁኔታ አሁንም መረጋጋት አለማሳየቱን የጠቀሰው የአሜሪካ መንግስት፣ ጉዳዩ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ለመተንበይ አስቸጋሪ እንደሆነበት ተናግሯል፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥ ስለሚችል፣ ቀደም ሲል የተሰጠውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ ትላንት ባወጣው መግለጫ አራዝሞታል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials