Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, December 2, 2016

በአማራነት ለመመከት ያቃተንን ፈተና በጎንደሬነት ለመወጣት አይሞከርም (ከይገርማል)





ጠላቴ ነው የምትሉት ሰው በሚያደርስባችሁ በደል አዝናችሁ ታውቃላችሁ? እናንተ የምትሰጡትን መልስ ባላውቅም የእኔ መልስ ግን “በፍጹም!” የሚል ነው:: ጠላት እኮ በቃ ጠላት ነው:: ደግ ነገር የማይመኝልን: ክፉ ነገር የሚያደርግብን: ሁልጊዜም ውድቀታችንን የሚመኝ:: ከጠላት ጥሩ ነገር የሚጠብቅ ካለ እርሱ የዋህ መሆን አለበት:: እና ጠላቴ መጥፎ ሰራብኝ ተብሎ እንዴት ይታዘናል! የሚታዘነው ደግ ያደርግልኛል ብለው ያሰቡት ሰው መጥፎ ሲሰራብዎት ነው:: መልካም ነገር ያጋጥመኛል ብለው ተስፋ ያደረጉት ነገር ባልጠበቁት መልኩ ጎጅ ሆኖ ሲመጣብዎት ነው:: ደግ ነገር እየጠበቁ ደግ ያልሆነ ነገር ሲያጋጥምዎት ነው:: ከጠላት ጥሩ ነገር ስለማይጠብቁ በሚሰራብዎ በያንዳንዱ ጎጅ ተግባር አዝኛለሁ ሊሉ አይችሉም::

የጎንደርና የጎጃም ሕብረቶችን መመስረት በተመለከተ በርካታ ሰዎች ትክክል አይደለም ብለው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል:: እኔም በበኩሌ የአካባቢ ድርጅቶች ምስረታ በአማራ መሀል የሚኖረውን አንድነትና አንድነቱን ተከትሎ የሚፈጠረውን ጥንካሬ ይጎዳል በሚል ተከራክሬአለሁ:: ይህን ስል ከምናልባት ተነስቸ ሳይሆን ከትክክለኛ ጭብጥ በመነሳት ነው::

የወልቃይት አማራ “አማሮች ሆነን እያለን በግድ ወደትግራይ እንድንካለል ተደርገናል: ዘራችንን እያጠፉ የትግራይ ሰዎችን እያመጡ እያሰፈሩብን ነው: በሕይወት ያለነውም ብንሆን በቋንቋችን እንኳ እንዳንናገር ተከልክለን በባርነት እየኖርን ነው” ብለው የተቃውሞ ድምጻቸውን በማሰማታቸው ነው አማራ የተባለ ሁሉ በአንድነት ተቃውሞውን ያሰማው:: በድፍን አማራ የሚኖረው ሕዝብ በአንድ መንፈስ በተቃውሞ የተንቀሳቀሰው አማራ አንድ ሕዝብ ነው ብሎ በማመኑ ነበር:: አማራውን አማራነት ካላስተሳሰረው ከሌላው በተለየ ሊያስተባብረው የሚችል ምን አለ! ወልቃይት የአማራ ነው ብሎ ጎጃሜው: ጎንደሬው: ወሎየው: ሸዬው የሚጮኸው: በተጠቃሁ ስሜት የሚብሰለሰለው: ወልቃይትን የራሱ አካል አድርጎ ስላየ ብቻ ነው:: እንጅ ከሌላው በተለየ የሸዋ ገበሬ ወይም የጎጃም ገበሬ ወልቃይት ሄዶ እፍኝ እህል አምርቶ ስለሚጠቀም አይደለም:: ወይም ከወልቃይት የሚያገኘው የተለየ ጥቅም እንዳይነጥፍ በማሰብ አይደለም::

በየአካባቢው የሚደረገው የአማራ የብሶት ድምጽ የመጠቃት ድምጽ ነው:: ያ የጥቃት ድምጽ ደግሞ አካሌ የሚለው የወልቃይት ሕዝብ የሚያሰማው የመከራ ድምጽ የፈጠረው “ተጠቃሁ” የሚል የምሬት ድምጽ ነው:: አማራነት ካላስተሳሰረን የወልቃይት ችግር የወልቃይት ብቻ ይሆናል:: የወሎ ችግር የወሎ: የጎጃሙ የጎጃም: የሸዋውም የሸዋ ችግር ብቻ ይሆናል:: ለወልቃይት ችግር ከባሌ ወይም ከጋሞጎፋ ገበሬ በተለየ መልኩ የጎጃምን: የወሎንም ሆነ የሸዋን ገበሬ የሚያሳስበው አይሆንም:: አማራ በአንድነት ካልተደራጀ ከአማራ ክልል ውጪ ተበታትኖ ለሚኖረው አማራስ ማን ነው ዋስ ጠበቃ ሊሆንለት የሚችለው?

ፕሮፌሰር አስራት መላው አማራ የተባለውን ድርጅት ያቋቋሙት የአማራውን ጩኸት ለመጮህ: አማራው ኃይሉን አስተባብሮ ራሱን ለመከላከል እንዲችል ለማድረግ ነበር:: እንደሚታወቀው በባለፈው የአማራ የዘር ጥፋት ዋና ተጠቂ የነበረው በሌሎች ክልሎች የሚኖረው አማራ ነበር:: ጎንደር በጎንደሬነት: ጎጃም በጎጃሜነት – – – ከተደራጀ በሌሎች ክልሎች ብትንትን ብሎ ለሚኖረው አማራ ማን አለሁ ይበለው!

ዘረኝነትን ያመጣው አማራው አይደለም! ወደድንም ጠላንም ሁሉም ቀደም ብሎ በየዘሩ ተደራጅቷል:: ኦሮሞው: አፋሩ: ሶማሌው: – – – የተደራጀው በቋንቋውና በዘሩ ነው:: በየክልሎች የሚኖረው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ የተተወው ለወያኔና ለክልል መንግሥታቱ እንጅ ለህግ አይደለም:: እነዚህ አካላት ደግሞ ከህግ በላይ ናቸው:: እናስ በነዚህ ክልሎች የሚኖረው አማራ ዕጣ ፈንታ ምን ይሁን ነው የምንለው? ወያኔ የሚፈልገው በቅድሚያ ከክልሉ ውጪ ነው የሚኖረው የሚለውን አማራ ማጥፋት ነው:: ሌሎች ክልሎች ከአማራ የጸዱ እንዲሆኑ ነው እየሰራ ያለው:: ከሞት በተአምር ለተረፉት ለእነዚህ ወገኖቻችን ማን ይከራከርላቸው?

ከሰሞኑ የጎጃምና የጎንደር ሕብረቶች በጋራ ባዘጋጁት የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም ላይ የጎንደር ሕብረት ሊቀመንበር አቶ አበበ ንጋቱ የተናገሩትን ሰምቸ በጣም አዝኛለሁ:: ማዘን ያለብን እንደዚህ የኛ ነው ብለን በምንለው ሰው ስንጠቃ ነው: አካሌ ነው ብለን በምንሳሳለት ሰው ክፉ ነገር ሲፈጸምብን ነው:: “የጎንደርና የጎጃም ሕብረቶችን መመስረት የሚቃወሙ ለአማራው የተቆረቆሩ በመምሰል ለጥፋት የተሰለፉ ዲያስፖራ የብአዴን አባላት ናቸው” ብለው አቶ አበበ ተናገሩ:: እናስ አያምም! አያሳዝንም! የኛን አመለካከት አልተከተሉም የምንላቸውን ሰወች በጠላትነት መፈረጅ የኢትዮጵያውያን መለያ ባህሪይ ነው ልበል! አቶ አበበ የጎንደር ሕብረትን ፈለግ በመከተል የጎጃም ሕብረት እንደተመሰረተና ወደፊት ደግሞ ሌሎች ሕብረቶችም እንደሚፈጠሩ በአዲስ የትግል ስልት ፈር ቀዳጅነታቸው ተኩራርተው ነግረውናል:: ወያኔ ማን ነው: እርስዎ ወይስ ስለአማራ አንድነት የሚከራከረው አማራ? ለመሆኑ ወያኔ የአማራን መደራጀት በበጎ ጎኑ አይቶት ያውቃል? ብአዴን የተመሰረተው የአማራውን መከራ ለአለም መንግስታትና ለአለም-አቀፍ ድርጅቶች ለማሳወቅ የተቋቋመውን የመአህድ ድምጽ ለማፈን ነበር:: ከተለያዩ ጎሣወች የተውጣጡ የአመራር አባላት እንደፈለጋቸው የሚያዝዙበት የአማራ ድርጅት መስርተው እየተባበሩም: ሽፋን እየተሰጣጡም ነው አማራውን የፈጁት:: ወያኔ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ለሞት ዳርጎ ድርጅቱን ያፈረሰው: አማራው ጠንካራ ድርጅት እንዲኖረው ከመፈለግ አልነበረም:: አቶ አበበ ወደፊት እንደጎጃምና ጎንደር ሁሉ የወለጋም ሕብረት እንደሚመሰረት ምኞታቸውን ይነግሩናል:: ይህ ምኞትዎ አጉል ምኞት መሆኑን ቢያውቁ እንዴት ደስ ባለኝ! የኦሮሞ ድርጅት የተባለ ሁሉ ተሰባስቦ ስለወደፊቷ ኦሮሚያ እየተነጋገረ ባለበት በዚህ ወቅት ኦሮሞው የዘር ድርጅቶችን ትቶ በአካባቢ ማሕበሮች ይሰባሰባል ብሎ ማሰብ የለየለት አጉል ምኞት ነው:: እንዲያ ቢታሰብ ኖሮ አማራው በዘር ለመደራጀት መቸ ምርጫው ያደርግ ነበር!

እንደ መኢአድ: ቅንጅትና አንድነት የመሳሰሉት ሕብረ-ብሔራዊ ድርጅቶች የፈራረሱት ወይም የተዳከሙት በአመራር ቦታ ወይም በአባልነት የተወሰኑ አማሮች ታይተዋል በሚል ነው:: አማራ የሚታይበት ክልልም ሆነ ድርጅት እንዲኖር አይፈለግም:: አማራ ታይቶባቸዋል የሚባሉት ድርጅቶች የነፍጠኛው ድርጅቶች ናቸው ተብለው እንዲፈረጁና እንዲዳከሙ የሚደረጉት በወያኔ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሰላማዊ ተቃዋሚ የጎሣ ድርቶችም ጭምር ነው:: ወገኖቻችን አማራ በመሆናቸው ብቻ በየቦታው የተጨፈጨፉት በወያኔ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጎሣ ድርጅቶችም ጭምር ነው:: ያልተሸፋፈነው ዕውነት ይኸው ነው:: ለእኛ ያለነው እኛው ብቻ ነን:: እየተፈጠረ ያለውን የመተሳሰብና ለትግል የመነሳሳት ስሜት እባካችሁ አታጥፉት!

አንድ የሆነ ሰው “የጎንደር ሕብረት የተመሰረተው ትግሉን ለማገዝ እንጅ ለማቀዛቀዝ አይደለም:: ማህበሮቹ ሕዝቡን እያስተባበሩ ለትግሉ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ነው የተቋቋሙት” አይነት አስተያየት ሲሰጡ ሰምቸ “እንደዚያ ከሆነ መልካም ነው: ድርጅቶቹ የያካባቢያቸውን ሕዝብ በማስተባበር ለአማራው እንቅስቃሴ መጠናከር እገዛ ሊያደርጉ ነው” ብየ አምኜ ደስ ብሎኝ ነበር:: አቶ አበበ ግን በዘር መደራጀት እንደማያስፈልግ በማመን ኢትዮጵያን ለማዳን በአካባቢ መደራጀት የተሻለ አማራጭ አድርገው ነው የተናገሩት:: ያልገባቸው ነገር ሌሎች ጎሣወች የርሳቸውን መንገድ ተከትለው የጎሣ ድርጅቶቻቸውን አፍርሰው የአክባቢ ድርጅቶችን ለመመስረት እንደማይፈቅዱ ነው:: ብዙ ተሞክሮ ብዙ ተደክሞ ያላስሄደውን መንገድ መከተል ከየዋህነት የዘለለ ሞኝነት ነው:: ጎንደር ላይ የኦሮሞው ደም ደሜ ነው ተብሏል:: አዳማ ላይም የአማራው ደም ደሜ ነው ተብሏል:: ይህ ማለት ግን የአዳማ ወጣት ኦሮሞነቱን ትቶ በክልል ለመደራጀት መምረጡን አያሳይም:: ከኦሮሚያ አልፎ ለኢትዮጵያ መቆምን አያመለክትም:: ጊዜአዊ ትብብርን እንጅ አንድነትን አያመለክትም:: በጃዋርም ይሁን በዳውድ ኢብሳ የተመራው የሀገር ውስጥ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያውያን አንድነትና እኩልነት: ፍትህና ሰላም የተደረገ ሊሆን አይችልም:: መሆን የሚችለው የወያኔን ኃይል ለመበተን እንዲያግዝ በሁሉም አካባቢ ትግሉን የሚያነሳሳ ጊዚያዊ ጓደኛ ለመፍጠር ነው::

ምንም ቢሉን የማይገባን ሆኖ ነው እንጅ እነርሱ እኮ በግልጽ የሚፈልጉትን ነግረውናል:: ጎሠኞች በሁሉም መልክ ከአንድነት ኃይሎች በልጠዋል:: እና እንደፈልጋቸው ይቀልዱብናል: ለአላማቸው ማስፈጸሚያ እንደመሳሪያ ይጠቀሙብናል:: ሲፈልጉ ለአንድነት የቆመ የሚመስል ተገነጠልሁ የሚል ኃይል ይልኩና መውጫ መግቢያችንን ሳይቀር ያሰልሉናል:: እኛ ደግሞ የቀረቡን መስሎን ልባችንን ሳይቀር ቦግ አድርገን ከፍተን እናሳያቸዋለን::

ወያኔ “ድንበር የምንካለለው ከቅማንት ጋር ነው: አማራ የሚባል የለም ብሏል:: የወያኔ የግዛት ፍላጐት ጋምቤላ ድረስ ይዘልቃል” እያሉን ነው አቶ አበበ:: እርሳቸውም እኮ እየደገፉ ያሉት አማራ የሚባል አያስፈልግም የሚለውን የወያኔ ፍላጎት ነው:: ያማራ ተሟጋች ሆነው ቢቀርቡ ኖሮ አማራ ነኝ እያለ የሚጮኸውን ወልቃይት ድምጹን እንዲያጠፋ: አማራ ነኝ እንዳይል አይታገሉም ነበር:: ደግሞስ ወልቃይትና ሁመራ የአማራ ክልል አካል ናቸው ብለን ተናንቀን ማስመለስ ከቻልን በየት ዞሮ ነው ወያኔ ጋምቤላ ድረስ ግዛቱን ማስፋፋት የሚችለው? በአማራነት ተደጋግፈን መውጣት ያስቸገረንን አቀበት በጎንደሬነት ብቻ ተያይዞ ለመውጣት አይታሰብም:: አማራው እንደአንድ ካላሰበ ሁሉም ለየራሱ ፍላጎት ብቻ የሚሰለፍ ይሆናል:: “መንግጌ አባስሁት” እንዳለችዋ ሴት የተሻለ ነገር አመጣን ብለን ለባሰ ጉዳት እንዳንጋለጥ ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልጋል!

በኢትዮጵያዊነቱ የሚያፍር አማራ እንደሌለ ማንም ያውቃል:: ነገር ግን ሁሉም ሊሆን የሚችለው በመጀመሪያ ራሱን በሕይወት ማቆየት ሲችል ብቻ ነው:: ስለዚህ ጠንካራ የአማራ ድርጅት መመስረት አለበት!

የአባይን ግድብ ቤንሻንጉል ላይ የሰሩት ታላቋን ትግራይ ሲመሰርቱ ለራሳቸው ብቻ ሊጠቀሙበት ፈልገው ነው የሚባለው ድምዳሜም ፍጹም የተሳሳተ ነው:: ይህን ስል ወያኔወች እንዲህ አይነት ቅዠት አይኖራቸውም በሚል እምነት አይደለም:: ነገር ግን እኛ ራሳችንን መከላከል ካልቻልን ጭስ አባይ ላይ ቢገድቡትና ወደራሳቸው ቢያካልሉትስ ማን ያስጥላቸዋል! ተሸናፊ ሁሌም ተሸናፊ ነው: በሀብት በንብረቱ ሊያዝ አይቻለውም:: ጎንደርንና ጐጃምን አልፈው በአሶሳ አድርገው ጋምቤላ ድረስ ያለውን ወደትግራይ ማካለል ከቻሉ ጣናን ለመውሰድ ምን ያግዳቸዋል!

አቶ አበበ የአማራውን አንድነት ለማፍረስ በቅማንትና በአገው አታሳቡ:: እንደማንኛውም ሁሉ ለወያኔ ያደሩ ጥቂት የቅማንትና የአገው ሰዎች ሊኖሩ ቢችሉም ብዙሀኑ ግን ኑሮውንም ሞቱንም ከአማራው ጋር ለማድረግ የሚፈልግ ለዚህም ሕይወቱን ሳይቀር እየከፈለ ያለ ሕዝብ ነው:: ለዚያም ነው በአፍራሽነት የተደራጁትን ኃይሎች መለማመጥ ሳይሆን ሕዝቡን መያዝ ይበጃል የምንለው:: ወደሕዝቡ ዘልቀን እውነቱን ከነገርነው ቀርቦት አብሮት ከኖረው ከአማራ ተለያይቶ ክትግሬ ጋር ያብራል ብሎ ማሰብ በፍጹም የሚቻል አይሆንም::

ከሰሞኑ የሀገር ቤት ፖለቲካ በሬዲዮና በቴሌቭዥን እየቀረቡ በልዩነት ውስጥ አንድነት አለ እያሉ ሊያጭበረብሩን የሚፈልጉ የወያኔ አሸርጋጆችን ስንሰማ ነበር:: እኛ ግን እንላለን; በልዩነት መሀል አንድነት የለም: አለ ከተባለም ያ አንድነት ከጊዜ በኋላ ሊፈርስ የሚችል በጀሶ የተያያዘ መሆን አለበት:: በመሰረቱ ልዩነት በአንድነት የሚለው አባባል በአንድ ወቅት ነጻ የነበሩ መንግሥታት በአንድነት ለመኖር ተስማምተው የጋራ ሀገር ሲመሰርቱ የሚሰጥ ስያሜ ነው:: ለምሳሌ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊት ነጻ ሀገር የነበሩት የአውሮፓና የሩሲያ አካባቢ አንዳንድ ሀገሮች በተለያየ ምክንያት አንድ የጋራ ሀገር መስርተው የተለያዩ የነበሩት አንድ ሆነው ቆይተዋል:: ልዩነት በአንድነት የሚባለው እንግዲህ የጋራ ታሪክና ማንነት ያልነበራቸው የተለያዩ ነጻ የነበሩ ሀገሮች የነበሯቸውን ልዩነቶች እንደያዙ አንድ ሀገር ሲመሰርቱ ነው ማለት ነው:: ኢትዮጵያ ግን እንደዚያ አይደለችም:: በአስገዳጅ ምክንያቶች የነበሯትን ስትነጠቅና አቅም ስታገኝ የቀድሞ ግዛቷን ስታስመልስ እንጅ ከሌሎች ነጻ ከነበሩ ሀገሮች ጋር ጋብቻና ፍች ስትፈጽም አትታወቅም:: በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ አካል የነበረችው ኤርትራ በአቅም ማነስ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ለ60 አመታት ያህል በጣሊያንና በእንግሊዝ ስር ስትተዳደር ቆይታ በኋላ ላይ ተመልሳ ወደእናት ሀገሯ መቀላቀል ችላ ነበር:: ይህ አንድነት በልዩነት ላይ የተመሰረተ አንድነት አልነበረም::

ወያኔን የመሰረቱት ሰዎች ምን አይነት አላማ እንዳላቸው ማሰብ ይከብዳል:: ሁልጊዜ የሚያጠነጥ ኑት በህዝቦቿ መሀል የነበረው የአንድነት መንፈስ ፍጹም ተበጣጥሶ በሂደት ኢትዮጵያ የምትባለዋ ሀገር እንድትበታተን ነው:: ለዚያም ነው በልዩነት መሀልም አንድነት አለ እያሉ ሊያጃጅሉን የሚፈልጉት:: ኢትዮጵያ ብዙ ጎድሎባት አሁንም በቀድሞ ስሟ እየተጠራች ያለች ታሪካዊት ሀገር ናት:: ሕዝቧም የተለያየ ቋንቋና የባህል መገለጫ ያለው አንድ ሕዝብ ነው:: የኢትዮጵያ ብሔር-ብሔረሰቦች በልዩነት ውስጥ በአንድነት የሚኖሩ ሳይሆን እንደአንድ የሰው የተለያዩ የአካል ክፍሎች ተሳስበው የሚኖሩ ናቸው:: ኢትዮጵያችንን እንደሰው ብንመስላት ብሔር-ብሔረሰቦቿን ደግሞ እንደተለያዩ የሰውነቷ ክፍሎች መውሰድ እንችላለን:: የሰው ልጅ እግር: እጅ: ጭንቅላት: – – -እንዳለው ሁሉ አንዲት ኢትዮጵያም የተለያዩ ጎሣወች አሏት:: የሰውነት ክፍሎቻችን የየራሳቸው የቅርጽና የተግባር ልዩነቶች አሏቸው:: ነገር ግን የአንዱ አካል መጎዳት የሌላው የአካል ክፍልም መጎዳት ነው:: የኢትዮጵያ ብሔር-ብሔረሰቦችም እንዲሁ የአንዲት ሀገር የተለያየ ቋንቋና ባሕል ያላቸው የአንዲት ሀገር ሕዝቦች ናቸው:: እንደሰውነት ክፍሎቻችን ሁሉ የአንዱ ጎሣ ጉዳት የሌላውም ጉዳት ነው:: ተጠጋግተው የበቀሉ ባሕርዛፍንና ጽድን በአንድ ገመድ ማሰር ልዩነት በአንድነት ሊባል ይችላል:: ባሕርዛፉን ለይተን ከስሩ ብንልጠው ግን የሚሞተው ባሕርዛፉ እንጅ ጽዱ አይሆንም:: የባሕርዛፉ መጎዳት ለጽዱ ምንም ማለት አይደለም:: የባሕርዛፉ መላጥ ግን የባሕርዛፉን ቅርንጫፎች ሁሉ ያደርቃል: ይገድላል::

የአማሮችን ጠንክሮ መውጣት የምንፈልገው አማሮች ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ ለማስቻል ብቻ አይደለም: ለኢትዮጵያም ተስፋ ናቸው ብለን ስለምናምንም እንጅ:: አማራው ስለሀገር መብሰልሰል የጀመረው ዛሬ አይደለም:: መላ ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ ሺወችን ኪሎሜትሮች በእግሩ እያቋራረጠ ነው ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቀ በደምና በአጥንት ይህችን በታሪኳና በነጻነቷ የምትኮራ ሀገራችንን ለእኛ ያስረከበን:: አማሮች ዛሬም እኮ እንደድሮው በባዶ እግራቸው ነው የሚሄዱት::

ወያኔ በኮንጎ ጫማ ገብቶ ብዙም ሳይቆይ ነው የሕንጻ ባለቤት የሆነው: ባለፋብሪካ የተባለው:: አስመጭና ላኪ: የሪልስቴት ባለቤት: – – – ተብሎ በአምራችነት እየተሸለመ ያለው:: አማራው ምንም አልነበረውም:: ሀብቴ የሚላት አርሶና ነግዶ የሚኖርባትን ሀገሩን ነበር:: እርሷንም ተነጥቆ ከተወለደበት ቀየ ለማኝ: ቆማጣ እየተባለ ሌጣውን ተባሯል:: የጠባብ ኃይሎች ጀሌወች ሳይቀሩ ይህን ሀቅ ይመሰክራሉ:: “አማራ ለማኝ ነው: አማራ ቆማጣ ነው: አማራ ሸርሙጣ ነው” አይደለም እንዴ የሚሉን? ወያኔ በ25 አመት ያደረገውን እነርሱ ባመኑት በመቶ አመት እንኳ አማራው ለራሱ ብቻ ቢያስብ ኖሮ በወርቅ ጫማ አይሄድም ነበር? ዘር የማጥፋት ሰይጣናዊ አባዜ ቢኖረው ኖሮ ከአማራ ውጪ አንድ ሰው ይገኝ ነበር? በባዶ እግር መሄድ ወይም ለሽርሙጥና መዳረግ የሀብታምነት መገለጫ አይሆንም:: አማራው ለራሱ ብቻ ቢያስብ ኖሮ በእግሩ የሚሄደው እራሱ አማራው አይሆንም ነበር:: ለሴተኛ አዳሪነት የሚጋለጡት አማሮች አይሆኑም ነበር::

ለአማራ ታጋይ ድርጅቶች የማሳስበው ነገር ቢኖር ስራችሁን ከክልሉ ሕዝብ ጋር ተቀራርባችሁ እንድትሰሩ ነው:: በሁለት እግሮቻችሁ ለመቆም ከራሳችሁ ሕዝብ በስተቀር ከማንም ድጋፍ አትጠብቁ:: ከማንም ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መዘፈቅም አያስፈልግም:: ቢቻል ከሌሎች የአንድነት ኃይሎች ጋርም በተጠና መንገድ ስልታዊ ግንኙነት ማድረግ ይጠቅማል:: ከኤርትራ የሚወረወረው ኃይል ከናንተ እንቅስቃሴ ጋር ስምሙ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል:: በእሳት ተፈትኖ የወጣ የስንት ጀግኖች ልጆች ናችሁ:: የአማራ መከራ ለልጅ የልጅልጅ እንዳይተላለፍ የሞት ሽረት ትግል ዛሬ ሊደረግ ይገባል:: ማንንም አትመኑ: ማንንም አትጥሉ::

ከመፈቀርና ከማፍቀር የቱን ትመርጣላችሁ የሚል ጥያቄ ቢመጣ መፈቀርን ነው የምንመርጠው የሚሉ ብዙወች ሊሆኑ እንደሚችሉ እገምታለሁ:: ተፈቃሪ ሰው ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ ነው:: አፍቃሪ ግን በብዙ መልኩ ሊጎዳ ይችላል:: አፍቅሮም ያፈቀሩትን አለማግኘት ይኖራል:: የብዙ አማሮች ምርጫ መፈቀር ሳይሆን ማፍቀር ነው:: በሀገር ፍቅር የተለከፈ: ብዙ ከፍሎ ትንሽ የተነፈገ:: ያም ሆኖ ማፍቀርን የመሰለ ጸጋ የለም:: ፍቅር ከሌለ ምኑን ሕይወት አለ ይባላል! ስናፈቅር ሕይወታችን ትጣፍጣለች: እያመመንም ቢሆን:: የሚፈቀሩ ሰዎች የፍቅርን ጣዕሙንም ሆነ ህመሙን መቸ ያውቁታል! ምኑም የማይገባቸው ቆርጠው ቢጥሏቸው እንኳ የማይሰማቸው የደነዘዘ ገላ ማለት እኮ ናቸው!

ሌሎች ጊዜያቸውን እየተሻሙ የሚጠቅማቸውን እያደረጉ ነው:: እናንተ የአማራ ልጆችም ትልቅ ሀላፊነት አለባችሁ:: በነበረከት ስምዖን: አዲሱ ለገሰ: ህላዊ ዮሴፍ: ገነት ገ/እግዚአብሔር: ታደሰ ጥንቅሹና ካሣ ተከብርሀን እስከተመራ ድረስ ብአዴን እንደድርጅት የአማራውን ጥፋት ከማቀላጠፍ የዘለለ ሚና አይኖረውም:: ነገር ግን የመሀልና የታች አመራሮችን መያዝ ያስፈልጋል:: በትክክል አማራ የሆኑትን እየለዩ የትግሉ አጋር ማድረግ ያስፈልጋል:: ትግሉ የራሳቸው ትግል እንደሆነ አምነው ተቀብለው የድርሻቸውን መስዋእትነት እንዲከፍሉ ሊነገራቸው ይገባል:: በየአካባቢው የግፍ ሰለባ እየሆኑ ያሉት ወገኖቻችን በጣዕር ላይ ሆነው የናንተን የልጆቻቸውን ትንፋሽ እያዳመጡ በተስፋ እየኖሩ ነው:: ልብ በሉ! ለአማራው ያለው እራሱ አማራው ብቻ ነው!!!

የጎንደር: የጎጃም: የወሎና የሸዋ ማሕበሮች በየአካባቢው ያለውን ሕዝብ እያስተባበራችሁ የአማራውን ትግል ለማገዝ የምትቆሙ ካልሆነ እባካችሁ በቁጭት የተነሱትን አማሮች ተዋቸው:: ትግሉ ቀላል እንዳልሆነ እናውቀዋለን:: እናንተን ባይገባችሁም የሚፋለመን ወያኔ ብቻ አለመሆኑንም እናውቃለን:: ይህን እየተነሳሳ ያለውን የሕዝብ ስሜት ለማቀዝቀዝ እየሰራችሁ እንደሆነ ተገንዝባችሁ ከድርጊታችሁ ታቀቡ::

ድል ለአማራ ታጋዮች!

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

No comments:

Post a Comment

wanted officials